የሰላም አየር—በደቡብ ሰማይ ስር
ዘአማን በላይ
የተፈጥሮ ዑደት በጋ መሆኑን ሲያበስር ‘የሚበጋው’፣ ክረምት ሲሆንም ‘የሚከርመው’ የደቡብ ክልል ሰማይ፤ የሀገራችን ህዝቦች አንድነት፣ መቻቻል፣ ፍቅርና አብሮነት ሁነኛ ማሳያ ነው። ክልሉ “ትንሿ ኢትዮጵያ” በመባልም የሚጠራውም ለዚሁ ነው። በአመዛኙ የዚያ ክልል ሰማይ የሐዘን ድባብ አጥልቶበት አያውቅም። ጥላቻንና ቂም በቀልን የማስተናገድ ተፈጥሮም የለውም። ያ ሰማይ የፍቅር አየር የሚናኝበት እንደ ምንጭ ውሃ ኩልል ያለ ሰላማዊ ፀዳልን የተላበሰ ነው። ግና ከመሰንበቻው የተከሰተው ያልተለመደ ክስተት ‘እናስ ክለሉ ዛሬ ምን ነካው?’ አስብሏል።
የክልሉ መንግስት በቅርቡ እንዳስታወቀው፤ በሀዋሳ፣ በወላይታና በወልቂጤ እንዲሁም በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች በተቀሰቀሰ ግጭት 27 ሰዎች ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል። የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመትም ተከስቷል። ለችግሩ ፈጠር ምክንያት የሆኑ አንድ ሺህ 130 ግለሰቦች ተይዘው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑም ተገልጿል። ይህም ከህግና ከህዝብ ክትትል ማንም ማምለጥ እንደማይችል ያሳየ ነው ማለት ይቻላል።
ያም ሆኖ ግን የሰው ህይወት ማለፉ፣ አካል መጉደሉና ንብረት መውደሙ፤ ከክልሉ ታሪካዊ ዳራ አኳያ ሲታይ በእጅጉ የሚያም ነው። ያሳዝናል፤ ያስቆጫልም። የፖለቲካ ሲራራ ነጋዴዎች ህዝቡን በማባላት ሊበሉት እንዳሰቡትም ያሳያል። በልተው የማባላት ሴራን ጠንስሰው የህዝቡን ሰላም እንዳወኩትም እንዲሁ። ይህ በደቡብ ክልል ውስጥ አጫራሽ አጀንዳን በመፍጠር ሰላማዊውን ህዝብ ለማባላት የሚደረገው ሴራ አንድ ቦታ መቆም ይኖርበታል እላለሁ።
። ዶክተር አብይ አህመድም ጉዳዩ ሳይባባስ ‘መጥቼ እስከምንነጋገር ድረስ ሁሉም ሰላሙን በየአካባቢው እንዲጠብቅ አሳስባለሁ’ ባሉት መሰረት በየአካባቢዎቹ ተከስቶ የነበረው ሁከት ወዲያውኑ ጋብ ሊል ችሏል። ወዲያውኑም ዶክተር አብይ ቃላቸውን ጠብቀው ችግሩ ወደ ተፈጠረባቸው አካባቢዎች በማምራት ከየአካባቢው ህዝቦች ጋር ተወያይተዋል።
ርግጥ በሀዋሳ በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ግለሰቦችና የሀገር ሽማግሌዎች የተፈጠረው ግጭት የሲዳማን ህዝብ እንደማይወክል ተናግረዋል። እንዲሁም ለ12 ዓመታት ሲንከባለል መጥቷል ያሉትን የሲዳማ ብሔር ራስን በራስ የማስተዳደር ወይም ክልል የመሆን ጥያቄንም አንስተዋል። ከዚህ በተጨማሪ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ የልማት ስራዎች ተጠቃሚ ያለመሆናቸውን፣ በልማት ምክንያት የሚነሱ አርሶ አደሮች ተገቢውን የካሳ ክፍያ አለማግኘታቸውና የወጣቶች የስራ አጥነት ችግር በጥያቄነት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ቀርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይም የፊቼ ጨምበላላን በዓልን ተከትሎ በሀዋሳ ከተማ የተፈጠረው ግጭት ሊፈጠር የማይገባውና መሆን ያልነበረበት እንደሆነ ገልፀው፤ ግጭቱ እንዲቆም ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎም ግጭቱ እንዳይባባስ አስተዋፅኦ ላደረጉ የሲዳማ ብሄር ተወላጆችና ሌሎች አካላት ምስጋናቸውን ቸረዋል። የተነሱት ጥያቄዎችም በህገ መንግስቱ መሰረት ምላሽ እንደሚያገኙም ገልፀዋል። የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በሆነው ፊቼ ጨምበላላ በዓል ላይ ግጭት እንዲፈጠር ያደረጉ አካላት የሲዳማ ህዝብ ጠላት ናቸውም ብለዋል። ግጭት እንዲፈጠርና ለሰው ደም መፍሰስ ምክንያት የሆኑ ግለሰቦችን መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን ለህግ ባሉት መሰረትም ከላይ በመግቢያዬ አካባቢ እንደገለፅኩት፤ አንድ ሺህ 130 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ ነው።
ይህም መንግስት የህዝቡን ጥያቄ ተቀብሎ የዜጎችን ህይወት እንዲቀጠፍና አካል እንዲጎድል እንዲሁም ንብረት እንዲወድም ያደረጉ አካላት ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ የሚያረጋግጥ ነው። ርግጥ በክልሉ የተፈጠረው የመልካም አስተዳደር ችግር ባለቤቶቹ የፖለቲካ ነጋዴዎች መሆናቸው ይታወቃል።
መልካም አስተዳደር ከህዝቡ የዕለት ተዕለት ሁኔታ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ህብረተሰቡ እነዚህን ሃይሎች በመታገል የፖለቲካ ንግዳቸውን እንዲያቆሙ ማድረግ ይችላል። የሚፈጠሩ ችግሮችን በመጠቆምና የጉዳዩ አካል ሆኖ ችግሮቹን ለመፍታት በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ ቀዳሚ ተዋናይ በመሆን በህዝብ ደም ለመነገድ የሚሹ አካላትን መታገል የመፍትሔው አካል ነው። እናም የሲዳማ ህዝብ ያልመለሱ ችግሮች ቢኖሩም እንኳን ችግሮቹን ህግንና ስርዓትን መሰረት ባደረገ መልኩ መፈታት ይኖርበታል።
ይህም የህዝቡን ጥያቄዎች ተንተርሰው የፖለቲካ ንግዳቸውን ለማጧጧፍ የሚሹ አካላትን ቦታ የሚያሳጣ ነው። እናም ህዝቡ ሰላሙን ከመንግስት ጋር በመሆን ማረጋገጥ ይኖርበታል እላለሁ። ይህ እውነታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውይይት በተገኙባቸው በወላይታና በጉራጌ ዞኖችም መረጋገጥ ይኖርበታል። ምክንያቱም በሁሉም አካባቢዎች የተፈጠረው ችግር የፖለቲካ ነጋዴዎች በሚለኩሱት እሳት አማካኝነት የተፈጠረና ክስተቱም በምንም ዓይነት መንገድ የህዝቦችን ፍላጎት ሊወክል ስለማይችል ነው።
የ“ትንሿ ኢትዮጵያ” መገለጫ በሆነችው የደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭት፤ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ በሀገራችን እየሰፈነ ያለውን ሰላምና መረጋጋት ብሎም እየታየ ያለውን ኢትዮጵያዊ መግባባት እንዲሁም የተሰናሰለ የህዝቦች አንድነትን የሚወክል አይደለም። ይህን ታላቅ ህዝብና ሀገር የማይወክል ኋላ ቀርና ጊዜው ያለፈበት “ፋሽን” ነው።
በተለይም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና መንግስታቸው፤ ሀገራዊ ጥቅማችንን ከማስጠበቅ አልፎ ቀጣናዊ ትስስር እየፈጠሩና ያጋጠሙንንም ችግሮች በመቅረፍ የህዝቦቻችንን የተከማቹ ችግሮች ለመፍታት ቀንና ለሊት እየሰሩ ባሉበት በዚህ ወቅት በክልሉ የተስተዋሉት ጊዜያዊ ግጭቶች በምንም ዓይነት ምድራዊ ሰሌት ተቀባይነት ያላቸው አይደሉም። እናም ከመጋረጃው በስተጀርባ ያሉት የሴራ ፖለቲካ ነጋዴዎች ይህን ሃቅ ማወቅ ይኖርባቸዋል እላለሁ።
ለዘመናት አብሮ በኖሩ ህዝቦች መካከል ድንበርንና ሌሎች ምክንያቶችን በመፍጠር ጥርጣሬን የሚፈጥሩ እንዲሁም ለግጭት የሚጋብዙ የፖለቲካ ነጋዴዎቹ ድብቅ ሴራዎች፤ ተቻችሎ በአንድነትና በፍቅር የሚኖረውን ህዝብ የሚያማክሉ አይደሉም። ተግባሩ የተጀመረው ሀገራዊ የለውጥ ሂደት ባልተዋጠላቸው አካላት ጠንሳሽነት የተመራና እንዲሁም የሀገራችን ህዝብ ሙሉ ለሙሉ የተቀበለውን የለውጥ ሂደት ለማደናቀፍ ያለመ መሆኑ ግልፅ ነው። ሆኖም ህዝቡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በሰላም፣ በፍቅርና በአንድነት መንገድ ውስጥ ስለገባ፤ ከዚህ የተቀደሰ ጎዳና የሚያወጣው አንዳችም ሃይል የለም። የችግሩ ፈጣሪዎች ምናልባትም በሴራቸው የተፈጠረውን የአንድነት ገመድ ያጠብቁት ካልሆነ በስተቀር ሊያላሉት የሚችሉበት ምንም ዓይነት አቅም ያላቸው አይመስለኝም።
ምንም እንኳን ይህን መሰል ጥፋትና ግጭት ያቀነባበሩትና ሁከቱን ያባበሱት አካላት ዓላማ በአሁኑ ወቅት የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ማወክ፣ መንግስት እየገነባው ያለውን ሀገራዊ አንድነት መናድ እንዲሁም አዲሲቷ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ውጤታማና ፈጣን የሪፎርም እንቅስቃሴ ማደናቀፍ ቢሆንም፤ ይህ ደባቸው በህዝቡ ሊታገዝ የማይችል ስለሆነ የሚሰምር አይደለም። ፉርሽና ወዳቂ ነው የሚሆነው። ህዝቡ ወደፊት በተጠናከረ ሁኔታ የሰላሙ ባለቤት እየሆነ በመጣ ቁጥር ሴራቸው እርቃኑን ስለሚቀር መደፈቁ አይቀሬ ነው።
እንደ እውነቱ ከሆነ የ“ትንሿ ኢትዮጵያ” መገለጫ የሆነችው ደቡብ ክልል ከዚህ በፊት ተፈፅሞ የማያውቀው ጊዜያዊ ግጭት በክፉውም ይሁን በደጉ ወቅት አብረው ተሳስረው በኖሩ ህዝቦች መካከል ያለውን የተጠናከረ አንድነት የሚፈታው አይደለም። ‘ለምን?’ ከተባለ የየትኛውም ህዝብ ፍላጎት ሁሌም ሰላም፣ ልማትና ብልፅግና እንጂ፤ ብጥብጥ፣ ሁከትና ውድመት ስላልሆነ ነው።
ይህ የህዝቦች ከብረት የጠነከረ የህዝቦች ፍላጎት እስካለ ድረስም፤ በአዲሱ አመራርና በመንግስታቸው የለውጥ መሪነት ሀገራችን ከቀውስ ለመውጣት የተጀመረው ጥረት እንደሚሳካ ማወቅ ብልህነት ይመስለኛል። እናም አሁን በምንገኝበት ታሪካዊ ወቅት የግል ጥቅምን ታሳቢ አድርገው ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት በስውር የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ነጋዴዎችን የመግታት ኃላፊነቱ በእያንዳንዱ የሀገሬ ህዝብ ጫንቃ ላይ መውደቁን መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህ ሲሆንም፤ የሰላም አየር በደቡብ ክልልም ይሁን በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች ሰማይ ስር መናኘቱ አይቀሬ ነው። ሰላም ለኢትዮጵያችን!