Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኑ! ለውጡንና መሃንዲሱን እንደግፍ!

0 797

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኑ! ለውጡንና መሃንዲሱን እንደግፍ!

                                              እምዕላፍ ህሩይ

ዕለተ ቅዳሜ። ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም። ለየት ያለ የሰላማዊ ሰልፍ ትዕይንት ተጠርቷል። ህዝቡ ጠሪም ተሰላፊም ነው። በአዲስ አበባ ከተማ፤ መስቀል አደባባይ። አደባባዩም ሰላምን፣ ፍቅርንና ይቅርታን በሚዘምሩ እድምተኞች ሲደምቅ ይታየኛል። በተለይ የከተማችንና በአቅራቢያው የሚገኙ ከተሞች ህዝቦች በሀገራቸው እየተካሄደ ያለውን የለውጥ ሂደትና የተግባሩን መሃንዲስና የፍቅር ሰው፤ ዶክተር አብይ አህመድን ለመደገፍ በነቂስ መስቀል አደባባይ ላይ አሸብርቆ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል፤ ሁለት ሚሊዮን ያህል ህዝብ።

 

መጪዋ ቅዳሜ የድምቀት ቀን ናት። ቀለል ባለ የሂሳብ ስሌት ምሳሌ ወስደን ብንሰራ እንኳን፤ በመዲናችንና በዙሪያዋ የሚገኙ ከተሞች ነዋሪዎች ብዛት ስድስት ሚሊዮን ቢሆን፤ ከስድስቱ ሰው ውስጥ ሁለቱ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ይገኛሉ ማለት ነው። ቅዳሜ የሳምንቱ መጨረሻና የገበያ ቀን እንዲሁም ሁሉም ሰው ግብይቱንም ሆነ ስራውን የሚያጠናቅቀው በዚህ ዕለት ከመሆኑ አንፃር፤ በእውነቱ በሰልፉ ላይ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ቁጥር ቀላል አይደለም። እጅግ ከፍተኛ ነው። ታዲያ የዚህ ቁጥር አካል አሊያም ተደማሪ ሆኖ መገኘት መታደል ጭምርም ይመስለኛል። ምክንያቱም በሀገር ጉዳይ ያለ አንዳች መሸማቀቅ ስሜትን በመግለፅ ዴሞክራሲን ተግባራዊ ማድረግ ስለሆነ ነው።

ይህ ህዝብ ማንም የጠራውና የቀሰቀሰው አካል የለም። በራሱ ፍላጎት ለውጡንና መሃንዲሱን ደግፎ ሰልፍ የሚወጣ ነው። ይህ ህዝብ ማንም ካናቴራ ሰጥቶት የሚለብስ አይደለም—ራሱ በውድ ዋጋ ገዝቶ አሊያም አዘጋጅቶ ወደ ሰልፉ አደባባይ የሚያቀና ነው። ይህ ህዝብ ማንም መፈክር አንግቦ እንዲወጣ ያደረገው አይደለም። የተፃፈን መፈክር በመግዛት ወይም ራሱ ፅፎ አደባባይ ለመገኘት የወሰነ ነው። እንደ እኔ ዓይነቱ ጦማሪ ደግሞ ማንም አዞት የሚፅፍ አይደለም፤ በየማህበራዊ ሚዲያው በራሱ ተነሳሽነት የሰላም መቅረዝን ከፍ አድርጎ በህገ መንግስቱ መሰረት ለውጡንና መሃንዲሱን ለመደገፍ ውስጡ ፈንቅሎት ሃሳቦችን እያነሳ የሚጥል እንጂ።…አርሶ አደሩ፣ ነጋዴው፣ የመንግስትና የግል ሰራተኛው…ወዘተርፈም እንዲሁ ነው።

አዎ! የሰላማዊ ሰልፈኛው ተግባር በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠውን ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቶቹን በአደባባይ ማረጋገጥ ነው። በዚህም ለውጡን እንዲሁም የአንድነት፣ የእርቅ፣ የፍቅርና የይቅርታ ቀያሽ መሃንዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን በመደገፍ በሀገራችን ጉዳይ ዋነኛ ተዋናይ ሆኖ መገኘት ብቻ ነው፤ ፍላጎቱ። ለዚህም ነው ‘ኑ! ለውጡንና መሃንዲሱን እንደግፍ!’ ያልኩት።

ለውጡንና መሃንዲሱን አለመደገፍ አይቻልም። ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ተጠቅመን ለሰላማዊ ሰልፍ ቅዳሜ የተጠራራነው ዜጎች፤ በሀገራችን ውስጥ እየሰፈነ ያለው የሰላም ድባብ ትክክለኛ፣ እርቅና ይቅርታ አስፈላጊ፣ አንድነትና ብሔራዊ መግባባት ተገቢ እንዲሁም ቀደም ሲል ያጣነው ትልቁ ግንድ ኢትዮጵያዊ ኩራት እጅግ ወሳኝ መሆናቸውን የምንገነዘብ ነን።

ባለፉት ሶስት ዓመታት በአንዳንድ አካባቢዎች በሚነሳ ሁከት ስንታመስ እንዲሁም ለመበላላት ቋፍ ላይ ስንቆይ ቆይተናል። የማይተካ ውድ ኢትዮጵያዊያንንም ህይወት አጥተናል። አካል ጎድሏል፤ ንብረትም ወድሟል። ይህ ሁኔታ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ በአንድነትና በመግባባት ኢትዮጵያዊ መንፈስ ተተክቷል።

አሁን የህዝቡን ችግርና ብሶት ቀርቦ የሚያዳምጥና አዳምጦም የችግሩ አካል የሚሆን መሪ ተገኝቷል። ሰላማችን በአንፃራዊ ሁኔታ እየተመለሰ ነው። በሁለት ወር ውስጥ ብቻ ይህን ያህል በሰላም ጎዳና መጓዝ ከቻልን፤ ምናልባትም በስድስት ወር ውስጥ የት ልንደርስ እንደምንችል ለመገመት ነብይ መሆንን አይጠይቅም። የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃልና። እናም ይህን ለውጥና ለለውጡ መገኘት “የሙሴን በትር” በማንሳት ከሁከት ባህር እያላቀቁን ያሉትን መሪያችንን አለመደገፍ አንችልም። ፈፅሞ አያስችለንም። ሰላማችን የራሳችን ስለሆነ፤ ቅዳሜ ይህን ለመግለፅ እንገናኛለን።

በእኛ ሀገር ፖለቲካ ውስጥ እርቅና ይቅርታ የተለመደ አይደለም። የተለመደው ነገር ጥላቻና ቂም በቀል ነው። የተለየ ሃሳብ ያለውን እንደ ጠላት መርዞ በመያዝ እስከ ህልፈተ ህይወቱ ድረስ ማሳደድና መበቀል ነው። “ሰዶ ማሳደድ ካማረህ ዶሮህን በቆቅ ለውጥ” እንደሚባለው፤ ፖለቲካው ያለ አንዳች ማስረጃና መረጃ እያሰረ የሚፈታ እንዲሁም መልሶ የሚያስር የሰዶ ማሳደድ ጨዋታ ነበር—ከእስር ወደ እስር ያመላለስ አባዜ የተጠናወተው ነበር ማለት ይቻላል። ታዲያ እንዲህ ዓይነቱን የማሳደድና የመወጣጠር ተግባር፤ የለውጡ መሃንዲስ “ፋሽኑ ያለፈበት” ሲሉ ይገልፁታል። ርግጥ ነው አስተሳሰቡ ራሱ አሮጌና ድሪቶ ነው—ወቅቱ ያለፈበት። እናም በአዲስ የይቅርታና የእርቅ መንገድ መታደስ አለበት።

አዎ! ይህ የሀገራችን የቂም በቀልና እርስ በርስ የመወጣጠር ፖለቲካ በይቅርታና በእርቅ ተተክቷል። በዶክተር አብይ የሚመራው የለውጥ አመራር በውስጥና በውጭ ይቅርታ ሲያደርግና ሲቀበል እየተመለከትን ነው። በሀገር ውስጥ በተለያዩ የህግ ታራሚዎችን በይቅርታና በምህረት ከእስር እንዲለቀቁ አድርጓል። መንግስትን በጠብ-መንጃ አፈሙዝ እንጥላለን ብለው የተነሱ ሃይሎች ሳይቀሩ የይቅርታና የፍቅር ተቋዳሾች ሆነዋል። ይቅርታና ፍቅር በሀገራችን እየነገሰ ነው።

በውጭ የሚገኙ ተቃዋሚዎችም የዶክተር አብይ የለውጥ ፍቅር ምርኮኛ ሆነው ወደ ሀገራቸው እየመጡ ነው። ቀሪዎቹም መምጣታቸው አይቀርም— ፍቅርና ይቅርታ ያሸንፋልና። በዚህች አጭር ጊዜ ውስጥ የፖለቲካው ምህዳር እየሰፋ መሆኑን የተጠራራነው ሰልፈኞች እማኝ ነን። ዴሞክራሲ እንደ አዲስ ውልደት እያበበ መሆኑንም እንመሰክራለን። የጠላትነትና የመጠፋፋት መንፈስ ከኢትዮጵያችን እየከሰመ መሄዳቸውን እጃችንን አውጥተን እንናገራለን። ሁሉም ነገር በህገ መንግስቱ ብቻ እንዲፈፀም እንጠይቃለን።

የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ህግ ውጭ ሲያሰቃዩ የነበሩበትና መንግስት ራሱም ጭምር አሸባሪ ሆኖ የተሳተፈበትን ሁኔታዎች እናወግዛለን። እነዚያ አስከፊ ሁኔታዎች ዳግም ተመልሰው እንዳይመጡና በይቅርታ መታለፋቸውንም እናውጃለን። ከጠብ ይልቅ ፍቅር እንደሚሻል ለጎረቤቶቻችን እንነግራለን። አዲሱ አመራር የኢትዮ-ኤርትራን ጉዳይ አስመልክቶ ያቀረበው የሰላም ሃሳብ ከፍቅር እንጂ ከእርስ በርስ ከመወጣጠር ምንም የማይገኝ መሆኑን የሚያስተምር ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን እናውጃለን። የኤርትራ መንግስትም የሰላም ጥሪውን ተቀብሎ ልዑካኑን ለቀጣይ ድርድር ወደ አዲስ አበባ ለመላክ የወሰደውን ትክክለኛ የሰላም አቋምም እናደንቃለን። ኢትዮጵያ ከወንድም ከሆነው የኤርትራ ህዝብ ጋር ብቻ ሳይሆን፤ ከሌሎቹም የቀጣናው ህዝቦች ጋር የሚኖራት በአዲስ መንገድ የሚንሰላሰል የልማት ትስስርን እናወሳለን። በሀገራችን የተገኘው ዕድገት መሬት ወርዶ ምን ያህል የድሃውን ጉሮሮ አርጥቧል? እያለ የሚጠይቅ አዲስ መንገድንና የጥርጊያውን መሃንዲስ አለማድነቅና አለመደገፍ ፈፅሞ አይሆንልንም። እናም እነዚህን ጉዳዩች ለመከወን ዕለተ ቅዳሜ መስቀል አደባባይ እንገኛለን።

አዎ! ለውጡንና መሃንዲሱን እንደግፋለን። በድጋፋችንም አንድነትንና ብሔራዊ መግባባትን እናወድሳለን። ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የሚበጃት ተደምረን አንድ መሆን እንጂ ተነጣጥለን መለያየት አለመሆኑን እንናገራለን። አንድ ስንሆን እንደምንከበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው በሄዱባቸው ሀገራት የተሰጣቸውን ክብር ሲናገሩ አድምጠናል። አንድነታችን የክብራችን ምንጭ እስከሆነ ድረስ በአደባባይ ስለ አንድነታችን የማንዘምርበት ምክንያት የለም። በአንድነታችን ኢትዮጵያዊነታችን ከፍ ሲልና የኩራት ምንጫችን ሲሆን ተመልክተናል። በባዕድ ሀገሮች በተለያዩ ምክንያቶች ታስረው የነበሩ ዜጎቻችን “ለእኛ የሚቆረቆር መንግስትና መሪ አለን” የሚል አዲስ አስተሳሰብ እንዲይዙ ያደረገውን የለውጥ መንገድና መሃንዲሱን የማንደግፍበት አንዳችም ምክንያት የለንም።     

ኢትዮጵያዊነታችን የውርደት ካባ ሳይሆን የክብር ጌጥ እንዲሆን በየሄደበት የሚጠይቅና ጠይቆም “እምቢ” የማይባል መሪንና ሃሳቦቹን መደገፋችን፤ ሰላማችንን ማብዛት ነው። የሀገራችንን ህዳሴ እውን ለማድረግ በሚደረገው የአዲስ መንገድ ውልደት ጥረት ላይ የየራሳችንን ጠጠር መወርወር ነው። ዴሞክራሲያችን በይቅርታና በመቻቻል ላይ እንዲመሰረት መወሰን ነው። እናም በስልጡን መንገድ ሃሳባችንን ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ለመግለፅ ሳንጠራ እኛው ራሳችን እዚያው እንገኛለን። መስቀል አደባባይ። ቅዳሜ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም። ኑ! ለውጡንና መሃንዲሱን አብረን እንደግፍ!…             

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy