Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መዋቀስና መካሰስ – መች ሊረቡን

0 1,135

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መዋቀስና መካሰስ – መች ሊረቡን

 

ወንድይራድ ሃብተየስ

በእኔ እይታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ የአገራችንን ህመም ተረድተው መደሃኒት እንድታገኝ በማድረግ ላይ ናቸው። አገራችን ባለፉት 27 ዓመታት በርካታ ስኬቶችን አስመዝግባለች፤ በማስመዝገብም ላይ ትገኛለች። ይህ የሚያኮራን ነገር ነው።  ይሁንና ስኬቶች ያልናቸው ነገሮች ሁሉ አገራችንን ከሁከትና ነውጥ እንዳላዳኗት ስንመለከት የጎደለ ነገር እንዳለ ያመላክታል። የስኬቶቻችን ሁሉ ማስታሳሰረያ የሆነው ዋናው ነገር ፍቅርን፣ መቻቻልን፣ አብሮነትና ፍትሃዊነት በተሟላ መንገድ ማጎልበት ባለመቻላችን አገራችን ከሁለት ዓስርት ዓመታት ብኋላ ወደ ቀውስ አምርተናታል።

 

ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል ያህል አገራችን በሁከት፣ ግጭትና ቀውስ ውስጥ  እንድትዘፈቅ ምክንያት የሆነው ዋንኛው ነገር ግለኝነት ወይም ስግብግብነትና እኔ ብቻ የሚል አስተሳሰብ  መስፋፋቱ ነው። ፍቅር ሲቀዘቅዝ ግለኝነትና ስግብግብነት የነግሳል፤ አብሮነት ይላላል፤ አንድነት አደጋ ላይ ይወድቃል።  ካለፍቅርና ሰላም ሁሉም ነገር ከንቱ መሆኑን የተመለከትነው ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰላም ወጥተን መገባት ሲሳነን ነበር። ዛሬ ጠቅላያችን በቀደዱት መንገድ አገራችን ወደ ፍቅር ጉዞ ጀምራለች። ያለፈን መውቀስና መክሰስ ለፍቅር ስንቅ አይሆንም። እንደእኔ የትላንትን ወይም የደርግን ወይም የአጼዎቹን  ነገር እያነሳን መነታረኩ የለነገ ፍቅራችን ሚበጅ አይሆንም። ዛሬ ዘመኑ የይቅርታና የፍቅር በመሆኑ መንግስት ብቻ ሳይሆን ዜጎችም ሆደ ሰፊ ልንሆን ይገባል።

 

አገራችን  በርካታ ልዩነቶችን  ማስተናገድ የግድ ይላታል።  የልዩነቶች ማስተሳሰሪያው ብቸኛው መንገድ ደግሞ “ፍቅር፣ መቻቻል፣ አብሮነትና ፍትሃዊነት” ብቻ ናቸው። ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ  የፍቅር፣ የመቻቻልና አብሮነት መንገድን እንዴትና ምን እንደሆነ በተግባር አሳይተውናል። እኚህ ሰው ፍቅር እንዲሰፍን መቻቻል እንዲጎለብት  ያላደረጉት ጥረት የለም። ጥረታቸውም ስኬታማነቱ በተግባር ታይቷል። እርሳቸው እንዳሉት ማሰር ቀላል ነው፤ ማሳደድ ቀላል ነው፤ መግደል ቀላል ነው፤ የታሰረን መፍታት፤ የተሰደደን መመለስ፤ የተበላሸን ማቅናት  ግን እጅግ ከባድና ውስብስብ ነው። እኚህ ሰው እስረኞችን መልቀቅ ብቻ ሳይሆን ማስለቀቅም እንዴት እንደሚቻል በተግባር አሳይተውናል። አስርት ሺዎችን ከእስር ለቀዋል፤ በየአገሩም እየዞሩ ዜጎቻቸውን ከመከራና እንግልት ገላግለዋቸዋል። እንደእኔ እኚህ ሰው በ60 ቀናት የከናወኗቸው  የመቻቻልና የአብሮነት ተግባራት በአገራችን የ60 ዓመት ታሪክ ተከናውኗል ብዬ አላምንም። በእኔ አረዳድ በአገራችን የ60 ዓመት ታሪክ ይህን ያህል የይቅርታና የምህረት ወርዷል ብዬ አላስብም።

 

ከሁለትና ሶስት ወራት  በፊት የነበረው የአገራችን  ሁኔታ እጅግ አስፈርቶን በርካቶቻችን  ተስፋ ቆርጠን ነበር። የሰላማችንና የልማታችን  መሰረት የሆነውን የፌዴራል ስርዓታችንን አያያዙን ያወቅንበት  አይመስልኝም። “በእጅ የያዙት ወርቅ…” እንደሚባለው ሆነና የአንዳንዶች  ለአንድነታችንና ለአብሮነታችን ጠንቅ የሆኑ ተግባራትን ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ ተመልክተናል።  እንደኢትዮጵያ ላሉ በርካታ ልዩነቶች የሚስተዋሉባቸው አገራት የፌዴራል ስርዓት መተግበር  ብቸኛው አማራጭ ነው ለማለት ባልደፍርም የተሻለ አማራጭ እንደሚሆን ግን በዕርግጠኝነት መናገር ይቻላል።  “አንድ አይና በአፈር አይጫወትም” እንደሚባለው እኛም አካሄዳችንን አላሳምር ብለን አገራችንን ለአደጋ  አጋልጠናት ነበር። ዛሬ ነገሮች ተቀይረዋል። አገራችን የፍቅር ጉዞዋን ጀምራለች።

   

የዓድዋ ድል  ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በአንድ ጥላ ማሰባሳብ  የቻለ ዓለምን ያስደመመ ታላቅ ተጋድሎ ነው። የዓድዋ ድልን ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል በቀዳሚነት የሚነሳው ሁሉም ኢትዮጵያዊያን  በመካከላቸው ያሉትን በርካታ ልዩነቶች ወደጎን በማድረግ የጋራ ጠላታቸው የሆነውን የውጭ ወራሪ ለመመከት አባቶቻችንን ከያሉበት እንዲሰባሰቡ  ያደረጋቸው የአገርና የወገን ፍቅር ነው። የአፍሪካ አገሮች እዚህ ግባ በማይባል ትግል አገራቸውን ለአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች አሳልፈው ሲሰጡ አባቶቻችን  ደምና አጥንታቸውን ከስክሰው አገራቸውን መታደግ የቻሉት ለአገር ፍቅር ባላቸው የማይናወጥ አቋም ነው። ይህ ለእኛ ዛሬ ትምህርት ሊሆን ይገባል። ፍቅር ካለ ሞት አያስፈራም፤ ለዚህም ጥሩ ማሳያው  የአድዋ ጦርነት ነው። አባቶቻችን ለአገር ፍቅር፣ ለወገን ፍቅር ብለው ስንቅ፣ ጦርና ጋሻቸውን ተሸክመው፣ በባዶ እግራቸው ሺህ ኪሎሜትሮችን አቋርጠው አድዋ ላይ መስዋዕት ሆነዋል። ይህ ነው ፍቅር ማለት። የዛሬው ትውልድ ከዚህ ዘመን ከማያደበዝዘው  የአገርና የህዝብ ፍቅር ትምህርት ልንቀስም ይገባል።

አገራችን  ህብረብሄራዊ ናት።  ህብረብሄራዊነትን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መያዝ ከተቻለ የጥንካሬና የአንድነት ምንጭ ነው።  የተለያዩ ልዩነቶችንና ፍላጎቶችን ተቀብሎ ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሁኔታ ማስተናገድ የሚችል ሥርዓት መገንባት ከተቻለ ህብረ ብሄራዊነት የልዩነት ምንጭ መሆኑ ቀርቶ ጠንካራ አንድነትን ይመሰርታል። ብዝሃነት በህብረ ብሄራዊ የፌዴራል ሥርዓት ውስጥ የሚኖር  ትልቅ አሴት ሲሆን በህብረብሄራዊነትን ማስተሳሰሪያው ገመድ ደግሞ ፍቅር ነው። የፌዴራል ሥርዓታችን ብዝሃነትን ለማስተናገድ መልካም ዕድል የፈጠረልንና ያህል እኛ በአግባብ ተጠቅመንበታል የሚል እምነት የለኝም። ብዘሃነትን ማስተናገድ ማለት ልዩነቶችን ማክበር ማለት ነው፤ ልዩነቶችን ለማከበር ደግሞ ትልቁ ነገር  መቻቻል ማጎልበት ነው። የእነዚህ ሁሉ ማሰሪያው ደግሞ ፍቅር ነው።

 

በአገራችን የሚስተዋሉ  ልዩነቶችና ፍላጎቶች አጣጥሞ መጓግዝ  የሚቻለው በፍቅርና በመቻቻል ነው። በ21ኛው ክፍለ ዘመን የተለያዩ ልዩነቶችንና ፍላጎቶችን ደፍጥጠን  በሃይል አንድነት እናመጣለን የሚባልበት ወቅት አይደለም። አገራችን ብዝሃነትን ማስተናገድ የሚችል የፌዴራል ስርዓት  ዕውን አድርጋለች። ይህን ስርዓት መንከባከብ አቅቶን አገራችንን ለቀውስ ዳርገናት ነበር። አብሮነታችንን አጠናክረን ለመቀጠል ያለን ብቸኛ አማራጭ በልዩነቶቻችን ውስጥ ያለውን አንድነት ማጎልበት፤ ፍቅርን ማጠናከር ብቻ  መሆኑን በሳለፍናቸው 60 ቀናት ተረድተናል።

ልዩነታችንን ሊያሰፉ ህዝብን  ሊያራርቁ የሚችሉ ነገሮች አገራችንን ለቀውስና ሁከት መዳረጋቸውን መንግስት ተረድቶ አሁን ላይ  የይቅርታና የምህረት ዘመን እንዲሆን በርካታ ስራዎችን በማከናወን ላይ ነው። ይህ መልካም ጅምር ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል። በቀል ማንንም አሸናፊም  ሆነ ተጠቃሚ አድርጎ አያውቅም። የፌዴራል ስርዓታችን የአዲሲቷ ኢትዮጵያ እስትንፋስ መሆኑን ተረድተን ልንከባከበው ይገባል። በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሸሸጉ ጥቅመኞች ለህዝብና  አገር ተቆርቋሪ በመምሰል ህዝቦችን ለማራራቅ የሚያደርጓቸውን ተግባራት ማጋለጥ የሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ሃላፊነት ሊሆን ይገባዋል።

 

አንዳንድ ሚዲያዎችም የወቅቱን ነበራዊ ሁኔታዎች በቅጡ አልተረዱትም አሊያም ግጭቶቹን በማራገብ የሚያገኙት ጥቅም ያለ በሚመስል ሁኔታ የግጭት ቆስቋሽ እንደነበሩ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። እንደእኔ እይታ  የሚዲያዎች ተግባር መሆን ያለበት ግጭቶች የሚበርዱበትን፣ ህዝቦች የሚረጋጉበትን፣ ተበዳዮች የሚካሱበትን እንዲሁም ጥፋተኞች ለህግ ተላልፈው የሚሰጡበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንጂ ግጭቶችን በሰበር ዜና መለፈፍ ለየትኛውም ወገን የሚበጅ  አካሄድ አይሆንም። መንግስትም እነዚህን የጥፋት ሃይሎች በአግገባብ በመለየት ሁሉም እንደየጥፋቱ ተጠያቂ የሚሆኑበትን አሰራር መዘርጋት ይኖርበታል።

 

እያስመዘገብናቸው ያሉ ስኬቶችን በማጎልበት እንዲሁም የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በመሙላት የአገራችንን ህዳሴ ማስቀጠል የዚህ ትውልድ ፈንታ ሊሆን ይገባል።  የኢኮኖሚ ስኬቶቻችን አገራችንን ከሁከትና ነውጥ መታደግ የተሳናቸው ዋንኛው ምክንያት የፍትሃዊነት ክፍተት ስለሚስተዋልባቸው እንደሆነ ይሰማኛል። ይህም ክፍተት መታከም  የሚገባው ጉዳይ ነው። የአገራችን መሰረታዊ ችግሮች መፍትሄ የሚያገኙት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትንና ፍቅርን ማንገስ ሲቻል ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ዕውን የሚሆነው ጠቅላያችን በቀደዱት መንገድ  መጓዛችንን አጠናክረን ስንቀጥል ብቻ ነው። ያለፈን መውቀስና መክሰስ ለፍቅር ጉዟችን ስንቅ አይሆንም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy