Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዛሬስ ግብርን እንደ ዕዳ እንቆጥረው ይሆን?

0 518

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዛሬስ ግብርን እንደ ዕዳ እንቆጥረው ይሆን?

ዮናስ

 

እያንዳንዱ ዜጋ ከአገሩ ሀብት ፍትሐዊ የሆነ ድርሻ፣ ተመጣጣኝ የሆኑ የሥራ ዕድሎችና ተጠቃሚነት ሲኖሩት በሃገሪቱ ማኅበራዊ ፍትሕ መረጋገጡ ይታወቃል፡፡ሃገራችን የምትከተለው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ዜጎች በሀብት ክፍፍል፣ በሥራ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በመኖሪያ ቤትና በመሳሰሉት በጥረታቸው መጠን ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባቸው ያምናል፡፡ይህ የመስመሩ እምነት የሚለካው ደግሞ የመንግሥት አሠራር ግልጽና አሳታፊ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በዜጎች መካከል ልዩነት የሚፈጠረውና ተመጣጣኝ ያልሆነ የኑሮ ዘይቤ የሚስተዋለው፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌለበት ሥርዓት ሲሰፍን ብቻ ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን የተዛባ አሠራር ማስወገድ የሚቻለው ማኅበራዊ ፍትሕ በማንገሥ ብቻ ነው፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ደግሞ ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ስልፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ስናወሳ ዋና ማጠየቂያ የሚሆኑን ዜጎች ሁሉ እንደየስራቸው ግብር የመክፈል ግዴታ ያለባቸው መሆኑን የተመለከተው ነው።  ግብር ያሻግራልና።

ብዙኃኑ የመንግስት ሰራተኛ እና የንግዱ ማኅበረሰብ በአግባቡ የሚፈለግበትን ግብርና ቀረጥ እየከፈለ የዜግነት መብትና ግዴታውን ሲወጣ፣ ከግብር ሥርዓቱ ተሸሽገው ለማመን የሚከብድ መጠን ያለው የአገር ሀብት የሚዘርፉ መኖራቸው በሚታወቅበት ሃገር ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን አስፍኖ ድህነትን መሻገር አይቻልም።ግብር በመሰወር፣ ቀረጥ ባለመክፈል፣ ኮንትሮባንድ በመነገድና በመሳሰሉት ሕገወጥ ተግባራት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የአገር ሀብት የሚዘርፉ አልጠግብ ባዮች ባሉበት አገር ውስጥ፣ የተለያዩ ጫናዎችንና የዋጋ ግሽበትን መቋቋም ተስኗቸው የሚደቆሱ ሞልተዋል፡፡ ግብር በመሰወር መደመር አይቻልም። ተደምረናል የምንል ከሆነ መክፈል ያለብንን በሰዓቱ መክፈል። ካልሆነ ግን ውሸታሞችና ለመሻገር ያልተዘጋጀን ነን።

በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት በሕጉ መሠረት ለጨረታ መቅረብ የሚገባቸው ፕሮጀክቶች በአቋራጭ በሙስና ሲጠለፉ፣ ግንባታቸው ከሚያወጣው ዋጋ በላይ በእጥፍ ሲጠየቅባቸው፣ በተፈለገው ጊዜ ሳይጠናቀቁ ሲቀሩና የትም ሲባክኑ በስፋት ይታያል፡፡ በጥቅም ሸሪክነትና በመሳሰሉት የተደራጁ ኃይሎች የአገር ሀብት እያወደሙ ያላግባብ ሲበለፅጉ ድህነትን መሻገር አስቸጋሪ ይሆናል። በመንግሥት በጀት የሚገነቡ ሆስፒታሎች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ መንገዶች፣ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ የመስተዳድር ሕንፃዎች፣ ወዘተ ጨረታዎች በሙሰኞች  ተጠልፈው ከፍተኛ የአገር ሀብት እየወደመ  ድህነትን መሻገር ህልም ሆኖ ይቀራል፡፡

‹ጉዳይ ገዳይ› ተብለው በሚታወቁ ደላሎች አማካይነት ሕገወጥ ተግባራት በመስፋፋታቸው ግዥዎችንና ጨረታዎችን በሕጋዊ መንገድ ተወዳድሮ ማግኘት ፈተና የሆነባቸው ዜጎች ብሶትና ምሬት ጣሪያ መንካቱንም ለፋታ መዘንጋት የሚያስከፍለው ዋጋ ውድ ነው፡፡ የመንግስት የፖሊሲ አቅጣጫ እኩል ተጠቃሚነትን የሚደግፍ አሠራር ቢሆንም፣ ሕገወጥነት የበላይነት ይዞ የጥቂቶች መፈንጠዣ ሆኗል፡፡ መደመር ይህን መጠየፍ ነው። በዚህ ዓይነቱ ዓይን አውጣ አሠራር ምክንያት ብዙኃን እየተገፉ፣ ጥቂቶች በአቋራጭ ባገኙት ሲሳይ ይከብራሉ፡፡ አሠራሮች ግልጽነትና ተጠያቂነት ስለሌላቸው በሕጋዊ መንገድ መንቀሳቀስ ሞኝነት፣ ሕገወጡን ጎዳና መያዝ የብልጥነት መለያ ከሆነ ድህነትን መሻገር ከቶም የማይቻል ይሆናል፡፡  

በፌዴራሉ የገቢዎችና ጉምሩክ  ባለስልጣን ከጉምሩክ ስርዓቱ ጋር ተያይዞ በወደብ፣ ደረቅ ወደብና በአውሮፕላን ማረፍያ አካባቢ የሙስና፣ የስራ መጓተትና ኢ-ፍትሃዊ ትመና በስፋት እንደሚታይ እንዲሁም ከገቢ ግብር ትመና ጋር በተያያዘ ዝቅተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ያለው ነጋዴ ላይ ከፍተኛ የግብር ግምት የሚጣልበት፤ በተቃራኒው ደግሞ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ያለው ነጋዴ ላይ አነስተኛ የግብር ግምት የሚጣልበት ሁኔታ በስፋት መኖሩ እንዲሁም ተመሳሳይ ጥፋት ያጠፉትን ተመሳሳይ ቅጣት አለመቅጣት አያሻግረንም፡፡ በጉምሩክ ስርዓቱ ባለጉዳይን ማስተናገድ ላይ የሚታይ የኢ-ፍትሃዊነት አሰራር ስር ሰዷል። ከነዚህም መካከል ሠነድ በፍጥነት አለመበተን፣ ታሪፍ እያሳሳቱ ያልሆነ ቀረጥና ታክስ መጠየቅ፣ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት መደራደርና ከጉምሩክ አስተላላፊዎች ጋር ተመሣጥሮ መስራት የሚጠቀሱና አላሻግር ያሉን ነቀርሳዎች ናቸው፡፡

በግብር አስተዳደር በተለይ በቁርጥ ግብር ውሳኔ፣ በግብር ከፋይ ደረጃ ሽግግር፣ ለተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይነት ምዝገባ እና የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ መጠቀም ያለባቸውን አንዲጠቀሙ ከማድረግ አኳያ በአመራሩና በባለሙያው አድሎ የሚፈጸም ስለመሆኑ በርካቶቹ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በእንባ እየገለጹ ነው፡፡ እንዲህ እየሆኑ መደመርም መሻገርም አይቻልም።

ብዙኃኑ ሕዝብ የሚፈለግበትን ግብር በአግባቡ ሲከፍል፣ ጥቂቶች በቢሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት ሲሰውሩ ማኅበራዊ ፍትሕ ስለሚጠፋ ሁከት መንገሱ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ጥቂቶች የአገሪቱን መሬት ወረው እየቸበቸቡ ሲከብሩና ቢጤዎቻቸውን ሲያበለፅጉ፣ ብዙኃኑ አንጀታቸው እያረረ መሻገር አይቻልም ብቻ ሳይሆን አገር ሰላም አይሆንም፡፡  

 

ማኅበራዊ ፍትሕ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲ መብቶቻቸው የሚከበሩበት፣ በሁሉም መስኮች ጥቅሞቻቸው በአግባቡ የሚስተናበሩበት፣ በጥረታቸው መጠን የሚያገኙበት፣ በሕግ ፊት እኩል የሚሆኑበት፣ ሐሳባቸውን በነፃነት የሚገልጹበት፣ የመንግሥት ጥበቃ የሚያገኙበት፣ በሕጉ መሠረት ብቻ የሚዳኙበት የአሰራር ስርአት ተዘርግቷል፡፡ ለመሻገር እስከሻን ድረስ የቀን ገቢ ግምቱ ወደታክስ ስርዓቱ ያልገቡትን ህጋዊ መስመር ለማስያዝ እንጂ ህጋዊ ነጋዴው ላይ ተጨማሪ ግብር ለመጫን እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡በታክስ እና ግብር ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተሰበሰበ ያለው ግብር ከ 13 በመቶ የበለጠ አይደለም፡፡ይህ ደግሞ ከሰሃራ በታች ካሉ ሃገራት  በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ነው፡፡በአዲስ አበባም ቢሆን በዓመት ከ 40 እስከ 50 ቢሊዮን ብር የመሰብሰብ አቅም ቢኖርም በተጨባጭ እየተሰበሰብ ያለው ግን ከግማሽ  የዘለለ አይደለም ፡፡   

ይሁን እንጂ ጥናቱ ነጋዴውን ያላሳተፈ፣ በቂ ግንዛቤ ያልተፈጠረበት፣ በተከታታይ ቀናት የነጋዴውን የሽያጭ መጠን ከግንዛቤ ያላስገባና በአንድ ቀን እይታ ብቻ የቀን ገቢ ግምት የተወሰነበት፤ ነጋዴው ካመነው ሽያጭ በሶስትና በአራት እጥፍ ውሳኔ የተሰጠበት መሆኑን ዋልታ ባዘጋጀው እንነጋገር ፕሮግራም ላይ የተሳተፉ የነጋዴ ተወካዮች መናገራቸውን እናስታውሳለን፡፡

የቀን ገቢ ግምቱ ነጋዴው ሸጦ ወይም አገልግሎት ሰጥቶ በሚያገኘው ገቢ መሰረት መሰላት ሲገባው የተጋነነና ነጋዴው ከሚሸጠው ጋር ሲነፃጸር የተራራቀ በመሆኑ አብዛኛውን ነጋዴ ቅሬታ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል ብለዋል የነጋዴ ተወካዮቹ፡፡ አዋጁ ከግብር ውጭ ያደረጋቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በቀን ገቢ ግምት ውስጥ እንዲካተቱ ማደረጉንም ተወያዮቹ ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው ከ2003 ጀምሮ ላለፉት ስድስት ዓመታት የቀን ገቢ ግምት መረጃና ጥናት በወቅቱ ባለመካሄዱ ፍትሃዊ የንግድ ሥርዓት ለማስፈን አዳጋች ሆኖ መቆየቱን አመልክተዋል ።አዲሱ የቀን ገቢ ግምት ወደ ታክስ ሥርዓቱ ያልገቡትን ህጋዊ መስመር እንዲከተሉ የሚያስችል እንጂ በህጋዊ ነጋዴ ላይ ተጨማሪ ግብር ለመጣል ያለመ እንዳልሆነ አብራርተዋል፡፡

የቀን ገቢ ግምቱ ጥናት ሲካሄድ የንግድ ቦታ ዘግቶ መጥፋት፣ከንግድ መደብሩ እቃ ማሸሽ፣ ለመረጃ ሰብሳቢዎቹ የተዛባ መረጃ መስጠትና ሽያጭን አሳንሶ መናገር በነጋዴው በኩል የታዩ ችግሮች እንደነበሩ ሃላፊዎች አስገንዝበዋል፡፡ በግብር ሰብሳቢው በኩል ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ያለመሰራታቸውና በነጋዴውም በኩል በተሟላ መልኩ ተገቢውን ግብር መክፈል አለብኝ የሚል አመለካከት አለመዳበሩ እንደችግር ተጠቅሰዋል፡፡ስለሆነም እንዚህን ችግሮች በጋራ በመቅረፍ ወደመፍትሄው ለመምጣት ብቸኛው አማራጭ ይልቁንም ለመሻገርና ለመደመር የሚያስችለው ፍትሃዊና ዘመናዊ የታክስ ስርዓት እንዲዘረጋ ነጋዴውም ሆነ መንግስት የየበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት መስራት ነው።

መንግስት አብዛኛውን አገሪቱን የልማት ወጪዎች በራስ አቅም ለመሸፈን ባለው አቋም መሠረት 80 በመቶ ያህል ወጪዎቹን በዚሁ አግባብ ከአገር ውስጥ ምንጮች ለመሸን እንደቻለም ሲገልጽ ይደመጣል፡፡ ይሁንና አሁንም ድረስ በታክስ መረብ ውስጥ ያልተደመረ ሰፊ የንግድ ማኅበሰረብ እንደሚገኝ ሲገልጽ ዋናው መደበቂያ ደግሞ የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች ውስጥ የሚገኙት እንደሆኑ አስታውቋል፡፡ ከዘጠኝ ሺሕ ያላነሱ ነገር ግን ከፍተኛ ግብር ከፋይ መሆን የሚገባቸው ነጋዴዎች እንደሚገኙ ጥናቶች ያረጋግጣሉና በግብር እንሻገር፤እንደመር ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy