Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አባልተው ሊበሉን ላሰቡ …

0 835

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አባልተው ሊበሉን ላሰቡ

ወንድይራድ ኃብተየስ

ትንሿ ኢትዮጵያ እያልን በምናቆላምጣት  ከደቡብ ክልላችን ሰሞኑን የምንሰማው ነገር  አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን አስፈሪም ጭምር ነው። ከትንሿ  ኢትዮጵያ ሃዋሳ ይህን አይነት ነገር የሚጠበቅ ነገር አይደለም። ጠቅላይ ሚንስትር አብይ በአንዳንድ ቦታዎች እየተከሰቱ ያሉት ግጭቶች፣ እኛን አባልተው ሊበሉን ላሰቡ የቀን ጅቦች አሳልፈው የሚሰጡን መሆናቸውን ህብረተሰቡ ሊገነዘብ ይገባል!” ሲሉ  የኪራይ ሰብሳቢዎችን አካሄድ ህብረተሰቡ ሊገነዘበው እንደሚገባ  አስረግጠው ተናግረዋል። በሰሞኑ የተቀሰቀሰውን ግጭት  እንደው በአጋጣሚ  የተፈጠረ ነው ብዬ አላምንም።  ሆን ተብሎ እየተሸነፈ ያለው የሌቦች  ቡድን የሚያደርገው  አልሞትኩም  አለሁ የማለት  አካሄድ ይመስላል። ግጭቱን ለማዛመት  የፌስ ቡክ አብዮተኞች የምታደርጉት ጥረት  ሌላው አሳፋሪ ድርጊት ነው። እስኪ እናንተ ሰዎች  እባካችሁ ግጭት ለማብረድ፣ ህዝብ እንዲቀራረብና አብሮነት እንዲመለስ  ለማድረግ ባትችሉ እንኳን እስኪ ቢያንስ ዝም በሉ።

 

በሁለት ጽንፎች  መካከል የቆመች አገር – ኢትዮጵያ። እንደእኔ አተያይ አገራችን በሁለት ተቃራኒ ነገሮች መካከል ከወዲያ ወዲህ እየዋለለች ያለች ትመስላለች። በአንድ በኩል በሁሉም መስክ ሊባል የሚችል መልኩ ተስፋ ሰጪ ጅምሮችን እናስተውላለን፤  ተጨባጭና አማላይ የኢኮኖሚ ዕድገት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጥቅመኛ ሃይሎች ህዝቦችን በማጋጨት የማይገባ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ የፈጠሯቸው ህዝቦች ግጭቶች። እስኪ አንዴ ዝም በሉና ነገሮችን በአንክሮ ተመልከቷቸው። አገራችን በፍጥነት ዕድገት እያስመዘገበች ነው እያልን ቅጥ ያጣ ዝርፊያና ቡድንተኝነት የፈጠረው  ግጭት ያስደምማልም አያስፈራልም። አሁን ላይ በአገራችን የምናስተውለው መሳሳብ እውነት በአንድ አገር ውስጥ በሚኖሩ ህዝቦች መካከል ሊኖር የሚችል ነገር ነውን? የሚያስብል ነው። አማራው ከትግራዩ፣ ኦሮሞው ከአማራው፣ ሶማሌው ከኦሮሞው፣ ሲዳማው ከወላይታ፤ ወዘተ መካከል እየተደረገ ያለው ግጭት አሳፋሪና አስፈሪም ነው። ከሁለት ወር  በፊት በአገራችን የነበረው ሁኔታ አስጊ በነበረበት ወቅት አንድ ወዳጄ እንዲህ ሲል አጫወተኝ፤ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ከአካባቢህ (የብሄርህ ወይም የብሄረሰብህ መኖሪያ ተብሎ ከተወሰነልህ አካባቢ ማለቱ ነው) ውጪ መኖር በቀውስ እየተናጡ ካሉ ደቡብ ሱዳን ወይም የመን ወይም ሶማሊያ ከመኖር ያልተናነሰ ስጋት የሚፈጥር ነው ሲል  ምርር ብሎ አጫወተኝ። እውነት ነው ዜጎች ስለነገ ዋስትና እያጡ ይመስላሉ።

ሰሞኑን በደቡብ ኢትዮጵያ እየተመለከትን ያለነው ይህንኑ ነው። ዛሬም መርዝ ይረጫል፤ ዛሬም በብሄር ተደራጅተን እንጠቃቃለን። ዛሬም  ህዝቦችን ለመከፋፈል ሴረኞች እየተሯሯጡ ናቸው። በህብረብሄራዊነቷ ተምሳሌታችን ነች የምንላት ሃዋሳ አሳፋሪ ድርጊቶች እየተከናወኑባት ነው። ሁላችንም  ለህግ የበላይነት መከበር ወደኋላ ማለት የለብንም። መንግስትም የህግ የበላይነትን ለድርድር ማቅረብ ከቶ የለበትም። ነውጠኛንና ሌባን መቅጣት ካልቻልን አገራችን ከድጡ ወደ ማጡ እንዳትሄድ እሰጋለሁ።  አሁን ላይ አንዳንዶች የመንግስትን የበዛ ትዕግስትና ይቅር ባይነት በተሳሳተ መንገድ እየተረዱት ይመስለኛል። የመንግስትን የበዛ ትዕግስት አቅም ወይም ፍላጎት የማጣት ስሜት እየፈጠረባቸው ጥቂት ናቸው  ብለው በሚገመቷቸው ዜጎቻችን ላይ በጠራራ ጸሃይ ወንጀል መፈጸምን እንደጀግንነት እየተቆጠሩት ይመስላል።

የእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ከሌሎች አገሮች የተለየ ነውን? ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው ያሉትን? የሃሳብ ልዩነት እኛ አገር ብቻ ነው ያለውን? የእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ለምን የተለየ እስኪመስል በልዩነቶች ላይ ትኩረት ተደረገ ስል ሁሌ ራሴን እጠይቃለሁ። አሁን ላይ በ27 ዓመታት በልዩነቶቻችን ላይ አብዝተን  የዘራነውን አዝመራ መሰብሰቡ የከበደን ይመስላል። በ21ኛው ክፍለ ዘመን በዘርና በጎጥ ተቧድኖ የሚናጭ አገር እየተመለከትን ያለነው የእኛኑ የጉድ አገር ብቻ ይመስለኛል። እውነታን ክደን መደሃኒት ማፈላለጉ የሚበጅ አይደለምና ነገሮችን ፍርርጥ አድርጎ መነጋገሩ ይበጃል። የሰሞኑ የሲዳማና የወላይታ ግጭት እጅግ አሳዛኝ፣ አሳፋሪና አስፈሪም ጭምር ነው። ማንም ፈልጎ ወይም ምርጫው አድርጎ ብሄሩን ወይም ብሄረሰቡን ወይም  አካባቢውን መርጦ የተወለደ የለም። እስኪ አንዴ ሁላችንም በአርምሞ ውስጣችንን እንመርምረው። ውስጣችንን እንመልከተው። እየሄድንበት ያለው መንገድ ምን ያህል አስጠሊታና አሳፋሪ መሆኑን መረዳት የሚከብድ አይደለም። ለመሆኑ የአገር መውደድ ስሜታችን፤ አንዱ ለሌላው እስከመስዋዕትነት ይደርስ የነበረው ህዝባዊነት ዛሬ ወደየት ደርሶ ይሆን እንዲህ የምንናጨው?

ለእኛ ኢትዮጵያዊያን  አገር መውደድ ማለት ጥልቅ ትርጉም ያለው ነገር ነው፡፡ አገር ማለት ህዝብ፤ ህዝብም ማለት አገር እንደሆነ  በየአደባባዩ ስንመሰክር ነበር። አገርና ህዝብ የማይነጣጠሉ አንዱ ካለአንዱ ትርጉም የማይኖረው እጅግ የተቆራኙ ነገሮች ናቸው ስንልም ምስክርነታችንን ስንሰጥ ነበር። አገር መውደድ ማለት ህዝብን መውደድ፣ ህዝብን ማገልገል፣ ለህዝብ መሞት፣ ለህዝብ መጎዳት  ማለት አይደለምን? አዎ አገር ወዳድ ዜጋ ማለት ራሱን ለብዙሃኑ ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ እንዲሁም ብዙሃኑም ስለአንዱ የሚገዳቸው ማለት ነው። ይህ ነው የአገር ፍቅር፤ ይህ ነው የህዝብ ፍቅር ማለት። ታዲያ ዛሬ ይህ ቅን ልቦናችን ወደየት ከዳን?

የአገር ፍቅር የሚገለጽበት ሁኔታ  ከጊዜው ጋር የሚለያይ ይሁን እንጂ በመሰረታዊነቱ  አንድና ያው ነው። ለአብነት የጥንት አባቶቻችን አገራቸውን ከውጭ ወራሪ ለመከላከል ሲሉ በባዶ እግራቸው ሺህ ኪሎ ሜትሮችን  አቋርጠው አድዋ ድረስ ተጉዘው እንደራባቸው እንደጠማቸው ለዘለዓለሙ አሸልበዋል። ዛሬ እነርሱ ባቆዩልን ምድር ስንናጭ ቢመለከቱን ምን ይሉን ይሆን።  ያ ትውልድ በመባል የሚታወቀው አሁን ላይ በ50ዎቹና በ60ዎቹ ዓመታት የሚገኘው ትውልድ ደግሞ እንደተራራ የገዘፈውን አምባገነኑን ደርግ በመፋለም ውድ ህይወቱንና   አካሉን ገብሮ ህዝብንና አገርን ነጻ አውጥቷል። የእኛ ትውልድስ የት ይሆን? እስኪ ሁላችንም ራሳችንን እንጠይቅ?

በእኔ አተያይ እኛ  እድለኞች ነን። የእኛ ትግል ከድህነትና ከኋላቀርነት እንጂ ሞትን የሚሻ  ትግል ማድረግ የሚጠበቅብን አልነበረም። የአሁኑ ትውልድ ድህነትን መታገል  ፍትሃዊነትን በማንገስና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታውን በማጎልበት የአገር ወዳድነት  ግዴታውነ መወጣት ሲገበው በትንሽ በትልቁ መናጨትን መርጧል። የእኛ ዘመን የአገር ወዳድነተ መገለጫው   ላብን እንጂ ደምን የሚፈልግ ትግል አልነበረም። ግና ያወቅንበት አንመስልም። ጥቂት የማይባል የእኔ ነው የሚለውን ሃይል አደራጅቶ በሌብነት  መሰማራቱ ሳያንሰው ጸያፍ ድርጊቱን ለመሸፈን በአብዛኛው ወጣቶችን በዘርና በጎጥ አራጅቶ ሁከትና ነውጥ ለመቀስቀስ በመሯሯጥ ላይ ነው።

የአገራችን ህዝቦች በእነዚያ ከፋፋይና ጨቋኝ ስርዓቶች ብለን በምንጠራቸው ጊዜ እንኳን እንዲህ አይነት የብሄር ግጭት አድርገው አያውቁም ነበር። የገዥው መደብ ጫና  ቢበረታባቸውም ህዝቦች አልተለያዩም። በአብሮነታቸው ጸንተው ያንን ወቅት ተሻግረዋል። ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት አሁን ላይ በ50ዎቹና በ60ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኘው ትውልድ  የበርካቶችን ህይወትና አካል መስዋዕት አድርጎ አዲሲቷን ኢትዮጵያ እውን አድርጓል። ይህ መቼም የማይረሳ ሃቅ ነው። ይሁንና የዴሞክራሲ ስርዓት አተገባበሩን በአግባብ የተመሰረተና በእውቀት የተመራ  ባለመሆኑ ይኸው ከ27 ዓመታት ብኋላ አገራችን እንደገና ለቀውስና ሁከት ተዳርጋለች። ያውም በብሄር ተከፋፍሎ በመናጨት። ይህ ከእኛ ከ21ኛው ክፍለዘመን ሰዎች የሚጠበቅ አይደለም።

ከላይ እንዳነሳሁት የአዲሱ ትውልድ የአገርና የህዝብ ፍቅር መገለጫ እንደቀድሞ አያቶቹና አባቶቹ በመሞትና በአካል መጉደል አይደለም። እንደዛ ያለ መስዋዕትነት አሁን ላይ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት አይደለም። በመሆኑም  የዛሬው ትውልድ የህዝቦች ትስስርና አብሮነት እንዲጎለብት፣ ማንነቶች እንዲከበሩ፣ ፍትሃዊነት እንዲሰፍን፣ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ጥረት ማድረግ ሲገባው በትናንሽ ልዩነቶች በመናጨት ሁከትና ነውጥ እንዲሰፍን ማድረግ ከእኛ የሚጠበቅ ነገር አይደለም።  ወጣቱ ለአገርና ለወገኑ ሊበጅ የሚችለው ከስሜታዊነት ራሱን ማራቅ ሲችል ብቻ ነው። አሁን ላይ በየሰፈሩ የምንመለከታቸው ቅጥ ያጡ አካሄዶችን ሁላችንም ልናወግዛቸው ይገባል። በቀል ማንንም ተጠቃሚ ሲያደርግ አልተመለከትንም። የሃይል እርምጃዎች  ለየትኛውም ችግር መቼም ይሁን የትም ዘላቂ መፍትሄ ሲያመጡ አልተመለከትንም። ስሜታዊነት አገር ያፈርሳል፤ አገር ይበትናል። በዘር፣ በሃይማኖትና በጎጥ ተቧድኖ መቆራቆስ የትም አያደርስም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy