Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተደምረን እንበርታ

0 541

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተደምረን እንበርታ

ኢብሳ ነመራ

በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎትና ግፊት አዲስ ወይም የተሃድሶ አመራር ወደሃላፊነት  በቅ ማለት ከጀመረ ሁለት ዓመታት ሊያስቆጥር ነው። በ2008 ዓ/ም መግቢያ ላይ በተለይ በኦሮሚያ የተቀሰቀሰውና በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የተካሄደው በአመዛኙ ወጣቶች የተሳተፉበት ተቃውሞ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በዋዛ ሊያለፈው የማይቻለው ችግር እንዳለበት እንዲገነዘብ አድርጎታል። በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው ንቅናቄ በሌሎች ክልሎችም አንዳንድ አካባቢዎች ተዛምቶ ኢህአዴግ በመጣበት መንገድ መዝለቅ እንደማይችል፣ በመጣበት መዝለቅ አለመቻል የኢህአዴግ ችግር ብቻ ሳይሆን ሃገሪቱን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን ተገንዝቦ ችግሮቹን ለማከም በሚያስችለው ልክ ለመታደስ ወሰነ። ይህ የተሃድሶ እርምጃ በተለይ ሃያል ህዝባዊ ተቃውሞ በተካሄደበት የኦሮሚያ ክልል በ2008 ዓ/ም ማገባደጃ ላይ ውጤት ይዞ ብቅ አለ፤ አዲስ የክልላዊ መንግስት የአመራር ቡድን ይዞ።

ይህ የኦሮሚያ ክልል አዲስ አመራር የለውጥ ሃዋርያ ሆኖ ወጣ። በክልሉ ውስጥ ከዚያ ቀደም በነበሩት ሁለት ተኩል አስርት ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በህዝቡና በአመራሩ መሃከል መተማመን ተፈጠረ። ህዝብ ጌታዬ ነው ብሎ ራሱን ለህዝቡ የቀረበው አዲሱ አመራር፣ በክልሉ የተንሰራፋውን የመልካም አስተዳደርና የፍትህ መጓደል፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና የወጣቶች የስራ አጥነት ችግር ወዘተ ሊያቃልል ይችላል፤ ቢያንስ ችግሮቹን ለማቃለል ቁርጠኝነት አለው በሚል በህዝብ ታመነ። ይህ ታይቶ የማይታወቅ የህዝብ አመኔታ ያገኘ አመራር፣ የአሁኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የያዘው የእነ አቶ ለማ መገርሳ ቡድን ነው።

የኦሮሚያን ክልል በሚያስተዳድረው የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) እና በክልላዊ መንግስቱ ውስጥ የተካሄደው የመታደስ እርምጃ በሌሎች የኢህአዴግ እህት ድርጅቶችና ክልላዊ መንግስታትም ውስጥ ቀጠለ። እነሆ አሁን በመላ ሃገሪቱ በህዝብና በመንግስት መሃከል መተማመን የተፈጠረበት፣ በህዝቡ ዘንድ መጪው ዘመን ብሩህ ነው የሚል ተስፋ የተፈጠረበት ወቅት ላይ ደርሰናል።

አሁን ስለምንገኝበት ጊዜ ይህን ያህል ብዬ፣ በጊዜ ጎዳና ላይ ወደኋላ ለመልሳችሁ። ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ እድሜ ባስቆጠረ የሃገሪቱ ታሪክ ውስጥ ሁለት ተጻራሪ አመለካከቶች ውጥረት ነግሶ ኖሯል። ውጥረቱ በአንድ ወገን የብሄራዊ ነጻነትና እኩልነት ጥያቄ ባነሱ ህዝቦች፤ በሌላ በኩል የብሄራዊ ነጻነትና እኩልነት ጥያቄውን እንደሃገር አንድነት ስጋት በሚመለከቱ ወገኖች መሃከል የተፈጠረ ነበር። ይህ የሃገሪቱ መሰረታዊ የፖለቲካ ቅራኔ የነበረ መሆኑ ላይ ብዙዎች ይስማማሉ።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት ፌደራላዊ ስርአት ከተገነባ በኋላ የቅራኔው ምንጭ የሆነው ብሄራዊ ጭቆና ቢወገድም፣ በሁለቱ አመለካከቶች መሃከል ፍትጊያው ቀጥሏል። የብሄራዊ መብት ጥያቄያቸው የተመለሰላቸው ህዝቦች ፌደራላዊ ስርአቱን ጠብቀው ለማቆየት፣ በሌላ በኩል የብሄሮች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር የሃገር አንድነትን ለመፍረስ አደጋ አጋልጧል የሚሉት ደግሞ ፌደራላዊ ስርአቱን ቢያንስ በአወቃቀር ለመለወጥ ያላቸው ፍላጎት ነበር ፍትጊያውን የፈጠረው።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና ክልሉን የሚያስተዳድረው ገዢ ፓርቲ ኦህዴድ በአንዳንድ ወገኖች ለሃገር አንድነት እንደስጋት ከሚታዩት ወገን ቢሆንም፣ በክልሉ ወደሃላፊነት የመጣው የተሃድሶ አመራር ከሚጠረጠርበት ባህሪው የተለየ ሆኖ ተገለጠ። የተሃድሶ አመራሩ የብሄራዊ ማንነት ልዩነት የአንድነት መሰናክል ሳይሆን የጠንካራ ኢትዮጵያዊ አንድነት መሰረት ሊሆን ይችላል የሚል አጀንዳ ግንባር ቀደም አራማጅ ሆነ። ይህ በተለይ በክልሉ ርእሰ መስተዳድር የሚመራ፣ የአሁኑ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የክልሉን አመራሮች፣ አባገዳዎች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች ይዞ ወደአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በተጋዘው የልኡካን ቡድን በይፋ ተገለጠ። ይህ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር የተካሄደ ጉባኤና ፌስቲቫል በፌደራላዊ ስርአቱ ስር ያሉ ክልሎችና ክልሎችን የሚያስተዳድሩ ብሄራዊ ድርጅቶች የሃገር አንድነት ስጋት እንዳልሆኑ በተጨባጭ እንዳመላከተ እርምጃ ሊወሰድ ይችላል።

ይህ በሆነ በወራት ውስጥ የኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተፈጠረው የተሃድሶ አመራር ቡድን አባል የሆኑት ዶ/ር አብይ አህመድ ወደኢህአዴግ ሊቀመነበርነት ብሎም ወደኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርነት መጡ። በዚህም በኦሮሚያ የታየው፣ በህዝብና በመንግስት መሃከል የመተማመን መንፈስ፣ የለውጥ መነቃቃት፣ ተስፋ፣ የሃገራዊ አንድነት መንፈስ ወደመላው ኢትዮጵያ መጣ። ዶ/ር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በተሰየሙበት ስነስርአት ላይ ባደረጉት ንግግር ለጠንካራ ኢትዮጵያዊ አንድነት ልዩ ትትኩረት እንደሚሰጡ አረጋገጡ። ኢትዮጵያዊ አንድነትን አስመልክተው ከተናገሯቸው መሃከል፤

አማራው በካራ ማራ ለሃገሩ ሉአላዊነት ተሰወቶ የካራ ማራ አፈር ሆኖ ቀርቷል። ትግራይ በመተማ ከሃገሬ በፊት አንገቴን ውሰዱ ብሎ የመተማን አፈር ሆኗል። ኦሮሞው በአድዋ ተራሮች ላይ ስለሃገሩ ደረቱን ሰጥቶ የሃገሩን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ከአድዋ አፈር ተቀላቅሏል። ሱማሌው፣ ሲዳማው፣ ቤኒሻንጉሉ፣ ወላይታው፣ ጋምቤላው፣ ጉራጌ፣ አፋሩ፣ ስልጤው፣ ከምባታው፣ ሃድያው፣ እና ሌሎቹም የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ በባድመ ከሃገሬ በፊት ብለው እንደወደቁ ከባድመ አፈር ጋር ተዋህደዋል። አንድ ኢትዮጵያዊ አባት እንዳሉት፣ እኛ ስንኖር ሰዎች፣ ስናልፍ አፈር፣ ስናልፍ ሃገር እንሆናለን። የየትኛውም ኢትዮጵያዊ ክቡር ስጋና ደም በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ አፈር ሆኖ ታገኙታላችሁ። ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ እንሆናለን።

የሚለው ተጠቃሽ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዳሉት፣ የተለያየ ቋንቋ፣ ባህልና ወግ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሃገራቸውን የእነርሱ ቃንቋ ተናጋሪ በሚኖርበት መልከዓምድር አጥረው አየተመለከቱ አልኖሩም። ከደቡብ ጫፍ፣ ከምእራብና ምስራቅ ጠርዝ የጣሊያንን ወራሪ ሃይል ለመመከት አድዋ የዘመቱት ለዚህ ነው። ኦሮሞው፣ ሲዳማው፣ ወላይታው፣ ጉራጌው . . . ከአባይ ማዶ ወዳለ መሬት የዘለቀ ጠላት ሃገሬን እንደነካብኝ አይቆጠርም ብለው  በየሚኖሩበት ምድር ተከለለው አልተቀመጡም። ኢትዮጵያን እንደነጻነት ምድራቸው ስለሚያስቡ ነጻነታቸውን ጠብቀው ለትውልድ ለማስተላለፍ ህይወታቸውን ለመሰዋት ቆርጠው ዘምተዋል። በየቋንቋቸው እየፎከሩ፣ እንደየባህላቸው ታጥቀው፣ በየባህላቸው ስልት ሊዋጉ ነበር የዘመቱት። የአድዋ ጦርነት በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነት የተንጸባረቀበት የታሪክ አምድ ነው። ይህ የኢትዮጵያ ህዝቦች በአንድ ግንባር ተሰልፈው፣ ደማቸውን አፍሰው በአንድ ጉድጓድ እንዲቀበሩ ያደረገ የነጻነት ቀነአዊነት የአንድነታቸው ውል ነው። ኢትዮጵያዊነት ከብሄር ልዩነት በላይ ያለ ነጻነትን በሚያህል ውድ እሴት የተሳሰረ የአንድነት እሳቤ ነው። እናም ኢትዮጵያዊ አንድነት ሊከበርና ዘላቂነቱ ሊጠበቅ ይገባል።

እንግዲህ በኢትዮጵያውያን መካከል ያለው ልዩነት የቋንቋና የባህል ብቻ አይደለም። በፖለቲካ አመለካከትም ይለያያሉ። የአመለካከት ልዩነቱ  ከብሄር እኩልነትና ነጻነት ጥያቄ፣ ራስን በራስ ከማሰተዳደር ጥያቄ ወዘተ ጋር የተገናኘ ብቻ ሳይሆን ከዚህ የተሻገረ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለም ልዩነትንም ይጨምራል። ምንጩ ምንም ይሁን ምን ልዩነት አለ። ዋናው ነገር የአመለካከት ልዩነት የኢትዮጵያ አንድነት ስጋት እንዳይሆን ማድረግ ላይ ነው ያለው። ዶ/ር አብይ አህመድ የአመለካከት ልዩንትን አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በተሰየሙበት ስነስርአት ላይ ባደረጉት ንግግር የሚከተለውን ብለው ነበር።

በአንድ ሃገር ውስጥ የሃሳብ ልዩነቶች ይኖራሉ። የሃሳብ ልዩነት እርግማን አይደለም። ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ መደማመጥና በመርህ ላይ ተመስርተን መግባባት ስንችል የሃሳብ ልዩነት በረከት ይዞልን ይመጣል። በሃሳብ ፍጭት ውስጥ መፍትሄ ይገኛል። በመተባበር ውስጥ ሃይል አለ። ስንደመር እንጠነክራለን። አንድነት የማይፈታው ችግር የለም፤ ሃገር ይገነባል። ‘የእኔ ሃሳብ ካላሸነፈ ሞቼ እገኛሉ’ ማለት ግን እንኳን ሃገርን ሊያቆም ቤተሰብ ያፈረሳል። ያለችን አንድ ኢትዮጵያ ነች። ከየትኛውም ፖለቲካዊ አመለካከት በላይ  ሃገራዊ አንድነት ይበልጣል። አንድነት ማለት ግን አንድ አይነትነት ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል። አንድነታችን ልዩነታችንን ያቀፈ ብዝሃነታችንን በህብረ ብሄራዊነት ያደመቀ መሆን አለበት።

እንግዲህ፤ በኢትዮጵያ የአመለካከት ልዩነትን የሚያስተናግድ ስርአት በማጣት በሚሊየን ለሚቆጠሩ ዜጎች ህይወት መጥፋትና ስደት ምክንያት የሆኑ ግጭቶች አጋጥመዋል። ከ1967 እስከ 1983 ዓ/ም የነበረውን ሁኔታ ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እነዳሉት፤ የእኔ ሃሳብ ካላሸነፈ ማለት እንኳን ሃገርን ሊያቆም ቤተሰብ ያፈርሳል። ይህን ቅድመ 1983 በመላ ሃገሪቱ ይካሄድ በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት በተግባር አይተነዋል።

ከ1983 ዓ/ም በኋላ የአመለካካት፣ አመለካከትን በይፋ የመግለጽ፣ የማራመድ ወዘተ መብት ህገመንግስታዊ እውቅና ቢያገኝም፣ በአተገባበር ላይ ግን ክፍተቶች ታይተዋል። የአፈጻጸም ክፍተቱ በአመዛኙ ዴሞክራሲ የሚጠይቀውን መቻቻልና መከባበር ካለመለማማድ የመነጨ ነው። ይህ ችግር በመንግስትና በገዢው ፓርቲ በኩል ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚነት በተሰለፉትም ወገን ያለ ነው፤ ሁለቱም ወገኖች የዴሞክራሲ ተለማማጆች በመሆናቸው።

ኢትዮጵያውያን የአመለካከት ልዩነት ቢኖራቸውም፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በመሆናቸውና ከልዩነት በላይ የሚጋሩት እሴት ስላላቸው ኢትዮጵያዊ አንድነታቸውን ሊዘነጉ አይገባም። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዳሉት፤ የሃሳብ ልዩነት እርግማን አይደለም። ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ መደማመጥና በመርህ ላይ ተመስርተን መግባባት ስንችል የሃሳብ ልዩነት በረከት ይዞልን ይመጣል። ልዩነት በረከት ይዞ መመጣት የሚችል ከሆነ፣ አንድነት የሚለውን እሳቤ መመሳሰል አድርገን ብቻ መወሰድ አይኖርብንም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ አንድነት ማለት አንድ አይነትነት ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል። አንድነታችን ልዩነታችንን ያቀፈ፤ ብዘሃነታችንን በህብረብሄራዊነት ያደመቀ መሆን አለበት።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በልዩነት ውስጥ ያለ ኢትዮጵያዊ አንድነትን በንግግር ብቻ በመግለጽ አልተገደቡም። በብሄራዊ ጥያቄም ይሁን ከዚህ ውጭ በሆነ ርዕዮተዓለማዊ አመለካካት ተደራጅተው በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት ለሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል። አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪውን በመልካምነት ተቀብለውታል። በዚህ ጥሪ መሰረት በውጭ ሃገር ሲንቀሳቀስ የነበረው አንጋፋ የኦሮሞ የነጻነትና የእኩልነት ታጋይ በነበሩ ግለሰቦች የተደራጀው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) አመራሮች  በሃገር ቤት ለመስራት በቅርቡ ወደሃገር ቤት መጥተዋል።

ይህ ብቻ አይደለም። የተለያየ አመለካካት ሲያራምዱ የነበሩና በተለያየ የወንጀል ክስ ጥፋተኛ ተብለው የተፈረደባቸውና በክስ ሂደት ላይ የነበሩ ፖለቲከኞች በይቅርታና ክሳቸው ተቋርጦ እንዲፈቱ ተደርጓል። ይህ የአመለካካት ልዩነትን መሸከም የሚችል የፖለቲካ ምህዳር የመፍጠርና በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነትን ለማጠናከር የተወሰደ እርምጃ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎረቤት ሃገራትና በመካከለኛው ምስራቅ ሳኡዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ባደረጉት ጉብኝት፣ በሃገራቱ በተለያየ መክንያት የታሰሩ ኢትዮጵያውያን ይቅርታ ተደርጎላኘው እንዲፈቱ ጠይቀው ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቷል። ይህ እርምጃ በየትኛውም የዓለም አካባቢ በስደትም የሁን በዜግነት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው እንዲኮሩ አድርጓል። ይህ በሃገር የመኩራት ስሜት ለኢትዮጵያዊ አንድነት መሰረት ነው።

በአጠቃላይ፤ አሁን ሃገሪቱን እየመራ ያለው የተሃድሶ አመራር ከልዩነት በላይ ያለ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለመገንባት ተነሳሽነት ወስዶ እየሰራ ነው። እስካሁን በተወሰዱ እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል። የእስካሁኑ ውጤቶች በቀጣይ ድንቅ ወጤቶችን ማምጣት እንደሚቻል ያመላክታሉ። ኢትዮጵያዊ አንድነት ሃገሪቱን ከወራሪ ጠብቆ ነጻነቷን ማስከበር ችሏል። ይህ ኢትዮጵየዊ አንድነት ለዘላቂ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መከበር፣ ሰላም፣ ልማትና ብልግና መሰረት ነው። ኢትዮጵያውያን አንድነት ካለን ሰላም ይኖረናል፤ ሰላም ካለን እንበለፅጋለን። እናም ልዩነት ቢኖረንም በልዩነታችን ከመራራቅ ይልቅ ተደምረን እንበርታ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy