Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢህአዴግ ወዴት አለ?

0 780

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢህአዴግ ወዴት አለ?
ኢብሳ ነመራ
ኢህአዴግ በ1983 ዓ/ም ሰኔ የተመሰረተውን የሽግግር መንግስት፤ በኋላም በኢፌዴሪ መንግስት በገዢ ፓርቲነት ሃገሪቱን ሲመራ መቆየቱ ይታወቃል። በድምሩ ከሃያ ሰባት ዓመታት በላይ ሃገሪቱን መርቷል። ኢህአዴግ እንደ ግንባር የፌደራል መንግስቱን ሲመራ ግንባሩን የመሰረቱት አራት እህትማማች ብሄራዊ ድርጅቶች – ህወሃት፣ ብአዴን፣ ኦህዴድና ደኢህዴን ደግሞ የትግራይን፤ የአማራን፤ የኦሮሚያንና የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስታትን ሲመሩ ቆይተዋል። የተቀሩትን ክልሎች – አፋር፣ የኢትዮጵያ ሱማሌ፣ ሃራሪ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝና የጋምቤላ ህዝቦች ክልሎች ደግሞ የኢህአዴግ አባል ባልሆኑ ሆኖም ከኢህአዴግ ጋር የዓላማ አንድነት ባላቸውና በአጋርነት በተሰለፉ ብሄራዊ ድርጅቶች ሲመሩ ቆይተዋል።
የአንድ ትውልድ እድሜ ያህል ማለትም ለሶስት አስርት ዓመታት ያህል ኢህአዴግና አጋር ድርጅቶቹ ገዢ ፓርቲ ሆነው መቆየታቸው ያላስደሰታቸው ወገኖች አሉ። በመሰረቱ አንድ ፓርቲ ወደስልጣን የመጣበት መንገድ ዴሞክራሲ የህዝብ ውክልና የተረጋገጠበት ከሆነ ለሁለትና ለሶስት ትውልድም ገዢ ፓርቲ ሆኖ መቆየቱ በራሱ እንደችግር ሊነሳ አይችልም። በዴሞክራሲያዊ ስርአት የስልጣን ውክልና የሚገኝበት ብቸኛው መንገድ በምርጫ የሚገኝ የስልጣን ውክልና ብቻ በመሆኑ፣ በዚህ ሂደት ወደስልጣን የሚወጣ ፓርቲ ለበርካታ ዓመታት ገዢ መሆኑን መቀበል የግድ ነው። በዴሞክራሲያዊ ስርአት ስልጣን በምርጫ የሚገኝ እንጂ በተራ የሚዘዋወር ባለመሆኑ ምንም ማድረግ አይቻልም። አንድ ፓርቲ ስልጣን ላይ የሚቆየው ዴሞክራሲን በሚያፋልስ መንገድ ከሆነ ግን ተቀባይነት አይኖረውም። እናም የኢህአዴግ ለአንድ ትውልድ ዘመን ያህል ስልጣን ላይ የመቆየት ጉዳይ ከላይ ከተገለጸው የዴሞክራሲ አካሄድ አኳያ ብቻ የሚታይ ነው የሚሆነው።
ይሁን እንጂ ኢህአዴግ ስልጣን ላይ የቆየው በዴሞክራሲያዊ መንገድ (ፍጹም ጥሩ ፓርቲ ሆኖ ሳይሆን ከነችግሮቹ ከተፎካካሪዎቹ የተሻለ ሆኖ) የህዝብ ውክልና አግኝቶ ነው ብለን ብንወስድም ከተቃውሞ አለማምለጡ ግን ገሃድ እውነት ነው። በተለይ በአምስተኛው ዙር ምርጫ አሸንፎ ስልጣን በተረከበ በጥቂት ወራት ውስጥ ቀደም ሲል ከነበረው የመረረና የከረረ ህዝባዊ ተቃውሞ አስተናግዷል።
በተደጋጋሚ ሲነገር እንደቆየው የተቃውሞው ቀዳሚ መነሻ ምክንያቶች የተከማቹና ህዝብን ያንገሸገሹ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ መጓደል፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል መዛባትና ከተሞችን ያጥለቀለቀ የስራ አጥነት ችግሮች ናቸው። በቀላል አብላጫ የምርጫ ስርአት ኢህአዴግና አጋር ድርጅቶቹ ከጊዜ ወደጊዜ የፌደራልና የክልል መንግስታትን ስልጣን ሙሉ በሙሉ እየተቆጣጠሩ ሄደው፣ ሌሎች የተቃውሞ ድምጾች የሚሰሙበት እድል የተዘጋበት ደረጃ ላይ መድረሱም ተቃውሞውን ከዚያ ቀደም ከነበረው እንዲባባስ በማድረግ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንዳላለው ይታመናል።
ይህን ሁኔታ አንዳንድ ወገኖች ኢህአዴግ ሃገር ማስተዳደር የሚያስችል መተማመኛ ድምጽ እንዳጣ አድርገው ወስደውታል። ይሁን እንጂ ሃይል የተቀላቀለባቸው የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ብቻ በመመልከት የመተማመኛ ድምጽ ማጣት አመላካች አድርጎ መወሰድ አይቻልም። የአደባባይ ተቃውሞዎች በተለይ ሃይል የተቀላቀለባቸው የአደባባይ ተቃውሞዎች ከዚህ ውጭ ከሆኑ ከፍተኛ ቁጥር ካላቸው ዝምተኛ ደጋፊዎች ድምጽ እጅግ በበለጠ ጎልቶ የመሰማት ጉልበት ስላለው የአደባባይ ተቃውሞን የመተማመኛ ድምጽ ማጣት አመላካች አድርጎ መወሰድ ትክክል አይመስለኝም።
ያም ሆነ ይህ፤ ኢህአዴግ በተለይ በኦሮሚያ በሰፊው፣ በአማራና በደቡብ አንዳንድ አካባቢዎች ያልተቋረጠ ህዝባዊ ተቃውሞ ገጥሞታል። ይህ ተቃውሞ ኢህአዴግ ውስጡን በጥልቀት ፈትሾ ዳግም የመፈጠር ያህል ራሱን እንዲያድስ አስገደዶታል። ይህን ያለማደረግ አማራጭ አልነበረውም። ይህ የመታደስ እንቅስቃሴ በመጀመሪያ በኦህዴድ ውስጥ፣ በመቀጠል በሌሎች አጋር ድርጅቶች ውስጥ የአመራር ለውጥ እንዲካሄድ አድርጓል። በመንግስት መዋቅርም ውስጥ ከፌደራልና ከክልል የካቢኔ አባላት ጀምሮ እስከ ወረዳና ቀበሌ መዋቅር የአመራር ለውጥና ተያያዥ እርምጃዎች እንዲወሰድ አድርጓል። የዚህ የአመራር ለውጥ ዓላማ ህዝቡን ያስቀየመውንና የስቆጣውን ችግር ማቃለል ያልቻሉ የድርጅቱንና የመንግስት አመራሮችን አንጓሎ በማስወገድ መፍትሄ አማጭ አመራር ማስቀመጥ ነበር። ይህ የአመራር ለውጥ በመጨረሻም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የመፍትሄው አካል ለመሆን በሚል በገዛ ፍቃዳቸው ስልጣን እንዲለቁ እስከማድረግ ዘልቋል። ይህም አዲስ የተሃድሶው ውጤት የሆነ አመራር ወደኢህአዴግ ሊቀመነበርነትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሃላፊነት እንዲመጣ አድርጓል። የአሁኑ የኢህአዴግ ሊቀመነበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደስልጣን የመጡት በዚህ ሂደት ነው።
ይህ በኢህአዴግ ውስጥ የታየው የአመራር ለውጥና የአቋም ማስተካከያ በድርጅቱ ውስጥ ባለ ተቃርኖ የመጣ ተፈጥሯዊ የእድገት ሂደት ውጤት ተደርጎም ሊወሰድ ይችላል። ኢህአዴግ እንደ ድርጅት በማንኛውም አካል (entity) ውስጥ የሚኖረው የነባርና አዲስ የሚወለድ አመለካካት ተቃርኖ (contradiction) ትግል ይካሄድበታል። ይህም ድርጅቱን በመሰረቱና እስካሁን በዘለቁና፣ አዲስ በተፈጠሩ ወጣት የድርጅቱ አባላትና አመራሮች መሃከል ባለ የአመለካከት ልዩነት ተቃርኖ የሚገለጽ ነው። ይህ ተቃርኖ እንደችግር የሚታይ አይደልም። በማንኛው አካል ውስጥ የማያቋርጥ እድገት እንዲኖር የሚያደርግ ነባራዊ ሁኔታ ነው። ጤናማም ነው። በውስጡ ተቃርኖ የሌለው አካል የለም። ካለም ሙት ነው፤ ከጊዜ ጋር ሳይለወጥ በተወዘተበት ቦታ የሚኖር ሙት። እናም ኢህአዴግ ሙት ስላልሆነ ይህ የተቃርኖዎች ፍትጊያ የለውጥ ሂደት ሲካሄድበት ቆይቷል።
በዚህ የተቃርኖዎች ፍትጊያ የለውጥ ሂደት ነባሩ በቀላሉ እጅ ይሰጣል ተብሎ አይጠበቅም፣ መጪውም የሚኖርበትን አካል ሳይለውጥ አንቀላፍቶ ለዘለቄታው መኖር አይችልም። ቅራኔዎች የሚስተናገዱበት ስርአት ባለበት አካልና ማህበረሰብ ውስጥ የለውጥ ሂደቱ ሳሰይስተዋል በአዝጋሚነት ይቀጥላል። ቅራኔዎች እነደተፈጥሯዊ ባህሪ በማይወሰዱበትና የሚስተናገዱበት ስርአት በሌለበት አካል/ማህበረሰብ ውስጥ ግን ይካረሩና ለውጡ የመፈንዳትና እመርታዊ የመሆን ባህሪ ያሳያል። አብዮት ታፍኖ የሚካረር ቅራኔዎች የለውጥ ደረጃ ነው።
አሁን ኢህአዴግ ውስጥ በመሪዎችና በድርጅታዊ አቋሞች ሽግግር የተገለጸው ለውጥ በግንባሩ ውስጥ የነበረ ተፈጥሯዊ የተቃርኖዎች ፍትጊያ የእድገት ሂደት ውጤት ነው። በተወሰነ ደረጃ ተቃርኖዎችን እንደተፈጥሮ ህግ የመስወድ ክፍተት ግን የነበረ ይመስለኛል። ለውጡ አዝጋሚ ከመሆን ይልቅ በተወሰነ ደረጃ እመርታዊ ባህሪ ማሳየቱ የዚህ አመላካች ነው። በለውጡ ዙሪያ ያሉ ያአሁንም ልሰከኑ ሁኔታዎችም ይህን ያመለክታሉ። ይህ በኢህአዴግ እመርታዊ ለውጥ ዙሪያ የሚታየውን ያልሰከነ አቧራ አንዳንድ ወገኖች እንደ ኢህአዴግ ፍጻሚ ማሳያ አድገው የወሰዱበት ሁኔታ ታይቷል። እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው። ኢህአዴግ በውጫዊ ግፊትና በውስጣዊ ተቃርኖ ፍትጊያ ሂደት መሰረታዊ ባህሪውን ሳይቀይር አዲስ መልክ ይዞ ወጣ እንጂ አልከሰመም፤ እየከሰመም አይደለም።
የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድና ከእርሳቸው ጋር ያለው የአመራር ቡድን የዚህ የኢህአዴግ ለውጥ ውጤቶች ናቸው። የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የተወሰዱ የታራሚዎችና የተጠርጣሪዎች ይቅርታ፣ በሃገር ውስጥ ህጋዊ ሆነው ከሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ድርድር ለማድረግ የተላለፈው ጥሪ፣ ከመንግስትና ከኢህአዴግ በተቃራኒ ጽንፍ ቆመው ሲታገሉ ለነበሩ ድርጅቶችና ሚዲያዎች የተላለፈው የሰላም ጥሪ፣ ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል የዘለቀውን የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላም ችግር ለመፍታት የተወሰደው እርምጃ አዲስ ሆኖ የወጣው ኢህአዴግ ውሳኔ ውጤት ነው።
በመሆኑም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድንና የአመራር ቡድናቸውን፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችና እያስገኙት ያለው ከአመታት በፊት ይሆናል ተብሎ ያልተገመቱ ውጤቶች ከኢህአዴግ ተነጥለው የሚታዩ አይደሉም። የእመርታዊነት ባህሪ ባለው ለውጥ አዲስ መልክ ይዞ የወጣው ኢህአዴግ ውጤቶች ናቸው።
በተለይ ከ2008 ዓ/ም መግቢያ ጀምሮ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ውስጥ የነበረውና ተቃውሞው ሊያመጣ የሚችለውን አሉታዊ ውጤት ይናፍቅ የነበረው ህዝብ ለኢህአዴግ ሊቀመነበርና ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ እንዲሁም ኢህአዴግ ላሳለፋቸውና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተግባራዊ ተደርገው ወጤት ላሰገኙ እርምጃዎች ይሁንታውን ሰጥቷል። ሰሞኑን በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች የተካሄዱ የእውቅናና የምስጋና ህዝባዊ ትዕይንቶች የዚህ ይሁንታ መገለጫዎች ናቸው።
ይህን በኢህአዴግ ውስጥ የተካሄደ ለውጥና ለውጡ ያስከተላቸውን እርምጃዎችና የተገኙ ውጤቶች አለመቀበል፣ አይቀሬ የሆነውን የለውጥና እድገት ሂደት ያለመቀበል ግትርነት ነው። ይህ ግትርነት አይቀሬና ተፈጥሯዊ የሆነውን፤ የህዝብ ይሁንታ ያገኘውን የለውጥ ሂደት የመቀልበስ አቅም የለውም። እናም የኢህአዴግን ተፈጥሯዊ የለውጥ ሂደት ያመጣውን እመርታዊ እድገትና ወጤቶቹን መቀበል አስተዋይነት ብቻ ሳይሆን አማራጭ የሌለው ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy