Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ሲባል…?

0 315

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ሲባል…?

ገናናው በቀለ

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዜጎች ውስጥ የፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ቢያገኙም አሁንም የሚቀሩ ጉዳዩች መኖራቸውን መንግስት ገልጿል። ይሁን እንጂ ‘ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ምንድነው?’ ብሎ መጠየቅ ይገባል። ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማለት ዜጎች በአገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮች ያለ አንዳች አድልኦ እኩል ተጠቃሚ መሆን ማለት ነው።

አገሪቱ ህዝቧቿን በአንድነት በማሰለፍ ከምታገኛቸው የዕድገት ትሩፋቶች ሁሉም ዜጋ በእኩልነት ሲጠቀም ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ነግሷል ይባላል። በዜጎች መካከል ያለው የነፍስ ወከፍ ገቢ በአመዛኙ በአንድ ዓይነት ደረጃ መገኘትም የተጠቃሚነቱ አንድ ማሳያ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ፤ ‘አገራችን አድጋለች ማለት ብቻ ሳይሆን፣ ዕድገቱ ዜጎችን ምን ያህል ተጠቃሚ አድርጓል? ብሎ መመልከት ያስፈልጋል’ በማለት እንደገለጹት፤ ተጠቃሚነቱ የህብረተሰቡን ጉሮሮ እስየት ድረስ ማርጠብ እንደቻለ ማየት ይገባል። ታዲያ ይህ የመንግስት አቋም መጪው ጊዜ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ከምንግዜውም በላይ እውን የሚሆንበት ወቅት እንደሚሆን የሚያሳይ ነው። እናም ዜጎችም ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ከእርሳቸው ጎን መቆም ያለባቸው ይመስለኛል።   

ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የኢትዮጵያ ህዝቦች ካጸደቁት ህገ መንግስት አኳያም መመልከት ያስፈልጋል። ህገ መንግሥቱ አገሪቱ ፍትሃዊ የምጣኔ ሀብት ዓላማዎችን ማራመድ እንዳለባት በግልጽ ደንግጓል። ይህንን ዓላማ ለማረጋገጥ መንግሥት ዜጎች በአገሪቱ የሚገኘውን ሀብት በፍትሃዊነት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር የመቀየስ ኃላፊነት ወድቆበታል።

በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ክልሎች በመንግሥት ልዩ እገዛ ተደርጐላቸው ጭምር የልማቱ ተጠቃሚነታቸው መረጋገጥ እንዳለበትም ህገ መንግሥቱ በማያሻማ መልኩ ደንግጓል። መንግሥት መሬትንና የተፈጥሮ ሀብቶችን በሕዝብ ስም በይዞታው ስር በማድረግ ለዜጎች የጋራ ጥቅምና እድገት የማዋል ኃላፊነት እንዳለበትም እንዲሁ።

ከዚህ በተጨማሪ ዜጐች ለልማት መሠረት የሆኑ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶች፣ የምግብ ዋስትና፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ የመኖሪያና የማህበራዊ ዋስትና የማግኘት መብት እንዲኖራቸው ደንግጓል።

ህገ መንግሥቱ የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት የማይሸጥ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ንብረት እንደሆነ በግልፅ አስፍሯል። ይህም በመሬት ስሪት ጉዳይ የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት በፅኑ መሠረት ላይ ለመጣል አስችሏል።

እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ እንደሆነ ተደንግጓል። የኢትዮጵያ አርሶና አርብቶ አደሮች መሬትን በነፃ የማግኘት፣ በመሬቱ የመጠቀምና ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብታቸው ህገ መንግሥታዊ ዋስትና ያለው ነው።

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጋ በማንኛውም የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ውስጥ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመከወን መብት እንዲሁም በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄዱ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በእኩልነት የመጠቀም መብት ተረጋግጦላቸዋል።

በህገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መሠረትም ሕዝቦች የኑሮ ሁኔታቸው የመሻሻልና የማያቋርጥ እድገት የማግኘት መብት እንዳላቸው በተግባር እየታየ መጥቷል። ዜጐች በብሔራዊ ልማት የመሳተፍ፣ በሚቀረፁ ፖሊሲዎችና ኘሮጀክቶች ላይ አስተያየት የመስጠት መብትም አላቸው።

የዜጐችን እድገትና መሠረታዊ ፍላጐቶችን ማሟላት፣ መንግሥት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና የሚያደርጋቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱን ሕዝቦች ተጠቃሚነት መብት የሚያስከብሩ ስለመሆናቸው ከጋራ መግባባት ላይ  መድረስ እንዲሁም ዜጐች በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄዱ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብት የፍትሐዊነት ማሳያዎች ናቸው።

ህገ መንግስቱ በተለይ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ሕዝቦች በመንግሥት ልዩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ዋስትና ሰጥቷል። በመሆኑም ፌዴራል መንግሥት ፍትሃዊ የልማት እንቅስቃሴ ከማረጋገጥ ባሻገር፤ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ሕዝቦች መላ አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ ለማስቻል ልዩ ድጋፍ እየሰጣቸው ነው።

ፌዴራል መንግስት ለእነዚህ አካባቢዎች የመንግሥት አስተዳደርን የመገንባት፣ ቀልጣፋ አሰራርንና አደረጃጀት የመፍጠርና የሰው ኃይል አቅም ማጎልበትንን ተግባር በመከወን ከሌሎች ህዝቦች እኩል እንዲራመዱ የማድረግ ህገ መንግስታዊ ግዴታ አለበት።

ዜጐች ንብረት የማፍራት፣ በመረጡት የሥራ መስክ የመሰማራት መብቶች በማረጋገጥ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት የሚመራ ፈጣንና ፍትሃዊ ልማት የማምጣት ጠቀሜታን ህገ መንግስቱ ይገልጻል።

እርግጥ በፍትሐዊ አንድነት ውስጥ የሕዝቦችን ልማታዊ አቅም ማሳደግና ለአገር ግንባታ ወሣኝ እንዲጫወቱ ማድረግ ያስፈልጋል። የዜጐችን የልማት ባለቤትነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በልማት እንቅስቃሴዎች ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን እውን ማድረግ ነው።

በህገ መንግስት ልማት የመብት ጉዳይ እንደሆነ ተገልጿል። በመሆኑም የክልሎችን እኩል የመልማት እድል ማረጋገጥና ልዩ ድጋፍ መስጠት መገንባት ለሚፈለገው በነፃ ፍለጐት ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መረጋገጥ ቁልፍ ሚና እንዲጫወት ያደርጋል።

በራስ አቅምና ፍላጐት ነፃ አገራዊ ኢኮኖሚ መገንባት ለአገሪቱ ዘላቂ ሠላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ወሳኝ በመሆናቸው የፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ጉዳይ ተገቢና ትክክል እንዲሆን ያደርገዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይም ፈጣን ልማትን ማረጋገጥ የሞትና የሽረት ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ርብርብ እያደረገ ነው። ከአንዴም ሁለቴ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶችን በመንደፍ ተግባሩን ወደ መሬት አውርዶ እየሰራ ነው። በእስካሁኑ ድረስ ዕድገትም ተገኝቷል።

በዚህም አብዛኛውን ህዝብ መሰረት ያደረገ ዕቅድ ነድፎ የሀገሪቱን የህዳሴ ጉዞ በማሳለጥ ላይ ይገኛል። የተገኘው ዕድገት ግን “ምን ያህል ወደ ህዝቡ ውስጥ ዘልቋል?” የሚል ጥያቄ በመንግስት በኩል ተነስቷል። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ይህ ጥያቄ መንግስት ምን ያህል ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን በህዝቡ ውስጥ ለማስፈን ፍላጎት እንዳለው የሚያሳይ ነው። ህዝባወመቱንም የሚያረጋግም ጭምር ነው።

ስለሆነም ህብረተሰቡ መንግስት ዕድገት ቢኖርም ዕድገቱ ምን ያህል የህዝቡን ተጠቃሚነት እንዳረጋገጠ ማየት እንደሚገባ መግለፁ ትክክለኛና ወቅታዊ ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ይኖርበታል። ዞሮ…ዞሮ ተጠቃሚው እርሱ በመሆኑ ከመንግስት ጎን በመቆም ፍትሐዊ ተጠቃሚነተቱን ለማረጋገጥ መስራት አለበት።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy