Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አዲሱ አቋም

0 267

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አዲሱ አቋም

                                                           ታዬ ከበደ

በቅርቡ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የኢትዮ-ኤርትራን የድንበር ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ውሳነወን ገልጿል። ኮሚቴው የአልጀርሱን ስምምነት ተቀብሎ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ለመተግበር የተዘጋጀው፣ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃና በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ከማሰብ የመነጨ ነው። ውሳኔው በሁለቱ አገራት መካከል የእውነት ሰላም ለማስፈን ከቀድሞው አዲስና የተለየ አቋም እንዲሁም አካሄድ በማስፈለጉና የህዝቦችን ጥያቄ ለመመለስ ያለመ ነው።

ኮሚቴው የኢትዮ-ኤርትራ ወቅታዊ ሁኔታን በጥልቀት በመገምገም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃና በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ጥሪ አቅርቧል። በኢትዮጵያና በኤርትራ መሃከል ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተውን ጦርነት በአፍሪካ ከተከሰቱ የድንበር ጦርነቶች ሁሉ ደም አፋሳሹ መሆኑን ያተተው የኮሚቴው ውሳኔ ከሁለቱም ወገን በርካታ ሺህ የሰው ህይወት ጠፍቷል።  በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከኤርትራና ከኢትዮጵያ የድንበር አካባቢ ከመኖሪያ ቀዬአቸው አፈናቅሏል።

በሁለቱ ሀገራት መሃከል የተደረገው ጦርነት በሁለቱም ሀገራት ያሉ ቤተሰቦችን አፍርሷል፣ በድንበር አቅራቢያ የሚኖሩ ዜጎች ሁሌም ያለመረጋጋትና የስጋት ስነ ልቦና ሰለባ እንዲሆኑ አድርጓል። በድንበር አካባቢ በንግድ የሚተዳደሩ ሰዎች ላይም ተፅዕኖ አሳርፏል።

በሁለቱ አገራት መካከል የነበረው ግንኙነት ለፉት 20 ዓመታት በሁለቱም ሀገራት ህዝቦች ላይ መጠነ ሰፊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ፈጥሯል ያለው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው፤ የአገራቱ የወደፊት ግንኙነት ምን ሊሆን ይችላል? የሚለው ጥያቄ የአብዛኛው ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን እንዲሁም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል።

ከጦርነቱ በኋላ በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በተባበሩት መንግስታት አደራዳሪነት የአልጀርሱ ስምምነት ቢደረግም ላለፉት 18 ዓመታት በሁለቱ ወንድማማች አገሮች መካከል ጦርነትም ሆነ ሰላም የሌለበት ሁኔታ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።

በመሆኑም የአገራቱን ወዳጅነት ወደነበረበት ለመመለስ ላለፉት 18 አመታት የተደረጉ ሙከራዎች በሙሉ ውጤት ማምጣት አልተቻለም። በዚህም ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በሁለቱ ሀገራት መካከል የዕውነት ሰላም ለማስፈን ከቀድሞው በተለየ አዲስ አቋም መጓዝ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።

ብግሩን ለመፍታት ተራ ፉክክር ለሁለቱም አገራት ዘላቂ ግንኙነት ጠቃኚ አለመሆኑን መረዳት ይገባል። እንዲሁም የአገራቱ ወደ ነበረው ሁኔታ መመለስ ለአፍሪካ ቀንድ አገሮችና አካባቢ የፖለቲካ ቀውስ መብረድና መረጋጋት ዘላቂ መፍትሄ ይሆናል። ይህም ለሁለቱ እህትማማች ሀአሮችም እንዲሁም ለአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ትልቅ ፋይዳ አለው። ከሰላም መጠቀም የሚገባቸውን ማናቸውንም ጥቅሞች እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ቀድሞም ቢሆን ወዳጆች ናቸው። ህዝቦቻቸው በደም፣ በባህል፣ በቋንቋና በረጅም ጊዜ የጋራ ታሪክ የተሳሰሩ ናቸው። ታዲያ ለእነዚህ ህዝቦች ሰላም ወሳኝ ነው።

በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለቱ አገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል የኢትዮጵያ መንግስት የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰነው ሰላም ለሁሉም ህዝቦች የሚያመጣውን ፋይዳ በመገንዘብ ነው።

ምንም እንኳን የኤርትራ መንግስት እስካሁን ድረስ በዚህ ዙሪያ ያለው ነገር ባይኖርም፤ ተመሳሳይ አቋም በመውሰድ ያለ ምንም ቅድመ-ሁኔታ የቀረበለትን የሰላም ጥሪ መቀበል ይኖርበታል። ጥሪውን ለሁለቱ አገራት ህዝቦች ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም የሚበጅ ስለሆነ ነው። ወንድማማች ህዝቦች መካከል ከዚህ በፊት የነበረውን አብሮነትና ሰላም ወደነበረበት ለመመለስና በቀጣይም ዘላቂነቱን ለመጠበቅም ሰላም ዋስትና ስለሆነ ነው።

የኮሚቴው ውሳኔ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምን ለማምጣት የምታደርገው ጥረት አንድ አካል ይመስለኛል። እንደሚታወቀው ሁሉ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) እና ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም የሚሰፍንበት ሁኔታን ለመፍጠር ጥረት ማድረግ የጀመሩት በአፍሪካ ህብረት ወቅት ነው። የሱዳንንና የወቅቱን የደቡብ ሱዳን አማፅያንን ችግር በኢጋድ በኩል ለመፍታትና ለቀውሱ እልባት ለመስጠት ኬንያ-ናይሮቢ በተካሄደው የሰላም ስምምነት ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ውጤታማ የሆነበትን ድል አስመዝግቧል። ይህ የሀገራችን ጥረትና የተገኘው ውጤት የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ አድናቆት ሊያገኝ ችሏል።

የኢትዮጵያ መንግስት በየትኛውም ሀገር ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ያደረገው ጥረት የሚመነጨው ሌሎች ሃይሎች በተሳሳተ መንገድ እንደሚተረጉሙት ሳይሆን፤ የጐረቤቶቻችን ሰላም ለሀገራችን የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታችን መፋጠን ካለው ፋይዳ አኳያ እንደሆነ ሊጤን ይገባል። “ለምን?” ቢሉ፤ እኛ ድህነትና ኋላ ቀርነትን ለመዋጋት የምናደርገው ትግል ሊሳካ የሚችለው ጐረቤቶቻችን ሰላም ሲሆኑ በመሆኑ ነው።

ርግጥም እንኳንስ የድንበር አዋሳኞቻችን ቀርቶ የሩቅ ሀገራት ሰላም መሆንም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለእኛ ሰላም መጐልበት ያለው ሚና የላቀ መሆኑ እሙን ነው። ይህም በአፍሪካ ደረጃ በጋራ ሰላም እጅ ለእጅ ለማደግና በዚህም አፍሪካዊ ህዳሴን ማጎልበቱ አይቀሬ ነው።

ያም ሆኖ ኢትዮጵያ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን አማፅያን መካከል የተካሄደው ዘግናኝ ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ትልቁን ድርሻ ለተጫወተው የኢትዮጵያ መንግስት ያላቸውን  ጠንካራ እምነት የገለፁበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህም ይህም ሀገራችን የተጎናፀፈችው ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው።

ደቡብ ሱዳን እንደ የራሷን ነፃ ሀገር ከመሰረተች ጀምሮም ኢትዮጵያ ከአዲሲቷ ሀገር ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ ያተኮረ ነው። ይህም በንግድ፣ በመሰረተ ልማት፣ በኢንቨስትመንትና በፀጥታ ጉዳዩች ላይ ያተኩራል።

በአሁኑ ወቅትም ከአዲሲቷ ሀገር ጋር ሀገራችን ያላት መልካም ግንኙነት ቀጣናውን በልማት ለማስተሳሰር የምታደርገውን ጥረት እንደሚያጎለብት ተስፋ ተጥሎበታል። ይህም አንዱ የዲፕሎማሲ ከፍታችን ነው። አዲሲቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን ነፃ ከወጣች ጉዜ ጀምሮም በውስጧ የተፈጠረውን የእርስ በርስ ግጭት የኢፌዴሪ መንግስት ከኢጋድ ጋር በመሆን ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው። በዚህም ውጤቶች ተገኝተዋል። ውጤቶቹ በዚህ ብቻ መቆም ስለሌለባቸው አገራችን ለቀጣናው አርአያ የመሆን ጥረቷን ማጠናከር አለባት። ከኤርትራ ጋር ያላትን ችግር በሰላማዊ ሁኔታ ለመፍታት ያቀረበችው የውሳኔ ሃሳብም የዚህ ተግባሯ ሌላኛው መገለጫ ነው። እናም ይህን አዲስ አቋም ህዝቡ መደገፍ ይኖርበታል።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy