Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ህገ ወጥነትን ለመቀነስ

0 349

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ህገ ወጥነትን ለመቀነስ

ገናናው በቀለ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በውጭ አገር ከእስር ያስለቀቋቸው ወገኖቻችን በአንድ ወቅት በስደት የሄዱ መሆናቸው ግልፅ ነው። ያም ሆኖ ሀገራችን ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በዜጎቿ ላይ ሊያስከትለው የሚችለውን ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት ተግባሩ ተፈፃሚ እንዲሆን አትሻም። ይህን ችግር ለመከላከል ግብረ ሃይል በሀገር ደረጃ አቋቁማ እየሰራች ነው።

 

ኢትዮጵያ አንድ ሚሊዮን ያህል የሚሆኑ የውጭ አገር ስደተኞችን (በተለይ ከአፍሪካ ቀንድና የመንን ጨምሮ ከመካከለኛው ምስራቅ) ተቀብላ መብቶቻቸውንና ክብራቸውን ጠብቃ እያስተማረችና አቅም በፈቀደው መጠንም ስራ እያስያዘች ያለች አገር ናት። ዜጎቿም ውጭ ሄደው ለመስራት እስከ ፈለጉ ድረስ በህጋዊ የውጭ አገር ስምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008 መሰረት የመንቀሳቀስ መብት እንዳላቸው ገልጻለች።

 

በዚህ መሰረት የዜጎችን መብትና ክብር የሚያስጠብቁ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ከተለያዩ አገራት ጋር ተፈራርማለች። እየተፈራረመችም ነው። ከዚህ አኳያ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ስምምነት የተፈራረመች ሲሆን፣ ከተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ጋርም ስምምነት ላይ ደርሳለች።

 

ያም ሆኖ ወደ ውጭ መሄድ የሚፈልጉ ዜጎች በውጭ ሀገር ስምሪት አዋጁ ላይ የተዘረዘሩትን መስፈርቶች ማወቅ ይኖርባቸዋል። እንዲሁም ስምምነት የተደረገባቸውን አገራት ከሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማት በመረዳትና ትክክለኛውንም መረጃ በመያዝ ወደ ውጭ ሄደው መስራት ይችላሉ። ይህም የህገ ወጥ ደላላዎችን ተግባር የሚያመክንና የዝውውሩን ህገ ወጥነት በእጅጉ የሚቀንስ ይሆናል።

 

ዜጎች ምንም እንኳን በሀገራቸው ውስጥ በመስራት መለወጥ የሚችሉ ቢሆንም፣ ድህነትን ለመቅረፍ የሚያደርጉት ተነሳሽነት ትክክል አይደለም ሊባል የሚችል አይመስለኝም። እዚህ ሀገር ውስጥ መስራት እየቻሉ በህገ ወጥ መንገድ ተታልለው የህገ ወጦች ሲሳይ መሆናቸው ማሳዘኑ አይቀርም።

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢትዮጵያ መንግስት በሀገራችን የተንሰራፋውን ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስወገድ የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ መንቀሳቀስ ሲጀምር፤ ስራ አጥነት መቅረፍ አንደኛው ተግባሩ በማድረግ ነበር።

በከተሞች የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራትን በማደራጀት እንዲሁም የብድር አገልግሎት በመስጠት ለዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል።

ታዲያ ዜጎችም በየሙያቸው በመሰማራት ለአገራዊው ልማት ከፍተኛ ጉልበትና አቅም መሆን መቻላቸው የትናንት ትውስታችን ነው። በገጠርም እንዲሁ ግበርናው ስራን እንዲፈጥር በማድረግ አጥጋቢ ውጤቶች ተገኝተዋል። ያም ሆኖ ዜጎች ውጭ ሄደው ለመስራት እስከፈለጉ ድረስ በሀገራችን ህገ መንግስት መሰረት የመንቀሳቀስ መብታቸው የተጠበቀ ነው።

ስደት ኢኮኖሚያዊ አንድምታ ያለው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ‘እኛ ያለን የሰው ሃይል ነው’ እንዳሉት፣ የሰው ሃይላችንን ህጋዊ በሆነ መንገድ ከተሰማራ ከ’ሪሚታንስ’ ገቢ ልናገኝ እንችላለን። ትልቁ ጉዳይ ይህን ታላቅ ሃብት በአግባቡ የማስተዳደር ጉዳይ ነው። እናም አዲሱ አመራር ይህን ሃብት በተገቢው ሁኔታ በመጠቀም መልሶ ሀገር ገንቢ የሚያደርግበት ጊዜ ሩቅ አይመስለኝም።

የትኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ለመስራት ካልፈለገና ‘በውጭ ሀገር ሰርቼ ሃብት አፈራለሁ’ ብሎ ካሰበ የሚከለክለው አካል አይኖርም። ምክንያቱም በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት ህገ መንግስታዊ እውቅናና ጥበቃ ያለው ነው። ማንኛውም ዜጋ በፈለገው ጊዜና ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራትና ሃብት የማፍራት የማይገሰስ ህገ መንግስታዊ መብት አለው። ይህን ማንም ሊቀለብሰው አይችልም። ይህን መብት መቃወም ህገ መንግስቱን መፃረር ነው።

ይህን ህገ መንግስታዊ መብት በአግባቡና ህጋዊ በሆነ ሁኔታ መጠቀም ይገባል። አንድ ዜጋ ባሻው ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ስላለው ብቻ ራሱን ለአደጋ ቤተሰቡን ደግሞ ለችግርና ለስጋት አጋልጦ ህገ ወጥ መንገድን መጠቀም የለበትም።

መንግስት ይህን የዜጎችን እንግልትና ችግር በመመልከት ዜጎች ለስራ ወደ ውጭ ሲጓዙ ከሞት፣ ከእንግልትና ከስቃይ ይላቀቁ ዘንድ ህጋዊ የአሰራር ማዕቀፍን አበጅቷል።

በውጭ አገር የስምሪት አዋጅ ተመርቶ በህዊ መንገድ ወደ ውጭ የስራ ስምሪት ማድረግ ራስን ከአደጋ ቤተሰብን ደግሞ ከሃሳብና ከሰቀቀን የሚታደግ ይሆናል። ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ይህን አዋጅ ተጠቅሞ በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ መጓዝ የህገ ወጥ ደላላዎችን መንገድ ይዘጋል። ህጋዊነትን ተቀብሎ በህግ አግባብ ማንኛውንም ነገር ማከናወን ራስን ከአደጋና ከውርደት በመጠበቅ የሀገርን ክብርም ማስጠበቅ እንደሆነ ተጓዦቹ ሊገነዘቡት ይገባል።

አዋጁን በማስፈፀምና የስርፀት ስራ የማከናወን ተግባር በክልሎች ውስጥ ጠንካራ ተግባር መሰራት ይኖርበታል። ምንም እንኳን ለህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መፍትሔው በመንግስት አዋጅ ላይ ብቻ የተጣለ ባይሆንም፤ የህገ ወጥ ዝውውሩ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት ህገ ወጥ ደላሎችን ህዝቡ በሚገባ ያውቃቸዋል። የትኛው ሰም ምን ዓይነት ተግባር እንደሚከወን፣ ተግባሩን መቼና እንዴት እንደሚፈፅመው ብሎም ሰንሰለቱ እስከየት ድረስ የተዘረጋ መሆኑ ከህዝቡ የተሰወረ አይደለም።

እርግጥ ህዝቡ በየቀየው የህገ ወጥ ዝውውሩ አቀናባሪና ስደተኞችን ወደ ሞት የሚገፉ እነማን እንደሆኑ ያውቃል። እናም ህዝባዊው ጥረት ከመንግስት ህጋዊ አሰራር ጋር እንዲቆራኝ ማድረግ ይገባል። ይህም ችግሩን ሙሉ ለሙሉ እንኳን ባይሆን ከግማሽ በላይ ሄዶ ለመቅረፍ በር ይከፍታል።

ዜጎችን በህጋዊ መንገድ በማሰማራት ራሳቸውን ጠቅመው አገራቸውን እንዲጠቅሙ ማድረግ እየተቻለ፤ በተሳሳተ መንገድ ተጉዘው የችግር ሰለባ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ይገባል። ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱ ተግባር የወገንና የአገርን ክብር የሚነካ እንዲሁም ለአላስፈላጊ ችግር የሚዳርግ በመሆኑ ነው።

በመሆኑም በየትምህርት ቤቶች የፀረ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ክበባትን በማቋቋም ህገ ወጥ ስደት በወጣቶች ላይ ስለሚያደርሰው ጉዳት እንዲሁም ወጣቶች ችግሩን ለመቋቋም ማከናወን ስላለባቸው እንቅስቃሴዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠት ያስፈልጋል።

የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዩች መስሪያ ቤቶችም ዜጎች ፓስፖርት ለማውጣት ወደ ቢሮአቸው ሲመጡ ስለ ህገ ወጥ ስደት አደጋ፣ በሀገር ላይ ስለሚኖረው የገፅታ ግንባታ ችግርና አገራችን የውጭ አገር የስራ ስምሪት ስምም የደረሰችባቸውን አገራት እንዲሁም በአዋጁ መሰረት ተጓዦች ማሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ብሎም የትኛዎቹ ኤጀንሲዎች ህጋዊ እንደሆኑ በቂ መረጃ መስጠት ይኖርባቸዋል።

ይህ ተግባር የአንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መሆን አለበት። መቋረጥ አይኖርበትም። ህገ ወጥ ስደት የዜጎችንና የአገርን ክብር የሚንድ መሆኑንና በህገ ወጥ መንገድ መጓዝ ተጠቃሚ ህገ ወጥ ደላላው እንጂ ተጓዡ ህይወቱን እስከማጣት እንደሚደርስ ከበቂ ማሰረጃ ጋር አስደግፎ ማስረዳት ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy