Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ካለፍቅር … ከቶ ምን ሊረቡን?

0 420

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

 

አባ መላኩ

በስራ ምክንያት በርካታ የአገራችንን አካባቢዎች የመጎብኘት አጋጣሚውን አገኝቼ ነበርና  የክልልና የዞን ከተሞችን ዕድገትና መለወጥ አስደማሚ ሆኖ አገኝቼዋለሁ፤ ይበል የሚያሰኝ ነው። ባህር ዳር፣ ሐዋሳ፣ መቀሌ፣ አዳማ፣ ድሬዳዋ  እየተገነቡ ያሉ የሚያማምሩ ህንጻዎች፣ መንገዶች፣ ሆቴሎች፣ የከተማ ጽዳት ወዘተ እጅግ ማራኪ ለመዝናኛ፣ ለኑሮ ምቹ በቀጣይ ጥሩ ተስፋ የሚጣልባቸው አማራጭ ከተሞች እንደሚሆኑ በእርግጠኝነት ማየት ይቻላል። አገራችን በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ መሆኗን ከተሞቻችን ጥሩ አስረጂዎች ናቸው።   ሰሞኑን በስራ ምክንያት አማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና ከተማ ወደሆነችው ድብረ ብረሃን ተጉዤ ነበር። የደብረብረሃን ሁኔታ እጅግ ስላስደመመኝ አንድ ሁለት ነገሮች ለማንሳት ወደድኩ።

 

ደብረ ብረሃን በአገራችን እጅግ ዕድሜ ጠገብ ከሚባሉ ጥቂት ከተሞች በቀዳሚነት የምትጠቀስ ናት። ይሁንና ለዘመናት ረዥም እንቅልፍ ውስጥ የከረመች ከተማ ነበረች።  ደብረ ብረሃንን የዛሬ አስራ አምስት ዓመት አካባቢ በስራ ምክንያት አውቃት ነበር። በዚያን ወቅት እኔና የስራ ባልደረቦቼ ደብረ ብረሃን ስንደርስ በአጋጣሚ ሰዓት እላፊ ነበርና አንጀት የሚያንሰፈስፈውን ብርድ  የሚያስታግስልን ምግብና መኝታ እንኳን እንደልብ ለማግኘት እጅግ ተቸግረን እንደነበር አስታውሳለሁ። በወቅቱ እኔና የስራ ባልደረቦቼ ብርዱና ቅዝቃዜው ደብረ ብረሃንን ረዥም እንቅልፍ ውስጥ የከተቷትና ለመልማት ጊዜ የሚወስድባት መስሎን ይህችን ጥንታዊት ከተማ  የቆሮቆሯት አጼዎቹ ድንገት ቢነሱ ይህን ትውልድ ከትዝብት ላይ ይጥሉናል እያልን እርስ በርሳችን ስንወያይ ነበር።

 

ደብረ ብረሃን ከአስር አመት ብኋላ ስመለከታት ፍጸም ተቀይራለች፤  ልደቷን የምታከብር ኮረዳ መስላ አምራና ደምቃ ታየችኝ፤ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እንግዶቻቸውን በማስተናገድ ተጠምደዋል፣ አንዳንዶቹ ህንጻዎች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ስራ ጀምረዋል፣ ከፊሎቹ በከፊል ተጠናቀዋል። በርካታ  በጅምር የሚታዩ ህንጻዎች በየትኛውም የከተማዋ ኮርነር ማየት ያስገርማል። ከተማዋ በግንባታ እንደየጠመደች የሚያሳይ እውነተኛ ማስረጃዎች በከተማዋ በየትኛውም ክፍል ማየት ይቻለል። የከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ደረጃቸውን ጠብቀው  በአስፋልት ተገንብተዋል፤ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ሙሉ በሙሉ በሚያስብል መልኩ በኮብል ስቶን ተሸፍነዋል። የከተማዋ ንጽህና ይበል የሚያሰኝ ነው። ከተማዋ በርካታ ኢንቨስትመንት መሳብ ችላለች። አዳዲስ ፋብሪካዎች በመገንባት ላይ ናቸው፤  የቢራ ፋብሪካዎች እንኳን ሁለት የከተሙባት ለመሆን በቅታለች ። ዛሬ ላይ ደብረ ብረሃን በለውጥ ጎዳና መጓዟን ለመረዳት አያዳግትም። አዎ ከተሰራ በአጭር ጊዜ መለወጥ ማደግ እንደሚቻል ደብረ ብረሃን ጥሩ ማሳያ ናት።

 

የደብረ ብረሃን ዩኒቨርሲቲ  ለህብረተሰቡ ዛሬ ላይ በሰው ሃይል ልማት  አዲስ የለውጥ ብርሃን ፈንጥቋል። በርካታ የከተማዋ ወጣቶች  የከፍተኛ ትምህርት ዕድል በአካባቢያቸው ማግኘት በመቻላቸው ለመለወጥና ለማደግ ምክንያት እንደሆናቸው መረዳት ይቻላል። ትምህርት፣ ጤናና መሰል ማህበራዊ አገልግሎቶች የየትኛውም አገር ዕድገት ማሳያ  ተብለው በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ምሁራን ዘንድ የሚቀርቡ ጠቋሚ መለኪያዎች እንደሆኑ የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡ እነዚህ ዘርፎች ድህነትን ለመቀነስና በስልጣኔ ለመግፋት ትልቁን ሚና የሚጫወቱ በመሆናቸው አገሮች ለእነዚህ ዘርፎች መስፋፋት ትኩረት እንዲሰጡ ባለሙያዎች ያስገነዝባሉ፡፡ አገራችን በማህበራዊ ዘርፍ ያደረገችው ርብርብ  ስኬታማ እንዳደረጋት መካድ አይቻልም።

 

እውነት እውነቱን  እንነጋገር ከተባለ  በአገራችን የትምህርትና  የጤናው ዘርፍ ለውጥ እጅግ አስገራሚ ነው።  ባለፉት ሁለት አስርት አመታት አገራችን ለትምህርት ዘርፍ  በሰጠችው ትኩረት በየደረጃው ያሉ የትምህርት ተቋማትን በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍተዋል። ዛሬ ላይ ከሰላሳ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች  ከአንደኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ በትምህርት ገበታቸው ላይ ይገኛሉ። በክልል መንግስታትና በግል ባለሃብቶች የተቋቋሙ ዩኒቨርሲቲዎችንና ኮሌጆችን ሳይጨምር በአሁኑ ወቅት በፌዴራል መንግስት የሚተዳደሩ ከ47 ዩኒቨርሲቲዎች በላይ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። ከሃያ አመት በፊት በአገራችን ሁለት  የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የነበሩ ሲሆን የመቀበል አቅማቸውም እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲ የመግባት ዕድል እንደመንግስተ ሰማያት በር እጅግ የጠበበ እንደነበር የገፈቱ ቀማሾች ምስክርነታቸውን መስጠት ይችላሉ።

 

ዛሬ ላይ  መሰናዶ ትምህርቱን ያጠናቀቀ ተማሪ ከፍተኛ ትምህርት የመቀጠል መብት ብቻ ሳይሆን የመረጠውን ዲፓርትመንት የማግኘት መብት ጭምር እንደሆነ ማወቅ የተቻለበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። አሁን ላይ ተማሪዎቻችን  ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት ይህን የትምህርት ዘርፍ ማጥናት እፈልጋለሁ ማለት የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል እንጂ እንደቀድሞው ጊዜ በተገኘበት ዲፓርትመንት በገፍ የሚወረወሩበት ሁኔታ አክትሟል። ይህ ሲባል ዩኒቨርሲቲዎቻችን በሚፈለገው ጥራት  ደረጃ ላይ ናቸው ማለት አይቻልም። ነገር ግን እጥረቶቻችንን እየፈተሽን ጥራታቸውን ለማሻሻል የሚያስችል ሁኔታዎች እንዳሉም ማየት ይቻለል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ የትምህርት ስርዓቱ በተለይ የታሪክ ትምህርት እንደገና መከለስ እንዳለበት ገልጸዋል።

 

እውነት ነው! ትላንትን የማያውቅ ነገን አይናፍቅም ይባላል። ከትላንት መልካምነታችን ብቻ ሳይሆን ከስህተታችንም ልንማር የምንችለው ታሪክን ስናውቅ ነውና ዕውነታ ላይ ተመስርቶ  ትምህርቱ ቢሰጥ መልካም ነው። ትምህርት አገራዊ አንድነታችንን ሊያጠናክር በሚችል መልኩ መሰጠት መቻል ይኖርበታል። ከላይ ያነሳኋቸው የከተሞቻችን ስኬቶች ቀጣይነት የሚኖሯቸው አገራዊ አንድነታችን ሲረጋገጡ  ብቻ በመሆኑ መንግስት ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማሳካት ከሚያደርገው ጥረት ባልተናነሰ ለአገራዊ አንድነት መጠናከር መስራት ይኖርበታል።

 

ሁሉ ነገር ቢተርፈን፤   ሁሉ ነገር ቢሞላን ማሰሪያ ማጠንጠኛ የሆነው  አገራዊ ፍቅር ከሌለው ከቶ ምን ሊረባን? ከቶ ምን ሊተርፈን? የህዝቦችን አንድነት  የሚያስተሳስረው የህዝቦችን አብሮነት የሚያሰላስለው የመደመር ፖለቲካን ማራመድ ስንችል ብቻ መሆኑን በቅርቡ በአገራችን ከተከሰተው ነገር መረዳት የቻልን ይመስለኛል።   ባለፉት 27 ዓመታት አገራችን አንድ ነገር እንደጎደላት፣ አንድ ነገር እንዳጣች በርካቶች ይስማማሉ- አገራዊ ፍቅር። ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን፣ የኢኮኖሚ ዕድገታችን፣ ፍትሃዊነታችን እያልን 27 ዓመታት የዘመርንላቸው  ነገሮች በቅርቡ ከገጠሙን ነውጥና ሁከት ሊታደጉን አልቻሉም።

 

ባለፉት 27 ዓመታት ጽንፍ የረገጠ ብሄርተኝነት መገንገን፣ መቀነስን  ብቻ የሚያቀንቀን የፖለቲካ ሃይል መደራጀት፣ ስለልዩነትን እንጂ ስለአገራዊ አንድነት ማውራት እንደሃጢያት መቆጠር፣ በሁሉም ቦታና ጊዜ እኔ ብቻ የሚል የኢ-ፍትሃዊነት  አስተሳሰብና ተግባር መስፋፋተ የማታ ማታ አገራችንን ወደ ውድቀት አፋፍ ገፍቷታል። ፍትሃዊነትን ለማንገስ፣ አገራዊ አንድነትን ለማጎልበት፣ የህዝቦች አብሮነትን ለማጠናከር፣ ሌብነትን ለመከላከል፣ ወዘተ  አዲሱ አመራራችን የመደመር ፖለቲካን ይዞልን በመምጣቱ አገራችንን ከተደቀነባት የመበታተን አደጋ ታድጓታል። ምስጋና የመደመር ፖለቲካን ላመጣችሁልን ለዶ/ር አብይና ለአጋሮችህ!

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy