Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተስፋችን…

0 311

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተስፋችን…

                                                            ይሁን ታፈረ

ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገራችን ተከስቶ በነበረው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ የተነሳ የልማት ትብብርና ድጋፍ ማግኘት አስቸጋሪ ቢሆንባትም፣ አሁን ሁኔታዎቹ እየተለወጡ በመሆናቸው የልዩ ልዩ ትብብሮች፣ የቱሪስትና የኢንቨስትመንት ስበቶች መጨመር ችለዋል። ይህ ለውጥ የታየው ኢትዮጵያ ተስፋ ያላት አገር ስለሆነች ነው።

በአሁኑ ወቅት የልማት ፋይናንስ ድጋፍ የሚሰጡ አካላት ይህን የለውጥ ሂደት ለመደገፍ ቁርጠኛ ሆነዋል። እርግጥ እነዚህ የልማት ፋይናንስ ድጋፍ ሰጪ አካላት ገንዘባቸውን ዝም ብለው ሜዳ ላይ አይጥሉም። ገንዘባቸውን አውጥተው ከእኛ ጋር ለመስራት የሚፈልጉት እንደ አገር ያለንን ሁለንተናዊ ቀመና እና ተስፋችንን ስተገነዘቡ ነው። ኢትዮጵያ መደገፍ ከቻለች ከራሷ አልፋ ሌሎችን መጥቀም ትችላለች የሚል እምነት ስላላቸው ነው።

ይህን ሃቅ ብሉምበርግ የተሰኘው የሚዲያ አውታር “ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቻይና ነች” በማለት ያተተውን ዘገባ የሚያስረዳ ነው። ዘገባው ይህ ሁኔታ የተፈጠረው ኢትዮጵያ ለእድገቷና ለብልጽግናዋ መሰረት የህዝቧ ታሪክ፣ ጽናትና ተስፋ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ይገልፃል። ሌሎች ስኬቶቻችን እንደተጠበቁ ሆነው፣ በዚህ ረገድ የተገኘው ዲፕሎማሲያዊ እመርታም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

“አፍሪካዊቷ ቻይና” የተባለችው ኢትዮጵያ በዕድገት ግስጋሴ ላይ ትገኛለች። ላለፉት ሶስት ዓመታት ያህል ተቀዛቅዞ የነበረው የአገራችን ኢኮኖሚ ዛሬ የሚያንሰራራበትን ዕድል አግኝቷል።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዛሬ እንደ ትናንቱ ጦርነት ያንዣበበትን የሰቆቃ ህይወት መምራት አይፈልጉም። በጆሯቸው ላይ የጥይት አረሮች አይጮሁም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እንዳሉት ዛሬ ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን ለማምጣት ኢትዮጵያዊያን መሞት አይገባቸውም። ዛሬ በተገኘው አንጻራዊ የሰላም ቁመና ታጅበውም ህዳሴያቸውን ዕውን ለማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዘው ቆመዋል። በሰላማቸውና በመረጋጋታቸው ዕድገታቸውን ለማረጋገጥ ዝግጁ ሆነዋል። እናም እዚህም ሆነ እዚያ ይህን የሰላምና የመረጋጋት መንገድ እንዳይዘጋ ይፈልጋሉ። እነርሱን በማመንም መንግስት በመላ አገሪቱ ታውጆ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ አድርጓል።

እርግጥ በየትኛውም ሀገር ውስጥ እውን እንዲሆን የሚፈለግ ሰላም ያለ ህዝቡ ተሳትፎ ምንም ዓይነት ውጤት ሊያመጣ አይችልም። የሰላም ዋጋን ዋነኛ መዛኙ ኃይል ህዝብ ነው። ህዝብ ጥቅሙን የማያውቀው ሰላም ዕውን ሊሆን አይችልም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲነሳ ይህን የህዝብን ትክክለኛ አስተሳሰብ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው።

እርግጥም ለአንድ ሀገር ልማትና ዕድገት ሰላም ከምንም በላይ የገዘፈ ዋጋ ያለው መሆኑ አያጠያይቅም። እንደ እውነቱ ከሆነ የሰላም ዋጋ በምንም አይነት ምድራዊ ዋጋ ሊለካ የሚችል አይመስለኝም። ሰላም የሚተመንበት አሊያም የሚሰፈርበት ልኬት አለው ሊባል የሚችልም አይመስለኝም። ከግለሰብ የነገ ማንነት ህልም ጀምሮ እስከ የሀገር ህዳሴ ዕውን መሆን ድረስ ሰላም ዋጋው እጅግ የገዘፈ ነው። አዎ! የአንድ ሀገር ሰላም የልማቷ መሰረት ነው።

በመሆኑም ዜጎች መብትና ግዴታዎቻቸውን ሲያውቁና ሌላውን ለማስተማር ሲነሳሱ የሀገር ሰላም ይረጋገጣል። ልማትና ዕድገትም ይደረጃሉ፤ ዴሞክራሲያዊ እሴቶችም በዚያው መጠን እያበቡ ይሄዳሉ።

እርግጥ የአገርን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ የመንግስት ብቻ አይደለም—ዋነኛው ተዋናይ የሆነው የሀገራችን ህዝብ ጭምር እንጂ። ህዝቡ በያለበት ሆኖ ሰላሙን ከጠበቀ ሰላምን ለማደፍረስ የሚሮጥ የትኛውም ሃይል አቅም ሊኖረው አይችልም። ይህም የተጀመረው የልማይ ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው።

ብሉምበርግ የዜና አውታር “አፍሪካዊቷ ቻይና” ያላት አገር በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አጭር የስልጣን ጊዜ ውስጥ ከነበረችበት ከፍታ ወደ ላይ እየተመለከተች ነው። ሀገራችን ባለፉት ስድስት ዓመታት ዕውን እንዲሆኑ ያደረገቻቸው የልማት ዕቅዶች የነበረንን የዕድገት ፍጥነት ይበልጥ ያጎኑት ናቸው። በተለይም የመጀመሪያው የልማት ዕቅድ እጅግ በጣም የተለጠጠና ሊደረስበት የማይችል መስሎ ቢቀርብም፤ ሀገራችን አብዛኛዎቹን የዕቅዱን ውጤቶች ማሳካት ችላለች። ለሁለተኛው ዕቅድም ተሞክሮ በመውሰድ የልማት ትልሟን እያፋጠነች ትገኛለች። በተለይም በሁለተኛው የልማት ዕቅድ መጨረሻ ላይ መዋቅራዊ የምጣኔ ሃብት ለውጥ ለማምጣት ተግታ እየሰራች ነው።

ኢትዮጵያ የምትከተለው ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ከቀጣናው የምጣኔ ሃብት መሪነት ወደ አፍሪካ ተምሳሌታዊ አዳጊነት ሊዘል እንደሚችል ግልጽ ነው። ትናንት በተለያዩ ውጣ ውረዶች ውስጥ ከባዶ ካዝና ተረካቢነት ተነስቶ የቀጣናው ምጣኔ ሃብት መሪ መሆን ከተቻለ፤ በአንፃራዊ የሰላም ሁኔታ ውስጥ ወደ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማማነት ተሻግረናል። ቀዳሚነቱንም ከጋና ወስደናል።

አገራችን የተለመችው በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በተቻለና አቅም በፈቀደ መንገድ እንኳን ማከናወን ከተቻለ በኢኮኖሚው ውስጥ መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት “አፍሪካዊቷ ቻይና” የሚያደርጋት ነው። በተለይ ምርጥ ተሞክሮ ያላቸውን አርሶ አደሮች ውጤት ወደ ሌሎች አርሶ አደሮች በማስፋፋት የዋና ዋና ሰብሎችን ምርት በእጥፍ ለማሳደግ ከተቻለ ይህን መሆን አያቅትም።

የግብርናውን ዘርፍ አማካይ ዓመታዊ ዕድገት በመሠረታዊ አማራጭ ከነበረው 8 በመቶ ወደ 11 በመቶ ከፍ ማድረግ ከተቻለና ለኢንዱስትሩው ሽግግር ምቹ ሁኔታን እንዲፈጥር ከተደረገ የሚፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት ይቻላል። ያም ሆኖ  የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተቃኘው በመሰረታዊ የዕድገት አማራጭ ላይ ተመስርቶ በመሆኑ ህዝብና መንግስት ተናብበው ከሰሩ ዕቅዱን ማሳካታቸው አይቀርም። ይህም ህዳሴያቸውን የሚያሳልጥ ነው።

አሁን በተጀመረው በህዳሴ ጉዟችን ዙሪያ እየተፈጠረ የመጣው አገራዊ መግባባት እየጐለበተ ሲሄድ እንዲሁም ዜጎች ውጤቱን እያዩና ተጠቃሚ እየሆኑ ሲመጡ መነቃቃቱ ይጨምራል። ይህም ማህበራዊ አገልግሎቶችንና የኢኮኖሚ መሠረተ ልማቶችን ለዜጐች በጥራት የማስፋፋት አቅምን በመጨመር ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ከፍ ያደርጋል። በዚህም ሳቢያ በአገር አቀፍ የሚታየውን ድህነትና ሥራ አጥነት በመቅረፍ ረገድ ፈጣንና መሰረተ-ሰፊ ዕድገቱ ሚናውን እንዲወጣ ያስችላል።  

በአገራችን ውስጥ እየተከናወነ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ እመርታ በማምጣት በቀላል ማኑፋክቸሪንግ ሀገራችንን ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር ማድረግ ላይ ያለመ ነው። ይህን ለማረጋገጥ አሁን ባለው ሁኔታ ከፍተኛ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች እና ጥራት ያለው የውጭ ኢንቨስትመንት በከፍተኛ ደረጃ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲገቡ እየተደረገ ነው። መንግሥትና ህዝብም ከሁሉም የላቀ ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚታዩ ዋና ዋና እንቅፋቶችን ለመፍታት ውይይት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

መንግሥትና ህዝብ በሁለተኛው የልማት ዕቅድ የሁለት ዓመት ተኩል አጋማሽ አፈፃፀም ላይ የተገኙትን ውጤቶችና የታዩትን ተግዳሮቶች በመመልከት፤ የሚግባቡባቸውን ጉዳዮች ነቅሰው በማውጣት ጥንካሬዎቹን የማጎልበትና ክፍተቶቹን የመሙላት ስራዎችን መከተል ይኖርባቸዋል። ለዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ በመጎልበት ላይ ያለውን የዲፕሎማሲ መንገድ በመጠቀምና ራሳቸውን ለዓለም የበለጠ በማሳየት ህዳሴያቸውን ማረጋገጥ አለባቸው። ይህም በአገር ደረጃ የተገኘውን የመልማት ተስፋችንን ይበልጥ ከፍ የሚያደርገው ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy