Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

128ን ለመደገፍም ሆነ ለመቃወም ዕውነታን እንረዳ

0 399

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

128ን ለመደገፍም ሆነ ለመቃወም ዕውነታን እንረዳ

ፍ.ው

በቅርቡ የአሜሪካ ኮንግረስ ያሳለፈው ውሳኔ 128 የተሰኘ አሳሪና ቀፍዳጅ የሆነ ህግ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ መብት አያያዝና መልካም አስተዳደር በተመለከተ ተላልፏል፡፡ውሳኔው የአስገዳጅነት ባህሪ ባይኖረውም በአንድ ሉዓላዊት፣ነፃና በቅኝ ግዘት ቀምበር ሳትገዛ በኖረች አገር ላይ የተቃጣ የእጅ አዙር ጣልቃ ገብነት ይመስላል፡፡ህጉ እኔ አውቅላችኋለሁ፤እኔ ብቻ እንደምነግራችሁ አድርጉ የሚል ይመስላል፡፡ይህ ህግ በዜጎች የተባበረ ክንድ ተመክቶ ውድቅ መሆኑ ባያጠራጥርም አገር ለለውጥ እየተጋች ባለችበት ወቅት የተቃጣ ሴራ በመሆኑ በቸልታ ቢታይ አገርን ከማፍረስ ወደኋላ የሚል አይመስልም፡፡

ምዕራባውያን አገሮች በስንት ትንቅንቅ ከቅኝ ግዛት የተላቀቁ አገሮችን መልሰው ለመያዝና በግፍ አገዛዛቸው ስር ለማቆየት የተለያዩ ስልቶችን ነድፈው ተፈጻሚ ያደርጋሉ፡፡ከዚህ አንጻር በዚህ ዘመን እየተፈጸመ ያለው የኢኮኖሚ ባርነትና የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ በቀዳሚነት ተጠቃሽ ነው፡፡ይህ አልሆን ሲል ደግሞ በሽብርተኝነትና ሽብርተኝነትን በመዋጋት እንዲሁም ድጋፍ በመስጠት ስም ሉዓላዊ አገሮችን ብትንትናቸውን ማውጣት በገሃድ እየታየ ያለ ሃቅ ነው፡፡

ለአብነት እንኳን ቢታይ ሶሪያ፣ሊቢያ፣ኢራቅና የመን በራሳቸው መሪዎች የሚተዳደሩ አገሮች ነበሩ፡፡እነዚህ አገሮች በሽብርተኝነት ስም ከምዕራባውያን አገሮች በተደረገባቸው ጫናና ጦርነት ምክንያት ጠንካራ መንግስት ማቋቋም ተስኗቸው እስከወዲያኛው መንግስት አልባና የወሮበሎች መፈንጫ ሆነው ቀርተዋል፡፡ነገር ግን ኢትዮጵና ኢትዮጵውያን ይህንን የሚፈቅዱ አይደሉም፡

በሽብርተኝነት ስም በቀዳሚነት ተጠቂ የሆነችው ኢራቅ የነዳጅ ሃብቷ በአጅጉ ከመበዝበዙም በላይ ዜጎቿ የሚታደጋቸው አጥተው በመባዘን ቀርተዋል፡፡አሜሪካ እና የእሷ ሸሪኮች የሆኑት እንግሊዝና ፈረንሳይ ቀዳሚ አላማቸው በሽብርተኝነት ስም የአገሮችን ሉዓላዊነት በመዳፈር ጦርነት መክፈት ብሎም ነዳጅ ዘይት መዝረፍና የጦር መሳሪያ መሸጥ ቢሆንም በጉልበት ያፈራረሷትን ኢራቅ መልሰው መገንባት አልቻሉም፡፡የቻሉት ብቸኛ ነገር ነዳጅ ከአቅማቸው በላይ መዝረፍና መጓጓዝ አለፍ ሲልም ጦር መሳሪያቸውን መሸጥና ሕዝብን ማጫረስ ነው፡፡

በምእራባውያን የግፍ አሰራር ተገፍቶ ለመውደቅ ሌላዋ ነባራዊ ምሳሌ ሶርያም ከላይ በተጠቀሱት  አገሮች ጦስ እስከወዲያኛው ምድራዊ ሲዖል ሆና ቀርታለች፡፡ከፈራረሰች ድፍን ሰባት አመታት ሲያልፉ የሚታደጋት ምንም ነገር አልተገኘም፡፡ዜጎቿ ለውርደት፣ለስደትና ለሕልፈት ሲዳረጉ ብርቅና ድንቅ ቅርሶቿ የዶግ አመድ ሆነው እንደ ትቢያ በነዋል፡፡ከተሞቿ ከላይና ከታች በሚዘንብባቸው ቦንንብ የድንጋይ ክምር ብቻ ሆነዋል፡፡የምዕራባውያን እኔ ብቻ አውቅላችኋለሁ የሚል አባዜ ያመጣው መዘዝ ከሊቢያ እስከ ሶሪያ ከየመን እስከ ኢራቅ ለብዙ አገሮች ውድመት መንስዔ ሆኗል፡፡እየሆነም ይገኛል፡፡

ለዚህ አድራጎታቸው መታረምና ካሳ መክፈል ይቅርና ምንም ጸጸት አይታይባቸውም፡፡ሁሉም ሉኣላዊ አገሮች በራሳቸው መንገድ አገራቸውንና ህዝባቸውን መምራትና ማበልጸግ ሲችሉ ከአምባገነን ምእራባውን አገሮች በደረሰባቸው ጫናና ጦርነት እስከወዲየኛው አሸልበዋል፡፡አገሮቻቸውም የጦርነት አውድማ ሆነው ቀጥለዋል፡፡ዓለሙ በአምባገነኖች መድፍና ሚሳዔል ጫና ስር በመሆኑ ማንም ማንንም መክሰስና ተጠያቂ ማድረግ አልቻለም፡፡

ኢትዮጵያ በአደዋ ጦርነት ወቅት እንዳስመሰከረችውና የዓለምን ጥቁር ሕዝቦች እንዳኮራች የሚታዎቅ የአልገዛም ባይና የኩሩ ሕዝብ መኖሪያ ናት፡፡ሉኣላዊነቷንም ለማንም አሳልፋ ሰጥታ አታውቅም፤ወደፊትም አትሰጥም፡፡ይቺ ደሃና  በልማት እየገሰገሰች ያለች አገር እንደመካከለኛው ምስራቅ አገሮች በነዳጅ ሃብቷ የምትታዎቅ አገር አይደለችም፤ምንአልባትም የነዳጅ ሃብት ባለመታደሏ የምዕራባውያን ትኩረት ከአልገዛም ባይ ሕዝቦቿ ላይ እንዲሁም ለመካከለኛው ምስራቅና የአለማችን ንግድ ዋና መተላለፊያ ለሆነው የህንድ ውቂያኖስና ቀይ ባሕር ባላት ቅርበት እና  ስትራቴጅካዊ አቀማመጥ ወዘተ የመነጨ ሊሆን ይችላል፡፡

እስከ አሁን እንደዚህ አይነት አሳሪ ሕጎች በሌላ አገር ላይ ሲተላለፉ ታይቶ አይታዎቅም፡፡ምናልባትም ውሳኔ 128 የተሰኘው አሳሪ ህግ ምእራባውን እስካሁን ከሚከተሉት የማዳከምና የመደምስስ አካሄዳቸው ለየት ያለና የአቅጣጫ ለውጥ የሚታይበት አሰራር መጀመራቸውን ሚያሳይ ነው የሚሉም ተንታኞች አሉ፡፡

የኢትዮጵያ ህልውና፣ታላቅነት ክብር የሚወሰነው በገዛ ልጆቿ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ብቻ ነው፡፡  ሉዓላዊ አገር እንደ መሆኗ መጠን በውስጥ ጉዳይዋ የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ የመላ ኢትዮጵያውያን የማይገሰስ መብት እንጅ የውጪ ሃይሎች ውዴታና ግዴታ የሚጠየቅበት አይደለም፡፡ ምዕራባውያንም ሆኑ ሌሎች በውስጥ ጉዳያችን ገብተው እንዲፈተፍቱ ልንፈቅድላቸው አንችልም፤ፈቅደንላቸውም አናውቅም፤ለዚህ ጉዳይ ከጣሊያንና ከእንግሊዝ የተሻለ ምስክር የለም፡፡

ሁለቱም ከ1870ዎቹ ጀምሮ የራሳቸውን ፈቃድ በአገራችን ላይ ለመጫን ብዙ ዳክረዋል ነገር ግን  አልተሳካላቸውም፡፡በተለይም የጣሊያን ሽንፈት በአደዋ እንዲሁም በ1930ዎቹ በታየው የጸረ-ቅኝ አገዛዝና የአርበኝነት ተጋድሎ ምክንያት ጣሊያን ያሰበችው ሁሉ እስከመጨረሻው ሊሳካላት አልቻለም፤ይህም ለአገራችን ሉዓላዊነትና ታላቅነት ሕያው ምስክር ነው፡፡ይህ የአገርን ሉዓላዊነት የማስከበር አካሄድ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረና የሚቀጥል ነው፡፡

አሁንም እየታየ ያለው የውሳኔ 128 አካሄድ የዘመናዊ እጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ መሰሪ አካሄድ ዋና አብነት ሊሆን ይችላል፡፡ምንም እንኳን ኢትዮጵያዊን ዜጎች ይህ አሳሪ ህግ የአገራቸውን  ሉኣላዊነት እንዲያዳክም ዝም ብለው ሚያዩት ባይሆንም(ለዚህ ደግሞ የጋራ አቋም ይዞ በአንድነት መታገል የግድ ነው)፡፡

እርግጥ ነው የውጭ ኃይሎች ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ በጦርነትና በኢኮኖሚያዊ አሻጥር አልሳካ ሲላቸው እነሱን እስካገለገለ ድረስ አስፈላጊ ነው ብለው ያመኑበትን ሁሉ በማድረግ፣ አምባገነን ተላላኪያቸውን ሥልጣን ላይ ለማስቀመጥ ወደኋላ አይሉም፡፡ይህ ፍላጎታቸው በኢትዮጵያ ምድር ተቀባይነት የለውም፤ሊያገኝም አይገባም፡፡የኢትዮጵያ ልጆችም የእነሱን ዓላማ ለማስፈጸም የሚሯሯጡ ተላላኪዎቻቸውን መመከት ይኖርባቸዋል፡፡

በተለይም ይህ ውሳኔ 128 የተባለ ሕግ ኢትዮጵያ ሰላሟን ለማስጠበቅና ልማቷን ለማስቀጠል እንዲሁም ሙስናን በመከላከል መልካም አስተዳደርን የበለጠ ለማስፈን አላማ ቀርጻ ደፋ ቀና በምትልበት በዚህ የመስቀለኛ ጉዞ ወቅት መከሰቱ እጅግ ከጀርባ ያዘለውን መሰሪ ደባና ተንኮል አሳዛኝና አነጋጋሪ ያደርገዋል፡፡

ከለውጥ ጋር በተገናኘ በቅርቡ የሆነውን እንኳን ብንወስድ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አገራዊ አንድነትና መግባባት ላይ ያተኮሩ በርካታ ቁም ነገሮች ተወስተዋል፡፡ ሥራቸውን በሙሉ ኃይል ሲጀምሩ ደግሞ በፖሊሲና በስትራቴጂ ማዕቀፎች ላይ ሊደረጉ ስለታሰቡ ለውጦች ዝርዝር ማብራሪያ እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡

ለሚቀጥሉት ሁለት አመታት  ሥልጣን ላይ የሚቆዩት ጠቅላይ ሚኒስትሩና አዲሱ ካቢኔያቸው የአገርን ገጽታ ለመገንባት፣ሰላምና መረጋጋትን ለማጠናከር እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት የተገቡ ቃልኪዳኖችን ለመፈጸም የሚረዳ ጅማሮ ይዘው እየተንቀሳቀሱ ይገኛል፡፡ይሁንና በእንደዚህ አይነት ወሳኝ የለውጥ ወቅት ምዕራባያን ኃይሎች የውሳኔ 128 አይነት አሳሪ ህጎችን በአገሪቱ ላይ መጫን ለውጡን ካለመፈለግ የመጣ ያስመስለዋል፡፡

አሁን ያለንበት ዘመን አለም አንድ መንደር የሆነችበት የግሎባላይዜሽን ዘመን በመሆኑ አንዱ አገር ብቻውን ተነጥሎ የሚኖርበትና የሚቆምበት አይደለም፡፡ከዚህ አንጻር የአገሮች ህልውና፣ንግድና አለማቀፋዊ ግንኙነት እርስበርስ የተሳሰረ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ የአንዱ አገር ምሶሶ ሲነቃነቅ የሌላውን አገር ማገር ማላላቱ የማይቀር ሃቅ ነው፡፡

በመሆኑም ይህ አሳሪ ህግ ቢያንስም ቢበዛም አገራችን ባላት የውጭ ንግድና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ላይ ጥላውን ማጥላቱ አይቀርም፡፡ይህንን በመገንዘብና የሚያሳድረውን ጫና ከግምት ውስጥ  በማስገባት የውሳኔውን አሉታዊ ጫና መቋቋም፣ የአገርን ሉዓላዊነት ማስጠበቅና ልማትን ማስቀጠል የሁሉም ዜጎች ሃላፊነት ነው፡፡

ለዚህም ሁሉም ዜጎች በአንድነት መቆምና በአገር ላይ የተቃጣውን ትንኮሳ መመከት ይኖርባቸዋል፡፡በአሁኑ ወቅት የሕዝብ ድጋፍና ማበረታቻ ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው፡፡ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የተፎካካሪ ፓርቲዎችና ቡድኖች ድጋፍም የግድ ይላል፡፡ ይህ ድጋፍ በኢትዮጵያ ምድር የምንፈልገው ልማት እንዲመጣ፣ሙስና እንዲገታና መልካም አስተዳደር እንዲበለፅግ ብሎም ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የሚመጥን ምኅዳር እንዲፈጠርና የጠላቶቻችን አፍ እስከወዲኛው ለማዘጋት ወሳኝ ሚና ይጫዎታል፡፡

በመሆኑም አገራቸውን የሚወዱ ዜጎች እንዲሁም ፓርቲዎች በመለያየትና በመናቆር፣በእልህና በቂም በቀል  የተለመደውን የመቸከልና የለውጥ-አልባ ፖለቲካዊ አሰራር ማስቀጠል ለአገርም ለሕዝብም የማይጠቅም መሆኑን በመገንዘብ ከአሁኑ ወቅት ጀምሮ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚረዳ ጡብ ማስቀመጥ ይኖርባቸዋል፡፡ይህንን ሲያደርጉ የዜግነት ድርሻቸውን እየተወጡና ለአገራዊ አንድነትና ጥንካሬ መልካም ስራ እየሰሩ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያዊነት ከቃል በላይ በመስዕዋትነትና በተለያየ ተጨባጭ ተግባር የሚገለፅ ግዘፍ ማንነት በመሆኑ የሁሉም ዜጎች ድጋፍ ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬ ደግሞ ነገ  የተሻሻለችና የበለጸገች አገርን ለመገንባት ይጠቅማል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግቢያ ንግግራቸው እንዳስረዱት አሁን ዋናውና መሠረታዊው ጉዳይ በተጀመረው የለውጥ ሒደት አማካይነት ከእንደ ውሳኔ 128 ዓይነት አደጋ አገርን  እየተከላከሉ ሁሉን አሳታፊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት እንጂ፣ የአንድ ጎራን ርዕዮተ ዓለም ለመከላከል ሲባል ሌላ ትርምስ ማስነሳት አይደለም፡፡ አገር ከምንም ነገር በላይ ስለሆነች ለተጀመረው ለውጥ ቢቻል ደጋፊ መሆንና አገራዊ ችግሮችን በጋራ መጋፈጥ ካልተቻለ ደግሞ በውይይትና በመግባባት ወደ አወንታዊ አስተሳሰብ መምጣት አስፈላጊ ነው፡፡

በእርግጥም የአገሪቱ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነው  ሕዝብ ነው፡፡በመሆኑም ሰብአዊና ዴሞክራሲዊ መብቶችን ለማበልጸግ እንዲሁም መልካም አስተዳደርን ለማጎልበትና ልማትን ለማፋጠን ብሎም የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት የሚቻለው በሕዝብ ተሳትፎ እንጂ አንደ ውሳኔ 128 በባእዳን ኃይሎች ከውጪ በሚደረግ ግፊትና ጫና አይደለም፡፡ሕዝብ የለውጡ አካል ለመሆን ቁርጠኝነት እያሳየና እየታተረ በመሆኑ  የለውጡን ሒደት ለማደናቀፍ የሚሞከር ፀቡ ከሕዝብ ጋር በመሆኑ አይሳካለትም፡፡

ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ የኖረችው፣ አሁንም ያለችው፣ ወደፊትም የምትኖረው በታታሪና በምሥጉን ልጆቿ አለኝታነት እንጂ፣ ከውጭ በባዕዳን ኃይሎች በሚሰጥ ችሮታ እንዲሁም የእነሱ አርቲፊሺያል ቅጂ በሆኑ ህጎችና  ርዕዮተ-ዓለሞች አይደለም፡፡በመሆኑም አሁን አገራችን የሚያስፈልጋት ኢትዮጵያዊ ዜጎች ሁሉ በአንድነትና በጽናት ቆመው የውሳኔ 128 ዓይነት ፍርደ-ገምድል አሰራሮችን በማምከን በዜጎች ፈቃድና ጥረት የሚማጣ አገራዊ ለውጥና ልማትን ማስቀጠል ነው፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ ከምንም ነገር በላይ የሚያስፈልጋት የልጆቿ ጠንካራ አንድነትትና ትግል እንጂ ከውጪ የሚመጣ ምጽዋትና አልባሌ ጫና አይደለም፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy