Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የተምች ወረርሽኝ ላይ እንደተምች ለመዝመት

0 446

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

የተምች ወረርሽኝ ላይ እንደተምች ለመዝመት

 

ዮናስ

 

አሜሪካ መጤ ተምች ይባላል። ከ80 በላይ ሰብሎችን የሚያጠቃው ይህ ተምች በተለይ በቀጣናው ሀገራት ዋነኛ ምግብ የሆነው የበቆሎ ሰብልን በስፋት የሚያጠቃ በመሆኑ ጉዳቱ ዘርፈ ብዙ እንደሆነም ይነገርለታል። በተለይም ከኢሊኒኖ ድርቅ እያገገሙ ያሉ ሀገራት ለችግሩ ይበልጥ ተጋላጭ እንደሚሆኑ የሚያወሱ መረጃዎች፤ የተምች ወረርሽኙ አፋጣኝና የተቀናጀ የተባይ ስራ አመራር እርምጃዎች ካልተወሰዱ በምግብ ሰብል ላይ የምርት መቀነስና የዋጋ ንረት ስለሚያስከትል የቀጣናው ዜጎች ለምግብ ዋስትና እጦት ችግሮች ሊዳረጉ ይችላሉ። ይህ የተባለውም በአምናው የመኸር ወቅት  በሃገራችንም ተመሳሳይ አደጋ አስከትሎ የነበረ መሆኑን በማስታወስ ነው።

 

አምና በደቡብ ክልል ብቻ የተከሰተው የተምች ወረርሽኝ በ40 ሺህ ሄክታር መሬት በተዘራ ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል።ከ80 በላይ በሚሆኑ የእፅዋት እና ሰብል ዝርያዎች ላይ ጉዳት የሚያደርሰው ፎል አርሚ ወርም የሚባለው ይህ የተምች ዝርያ  በክልሉ በጋሞጎፋ፣ በወላይታ እና ከምባታ ጠንባሮ ዞኖች ከበቆሎ ባለፈ በእንሰት፣ በሰሊጥ እና በድንች ሰብሎች ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡በአማራም ተመሳሳይ ጥፋት አስከትሏል።

 

እንግዲህ ተምች የተለያየ ዝርያ ያለው ሲሆን፣ ከቢራቢሮ እንቁላል የሚፈለፈል ትል (አባ ጨጓሬ) ነው። ይህ ትል ኩብኩባ ሆኖ እድገቱን ሲጨርስ ክንፍ አውጥቶ ይበራል። ታዲያ ይህ የቢራቢሮ ውላጅ የሆነ ተምች እንደየዝርያው የተለያየ መጠን ያለው የሰብል ጥቃት ያደርሳል። በተለይ በወረርሽኝ መልክ ሲከሰት በማሳ ላይ ያለ ሰብልን ክፉኛ ይጎዳል። ይህም የምግብ እጥረት በማስከተል የቸነፈር ምክንያት ይሆናል።

አምና ከሳህራ በታች ባሉ ከ20 በላይ የአፍሪካ ሃገራት የተምች ወረርሽኝ ተከስቷል። በኢትዮጵያም እንዲሁ። ይህ ተምች በሳይንስ ስሙ ስፖዶፔትራ ፍሩጊፔራ ወይም ፎል ይባላል። የትውልድ ሃገሩ ከሰሜን አሜሪካ እስከ ደቡብ አሜሪካዋ አርጀንቲና የሚገኙ ምእራባዊ እርጥበታማ ሞቃት አካባቢዎች ናቸው። ይህ ተምች ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ግን ወደአፍሪካ ዘምቷል።

 

ከአሜሪካ ወደምእራብ አፍሪካ የተጓዘው ከበቆሎ ጋር ተጭኖ ነው የሚል መላ ምት አለ። ቢራቢሮው በንፋስ እየተገፋ አትላንቲክን አቋርጦ ነው ወደምእራብ አፍሪካ የደረሰው የሚል መላ ምት የሚያስቀምጡም አሉ። የተጓጓዘው በምንም ይሁን ምን አሜሪካዊው ተምች አምና  ሃያ ያህል የአፍሪካ ሃገራት ላይ ወረራ ፈጽሞ ጥቃት አድርሷል።

 

ቢራቢሮው በቀን ከ100 እስከ 500 ኪሎ ሜትሮች የመጓዝ አቅም ያለው ይህ ተምች እስከ 3 ሺህ ኪሎ ሜትር ሊጓዝ እንደሚችል በአሜሪካ የተካሄዱ ጥናቶች ያመለክታሉ። ተመቹ ከአርጀንቲና እስከ ካናዳ የተጓዘባቸው ወቅቶች ተመዝግበዋል።   

ፎል የተባለው አሜሪካዊ ተምች በተለይ የሚያጠቃው በቆሎና ማሽላን ነው። የሸንኮራ አገዳንም በተለየ ያጠቃል። በቆሎና ማሽላ ከ200 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ከሳህራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሃገራት ህዝቦች ዋና የምግብ ምንጭ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥም በተለይ በስምጥ ሸለቆ ቆላማና ወይና ደጋ አካባቢዎች፣ በምእራብ እርጥበታማና በምስራቅ ደረቃማ አካባቢዎች የሚኖረው ህዝብ ዋና የምግብ ሰብል በቆሎና ማሽላ መሆኑ ይታወቃል። ተምቹ በቆሎና ማሽላን በተለይ ያጠቃል ይባል እንጂ ሌሎች የሰብል ምርቶችንም አይምርም። ስንዴ፣ ገብስ፣ ማሽላ፣ ዳጉሳ፣ አኩሪ አተር፣ ድንች፣ ጥጥ፣ አትክልትና የተለያዩ ቅጠለ ሰፋፊ ሰብሎችንም ያጠቃል። ስለሆነም በዚህ መኸር ተመሳሳይ አደጋ እንዳይመጣ ጥንቃቄ ማድረግና ቅድመ መከላከል ዘመቻ ያስፈልጋል።

 

በደቡብ ክልል ሁሉም ዞኖች፣ በአሮሚያ ክልል ሰባት ዞኖች፣ በአማራ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ጎጃም፣ በጋምቤላ እና ቤንሻጉል ጉሙዝ ክልሎች ላይ መዛመቱ ይታወሳል። በአጠቃለይ በእነዚህ ክልሎች በ35 ዞኖች በ235 ወረዳዎች ውስጥ በሚገኝ በ146 ሺህ 320 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ የበቆሎ ሰብል ላይ ጉዳት አድርሶ የነበረ መሆኑም በተመሳሳይ። በዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት የሰብል ተመራማሪ የሆነው ልዊስ ሆቭ ስለተምቹ ጥቃት ሲያብራራ፣ “ተምቹ ከቦታ ቦታ በፍጥነት ከመዛመቱ ባሻገር የሚያደርሰው ጥቃት የከፋ ነው። ተምቹ በሚከሰትበት አካባቢ የሚገኝ ሰብልን እስከ 80 በመቶ ማጥቃት ይችላል። ይህ ጥቃት በአንዳንድ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ሊሆን ይችላል።” ብሏል። በመሆኑም የተምቹን ጥቃትና መዛመት ከወዲሁ የመከላከሉ ተግባር ከአዘቦት የግብርና ስራ ባለፈ በዘመቻ  ሊከናወን ይገባል። አሁንም በታየው ፍንጭ አግባብ በተለይ ተምቹ የከፋ ጉዳት ሊያስከትል በሚችልባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የተደራጁ የህብረተሰብ ክፍሎች – የመከላከያና የፖሊስ ሰራዊት፣ የትምህርት ተቋማትና ሌሎች የህብረተሰብ አደረጃጀቶች ጸረ ተምች ዘመቻ ላይ እንዲሳተፉ ህዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር ያስፈልጋል።

 

የእርሻና የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ተምቹን መከላከል የሚያስችሉ ዘዴዎች ብሎ ያስቀመጣቸው ርምጃዎች አሉ። ቀዳሚው ባህላዊ ዘዴ ነው። ይህ ዘዴ ተምቹን በእጅ እየለቀሙ በመግደል የሚከናወን ነው። አንድ የተምች ቢራቢሮ እስከ ሁለት ሺህ እንቁላሎችን በቅጠል ላይ ትጥላለች። በመሆኑም አንድ ተምች መገደል ከቀናት በኋላ ሊፈጠሩ የሚችሉ ሁለት ሺህ ተምቾች እንዳይፈጠሩ የማድረግ እርምጃ ነው። የሳይንስ ጥናት እንደሚያመለክተው ፎል የተባለው የተምች ዝርያ በአንድ የተክል ግንድ ላይ ከሁለትና ሶስት በላይ አይኖርም። ከዚህ በላይ ከሆነ እርስ በርስ ይበላላል። በመሆኑም እያንዳንዱ የበቆሎ ወይም የማሽላ ግንድ ላይ ያለ ተምች በመልቀም ተምቹን በከፍተኛ መጠን መቀነስ ይቻላል።

 

ተምቹን በእጅ ከመልቀም ጋር የሚከናወነው ሌላው ባህላዊ የመከላከያ ዘዴ፣ በሰብሉ ዙሪያ የሚገኙ ያለፈ እርሻ ቃርሚያን፣ አረሞችን፣ የሰብል ቅሪቶችን፣ በማረስ መገልበጥ ነው። መሬቱ ታርሶ ሲገለበጥ በማሳው ላይ የነበረው ተምች መሬት ውስጥ ተቀብሮ በስብሶ ይጠፋል።በባህላዊ ዘዴ የሚገኘወን ውጤት መነሻ በማደረግ ሳይንሳዊ ዘዴን የመጠቀም አማራጭም አለ። ይህ የኬሚካል ርጭትን የሚመለከት ነው። ይህ በበቆሎ ወይም በማሽላ አገዳ ሙሽራ ውስጥ የሚደበቀውን ተምች የመግደል እድሉ አነስተኛ በመሆኑ፣ ውጤታማነቱ አስተማማኝ እንዳልሆነ ባለሞያዎች የናገራሉ። ዓለም አቀፍ መረጃዎች ደግሞ ተምቹ አብዛኛዎቹን የመከላከያ መደሃኒቶች ተለማምዷል። በዚህ ምክንያት ውጤታማነቱ አስተማማኝ አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ በአካባቢና መድሃኒቱን በሚረጩ አርሶ አደሮች ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችልበት ሁኔታም አለ። ያም ሆነ ይህ የተምቹን ጥቃትና መዛመት ለመከላከል እንደአማራጭ የሚወሰድ እርምጃ ነው። ሌላውና ለዚህ መኸር ስኬት ሊዘመትበት የሚገባው ተጠባቂ አደጋ ጎርፍ ነው።እንደብሄራዊ ሜትሪዮሎጂ መረጃ በአብዛኛዎቹ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ የተጠናከረና የተስፋፋ ዝናብ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በኤጀንሲው ትንበያ መሰረት የአገሪቱ ሰሜናዊ ፣ሰሜን ምእራብና ሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች፣ በአብዛኛው ከመደበኛው በላይ የሆነ ዝናብ የምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብና ደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ደግሞ መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ ይጠበቃል።

 

በተጨማሪም ደቡባዊ ከፍታማ ቦታዎችን ጨምሮ በአገሪቱ ማዕከላዊና ምስራቃዊ አካባቢዎች በርካታ ቦታዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው ተንብይዋል ። በክረምቱ ወቅት ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው በሚጠበቁት አካባቢዎች ባለፉት ዓመታት ካጋጠሙት ተመሳሳይ ክስተቶች በመነሳት የጎርፍ ተጠቂ በሆኑት ካባቢዎች ከወንዞች ሙላትና ከከባድ ዝናብ ጋር ተያይዞ ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት እንዳለም አስታውቋል፡፡

 

በመሆኑም በክረምት የሚኖረው የጎርፍ ክስተት ስጋት በበልጉ ወቅት ከነበረው የጎርፍ አደጋ ጋር ተዳምሮ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመከላከልና ለመቀነስ ዝግጅት ማድረግ ይገባል፡፡ በዚሁ መሠረት በጎርፍ አደጋ ስጋት ውስጥ ለሚገኙ የኀብረተሰብ

ክፍሎች በሚመለከታቸው አካላት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መረጃ ማስራጨትን ጨምሮ የዝግጁነትና የመከላከል እርምጃዎችን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ከባድ ዝናብ የማግኘት እድል ባላቸው በላይኛው ወይም ደጋማ አካባቢ በሚገኙት ወረዳዎችና ከነዚህ ወረዳዎች በሚመጣ ጎርፍ ተጠቂ በሆኑ በታችኛው አካባቢ በሚገኙ ወረዳዎች

መካከል ያለውን ግንኙነትና የመረጃ ልውውጥ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡

 

በፌዴራልና በየክልሉ የተቋቋሙ የጎርፍ መከላከል ግብረ ኃይሎችን ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል፣ዝግጁትና ምላሽን ከማጠናከር አኳያ የመጠባበቂያ ወይም የምላሽ እቅድ

ማዘጋጀትም ይገባል። የጎርፍ ስጋት ባለባቸው ቦታዎች የጎርፍ መከላከያዎችን ማጠናከር፣ኅብረተሰቡን በጎርፍ ተጠቂ ከሆኑ ቦታዎች በማንቀሳቀስ ሁኔታው እስኪሻሻል በተሻሉ ቦታዎች ለማስጠለል የሚያስችል ዕቅድ ማዘጋጀት እንደሚያሻም በተመሳሳይ፡፡

 

ለፈጣን ምላሽም ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁስን የአደጋ ስጋት ወዳለባቸውና በቀላሉ ለመድረስ አዳጋች ወደሆኑ ቦታዎች አስቀድሞ ለማስጠጋት ዝግጅት ማድረግና ሁኔታውን በመከታተል እርምጃ መውሰድ ከብዙ በጥቂቱ በዘንድሮው መኸር  ጥንቃቄ ሊወሰድባቸው የሚገቡ ስፍራዎች ናቸው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy