Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሪፎርሙ አንድምታዎች

0 307

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሪፎርሙ አንድምታዎች

                                                          ታዬ ከበደ

አሁን የምንገኝበት አገራዊ ሁኔታ የኢኮኖሚ ሪፎርም ማድረግ የግድ የሚልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የልማታዊ መንግስት አንዱ መገለጫ የገበያ ክፍተትን መሙላት ይታወቃል። በአሁን ጊዜ አገራችን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደገጠማት ይታወቃል።

የአገራችን የብድር ጣሪያም ወደ ከፍተኛ ዕዳ ወዳለባቸው አገራት ምድብ መሸጋገር ጀምሯል። አሁን የብድር መክፈያ ጊዜው መድረሱና ይህም ተዓማኒነትን በማሳጣት በቀጣይ አበዳሪ አካል እንዳይኖር የሚያደርግ ነው።

ይህን ሁኔታ ለመቀየር መንግስት በእጁ ያሉትን የልማት ተቋማት በከፊልና ሙሉ ለሙሉ መሸጥ ይኖርታል። በአሁኑ ሰዓት በመንግስት ወጪ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅና በአገሪቱ የሚከናወኑ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ለመፈፀም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ይፈልጋሉ።

ስለሆነም መንግስት በመንግስት እጅ ያሉ ትላልቅ የልማት ድርጅቶችን ፕራይቬታይዝ በማድረግ የኢኮኖሚ ዕድገቱን ማስቀጠል ካልተቻለ የዋጋ ግሽበት እንዲሁም የኢኮኖሚው  ውድቀት ሊከሰት ይችላል። እናም መንግስት ደንብና መመሪያ ላይ ተመስርቶ እያንዳንዱን የልማት ድርጅት ወደ ግል በማዞር የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ተግባርን ይከውናል። በመሆኑም እንደ ቴሌ፣ አየር መንገድና የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎትና ሌሎች ኩባንያዎች በከፊልና ሙሉ ለሙሉ ወደ ግል እንዲዞሩ ይደረጋል።

እርግጥ ወደ ግል ይዞታ እንዲዘዋወሩ የሚፈለጉት ኩባንያዎች ከመንግሥት ሞኖፖሊ ወደ ግል ሞኖፖሊ እንዲዘዋወሩ ማድረግ የሚፈለገውን ሐሳብ የሚያሳካ አይደለም። ባለፉት ዓመታት ወደ ግል ይዞታ የተዘዋወሩ ኩባንያዎች በጥቂት ግለሰቦች የተገዙ ናቸው።

በዚህም ምክንያት ከመንግሥት ያልተሻለ ውጤታማነት ማስመዝገብ አልቻሉም። በአሁኑ ሂደት ዓይነት ስህተት አይደገምም። በአፍሪካ አገሮች የተስተዋሉ ስህተቶችም በኢትዮጵያ እንዳይደገሙ ጥንቃቄ እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶከተር አብይና የስራ ባልደረቦቻቸው በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

እንደ ቴሌና አየር መንገድ የመሳሰሉ ኩባንያዎች አብላጫው አክሲዮናቸው በመንግሥት ይዞታ ስር የሚቀጥል ይሆናል። ለሽያጭ ከሚቀርበው የአክሲዮን ድርሻ ውስጥ አምስት በመቶ የሚሆነው ውጭና አገር ውስጥ ላሉ ኢትዮጵያውን እንዲሰጥ ለማድረግ ታስቧል። እንዲሁም ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆነው በሚሹት የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ልምድ ያላቸው ኩባንያዎች ብቻ እንዲሳተፉ ይደረጋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም ለኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚሸጠው የአክሲዮን ድርሻ ገንዘብ ያላቸው ብቻ እንዳይጠቀልሉ ጥንቃቄ ይደረጋል። እንዲዘዋወሩ የሚፈለጉ ኩባንያዎችም ገበያውን በሞኖፖሊ ጭምር ይዘው ያለ ውድድር በበቂ ደረጃ ማደግ ያልቻሉ መሆናቸው ይታወቃል።

ለግንዛቤ እንዲሆነን ጥቂት ኩባንያዎችን በምሳሌነት አንስተን መመልከት አንችላለን። ቴሌ የአገር ውስጥ የስልክ ጥሪ የሚገኝ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ያደረገ ሲሆን፣ ከውጭ ጥሪ የሚገኝ ገቢ ከዓመት ዓመት በእጅጉ እየቀነሰበት ያለ ተቋም ነው። ይህ የሚሆነው ደግሞ በውስጥም በውጭም የቴሌኮም ማጭበርበር በመኖሩ እንደሆነ አይታበይም።  

በአሁኑ ወቅት በየትኛውም የዓለም ከፍል የቴሌኮም ማጭበርበር አለ። ይሁን እንጂ የእኛ አገር የከፋ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በኩባንያው የሃብት ብክነት አለ። ኩባንያው እየገዛ በየመጋዘኑ ያከማቸው ሃብትና ንብረት ስፍር ቁጥር የለውም። ይህ ሃብት የመንግሥት ስለሆነ እንጂ በግል ሴክተር ቢሆን ፈፅሞ የሚታሰብ አይደለም። እነዚህን ሁኔታዎች ለመቀየር ኩባንያው በከፊል ወደ ግል ይዞታ መዛወር አለበት።

ከጥራት አንፃርም ኩባንያውን የማያማርረው ህዝብ የለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በቅርቡ ለፓርላማ ሲገልፁ፤ በሶማሊያ 12 ሚሊዮን ህዝብን ለማገልገል አራት ኩባንያዎች የሚሰጡት ጥራት ያለው አገልግሎት፤ በመቶ ሚሊዮን ለሚቆጠረው የኢትዮጵያ ህዝብ አገልግሎት ከሚሰጠው አንድ የመንግሥት ኩባንያ በብዙ እጥፍ ይሻላል ማለታቸው መሰረታዊው ሁኔታ ይኸው ስለሆነ ነው።

ይህ የተፈጠረው በሶማሊያ ውድድር ስላለ መሆኑ ግልጽ ነው። እናም በአገራችን ውድድር ባለመኖሩ የአገር ሃብት እንዲባክንና የአገልግሎት ጥራት እንዳይኖር ስላደረገ ይህን መቀየር ያስፈልጋል።

ከሃይል አቅርቦት አኳያ በተደጋጋሚ መንግሥት የሚተቸው በየገጠሩ የኤሌክትሪክ ፖል ቆሞ መብራት ማድረስ አልተቻለም የሚል ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ መንግስት ኤሌክትሪክ አምርቶ እንደገና ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትር መስመር ዘርግቶ ማቅረብ ያዳግተዋል። ከአቅም አኳያም ከባድ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ በኢትዮጵያ የሚመረተው የኤሌክትሪክ ሃይል 35 በመቶ የሚሆነው በሥርጭት ወቅት ይባክናል። ይህን ችግር ለመፍታት እንደ ኢትዮጵያ ላለ አገር የሚያዋጣው ከብሔራዊ የሥርጭት ቋት ይልቅ አካባቢያዊ የስርጭት ቋት ወይም “ሎካል ግሪድ” መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስረዳታቸውን እናስታውሳለን። በመሆኑም እዛው በዛው ተመጋጋቢ የሀነ የሃይል አቅርቦትና ሽያጭ ያስፈልጋል።

ምንም እንኳን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመላው ዓለም ክብርና ዝና ያለው ቢሆንም፤ አሁን ያለው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ የሚጠይቀውን ኢንቨስትመንት በማለፍ፣ ይህንን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ዝናና ክብር ማስጠበቅ ደግሞ ጊዜው የሚጠይቀው ተግባር ሆኗል። አሁን አፍሪካዊያን ወደ አንድነት እየመጡ ያሉበት ውቅት ነው።

ለዚህም በቅርቡ በአፍሪካ ደረጃ አንድ አየር መንገድ ይኑረን የሚል አቋም ይዘዋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ይህን ሁኔታ ለማሳካት ተፈራርመዋል። በዚህ መሰረትም የማላዊ አየር መንገድ ግማሹ ሃብት የእኛ ሊሆን ችሏል፤ አየር መንገዱ የማላዊን አየር መንገድ 49 በመቶ ድርሻ ገዝቷልና።

እንዲሁም አየር መንገዳችን ከዛምቢያ አየር መንገድ 45 በመቶ፣ ከቻድ 49 በመቶ፣ ከጊኒ 49 በመቶ፣ ከቶጎ 49 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ገዝቷል። ከሌሎች ለመግዛትም በሂደት ላይ ነው። ይህም አየር መንገዱ  ውጤታማ ሆኖ መለያችን የሆነውን ባንዴራ ለዓለም ከማስተዋወቅ በላይ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ ሆኖ በአፍሪካ ደረጃም የኢትዮጵያን ባንዴራ እንዲያውለበልብ ይደረጋል።

እርግጥ አየር መንገዱ ከሌሎች አገሮች ከላይ የተጠቀሱትን ድርሻዎች እየገዛ እርሱ አልሸጥም ሊል አይችልም። ለእኛ የሚበጀንም ድርሻን ሸጦ አፍሪካዊ አየር መንገድ ቢሆን ነው። የአፍሪካ አየር መንገድ በመሆን ትርፋማነቱን ሊያጠናክር ይችላል። እናም የኩባንያው ወደ ግል የዞር ሁኔታ ከዚህ አኳያ መታየት ያለበት ይመስለኛል።

በጥቅሉ ከላይ የተጠቀሱት ኩባንያዎችና እዚህ ላይ ያልጠቀስኳቸው የልማት ደርጀቶች ወደ ግል በከፊልና ሙሉ ለሙሉ ሲሸጋገሩ በመንግስት ይዞታነት ስር በመሆናቸው ብቻ ሳያከናውኑ የቀሩትን ጉዳዩች እንዲሁም ትርፋማነትንና ተደራሽነትን ማረጋገጥ ይችላሉ። ስለሆነም መንግስት ኩባንያወቹን ለመሸጥ የኢኮኖሚ ሪፎርም ማድረጉን ከእነዚህ አንድምታዎች አኳያ መገንዘብ ያስፈልጋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy