Artcles

ፌዴራሊዝም እና የዴሞክራሲ ተቋማት

By Admin

May 03, 2018

ፌዴራሊዝም እና የዴሞክራሲ ተቋማት

አባ መላኩ

ፌዴራሊዝም ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ምርጫ ብቻ ሳይሆን አማራጭ የሌለው ሥርዓት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉንም መብቶች አቻችሎ ሕዝቦችን ለመምራት ፍቱን መድኃኒት ነው። ሥርዓቱ የሕዝቡን ሁለንተናዊ መብቶች በተሟላ መንገድ ለማስጠበቅ ወደር የለውም። ለመሆኑ ፌዴራሊዝም ከሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አኳያ ምን ፋይዳ አለው? በጥቂቱ እንቃኝ።

የፌዴራላዊ ሥርዓቱ ምሶሶ የሆነው የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን አጎናፅፏል። በተለይም መንግሥት እነዚህን መብቶች ለማረጋገጥ የወሰዳቸው የተለያዩ ገንቢ ርምጃዎች ለፌዴራላዊ ሥርዓቱ ወሣኝ ሚና እንዲጫወቱ አግዟል።

በፌዴራላዊ ሥርዓቱ መላ የኢትዮጵያ ዜጎች ከአገራቸው ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና  ማህበራዊ ህይወት ተገልለውና ተረስተው በባይተዋርነት ለመኖር የተገደዱበት አድሏዊና ፍትህ አልባ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ፣ ዜጎች በማንኛውም አገራዊ ጉዳይ ውስጥ እኩል ተሳታፊ የመሆን ዕድል አግኝተዋል። ይህንንም በተጨባጭ ሥራ ላይ በማዋል የአገሪቱንና  የሕዝባችን የማደግና የመበልፀግ ተስፋን ለማለምለም ችለዋል።

ሕዝቦች በመብቶቻቸው እየተገለገሉና ዘላቂ ጥቅሞቻቸውን እያስከበሩ በፈጣን ልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አቅጣጫ ላይ የተያያዙት ፈጣን የዕድገት ጉዞም የፌዴራላዊ ሥርዓቱ ተጨባጭ ፍሬ ነው።

በኢትዮጵያ እውን የሆነው ፌዴራላዊ ሥርዓት ለአገሪቱ ሕዝቦች አንድነት፣ ሠላምና ዕድገት መጠናከር ወሣኝ አስተዋጽኦ ያበረከተ ነው፤ በማበርከት ላይም ይገኛል። የዚህ አዲስ ሥርዓት ግንባታ ሂደት በተጨባጭ ተፈትኖ ፍቱንነቱም ተረጋግጧል።  

በመገንባት ላይ የሚገኘው ፌዴራላዊ ሥርዓት በአገሪቱ ላይ አንዣቦ የነበረውን የመበታተን አደጋ ያስወገደና በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ ለተመሠረተ ከብረት የጠነከረ የሕዝቦች አንድነት ዘላቂ ዋስትናን ያስገኘ ነው።

የኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓቱ አባል መንግሥታት የተደራጁት በመሠረቱ በብሔር ብሔረሰብ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ባለፈው ታሪክ ማንነቶች የተነፈጉትን መብት፣ ታፍኖ የነበረውን ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህልንና ሌሎች የማንነት መገለጫዎች በህገ መንግሥት ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ተፈፃሚ ማድረግ የሚችሉት ይህንኑ አወቃቀር በመከተል ስለሆነ ነው።

ማንነቶች የተዛባውን ግንኙነት መወገዱን ማረጋገጫ መሣሪያ እንደሆነ ስላመኑበትና በዚህ አወቃቀር አዲስ የእኩልነት ግንኙነትና የጋር ህልውና እንዲመሠረት ስለወሰኑ የተከተሉት አወቃቀር ነው። የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት አንዱ ልዩ ባህሪ ተደርጎ የሚወሰደው አንዱ ይህ በመሆኑ ነው። ባደጉት አገራት በተለምዶ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ተደርገው የሚወሰዱት ሕዝቦች ናቸው። ይህ አስተሳሰብ የቡድን መብቶችን ወደ ጎን መተውን ብዙዎች ምሁራን ይስማሙበታል፡፡

ዜጎች የአዲሲቷን ኢትዮጵያ የወደፊት ዕድል የመወሰን ሥልጣን ባለቤት መሆን እንዳለባቸው በወኪሎቻቸው አማካይነት ይፋ አድርገዋል። በምሥረታው ወቅት የገቡትን ቃል በአፈጻፀም ሂደት እንዳይዛነፍ የመጠበቅ ኃላፊነት የሚሰጣቸውን ህገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣን ወስደዋል። የዚህ ድንጋጌ ቁልፍ ትርጉም በመከባበር፣ በመተማመንና በመተባበር በእኩልነት አብሮ የመኖር ስምምነት ነው።

የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት የግል መብቶችን ለማረጋገጥ ወሣኝ እንደሆነ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚቴ ይገልፃል፡፡ ብዙ ፀሐፊዎች የቡድን መብቶች ከግል መብቶች ተለይተው መገደብ የሌለባቸው እንደሆኑ ይገልፃሉ፡፡ የግል መብቶችን በማረጋገጥ ብቻ የቡድን መብቶችን ማረጋገጥ እንደማይችል፣ የቡድን መብቶችን የሚከለክል ሥርዓት የግለሰብ መብቶችን ብቻ በማስከበር የተሟላ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊሆን እንደማይችል የሚገልፁም አሉ።

ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ያደጉ የዴሞክራሲ አገሮች የቡድን መብቶችን በተሟላ መልኩ ባለመረጋገጣቸው ምክንያት የቡድን መብት ጥያቄዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከሩ የአገራቱን ውስጣዊ ሠላም በማናጋት ላይ ይገኛሉ። የኢትዮጵያን ሁኔታ ስንመለከት ደግሞ የብሔሮችና ብሔረሰቦች እሥር ቤት ልትሆን የቻለችው የቡድን ማንነቶች ማፈን ዋነኛ የጭቆና መገለጫ ስለነበር ነው።

በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ከተደነገጉ የሕዝብ መብቶች ውስጥ አንዱ የኃይማኖት እኩልነት ነው። መንግሥትና ኃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን፣ ሁሉም ሰዎች በመካከላቸው የዘር፣ የብሔር፣ የብሔረሰብ፣ የጾታ፣ የኃይማኖት ልዩነት ሳይደረግ እኩል የህግ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው፣ ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የህሊናና የኃይማኖት ነፃነት፣ የመረጠውን ኃይማኖት ወይም እምነት ለብቻው ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን የማምለክ፣ የማስተማርና የመግለፅ መብት አለው።

የሥርዓቱ መሠረት የሆነው ህገ መንግሥት ለእነዚህ ድንጋጌዎች ልዩ ትርጉም የሚሰጣቸው የኃይማኖቶች እኩልነትና የእምነት ነጻነት ሳይረጋገጥ ያለፈውን የተዛባ ግንኙነት ማስተካከል አይቻልም ከሚል መሠረታዊ አስተሳሰብ በመነሳት ነው።

አዲስ የኢትዮጵያዊነት ማንነት የመገንባት ጉዳይም ከእነዚህ መብቶች ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ነው። ለሕዝብ የሚገደብ መብት መኖር የለበትም የሚል መሠረታዊ እምነት ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ስለሚያምንበት ነው። የኢትዮጵያ ሕዝቦች በግልም ይሁን በቡድን የመረጡትን እምነት የመከተል መብታቸውን ማረጋገጥ የሕዝብ ልዕልና አንድ አካል ነው።

ፌዴራላዊ ሥርዓቱ የሕዝቦችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግ የተለያዩ መብት አስጠባቂ ተቋማትን በማቋቋም የተለያዩ ርምጃዎችን ወስዷል፤ በመውሰድ ላይ ይገኛል። የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የእንባ ጠባቂ ተቋም፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤ ተጠቃሾች ናቸው።

ተቋማቱ ኅብረተሰቡ በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት አፈጻፀም ሣቢያ ሊፈጠሩ የሚችሉ ጉዳዮች ጥያቄ ሲቀርብላቸውና በራሳቸው ተነሳሽነትም ይመረምራሉ፣ ችግሮችን በመለየት የመፍትሔ ሃሳቦችን በማቅረብም ተግባራዊነታቸውን ይከታተላሉ። በዚህ ተግራቸውም በሥርዓቱ ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ሚዛናዊ ጉዳዮች እውን እንዲሆን ያደርጋሉ።

በአጠቃላይ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ በህገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡ በርካታ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ተግባራዊ ከማድረግ ባሻገር እነርሱን የሚቆጣጠሩ ተቋማትን በገለልተኝነት በማቋቋም ጭምር አፈጻፀማቸውን በመከታተል መብቶቹ ሳይሸራረፉ እውን እንዲሆን በማድረግ ላይ ይገኛል። በዚህም ከዛሬ 27 ዓመት በፊት ለመብቶቹ እውን መሆን ሕዝቦች የተሰውለትን ዓላማ እያሳካ ይገኛል።