Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እነዚህ  ሰዎች የገዳ…

0 1,141

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እነዚህ  ሰዎች የገዳ…

አባ መላኩ

ዘግይተህም ቢሆን የለውጥ  ሞተር ወይም ጊር መሆን የሚችሉ  ሃይላትን መፍጠር በመቻልህ ብራቮ ኦህዴድ  ለማለት ወደድኩኝ። ባርኔጣዬን ከፍ አድርጌ ከወገቤ  ጎንበስ ብዬ “ገለቶማ ኦቦ ለማ! ገለቶማ ዶ/ር አብይ!” ብያለሁ።  የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ አገር በቀል የሆነው የዴሞክራሲ ስርዓታችን  “የገዳ አስተዳደር”  በዓለም ዓቀፍ የማይዳሰሱ ቅርስ  መዝገብ  ላይ ሲሰፍር አገር ወዳድ ዜጋ ሁሉ በጣም ተደስቶ እንደነበር  አስታውሳለሁ። እውነት ነው! የሉሲ መገኛ የሆነችው አገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ጀማሪ መሆኗም   እውቅና ሲቸረው ለእኛ ኢትዮጵያዊ ተደማሪ ኩራት ነው። ዓለም ዴሞክራሲን በማያውቅበት ወቅት የኦሮሞ ህዝብ  በየስምንት ዓመቱ በሚካሄድ ምርጫ አስተዳዳሪዎቹን በመነጋገርና በመወያየት ይመርጥ እንደነበር ማረጋገጫ ለምትፈልጉ  ቦረናና ጉጂ ሄዳችሁ መመልከት ትችላላችሁ። ከስምንት መቶ ዓመታት ብኋላም ባህላዊ ስርዓቱን ሳይለቅ ሳይከለስ ሳይበረዝ ዛሬም እንደጥንቱ ይካሄዳል።

ከላይ እንዳነሳሁት ዓለም ስለዴሞክራሲና ስለእኩልነት፣ ስለነጻነትና አብሮነት እሳቤው ሳይኖረው  የኦሮሞ ህዝብ ስልጣንን በህዝብ ይሁንታ ከነባሩ ይቀበላል፤ ለአዲሱም ይሰጣል፤ ይህ ስርዓት የኦሮሞ ህዝብን  ከሌሎች ህዝቦች ጋር በሰላምና ፍቅር እንዲኖር መመሪያና ህጎችንም አካቶ በመያዙ ኦሮሞ አብሮነትን እንዲያጎለብት  አስችሎታል። በገዳ ስርዓት የስልጣን ሽኩቻ የለም። በዚህ ስርዓት እኔ ስልጣን ልያዝ የሚል የስልጣን ጥማት ከቶ እንዳይኖር  ተደርጓል። ይህን እውነታ ዛሬ በተግባር አይተነዋል።

ለዚህ ጥሩ ማሳያው  የአቶ ለማ መገርሳንና የዶ/ር አብይ አህመድን ቅንጅት  መመልከቱ መልካም ይመስለኛል። እነዚህ ሰዎች የኢትዮጵያ የለውጥ ሞተሮች፤  የዘረፋና የአፈና ስርዓቱ ደምዳሚዎች ናቸው ብል የሚበዛባቸው አይመስለኝም። በእኔ እይታ ታሪክ ሁሌም ሚዘክራቸው ቅንጅታቸው ለሌሎች ማስተማሪያ የሚሆን  ይመስለኛል። ዛሬ ላይ የቀበሌ ሊቀመንበርነት ስልጣን በሚያሳሳበት አገር ውስጥ እየኖርን አቶ ለማ መገርሳ ምንም ነገር ሳያጓጓቸው ዶ/ር አብይን ወደ መሪነት እንዲመጡ  በር ከፍተውላቸዋል። ይህ ነው የገዳ ስርዓት! ይህ ነው የገዳ ውጤት!

ጊዜ  ለእውነታ ቦታ አለው።  ለአቶ ለማ መገርሳ እንዲህ አይነት ከራስ ወዳድነት የጸዳ አካሄድ  ሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ትልቅ አክብሮት አላቸው። ምክንያቱም  አቶ ለማ መገርሳ በሞትና በህይወት መካከል ሆና ትቃትት የነበረችን አገራችንን  ዶ/ር አብይን ሰጥተውን ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ታድገዋታል። ዛሬ ዶ/ር አብይ አገራችንን ከመፈራረስ  አደጋ የታደጓት እርሶ መንገዱን ስላመቻቹላቸው፤ እርሶ ሁኔታዎችን ስላደላደሉላቸው እንጂ ኢህአዴግ ለውጥ ሰለፈለገ  ዶ/ር አብይን ወደ መሪነት እንዳላመጣቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው። ለዚህ ሃሳቤ አስረጅ አቅርብ የምትሉኝ ከሆነ   ሰሞኑን “የቀን ጅቦች” አልተሸነፍንም አለን ለማለት በየአካባቢው ነውጥና ሁከት እንዲነሳ የሚያደርጉት መሯርጥ መመልከቱ  ተገቢ ነው። ለማንኛውም ነገ ከነገ ወዲያ ታሪክ ብዙ ነገር ይነግረናል ብለን እናምናለን።

ለማንኛውም ብራቮ ኦህዴድ በማለት ባርኔጣዬን ከፍ ማድረግ  ወደድኩ! ኦህዴድ በመጨረሻ ሰዓትም ቢሆን የዴሞክራሲ ምንጭ የሆነው የገዳ ስርዓት  ውጤት መሆኑን በተግባር አሳይቶናል። አሁንም ኦህዴድ ከለውጥ ሃይሎች ጋር ያለውን ግንኙነት  አጠናክሮ መስራት ይኖርበታል፤ ትግሉንም ወደ ህዝብ አስተላልፈው። ከእንግዲህ ብቻችሁን አይደላችሁም።   ምንም ያህል የቀን ጅቦች አሁንም እየተሯሯጡ፤ አሁንም እየተቅበዘበዙ ቢሆንም ያ ያሳፋሪና አስፈሪ አስተዳደር  ተመልሶ ሊመጣ እንደማይችል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ለማና አብይ የገዳ ስርዓት ውጤት ናቸው ካልኩ አይቀር  አንድ ሁለት ነጥቦች ስለ ገዳ ስርዓት ላንሳ ወደድኩ።

የገዳ ሥርዓት በሦስት ዋና ዋና ዘርፎች የተከፈለ ነው። እነዚህም  ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የማህበራዊ ዘርፎች ናቸው፡፡ የገዳ አደረጃጀት እንደማንኛውም ዘመናዊ የመንግስት አወቃቀር  የሕግ አውጭ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈፃሚ አካላትን የያዘና በርካታ የዴሞክራሲ እሴቶችን በውስጡ ያካተተ ሲሆን ይህ ሥርዓት የኦሮሞ ሕዝብ  ራሱን የሚያስተዳድርበት ስርዓትን ከማስቀመጡም በላይ የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር አብሮ ለመኖር የሚያስችለውን ህግና ስርዓትም ያካተተ  ነው።

ከገዳ ስርዓት ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚነሱት የሞጋሣና ሜደቻ፣ የሲንቄና የሽምግልና የጉማ፣ የከለቻና ጫጩ፣ የቦኩና የቃሉ እንዲሁም  የአያንቱ ተቋማትን መጥቀስ ይቻላል። ይህ ሥርዓት የእድሜ እርከኖችን መሠረት በማድረግ በአምስት የገዳ መደባት (ፓርቲዎች) እና በ1ዐ እርከኖች በመከፋፈል የኦሮሞ ሕዝብ በአንድ የገዳ መንግሥት ጥላ ሥር የኮንፌደራላዊ ሥርዓትን በመከተል ያደራጀ  ጥንታዊና ጠንካራ የአስተዳደር ሥርዓት ነው፡፡ ስለገዳ ስርዓት እነዚህን ነጥቦች ካነሳሁ አዲሱ መንግስታችንም ስለዴሞክራሲ ስርዓት ከምዕራብ ሊኮርጅ ከሚኳትን እድሜ ጠገቡን የገዳ ስርዓት ከዘመናዊው አስተዳደር ጋር ቢያጣጥመው መልካም ነው እላለሁ።  

አሁን ላይ በአገራችን  እየታየ ያለው ለውጥ ጥቅማችንን ይነካል፣ እኛ  ኢትዮጵያን ካልመራናት ትበጣጠስ፣ የሚል አስተሳሰብ ያላቸው ሃይሎች እያደረጉ ያሉት አፍራሽ እንቅስቃሴ  አገራችንን ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይከቷት ትግሉን ሁላችንም ልንቀላቀለው ይገባል። ትዕግስት እንኳን ለመንግስት ለግለሰብም  አስፈላጊ እንደሆነ አምናለሁ። ይሁንና የመንግስት ትግስት ለከት ሊኖረው ይገባል። እንደእኔ እንደእኔ የህግ የበላይነት  መቼም የትም ለድርድር መቅረብ የለበትም። መንግስት የሕግ የበላይነት ለሰላም መረጋገጥ የመጀመሪያውና ትልቁ መስፈርት መሆኑን ተገንዝቦ  የህግ የበላይነትን በተመለከተ ቀይ መስመር ሊያበጅ ይገባል። ትላንት ሲሰርቅና ሲያሰርቅ፤ ሲገርፍና ሲያስገርፍ፤ አገርን ያለእውቀትና ብለሃት ሲመራ  የነበረ ሃይል ዛሬም ያንኑ ጸያፍ ተግባሩን ካልፈጸምኩ እያለ ሲወናጨፍ ማየት አሳፋሪም አስፈሪም አካሄድ ነው።

በየትኛውም አገር መንግስት መንግስት ሊባል የሚችለው በስልጣን ላይም የሚቆየው፣ በህዝቦችም ተቀባይነት  የሚኖረው ወዘተ የህግ የበላይነትን ማረጋገገጥ ሲችል ብቻ ነው። በዕርግጥ ለህግ የበላይነት መረጋገጥ መንግስት  የማይተካ ሚና ይኑረው እንጂ ህብረተሰቡም ያለው አስተዋጽዖም ከፍተኛ በመሆኑ ሁላችንም ለውጥ ፈላጊ ሃይሎች ከመንግስት ጎን ልንቆም ይገበል።  ህይወት የሚያጠፋና ንብረት የሚያወድም ሃይል የህግ የበላይነትን እንዲረጋገጥ አይፈልግም። ነውጠኛ ሃይል ሰርቶ ከማግኘት ለዝርፊያ እንዲያመቸው ዛሬም  ህዝቦችን ለማናቆር በመሯርጥ ላይ ነው። ይህን ሃይል መንግስትና ህዝብ በመተባበር ሃይ ማለት ካልቻሉ አገራችን ለሁላችንም ሳትሆን ትቀራለች።

ጥቅመኛው ሃይል ትላንት በሰራው ጥፋት ከቶ  አልተጸጸተም፤ ንሰሃ መግባትም ሆነ ህዝብን ይቅርታ  ለመጠየቅ ፍላጎት የለውም፤ እንኳን ይቅርታ ሊጠይቅ አርፎ መቀመጥ አልቻለም።  ይልቁንም ትላንት ይፈጽመው የነበረውን አሳፋሪ ድርጊት አንሶት ዛሬም አገሪቱን ለማወክ  በተለያዩ አካባቢዎች በህቡ ያደራጃቸውን የጥፋት ሃይሎች በማሰማራት ሁከትና ግጭት ለመፍጠር በመፍጨርጨር  ላይ ነው። እንዲህ ያለ የሞራል ውድቀት ውስጥ የተዘፈቀው የጥፋት ሃይል ነብሱ እስክትወጣ መወራጨቱ አይቀርም።   ነብስ ይዞት እንዳበደ ውሻ ሲወራጭ ደግሞ እንዳያበላሸን ሁላችንም ልንጠነቀቅ ይገባል ባይ ነኝ። ቸር ወሬ ያሰማን!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy