Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፍቅር ያሻግራል

0 573

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፍቅር ያሻግራል

 

ስሜነህ

 

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እርግማን ያለ ይመስል ከውይይት ይልቅ መተናነቅ፣ ከተፎካካሪነት ይልቅ መጠላለፍ፣ ከመደማመጥ ይልቅ መጯጯህ፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ መጠፋፋት ዋናዎቹ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ሥልጣን ላይ የሚወጡትም ሆኑ ለሥልጣን የሚታገሉት በአንደበታቸው ለዴሞክራሲ ቢዘምሩም በተግባር የሚታየው ግን ተቃራኒውን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያዊያን እርስ በርስ ባደረጉት ግጭት ሞት፣ እስራት፣ ስደትና እንግልት ዕጣ ፈንታቸው ሆኖ ስለመቆየቱ ያለፉትን ሶስት አመታት ብቻ የተመለከተ መመስከር ይችላል ፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተንሰራፍቶ የበቀለው ዓረም ጥላቻና ቂመኝነትን እያባባሰ በርካቶች መከራ ዓይተዋል፡፡ እጅግ በጣም የተከበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ያኖራቸው የጋራ እሴቶቹና አገር በቀል ዕውቀቶቹ እየተናዱ፣ በባዕዳን ርዕዮተ ዓለም የተጠመቁ ፖለቲከኞች በታሪክና በትውልድ የሚያስጠይቅ ጥፋት ፈጽመዋል፡፡ የጥፋቱን መጠንና ክብደት ደግሞ አገር ያውቀዋል፡፡   

 

ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አማካኝነት ቂምና ቁርሾን በማስወገድ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት የሚበጀውን መንገድ ሃገሪቱ ተያይዛዋለች።ይቅርታ እንደሚያሻግር አይተናል። ይህ መልካም ተነሳሽነት በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድም ተቀባይነት እያገኘ ነው፡፡ይህም በሚሊዮኖች ድጋፍ እየተረጋገጠ ነው።

የአዲስ አበባውን አስደማሚ ሰልፍ ተከትሎ በጎንደር በደብረ ማርቆስ ደሴ ጅግጅጋ ሃረር የተደረገው ሰልፍ፤በሆሳዕና በወልቂጤ ከተማ ተመሳሳይ ዓላማ ያለው ሰልፍ ተካሂዷል።በባህርዳርም ለፊታችን እሁድ የድጋፍ ሰልፍ የተጠራ መሆኑን አዘጋጆቹ ን ምንጭ ያደረጉ መረጃዎች ገልጸዋል።

 

በተያያዘ ዜናም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገር ቤት እየታየ ያለውን የለውጥ ሂደት በመደገፍ ፍቅር ያሻግራል ሲሉ የድጋፍ ሰልፍ አድርገዋል።የዋሽንግተንን ልብ ይሏል።

ይሁንና ከዚያ አሳዛኝ የመጠፋፋት ስሜት ውስጥ መውጣት ያቃታቸው ደግሞ፣ ቀናውን ጎዳና ለማሰናከል ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፡፡ በአንዳንድ ወገኖች በማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ የሚንፀባረቀው የነውጠኝነት ባህሪ አሁንም ገና የሚቀር ሥራ እንዳለ አመላካች ነው፡፡ ሰላማዊ ነን እያሉ ሰላም ለማደፍረስ የሚተጉ፣ በዴሞክራሲ ስም እየማሉ የሌላውን መብት የሚጋፉ፣ የሁሉም ነገር ሰጪና ከልካይ ለመሆን የሚዳዳቸውና ዘመኑ ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ ጋር እኩል መራመድ የተሳናቸው እዚህም እዚያም እየታዩ ነው፡፡ አገር ከቂምና ከጥላቻ አስተሳሰብ ተላቃ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በፍትሐዊነት የሚስተናገዱበት ዓውድ እንዳይፈጠር፣ ዛሬም አክራሪ ብሔርተኝነትን ሙጥኝ ያሉ አሉ፡፡ ጥላቻ እስከ አንገታቸው ድረስ የዋጣቸው ደግሞ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያለያይ አደገኛ የዘር ልዩነት ቅስቀሳ በማካሄድ መደመር ቅድመ ሁኔታው የሆነውን የዴሞክራሲያዊ ስርአት ለማኮላሸት እየተጉ ነው፡፡ ያም ሆኖ ፍቅር ያሻግራል።

 

በመሰረቱ በአገሪቱ ውስጥ የነበረው ችግር ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት የታየው ብቻ አይደለም፡፡ ችግሮቹ ለ267 ዓመታት የቆዩ ናቸው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት አዲስ ነገር ተፈጥሮ አይደለም የፖለቲካ ግጭቶች የጦዙትና እንደገናም ባልተጠበቀ መንገድ ወደዚህ መፍትሔ የተመጣው፡፡ ለ26 ዓመታት የፖለቲካ ውዝፍ ነበረብን፡፡ አገሪቱ ወደ ፌዴራል ሥርዓት ገብታለች፡፡ ወደ ፌዴራል ሥርዓት ስትገባ ተያይዘው በጥንቃቄ መታየት የነበረባቸው ጉዳዮች ነበሩ፡፡ በየወቅቱ ደግሞ መፍትሔ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮች በደንብ ሳይጤኑ፣ ውለው አድረው ችግር ያመጣሉ ሳይባል እንዲሁ ተጓተው የመጡ ችግሮች ናቸው፡፡

 

በእርግጥ በእነዚህ ዓመታት ሕገ መንግሥቱ የሚሰጣቸው የግለሰብና የፖለቲካ መብቶች እየተጓተቱ መሻሻል ሲገባቸው ድሮ ከነበረው የበለጠ ሲታፈኑ ውጥረቱም በዚያው ልክ  ጎልቶ የወጣው ባለፉት ሶስት አመታት ነው፡፡ እየተባባሰ የመጣው አፈና መጨረሻ ላይ የፖለቲካ ምኅዳሩ ጭራሹን የፖለቲካ ሐሳብን በሰላማዊ መንገድ ማንሸራሸር አቃተው፡፡ በሰላም ጥያቄ የማቅረብ፣ የፖለቲካ፣ የግለሰብ መብትና ማንኛውንም ዓይነት ጥያቄ በሰላም የሚያስተናግድ የፖለቲካ ምኅዳር ከሌለ የሕዝብ አማራጭ የሚሆነው ሕጉ በእጄ ነው የምፈልገውን አደርጋለሁ የሚል ነው፡፡ በኦሮሚያና አማራ የታየው ይህ ነው፡፡

 

አሁን ፍቅር አሻግሮን ሐሳብን በነፃነት መግለጽ ወደሚቻልበት መንገድ እየተጓዝን ለመሆኑ አመላካች ማሳያዎች እየወጡ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በፖለቲካ አመለካከታቸው ወይም በፖለቲካ ተሳትፏቸው ለእስር የተዳረጉ ሰዎችን መፍታት አንድ ለለውጥ መነሳሳት ነው፡፡ የነበረውን የጦዘና የተካረረ የፖለቲካ አየር ይፈታዋል፡፡ አሁን እንግዲህ ያየነው እሱን ነው፡፡ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከመጡ በኋላ ያየነው ይህንን ነው፡፡የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ የዚህ ማሳያ ነው።ፍቅር ያሻግራል።  

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከኤርትራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ጋር በብሄራዊ ቤተመንግስት ተገናኝተው ባደረጉት ንግግር የዛሬው ቀን ጥቁር መጋረጃ መቀደዱን ያሳያል ብለዋል፡፡ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያን የሰላም ጥሪ በመቀበላቸው ምስጋናቸውን አቅርበው ከኤርትራ ጋር በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በባህል ጉዳዮች ላይ ብዙ የሚያስተሳስሩን ነገሮች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

 

ጠብ ለልጅ ልጆቻችን ማውረስ የለብንም ያሉት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦርነት፣ ሰውን፣ ጊዜን እንዲሁም ቅንጭላትን የሚበላ ነውና መሻገር ይኖርብናል ብለዋል፡፡

ከኤርትራ ወገኖቻችን ጋር በይቅርታ ልብ ተጸጽተን በፍቅር ከመጣን እንሻገራለን፤ እንደመራለን፤ ያለንን ተካፍለን በመተሳሰብ መኖር እንችላለን ብለዋል ዶ/ር አብይ ባደረጉት ንግግር፡፡ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም ቀጣዩ ጊዜ ለቀጠናው መልካም ጊዜ እንዲሆን ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል፡፡የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡስማን ሳልህ በበኩላቸው ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አመስግነው፣ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የመደመር (በትግርኛ ምድማር) መርህ እንደግፋለን ብለዋል፡፡በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው ልዩነት ተዘግቶ አዲስ ምዕራፍ መከፈቱን ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያውያን ያለው የፍቅር እና የመተሳሰብ ፍላጎት በኤርትራውያን ዘንድም መኖሩን ክቡር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ሌላም ማሳያ እንጥቀስ።

ሰኔ 11 ቀን 2010 ዓም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ ለፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡትን የሥራ ዘገባ እና ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ በአንክሮ ተከታትለናል ያለው አርበኞች ግንቦት 7 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ላቀረቡት ጥሪ “የሰለጠነ ፓለቲካ” የምንመርጠው፣ የምናውቀውና የምንመኘው የትግል ስልት ነው! ሲል መልስ መስጠቱ ስለፍቅር ማሻገሪያነት ሊወሳ የሚገባው ነጥብ ነው። ዶክተር አብይ በዚሁ ማብራሪያቸው ስለዴሞክራሲያዊ ስርአት ሲያወሱ የኢህአዴግ መንግሥት የፀጥታና የደህንነት ኃይሎች የአሸባሪነት ተግባራትን የሚፈጽሙ እንደሆኑ በይፋ ከመናገራቸውም ባሻገር፤ ፓርቲና መንግሥት ተቀላቅለው ነፃ ተቋማት እንዳይኖሩ መደረጉን እና የዳኝነት ሥርዓቱ ከፍተኛ ችግር ያለበት መሆኑን ገልጸዋል። ግንቦት 7 በበኩሉ ንቅናቄዓችን ለዓመታት ሲናገር የነበረውን ሀቅ እሳቸው መናገራቸው፣ በአንድ በኩል እሳቸው በግላቸው ከእውነት ጎን ለመቆም ያላቸውን ቁርጠኝነት ሲያመለክት -በሌላ በኩል ደግሞ እሳቸው የሚመሩት የለውጥ ቡድን ለሀገራዊ መግባባት እያሳየ ያለው ዝግጁነት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ያመለክታል የሚል እምነት አሳድሮብናል ሲል በፍቅር መሻገሩን አረጋግጧል።  

 

አርበኞች ግንቦት 7፣ ኦነግና አብነግ ከአመጽ ትግል ተቆጥበው ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲሸጋገሩ ጠቅላይ ሚኒስት ዶ/ር ዓቢይ አህመድ በፓርላማው ንግግራቸው ጥሪ ባደረጉበት ወቅት፤ በመገዳደል ሥልጣን መያዝም ሆነ በስልጣን ላይ መቆየት ጊዜው ያለፈበት “ኋላ ቀር ፓለቲካ” መሆኑን ገልፀዋል።  በዚሁ አግባብ የተዘጉ የፖለቲካ በሮችና የተዘጉ የፖለቲካ መድረኮች እየተከፈቱ ነው፡፡

 

እዚህ ጋር መታወስ ያለበት አንድ ጉዳይ አለ። የሲቪል ማኅበራት ከመንግሥታዊ ተቋማት በበለጠ ለዴሞክራሲ መስፈንና ለሐሳብ መንሸራሸር ትልቅ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ወይ ከተባለ የሕዝብን ንቃተ ህሊና ለማሳደግና (አድቮኬሲ) በመሳሰሉት ጀምረውት የነበረው ሥራ ነበር፡፡ ዴሞክራሲ አድቮኬሲን ይጠይቃል፡፡ መዋቅራዊ ዴሞክራሲ አይሠራም፡፡ ምክንያቱም በየትም አገር ብንሄድ መንግሥት ለዴሞክራሲ መጎልበት ሊያደርገው የሚችለው ሁለት ነገሮች መስጠት ነው፡፡ አንደኛው የመንግሥትን መዋቅር አሳታፊ ማድረግ፣ ሁለተኛው ወካይ ማድረግ ነው፡፡ ከእነዚህ ውጪ መቻቻል፣ መግባባትና የመሳሰሉት የሚመጡት በኅብረተሰቡ ነው፡፡ በኅብረተሰቡ የሚመጡ ከሆነ ደግሞ የሲቪል ማኅበራት ትልቅ ሚና አላቸው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የዚህም አዋጅ ተከልሶ የጠበበው የፖለቲካ ምኅዳር መስፋት አለበት፡፡

 

አሁን ብረት ያነሳ የፖለቲካ ድርጅት አሸባሪ ሊባል የማይችል መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ብረት ወደ ማንሳት የሄደው ሰላማዊው መንገድ ስለተዘጋበት ነው ተብሏል ፡፡ ስለዚህ ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት በውጭም ያለ ሊሳተፍበት የሚችል የፖለቲካ ምኅዳር ተፈጥሯል፡፡ በዚህ መንገድ የሆነውን ሽግግር ከላይ በተመለከተው መልኩ ለመቀልበስ የሚተጉ ሃይሎች የመኖራቸውን ያህል የደገፉ መስሏቸው የመቀልበስ ሂደቱ ተሳታፊ የሆኑም እየታዩ ነውና ጥንቃቄ ያሻል።

 

ሀሳብን ስለመግለፅ ዶክተር አብይ አንድ ድንቅ ነገር ተናግረዋል። ስለ እስራኤል ፓርላማ። ብዙ ፅንፍ አለው። እስራኤልን የማይቀበል ቡድን እንዳለ በምሳሌ ገለጸዋል። ወደ ኢትዮጵየም ተመልሰው ክልሎች ይገንጠሉ ከሚለው አንስቶ የመንና ጅቡቲ የእኛ ናቸው የሚል አስተሳሰብ ያለው አካል መኖሩን በመጥቀስ፤ይህም ቢሆን መደመጥ አለበት ብለዋል። የትኛውም ሀሰብ በሰከነ መንገድ መደመጥ አለበት ። ይህ እጅግ የሰከነ አስተሳሰብ ነው።

 

የዴሞክራሲያዊ ስርአት መገለጫ የሆነውን ማህበራዊ ሚዲያ ስንመለከተው አንዳንድ የአብይ ደጋፊዎች ስሜታዊ ሆነዋል። ምንም ይሁን ትችት ከተፃፈ (ለአብይ የሚጠቅምም) ከድጋፍ ሰልፉ በፊት ፌስቡክ ላይ የስድብ ሰልፍ ይወጣሉ። ዶክተር አብይን የጠቀሙ መስሏቸው ነው። ዶክተር አብይን የሚጠቅሙት አስተሳሰቡን ሲያራምዱ፣ አርዓያነቱን ሲከተሉ፣ ክፍተቱንም ሲነግሩት ነበር። እሱ የትኛውም ድምፅ ይሰማ እያለ፣ እነሱ ፀጥ በል ካሉ፣ እንደማርክሲዝምና እንደወታደሮቹ መሆናቸው ነው። ማርክስን እያመለኩ፣ ርዕዮቱን ጭራቅ እንዳደረጉት። ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በየሀገሩ ማርክሲዝምን የገደለው ካድሬና ወታደር ነው። ክፉ ከሚለው ስርዓት ሲወጣ፣ ስርዓቱን ወድዶ “ምንም ትችት አልቀበልም” አለ። ዝም ያላሉትን ጭጭ አደረገ! የዶክተር አብይ ደጋፊዎችም ከሰውዬው አመለካከት ሳይቀር እያፈነገጡ ነው። ከአሁኑ። እሱ ልገንጠል የሚልም ይሰማ እያለ እነሱ ምክርንም በስድብ ይመልሳሉ! የሚጠቅሙት ሰከን ቢሉና የፍቅርን አሻጋሪነት ሲሰብኩ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy