Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እንሆ ዘመን

0 623

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እነሆ ዘመን…!
እምአዕላፍ ህሩይ
ዘመኑ ዘምኗል። ዘመኑ ፍቅርን በእንቀልባ ‘እሹሩሩ’ እያልን የምንቀኝበት ሜዳ እየሆነ ነው። ዘመኑ ይቅርታን ሰንቀን፣ ቂምና ቁርሾ ዳግም ፊታቸውን ወደ እኛ እንዳይመልሱ ወዲያ አሽቀንጥረን የምንጥልበት አውድ ነው። ዘመኑ በሰላም አፀድ ውስጥ ቁጭ ብለን፤ ተድላን፣ ፍሰሐንና ሐሴትን የምናጣጥምበት ነው። ዘመኑ በአንድነት እጅ ለእጅ ተያይዘንና ኢትዮጵያዊነትን በአዲስ መቅረዝ ላይ ተክለን ‘አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ’ እየተባባልን የምንተሳሰብበት ነው።
ይህ የእኔ የብላቴናው ዘመን በልማት የተከበበ አውድ ነው። ይህ ዘመን፤ ከጨለማ ወደ ጭላንጭላዊ ብርሃን፣ ከጭላንጭላዊ ብርሃን ፍንትው ወዳለችው ደማቋ ፀሐይ የምንሸጋገርበት ነው። የአዲስ አስተሳሰብ መንገድ የተቀየደበት ነው፤ ይህ የእኔ ዘመን፤ ይህ የአንተና የእርሷ ዘመን፤ ይህ የእነርሱና የእኛ ዘመን። ይህ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዘመን። ታዲያ ለዚህ በዘመን ለመሰልኩት አዲስ አውድ ፋና ወጊ ለሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ድርጀታቸው ከመቀመጫዬ በመነሳት የአክብሮት ባርኔጣዬን አንስቻለሁ።…“እነሆ ዘመን…!” እያልኩ።
የአዲስ አመለካከት ፋና ወጊዎቹ አዲስ አውድ፤ ዴሞክራሲን በንድፈ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ያዘመነ ነው። ትናንትን ወደ ኋላ ተመልሶ ላይመለከት የወደፊት መደመርን የሚያልም ነው። በዚህም አቀበት ቢኖረውም ወደፊት እየተንደረደረ የፖለቲካ ምህዳሩንና ሀገራዊ መግባባቱን እያሰፋው፣ እያጎነውና አያስመነደገው ነው። ይህ የእኔና የእርስዎ ትውልድ አዲስ አውድ፤ በፌዴራልና በክልል ደረጃ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ታራሚዎችን ከመፍታት ባሻገር ትምሀርትም እየሰጠን ነው። ያለ ማስረጃና መረጃ የታሰረ ታራሚ ሲፈታ “እልል!” ማለትን፣ ዓይን መቅላት የአውዱ ባህሪ የማይፈቅደው ኢ-ኢትዮጵያዊ ዝሴት አለመሆኑን እያስተማረን ነው፤ አዲሱ አውድ።
አዲሱ አውድ መሳሳብና መጠላለፍ ምንም ዓይነት ትርጉም የሌላቸው፣ ወደፊት ለሚገሰግስ አዲስ እሳቤ ረብ እንደሌላቸው በማሰብ የትናንት ቁርሾን ተቶ በአዲስ የሃሳብ ልዕልና ላይ የቆመ ነው። ሃሳቦች ሁሉ ተደምረው ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ግብዓት ይሆናሉ ብሎ ስለሚያምን፤ በትጥቅ ትግል ያምኑ የነበሩ ኢትዮጵያዊያንን ጭምር ወደ ሀገር ቤት የሳበ አውድ ነው። በዚህም በውጭ ሀገር ነፍጥ አንግበው በመሰለፍ ይታገሉ የነበሩት አርበኞች ግንቦት ሰባት እንዲሁም በብርጋዲየር ጄኔራል ከማል ገልቹ የሚመራው የኦሮሞ አንድነት ነፃነት ግንባር (ኦአነግ) የመሳሰሉ ድርጅቶች በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት የትጥቅ ትግላቸውን አቁመው ወደ ሀገር ቤት መምጣት እንዲጀምሩ ያደረገ የስበት ማዕከል ነው። ይህም ለዚህ ሀገር ‘ሃሳብ አለኝ’ ብሎ የተሰለፈ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ተደምሮ ለሀገሩ ልዕልና እና ህዳሴ አዲስ በር እንዲከፍት የሚያስችለው ይመስለኛል።
አዲሱ በር ሰፊ ነው— እንኳንስ ሀገር ቤት ቀርቶ ውጭ ያለውንም ዜጋ የሚያስገባ አውድ። በአንድ በኩል ሀገር ቤት ያለውን ኢትዮጵያዊ የምስጋና እና የእውቅና ሰልፍ ያለ አንዳች ቀስቃሽ በነቂስ ያስወጣል። በሌላ በኩል ደግሞ፤ በውጭ ያለውን ዲያስፖራ በያለበት ሀገር ስራውን አስጥሎ በከፍተኛ የድጋፍና የለውጥ ሂደት ናፋቂነት መስክ ላይ ያስውላል። በእውነቱ አዲሱ አውድ ተዓምረኛ ነው።
ትላንት ለኢትዮጵያ መንግስት እርዳታ እንዳይሰጠው እያለ የምዕራባዊያንን ደጅ ሲጠና የነበረው ወገኔ፣ ዶላር ወደ ሀገራችሁ እንዳትልኩ እያለ ያለመታከት በመለመን ተግባር ላይ የተሰለፈው ዜጋዬ እንዲሁም ስለ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና ስለ እኩልነት የሚዘምረው፣ ስለ ነፃነት የሚከራከረው…ወዘተርፈ ዲያስፖራ፤ ዛሬ ሳይጠየቅና ሳይጎተጎት “እኔ የዶክተር አብይ አህመድ ደጋፊ ነኝ” እያለ ነው። “የውጭ ምንዛሬ ለሀገራችን ያስፈልጋታል”ም ሲልም እየተደመጠ ነው። “ፍቅር ደምሮኛል” እያለን ነው። አባቴ ይሙት ይህ አዲስ አውድ ሙስሊሞቹ ወንድሞቼ እንደሚሉት “አጃኢብ!” የሚያሰኝ ነው። አንድ መሪ ደጋፊውንም ይሁን ተቃዋሚውን የሚደመርበት ሂደት በሀገራችን ፖለቲካ የመጀመሪያው፣ ምናልባትም የመጨረሻው ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ። እጅግ አስገራሚ ክስተት።
እነሆ ደማሪው ዘመን።…“ጋን በጠጠር ይደገፋል” እንዲሉ አበው፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የአዲሱ አውድ መሪ ተደማሪ እየሆነ ነው። የበኩሉን ድርሻ ለማበርከት ሌላው ቀርቶ፤ ትናንት “ፅንፍ የወጡ” እያልን ስናወግዛቸው የነበሩት እንደ ኢሳትና ‘ኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ’ (OMN) የመሳሰሉ ሚዲያዎች፤ ‘ሀገሬ ጠራችኝ’ በማለት ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውና ስራም ለመጀመር ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ስንመለከት፤ መደመሩ የፈጠረውን የፖለቲካ ምህዳር ስፋት ለመገንዘብ ነብይ መሆንን አይጠይቅም። ለእኔ ለብላቴናውም ሳይቀር ግልፅ ነውና።
ይህ እውነታም፤ ሃሳብን በነፃነት የመያዝና የመግለፅ ህገ መንግስታዊ መብት እስከ የት ድረስ እንደዘለቀ የሚያስረዳን ይመስለኛል። የተለየ ሃሳብ መያዝና መግለፅ የህብረተሰቡ ማንነት ማሳያ ነው። ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊኖረው የሚችለው አንድነት እንጂ አንድ ዓይነት አይደለምና። እናም ይህን የህብረተሰብ መገለጫን አፍኖ መያዝ ጉዳቱ ካልሆነ በስተቀር ምንም ዓይነት ጥቅም የለውም። የታፈነ ነገር በአንድ ወቅት ፈንድቶ መውጣቱ አይቀርምና።
ያም ሆኖ ግን ሚዲያዎች ወደ አዲሱ አውድ ሲደመሩ፤ የህዝቡ ዓይንና ጆሮ በመሆን ያሉባቸውን ሙያዊ ማህበራዊ ኃላፊነት (Professional Social Responsibility) መዘንጋት አይኖርባቸውም። በአዲሱ አውድ ውስጥ በመደመር ስልተ ምት ስለ ህዝቦች አንድነትና ስለ ኢትዮጵያዊነት ሊዘምሩ ይገባል። ጥላቻን የሚፈጥሩ፣ ህዝብን ከህዝብ ጋር የሚያጋጩና የስርዓተ ማህበሩን ዕድገት የሚያቀጨጩ ዘገባዎችን ከፊታቸው ማራቅ ይኖርባቸዋል። ምናልባት ‘ምከንያትህ?’ ካሉኝ፤ ምላሼ የሚሆነው ‘የመደመሩ ምህዳር አውድ ሊያድግና ሊበለፅግ የሚችለው በዚህ መልኩ ነው’ የሚል ነው።
አሁንም ‘እነሆ ዘመን…!’ እላለሁ።…ዛሬ የመደመሩ አውድ፤ ከሚዲያ ባለፈ የዜጋ ጋዜጠኞችን (Citizen Journalists)፣ ጦማሪዎችን (Bloggers) እና በርካታ ድረ ገፆችን (Websites) ምህዳሩን እንዳሻቸው ይጠቀሙበት ዘንድ ክፍት አድርጓል። ቀደም ሲል ተዘግተው የነበሩ ከ246 በላይ ድረ ገፆች ክፍት ሆነው በሰፊው ምህዳር ውስጥ ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ተደርጓል። የዜጋ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪዎችና ድረ ገፆች በእንዲህ ዓይነቱ የመደመር አውድ ውስጥ ሲገቡም ድባቡን ማፍካት ይጠበቅባቸዋል። ድባቡ ፈክቶ የሚሰፋው ተግባራቸውን በኃላፊነትና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት መንፈስ ሲወጡ ይመስለኛል።
እናም እነዚህ የማህበራዊ ሚዲያ አካላት የተለያዩ መልዕክት ማስተላለፊያዎችን ሲጠቀሙ ለሀገርና ለህዝብ የሚጠቅሙ እንዲሁም ካለንበት ችግር ሊያወጡን የሚችሉ የሃሳብ ልህቀቶችን ማፍለቅና ተደራሽ ማድረግ ይኖርባቸዋል ብዬ አምናለሁ። የፖለቲካ ምህዳሩም ይሁን ሀገራዊ መግባባቱ ሊያደግና ሊጎለብት እንዲሁም ጥልቀት ሊኖረው የሚችለው በእንዲህ ዓይነቱን ለወገን የሚጠቅምና ለነገ “ስንቅ” የሚሆን ሀገራዊ ስራ አማካኘነት ስለሆነ ነው። ይህ የእኛ ዘመን አዲስ ምልከታ ብዙ ነገር እያሳየን ነው። ኢትዮጵያዊነት መቻቻልና ይቅር ባይነት፤ ኢትዮጵያዊነት ፍቅርና መደመር፤ ኢትዮጵያዊነት ቂም በቀልና ቁርሾን ተፀያፊነት፤ ኢትዮያዊነት ዘረኝነትንና ስግብግብነትን አውጋዥነት እንዲሁም ኢትዮጵያዊነት ሁሉንም ዓይነት ሃሳቦችና አመለካከቶች አክባሪነት እየሆነ ነው።..
ምን ይህ ብቻ! ኢትዮጵያዊነት ከራስ አልፎ ለጎረቤት ሀገራትና ህዝቦች አሳቢነት፤ ኢትዮጵያዊነት የፍትህ፣ የእኩልነትና የጋራ ተጠቃሚነት እሳቤ አራማጅነት ብሎም ኢትዮጵያዊነት ቀጣናዊና አፍሪካዊ ተምሳሌትነት በመሆን ላይ ይገኛል። ይህ የዘመናችን ክዋኔ አንዱ ጨረፍታ ነው—ጅማሮ። ሆኖም በህዝቦች ድጋፍ ታጅቦ ገና ይቀጥላል። ወደፊት ያመራል። የአዲሱ አውድ ጅማሮ ትስስርና ጥንካሬ ላይበጠስ እንዲንሰላሰል የአውዱን መሪ እያመሰገንና እውቅና እየሰጠን ደግመን ደጋግመን ልንደመር ይገባል።…እነሆ ዘመን…!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy