Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ህይወት ቀጣፊው…

0 418

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ህይወት ቀጣፊው…

ገናናው በቀለ

ዛሬ ህገ ወጥ ስደት የሰውን ልጅ እንደ ዕቃ እስከመሸጥ ድረስ ደርሷል። እንደሚታወቀው ሁሉ ማንኛውም ዜጋ በሀገሩ ለመስራት ካልፈለገና ‘በውጭ ሀገር ሰርቼ ሃብት አፈራለሁ’ ብሎ ካሰበ የሚከለክለው አካል አይኖርም። ምክንያቱም በለውጥ ሂደት ውስጥ በምትገኘው በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት ህገ መንግስታዊ እውቅና እና ጥበቃ ያለው ነው።

ማንኛውም ዜጋ በፈለገው ጊዜና ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራትና ሃብት የማፍራት የማይገሰስ ህገ መንግስታዊ መብት አለው። ይህን ማንም ሊቀለብሰው አይችልም። ይህን ህገ መንግስታዊ መብት ለማክበር መንግስት ከተለያዩ አገራት ጋር የውጭ አገር የስራ ስምሪት በመፈራረም ዜጎቹ እንዳይንገላቱ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ታዲያ ይህን ህገ መንግስታዊ መብት በአግባቡና ህጋዊ በሆነ ሁኔታ መጠቀም ይገባል። አንድ ዜጋ ባሻው ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ስላለው ብቻ ራሱን ለአደጋ ቤተሰቡን ደግሞ ለችግርና ለስጋት አጋልጦ ህገ ወጥ መንገድን መጠቀም አይኖርበትም።

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢፌዴሪ መንግስት ይህን የዜጎችን እንግልትና ችግር በመመልከት ዜጎች ለስራ ወደ ውጭ ሲጓዙ ከሞት፣ ከእንግልትና ከስቃይ ይላቀቁ ዘንድ ህጋዊ የአሰራር ማዕቀፍን በአዋጅ መልክ አበጅቷል። መንግስት ባዘጋጀው በዚህ አዋጅ ተመርቶ በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ የስራ ስምሪት ማድረግ ራስን ከአደጋ ቤተሰብን ደግሞ ከሃሳብና ከሰቀቀን የሚታደግ ይሆናል።

ይህን አዋጅ ተጠቅሞ በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ መጓዝ የህገ ወጥ ደላላዎችን መንገድ ይዘጋል። በጥቅሉ ህጋዊነትን ተቀብሎ በህግ አግባብ ማንኛውንም ነገር ማከናወን ራስን ከአደጋና ከውርደት በመጠበቅ የሀገርን ክብርም ማስጠበቅ መሆኑን ግንዛቤ መያዝ የሚገባ ይመስለኛል።

ከአዋጁ ጎን ለጎንም በክልሎች ውስጥ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት ብርቱ ጥረት መደረግ ይኖርበታል። እርግጥ ለህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መፍትሔው በመንግስት አዋጅ ላይ ብቻ የተጣለ አይደለም። የህገ ወጥ ዝውውሩ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት ህገ ወጥ ደላሎችን ህዝቡ በሚገባ ያውቃቸዋል። ደላሎቹ ምን እንደሚሰሩ ከህዝብ ዓይን የተሰወረ አይደለም።

ህብረተሰቡ በየቀየው የህገ ወጥ ዝውውሩ አቀናባሪና ስደተኞችን ወደ ሞት የሚገፉ እነማን እንደሆኑ ያውቃል። አሁን ደግሞ በባዕድ አገር ውስጥ ህገ ወጥ ስደቶኞችን እንደ ዕቃ መሸጥ ተጀምሯል። ይህ ደግሞ ከሀገራችን ክትትል ውጭ በመሆኑ በማንኛውም መንገድ ህገ ወጥ ስደት ተመራጭ አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ክስተት ሆኗል።

ያም ሆኖ ግን የትኛውም አካል ቢሆን ህገ ወጥ ስደት ህይወትን የሚያሳጣና ክብርን የሚያዋርድ ዘግናኝ ተግባር መሆኑን ለመገንዘብ በጉዳዩ ዙሪያ በቂ ዕውቀት መፍጠር ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የተቋቋሙ አገራዊ ኮሚቴዎች ለችግሩ እልባት ለመስጠት የተፋጠነ መፍትሔን መከተል ይኖርባቸዋል።

እንደሚታወቀው ሁሉ በመላ ሀገሪቱ በተዋረድ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተከላካይ ምክር ቤት ተቀቁሟል። በዚህም ህብረተሰቡ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ሰፋፊ መድረኮች ተፈጥረው እንዲወያይበትና የመፍትሔው አካል እንዲሆን በየክልሉ በርካታ ተግባራት ዕውን ሆነዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ችግሩን ለመቅረፍ በጥናት ላይ የተመሰረተ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልፀዋል። ይህ ትክክለኛ ውሳኔ ነው።

የህገ ወጥ ስደት ችግር ሲንከባለል የመጣ እንደመሆኑ መጠን በአንድ ጀንበር ችግሩን መፍታት አይቻልም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በጥናት ላይ ተመርኮዞ መፍትሔ ማበጀት ተገቢ ነው። በጥናቱም ውጤት እንደሚገኝበት አያጠያይቅም።

ጥናቱ ተጠናቆ ወደ መፍትሔ እስከሚገባ ግን ህብረተሰቡ የበኩሉን ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። ከላይ እንዳልኩት በተለይ በአቅራቢያው የሚገኙትን ህገ ወጥ ደላላዎችን ማጋለጥ አለበት።

እንደ እኔ…እንደ እኔ ህዝባዊው ጥረት ከመንግስት ህጋዊ አሰራር ጋር እንዲቆራኝ ማድረግ ከተቻለ፤ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ እንኳን ባይሆን ከግማሽ በላይ ሄዶ መቅረፍ የሚቻል ይመስለኛል።

በተለይም በየክልሉ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ በሚፈለገው መጠን ከተሰራ የችግሩን መንስኤ ነቅሶ በማውጣት ተገቢውን ማስተካከያ ማድረግ ይቻላል። በየጊዜው ‘ኢትዮጵያውያን በኮንቴይነር ሲጓዙ እገሌ በሚባል ሀገር ውስጥ ተያዙ’ የሚል ዜናን ላንሰማ የምንችልበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።  

ታዋቂ የሆኑትንና ተሰሚነት ያላቸውን የተለያዩ የማህበረሰቡን አካላት ወደ ህዝቡ ውስጥ በማሰማራት ስለ ጉዳዩ እንዲያስረዱና እንዲያሳውቁ መደረጉ፤ እነዚህ አካላት በማህበረሰቡ ውስጥ ባላቸው እውቅና ውጤት ሊያመጡ ይችላሉ።

ታዲያ ይህን መሰሉ ጥረት በአንድ መንገድ ብቻ መከናወን የለበትም። ባርነት የሆነው ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እውነታ ዋነኛ ተጠቂ የሆኑትና በህገ ወጥ ደላላዎች ሊታለሉ የሚችሉት ወጣቶች ዘንድም በተጠናከረ ሁኔታ መድረስ ይኖርበታል።   

ለዚህም በየትምህርት ቤቶች የፀረ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ክበባትን በማቋቋም ህገ ወጥ ስደት በወጣቶች ላይ ስለሚያደርሰው ጉዳት እንዲሁም ወጣቶች ችግሩን ለመቋቋም ማከናወን ስላለባቸው እንቅስቃሴዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠት ይገባል።

ታዲያ እነዚህ ጥረቶች የአንድ ወቅት ተግባር እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ይገባል። ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቱ በየዘርፉ ሊቋረጥ አይገባም። የተገኙ ልምዶችንና ተሞክሮዎችን ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ማስፋት ያስፈልጋል። ይህ ሁኔታም ተከታታይነት ያለው ሊሆን ይገባል።

በህገ ወጥ መንገድ መጓዝ ተጠቃሚ ህገ ወጥ ደላላው እንጂ ተጓዡ ህይወቱን እስከማጣት የሚያደርስ እንደሆነ ማስረዳትም ያስፈልጋል። ህብረተሰቡ በየጓዳው ልጆቹን በመምከርና የችግሩን አደገኛነት በማብራራት ወጣቶችን ከዚህ ህይወት ቀጣፊ ተግባር እንዲቆጠቡ ካደረገ ችግሩን ለመቅረፍ ይቻላል።

በአሁኑ ሰዓት አገራችን በህዝባዊ የለውጥ ሂደት ላይ ናት። ለውጡ ብዙ ነገሮችን ያካተተ ነው። የወጣቶችን ተጠቃሚነትና ስራ ፈጠራን ጭምር የሚያጎለብት ነው። እናም ከህገ ወጥ ስደት ራስን መቆጠብ ያስፈልጋል።

ወጣቶች ሁሉም ችግሮች አሁኑኑ ይፈታሉ ብለው መጠበቅ አይገባቸውም። ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ማናቸውም ችግሮች በለውጡ እንደሚፈቱ በማሰብ ከህይወት ቀጣፊው ህገ ወጥ ስደት ራሳቸውን በማቀብ ወደ ህጋዊነት ፊታቸውን ማዞር ይኖርባቸዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy