Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

         ሀገራዊ ሰላም ይቅደም

0 352

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

         ሀገራዊ ሰላም ይቅደም

ይልቃል ፍርዱ

ኢሕአዴግ በጥልቅ ተሀድሶው ሂደት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ከመረጠ ጀምሮ በሀገራችን ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ሰላም ሰፍኖአል፡፡በሀገር ደረጃ ደፍርሶ የነበረው ሰላምና በየቦታው የነበሩ አላስፈላጊ ግጭቶችን መግታት ተችሎአል፡፡ይህ ሊሆን የቻለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየክልሎቹ በመዘዋወር ከሕዝቡ ጋር ባደረጉት ቀጥተኛ ውይይት ነው፡፡

በሕዝቡ በኩል የቀረቡትን የተለያዩ ጥያቄዎች በጥሞና ያዳመጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት ሀገራዊ አንድነታችንን መጠበቅ ዋነኛ ተግባር መሆን እንደሚገባው በተደጋጋሚ ገልጸዋል፡፡በግጭቶች መነሻነት የሚከሰተው የዜጎች ሕይወት መጥፋትና የንብረት መውደም የተሰሩትን ታላላቅ የሀገር ግንባታ ስራዎች ማፍረስ ሕዝብና ሀገርን የሚጎዳ ተግባር በመሆኑ ችግሮቻችንን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብና መፍታት እንደሚገባ ይህንኑ መልእክት በዋነኛነት በሁሉም ክልሎች አስተላልፈዋል፡፡

ሕዝቡ በግልጽ በቂ ግንዛቤ በማግኘቱ ግጭቶችንና ሁከቶችን ከእንግዲህ ማየት አይፈልግም፡፡ድርጊቶቹ ሊወገዙ ሊኮነኑ ይገባል፡፡በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ድንበሮች አካባቢ በተነሳው ግጭት አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ ጉዳት መድረሱ የትላንት ታሪክ ነው፡፡ዳግም ሊከሰት አይገባውም፡፡ሁለቱም ወንድማማችና ቤተሰብ የሆኑ የአንዲት  ሀገር ልጆች ናቸው፡፡ይሄን ያሕል ደረጃ የሚያደርስ ነገርም አልነበረም፡፡

በሁለቱም በኩል የደረሰው ጉዳት መፈናቀል የሰው ሕይወት መጥፋት የንብረት መውደም የጎዳው ራሳችንን ነው፡፡የተጎዳው ሕዝባችን የተጎዳችው ሀገራችን ናት፡፡በመሰረቱ ሕዝብ ከሕዝብ ጋር አይጋጭም፡፡ሊጋጭም አይችልም፡፡ለማጋጨት የሚነሱት ሴራ የሚጠነስሱት እሳት የሚለኩሱት የራሳቸውን ጥቅም የሚያሳድዱ በዚህ ተጠቃሚ እንሆናለን ብለው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ናቸው፡፡ይህንን እኩይ ሴራ በመበጣጠስ ማምከን ይገባል፡፡

በአካባቢው የተከሰተውን የሕዝብን ልብ ያደማ ችግር ለመፍታት የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ኃላፊነት በተረከቡ ማግስት ዶ/ር አቢይ አሕመድ ወደ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በማምራት የክልሉ አመራር በተገኘበት ከሀገር ሽማግሌዎችና ከሕዝብ ተወካዮች ከሕዝቡም ጋር ሰፊ ወይይት አድርገዋል፡፡በጋራ መግባባት ላይ በመመስረት ችግሩ ዳግም እንዳይከሰት የጋራ ስምምነት ላይ ተደርሶአል፡፡ኦሮሞና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሕዝብ ድንበር ተጋሪ ከመሆንም በዘለለ የተጋባ የተዋለደ በአብሮነት የኖረና አንዱ የሌላውን መጎዳት የማይፈልግ ነው፡፡

የሁለቱም ክልል አጎራባች በሆኑት አካባቢዎች ያለውም ሆነ መላው ሕዝብ ስለጉዳዩ በቂ ግንዛቤ ያገኘ በመሆኑ ሰላሙን ነቅቶ ይጠብቃል፡፡የሰላሙ ጠባቂ አስከባሪ ድሮም ሕዝብ ነው፡፡በአሁን ሰአት በኢትዮጵያ ውስጥ የተረጋጋ ሰላም ሰፍኖአል፡፡ሕዝብ የሀገሩን ሰላም በመጠበቅ የተጀመረውን ልማትና እድገት ለማስቀጠል ሙሉ በሙለ ሊባል በሚችል መልኩ የጋራ ብሔራዊ መግባባት ላይ ደርሶአል፡፡ለግጭቶች የሚሆን ክፍተት ሊፈጠር አይገባውም፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ አመራር ሰፊ የሕዘብ ድጋፍ ያገኘ በመሆኑ ሁከት ለመፍጠርና ግርግር ለማስነሳት ለሚሞክሩ ክፍሎች በሩ ዝግ ነው፡፡ሆኖም አልፎ አልፎ ግጭትና ሁከት ለመቀስቀስ የሚጥሩ ታይተዋል፡፡እነዚህ ኃይሎች በሰፊ የሕዝብ ድጋፍና መሰረት ላይ የቆመውን የጠቅላይ ሚኒስትሩን አመራርና የተገኘውን ተቀባይነት ለማናጋት አቅደው የሚሰሩት ሴራ ከሆነም አይሳካም፡፡ኢትዮጵያ ከመቸውም ግዜ በጠነከረና በጎለበተ አንድነት ላይ ጸንታ የቆመች ሀገር መሆኗን መረዳት ይገባቸዋል፡፡

ዛሬ ኢትዮጵያዊነት ገዝፎአል፡፡ለልዩነት ለዘረኝነት ለመከፋፈል የሚሆን ቀዳዳ የለም፡፡ ሊኖርም አይችልም፡፡ትናንሽ ግጭቶችን በየቦታው ለመፍጠር ደፋ ቀና የሚሉ አስተሳሰበ ደካሞች የሚላተሙት ማእበላዊ ኃይል ካለው ሕዝብ ጋር ነው፡፡የተጀመሩት ስርነቀል የለውጥ እርምጃዎች በተጨባጭ ስኬታማ ሆነዋል፡፡ማየት ማመን እንዲሉ በየቀኑ አዳዲስ እርምጃዎችን በመውሰድ የሕዝቡን ድጋፍ እያጎለበተ ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ አመራር ድጋፉ በሀገር ቤት ውስጥ ብቻ አይደለም ያለው፡፡በዳያስፖራውም ውስጥ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ለብሔራዊ ሰላምና መግባባት ለይቅርታና እርቅ የሚሰራ አዲስ መንገድን መከተሉ ነው የሕዝብን ልብና ድጋፍ ያስገኘለት፡፡ኢሕአዴግ በስኬት ጎዳና መራመድ ጀምሮአል፡፡  

ኢትዮጵያ ውስጥ በቅርቡ በሕዝቡ ውስጥ የተካሄደ አንድ ጥናት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በሀገራችን ለውጥ ያመጣሉ ብሎ የሚያምነው ሕዝብ ቁጥር 85 በመቶ መሆኑን ይገልጻል፡፡የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ላይ በወጡ 60 ቀናት ውስጥ የወሰዷቸው ሊታመኑ ቀርቶ ሊገመቱ የማይችሉ ድንቅ እርምጃዎች የሕዝቡን ድጋፍና እምነት 90 በመቶ አድርሶታል ብሎ ያምናል፡፡ሕዝቡን በደስታ ስሜት ፈንቅለውታል፡፡ መሳጭ በሆኑ ንግግሮቻቸው አስለቅሰውታል፡፡ኢትዮጵያዊነትን አድምቀው ለዜጎቻቸው ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር በተግባር አሳይተዋል፡፡ይሄ እርምጃ ለኢሕአዴግ ቀጣይ ጉዞ  ሕዝባዊ ተቀባይነትን ያስገኘ ነው፡፡

በሀገር ውስጥ እስር ላይ የነበሩትን ጨምሮ ከማድረግም አልፈው በኬንያ በሱዳን በሳኡዲ አረቢያ በአረብ ኢምሬት በእስር ላይ ይገኙ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን  አስፈትተዋል፡፡ይህ ሁሉ ድንቅ እርምጃ የተሀድሶ ለውጡ ውጤት ነው፡፡ የሚታሰብና የሚገመት አልነበረም፡፡ግን ሆነ፡፡ተደረገም፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ እርምጃ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን የአለምንም መሪዎች ያስደመመ ሆኖአል፡፡በእርግጥም ኢትዮጵያ ወደኃላ በማይመለስ ስርነቀል በሆነ የለውጥ ጉዞ ላይ የምትገኝ ሀገር ነች፡፡የዲሞክራሲ ምሕዳሩን ለማስፋት የወሰነች በእርቅ በሰላምና በፍቅር በመግባባት የምታምን ሀገር መሆኗን ለአለም አሳይታለች፡፡በዚህም የአለም ታላላቅ መሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ያላቸውን አድናቆትና ድጋፍ በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡

ይህ ሁሉ ሲደመር ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ እንዳሉት ኢትዮጵያን ታላቅ ሀገር የማድረግ በሕዝቦቿ መካከል ታላቅ መግባባትና መስማማትን የመፍጠሩ የመደመር ጉዞ በተሳካ ሁኔታ ቀጥሎአል፡፡በነዚህ መሰረታዊ ምክንያቶች የተነሳ  ምንም አይነት ግጭቶች ሁከቶች ለመፍጠር ለመቆስቆስ የሚደረጉት ጥረቶች ከመምከን ውጭ ቦታና ስፍራ የላቸውም፡፡ እያጋለጠ የሚያመክናቸው ሕዝቡ ነው፡፡ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡እንዲህ አይነቱ የግጭት አካሄድ ለሀገራችን የማይበጃት መሆኑን በተደጋጋሚ በተጨባጭ በተከሰቱ ጥፋቶችና አደጋዎች ሕዝቡ አይቶአል፡፡

ማንኛውንም ችግር በሰላም በውይይት ከመፍታት ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለ በተግባር ታይቶአል፡፡ሌላው አማራጭ የጥፋትና የውድመት መንገድ ነው፡፡ሀገርን ለብተና ሕዝብን ለአደጋና ለእልቂት ሀብትና ንብረትን ለውድመት ይዳርጋል፡፡ይህ መንገድ ለእኛ አይበጀንም፡፡ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ተቀባይነት የለውም፡፡

ገና ከድህነት ያልተላቀቅን ብዙ መስራት ሀገርን መለወጥ ማልማት ያለብን ነን፡፡ የተመዘገቡትን የልማትና የእድገት ውጤቶች ጠብቀን ለበለጠ ድል በመስራት ሀገራችንን ወደ  ከፍታ ማማ ማውጣት መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ማድረግ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡

በሀገርና በሕዝብ ሰላምና መረጋጋት ጉዳይ ከማንም ጋር መደራደር አይቻልም፡፡ልማትና እድገት የሚፋጠነው ሰላም ሲኖር ነው፡፡ሀገር የምታድገው በሰላም ውስጥ ነው፡፡ከሀገራዊ ሰላማችን በላይ የምናስቀድመው ምንም የለም፡፡በተለያዩ አካባቢዎች አለመረጋጋት ለመፍጠር የሚጥሩትን አስተሳሰበ ደካሞች ሕዝቡ እየተከታተለ አጋልጦ ለሕግና ፍትህ ያቀርባል፡፡ከሕዝብ የሚደበቅም ሆነ የሚሰወር ምንም ነገር የለም፡፡

ሰላም መጠበቅና ማስጠበቅ ለወታደሩና ለፖሊሱ ብቻ የሚተው ጉዳይ  አይደለም፡፡እነሱ በሙያቸውና በስራቸው ኃላፊነት የተነሳ በመጀመሪያው ረድፍ ላይ ይገኛሉ፡፡በዋነኛነት ሰላሙን በጽናት ቆሞ የሚጠብቀው ሕዝብ ነው፡፡የሠራዊቱም አባላት ከሕዝብ የወጡ የሕዝብ ልጆች ናቸው፡፡ሰላምን በጋራ ቆሞ መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ግዴታና ኃላፊነት መሆኑ በግልጽ ሊታወቅ ይገባል፡፡

በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ሀገራዊ የመግባባት ስሜት ሰፍኖአል፡፡መንግስት ለሀገራዊ መግባባቱ የሚበጁ ስርነቀል እርምጃዎችን በመውሰዱ የተነሳ በሕብረተሰቡ ውስጥ ሰፊ ተቀባይነትን አግኝቶአል፡፡በዚህ ወቅት በተለያዩ ቦታዎች የሚታዩ አነስተኛ ግጭቶችን ለመፍጠር መሞከር ሀገራዊ ሰላምን ለማናጋት አቅም አይኖረውም፡፡እነዚህን  እኩይ ጥረቶች ሕብረተሰቡ በግንባር ያመክናል፡፡ሕብረተሰቡ የተሻሉ ለውጦችን ለመመልክት ችሎአል፡፡ከመንግስት ጎን ተሰልፎ በጋራ ሰላሙንና ሀገሩን ይጠብቃል፡፡ከተሳሳቱ እሳቤዎችና ከስሜታዊነት በመውጣት ቅድሚያ ለሀገር ሰላም መስጠት የሁሉም ዜጋ ቀዳሚ ግዴታ ነው፡፡ሰላም የሀገርና የሕዝብ ሕልውና ዋነኛ መሰረት ነው፡፡ በዚህ የተለየ ታሪካዊ ወቅት ሰላም ለማደፍረስ  መሞከር አንዳችም ውጤት አያስገኝም፡፡

በአንዳንድ ኩታ-ገጠም ቀበሌዎች በትንሹም በትልቁም የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮች በአካባበዊ ሽማግሌዎች በመንግስት አካላት በሕዝብ ተወካዮች የጋራ ትብብርና ምክር ሽምግልና ሊፈቱ የሚገባቸው ናቸው፡፡በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ሰፍኖ የሚገኘውን ሀገራዊ ሁኔታ አይወክልም፡፡ተጎራባች ክልሎችና ሕዝቦችንም አይወክልም፡፡   

 

አንድን ሕዝብን ጎድቶ ሌላውን ለመጥቀም መሞከር እጅግ ደካማ ከሆነ ጨለምተኛና  ኃላቀር አስተሳሰብ የሚመነጭ ስለሆነ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ተቀባይነት የለውም፡፡ ቆሜለታለሁ ለሚሉትም ሕዝብ አይጠቅምም፡፡አይበጅም፡፡ኦሮሞ ሆኖ ሶማሌን የሚጎዳ፣ ወይም ሱማሌ ሆኖ ኦሮሞን የሚጎዳ ተግባር መፈጸም ማንንም ተጠቃሚ የማያደርግ የዜሮ ድምር ውጤት ላይ የሚያደርስ በመሆኑ አከሌ  ከአከሌ ሳይባል ሁሉም በጋራ ሊያስቆመው የሚገባ አፍራሽ ተግባር ነው፡፡የተረጋጋውን ሀገራዊ ሰላም በዚሀ መልኩ ማደፍረስ አይቻልም፡፡ሕዝቡ ካለፉት ስህተቶች ብዙ የተማረ በመሆኑ ይህን የጥፋት አካሄድና ሙከራ አይቀበልም፡፡ ሕዝብንም አይወክልም፡፡

በብሔር ሥም የሚካሄዱ ግጭቶች ከሰለጠነው ዘመን የተፋቱ እጅግ ኃላቀር የሆኑና ሕዝብ የሚጸየፋቸው የሚያወግዛቸውም ናቸው፡፡ይህ ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም በጸና መሰረት ላይ የቆመውን ኢትዮጵያዊነት ለመሸርሸር የሚደረገው ከንቱ ሙከራ የግለሰቦች ሴራ ውጤት እንጂ የትኛውንም ብሔረሰብ አይወክልም፡፡ሊጋለጡ በአጭሩም ሊመከቱ ይገባል፡፡  

 

የግለሰቦችን እኩይ ፍላጎት ለማሳካት በሕዝብና በብሔር ስም ለመነገድ መሞከር ግዜው ያለፈበትና የመሸበት አስተሳሰብ ነው፡፡የትም አያደርስም፡፡በጸና አንድነት በመቆም ሀገርን ከማልማትና ከማሳደግ ውጭ እኛ እና እነሱ የሚለው ከፋፋዮች ጎራ ለመለየት የሚያደርጉት ጥረት ኢትዮጵያዊነትን የሚጎዳ, ለሀገር ግንባታም ጠንቅ ስለሆነ ሕዝቡ አጥብቆ ይታገለዋል፡፡

ዛሬም ድረስ ብልጭ ድርግም የሚሉ እዚህም እዚያም የሚታዩ ጥቃቅን ሊባሉ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮች አሉ፡፡የሰፈነው አጠቃላይ ሀገራዊ ሁኔታ ሲታይ ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ ነው፡፡እነዚህ ጥቃቅን ሙከራዎች በሀገሪቱ የሰፈነውን በሕዝብ የተደገፈውን ሰላም ሊያደበዝዝ የሚችል አቅም የላቸውም፡፡ሊኖራቸውም አይችልም፡፡ችግሮቹ በአነስተኛ ደረጃ በታዩበት አካባቢ ሕዝብ መንግስትና የሀገር ሽማግሌዎች ጠንካራ ስራ በመስራት ሊፈቱት ይገባል፡፡በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ አመራር ኢሕአዴግ እያስመዘገባቸው ያሉት ታላላቅ ሕዝባዊና ሀገራዊ ድሎች በሕዝብ የተደገፉ ስለሆነ ጎልብተው ይቀጥላሉ፡፡ሀገራዊ ሰላማችንን የመጠበቁ ስራ ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው ነው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy