Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢትዮጵያዊነትን የሚሸረሽሩ ሃሳቦች

0 350

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢትዮጵያዊነትን የሚሸረሽሩ ሃሳቦች

                                                        ዘአማን በላይ

በአንዳንድ ኩታ-ገጠም ቀበሌዎች በትንሹም በትልቁም የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች አጠቃላዩን ሀገራዊ ምስል የሚወክሉ አይደሉም። እንዲያውም ተጎራባች ክልሎችን አሊያም ህዝቦችን እንኳን የማይወክሉ ተግባሮች ናቸው። እዚህ ሀገር ውስጥ አንድን ህዝብን ጎድቶ ሌላውን ለመጥቀም መሞከር ከኋላ ቀር አስተሳሰብ የሚመነጭና ‘ቆሜለታለሁ’ ለሚሉትም ህዝብ ቢሆን የማይጠቅም መንገድ ነው። ለአብነት ያህል፤ ኦሮሞ ሆኖ የኢትዮጵያ ሶማሌን የሚጎዳ አሊያም የኢትዮጵያ ሶማሌ ሆኖ ኦሮሞን የሚጎዳ ተግባር መፈፀም ማንንም ተጠቃሚ የማያደርግ የዜሮ ድምር ጨዋታ ውጤት ነው። በዚህ ጨዋታ ላይ የተንተራሰ አመለካከት “ውሃ ቢወቅጡት እንቦጭ” እንደሚባለው አንዳችም ሀገራዊም ይሁን ብሔር ተኮር ጥቅም የሌለው አፍራሽ ተግባር ነው።

እናም እንዲህ ዓይነቱን አፍራሽ ተግባር እገሌ ከእገሌ ሳንል ሁላችንም በጋር ልናስቆመው ይገባል። በብሔር ስም የሚካሄዱ ግጭቶች ወይም ኢትዮጵያዊነትን መንፈስ ለመሸርሽር  የሚደረጉ ሙከራዎች ሁሉ የትኛውንም ብሔር የሚወክሉ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ በመቻቻልና በሆደ ሰፊነት ‘አጥፊም ከሆነ የእኛ ነው፣ ተበዳይም ከሆነ የእኛ ነው’ በማለት ሁሉንም በኢትዮጵያዊነት መንፈስ መመልከት ይገባል። እንደ እውነቱ ከሆነ ‘እኛ’ እና ‘እነርሱ’ የሚባሉ አገላለፆች፤ ኢትዮጵያዊነትን የሚሸረሽሩና ለሀገር ግንባታችንም ፀር መሆናቸውን መካድ አይቻልም።

ርግጥ በአሁኑ ወቅት አሁንም ድረስ እዚህም..እዚያም የሚነሱ ጥቃቅን የፀጥታ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ግና ሀገራዊ ሁኔታችን ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ በመሆኑ ይህን ሃቅ የማደብዘዝ አቅም የላቸውም። ሊኖራቸውም አይችልም።

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ውስጥ ግጭት ሊኖር ይችላል። ግጭት የተፈጥሮ ነባራዊ ክስተት ነው። በማህበራዊ የህይወት ዑደት ውስጥ ለ24 ሰዓታት እዚህና እዚያ የሚላተመው የሰው ልጅ ቀርቶ፤ በተፈጥሮአዊ እንቅስቃሴዎች ሃይል (dynamism) ሳቢያ ግዑዝ ነሮችም ይጋጫሉ። ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ግጭቶቹ የብሔር መብትን የሚያሳጡ አንድነትን የሚያቀጭጩና ኢትየፐጵያዊነትን የሚያደበዝዙ መሆን አይኖርባቸውም።

እንደ እውነቱ ከሆነ አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ለመገንባት በህገ መንግስቱ ላይ ስምምነት የደረሰ ኢትዮጵያዊ ‘እኛ’ እና ‘እነርሱ’ መባባል ያለበት አይመስለኝም። የሀገራችን ህገ መንግስትን መግቢያ በከፊል እይታ ስንቃኘው፤ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገታቸው እንዲፋጠን፣ የራሳቸውን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታቸውን ተጠቅመው፣ በነጻ ፍላጐታቸው፣ በህግ የበላይነትና በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠው መነሳታቸውን ገልፀዋል።

ምን ይህ ብቻ— ያፈሩት የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን ብለውም ያምናሉ። መጪው የጋራ ዕድላቸው መመስረት ያለበትም ከታሪካቸው የወረሱትን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማቸውን በማሳደግ ላይ መሆኑን እንደሚቀበሉም አስምረውበታል።

እነዚህ የኢትዮጵያ ህዝቦች የጋራ ስምምነቶች በዘላቂ ሰላም አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ በመገንባት የጋራ ጥቅማቸውን በማሳደግ በፍትሐዊነት ተጠቃሚ መሆንን ነው። ይህ እንደ አንድ የመቆም ህገ መንግስታዊ ስምምነት ‘እኛ’ እና እነርሱ የሚባሉ የአንድነት መንፈስን የሚቀበሉ አይደሉም።

ርግጥ ነው—የኢትዮጵያ ህዝቦች እምነታቸውም ይሁን መፃዒ ዕድላቸው በሚመሰርቱት አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘውግ ያለው ሥርዓት ላይ እንጂ፤ ያለፉት ስርዓቶች ጥለውት የሄዱትን የተበላሸ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አስተሳሰቦችን መልሶ መላልሶ በማመንዠግ ቁርሾ መያዝና ይህንንም ለግጭት ብሎም ለንፁሃን ህይወት መጥፊያነት በማለም አይደለም። ሊሆንም አይችልም።

የጋራ አስተሳሰብ ያለው ኢትዮጵያዊ ቀደምት የተበላሹ ግንኙነቶችን ያስተካክላል፣ አንዱ የሌላውን ሃይማኖት፣ እምነት፣ አስተሳሰብ፣ ቋንቋና ባህል በማክበር እጅ ለእጅ ተያይዞ ያድጋል፤ የጋራ ተጠቃሚነትንም ያሳድጋል።

እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ አንዱ ብሔር ከሌላኛው ጋር ተስማምቶና የጋራ ሃብቱን በጋራ በማልማት እንዲሁም ጥቅሙን በፍትሐዊነትና በእኩልነት እንዲያጣጥም ያደርገዋል። ይህም የጋራ ማህበረሰብን በመፍጠር ‘አንተ’ እና ‘እኔ’ የሚል ኢትዮጵያዊነትን የሚያደበዝዝ ምልከታ እንዳይኖር ያደርጋል።

በአንድ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ስርዓት ውስጥ ድንበር ተከፋፍሎ እነርሱና እኛ እየተባባሉ የፀጥታ መደፍረስ ችግሮችን ይገታል።  እንዲያውም ‘አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ’ እየተባባለ ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጠናከር የተጀመረውን የጋራ ዕድገት ትርጉም ባለው ሁኔታ የድሃውን ጉሮሮ በሚያርስ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ ዕድል ይሰጣል።

ቀደም ሲል በመግቢያዬ ላይ በአብነት ለማንሳት የመሞከርኩትን የኦሮሚያንና የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦችን ጊዜያዊ ግጭት ብንመለከት፤ አንድ በምጣኔ ሃብት የዳበረ ማህበረሰብ ለመገንባት ምንም ዓይነት ፋይዳ የለውም። ምጣኔ ሃብታችን እንዲያድግ በኢትዮጵያ ሶማሌ ውስጥ ያለው ዜጋ ኦሮሚያ ክልል ሄዶ፣ በኦሮሚያ ክልል ያለውም የኢትዮጵያ ሶማሌ ሄዶ መስራት አለበት። ማንኛውም ዜጋ የመንቀሳቀስና በየትኛውም ክልል ሄዶ ሃብት የማፍራት ህገ መንግስታዊ መብት ያለው መሆኑ ሁሌም ታሳቢ መሆን ይኖርበታል።

በግጭት ውስጥ የሚጎዳው ኢትዮጵያዊ እንጂ ‘እኛ’ን ወይም ‘እነርሱ’ን አይደሉም። ግጭት እስካለ ድረስ የተኛውም ወገን ተጠቃሚ አይሆንም። ተጎጂው ዜጋ ነው። በጥቃቅን ጉዳዩች በየጊዜው የሚጋጭ ህዝብ ሀገራዊ ምጣነወ ሃብት ዕድገት ላይ ማሳረፍ የሚገባውን አሻራ እንዳያኖር ያደርገዋል። ይህን ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን ከማደብዘዝ ባሻገር በሀገር ደረጃ የሰንቅነው ራዕይ እንዲዘገይ አሊያም እንዲደናቀፍ ምክንያት የሚሆን ይመስለኛል።

በእኔ እምነት የጋራ ወግ፣ ባህልና ትውፊት ያለው፣ በዘመናት አብሮነት ገመድ የተሳሰረ፣ በተለይም አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብን ገንብቶ የማየት ራዕይ ያለው የሁለቱም ክልል ወንድማማች ህዝብ ‘እኛ’ እና ‘እነርሱ’ በሚል እሰጥ አገባ የሚለያይ አይደለም።

ላለፉት ዓመታት አብረው በመፈቃቀድ በጋራ ኖረውና በሀገራችን ለተገኘው ሁለንተናዊ ለውጥ የራሳቸውን አሻራ በማኖር ላይ ያሉት ወንድምና እህት ህዝቦች ኢትየጵያዊነትን የሚሸረሽሩ ተግባራት ማንንም የማይጠቅም መሆኑን የሚገነዘቡ ናቸው። በግጭት ወቅት ተጎጂው ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንጂ ማንም ሊሆን እንደማይችል በሚገባ የሚያውቁ ብልህ ህዝቦች ናቸው። እናም እገሌና እገሌ ከመባባል የአንዲት ኢትዮጵያን ሰንደቅ ከፍ በማድረግ በህገ መንግስታቸው ላይ በጋራ ተስማምተው ላፀደቋቸው አካባቢዎች መትጋት አለባቸው።

ርግጥ ይህን ስል ሀገራችን ውስጥ ግጭት አለ ለማለት አይደለም። ቀደም ሲል የነበሩት ግጭቶች ተወግደዋል። የፀጥታ ችግሩ በቁጥጥር ስር የዋለ ለመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መወሰኑን ብቻ በመመልከት መረዳት ይቻላል። ያም ሆኖ ጉዳዩን ከኦሮሚያና ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አልፎ አልፎ በመጠኑ ከሚስተዋሉ የፀጥታ መደፍረሶች አኳያ ለመመልከት ሞከርኩ እንጂ ኢትዮጵያዊነትን የሚያደፈርሱ ሃሳቦች በሁዑም አካባቢዎች ሊኖሩ እንደማይገባ ለማስታወስ ነው።

ኢትዮጵያዊነትን የሚሸረሽሩ ሃሳቦችን ሁሉም ዜጋ ሊታገላቸው ይገባል። የአንድ አካባቢ ህዝብ ወይም የመንግስት የቤት ስራ ብቻ መሆን የለበትም። ‘እኛ’ እና ‘እነርሱ’ መባበል ማንንም አይጠቅምም። በአዲስ መልክ የተጀመረውን የሀገር ግንባታ ጥረት ያደፈርሰዋል። በተለይም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኢትዮጵያዊነትንና አንድነትን ለማምጣት በጀመሩት ሂደት ውስጥ ቦታ የለውም። ዐእኛ’ እና ‘እነርሱ’ አሰናካይ አስተሳሰብ ነው። እናም ማንኛውም ዜጋ ኢትዮጵያዊነትን የሚሸረሽሩ ሃሳቦችን በያለበት ቦታ “ሳይቃጠል በቅጠል” ማለት ይኖርበታል።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy