Artcles

ለጋራ ተጠቃሚነት…

By Admin

June 25, 2018

ለጋራ ተጠቃሚነት…

                                                            ደስታ ኃይሉ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ኃላፊነት ከመጡ አጭር ጊዜ ቢሆናቸውም፤ የተለያዩ የውጭ አገር የስራ ጉብኝቶች በማድረግ አገሪቱ የገጠማትን ቀውስ ለመፍታት እና አገራዊ ገጽታችን ለመቀየር እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን  ለማሳደግ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በዚህ ጥረታቸውም ተጨባጭ ድሎች ተመዝግበዋል።

ሸለአብነት ያህልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ሲል በጅቡቲ፣ በሱዳን፣ በኬንያ፣ በኡጋንዳ፣ በሳዑዲ አረቢያ የተባበሩት የአረብ ኤሚሬትስና በግብጽ ያደረጓቸው ጉብኝቶች ስኬታማ ነበሩ። ዜጎችን ከእስር በማስፈታት፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና ወደብን በጋራ በማልማት ከአገራቱ ጋር የደረሱባቸው ስምምነቶች የአገራችንን ተጠቃሚነት ከፍ ያደረጉ ናቸው።  

ጠቅላይ መኒስትሩ በቅርቡ በሶማሊያ ያደረጉትን የስራ ጉብኝትም ውጤታማና የአገራችንና የምስራቅ አፍሪካን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው። ኢትዮጵያና ሶማሊያ ረጅም ድንበር የሚጋሩ፣ ህዝቦቻቸውም በባህል፣ በቋንቋና በሐይማኖት የተሳሰሩ በመሆናቸው ተቀራርበው መስራታቸው ሁለቱንም ህዝቦች ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኔ 9 ቀን 2010 ዓ.ም በሞቃዲሾ ባደረጉት ጉብኝት፣ በኢትዮጵያና ሶማሊያ ድንበር እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ሽብርተኝነትንና ፅንፈኝነትን በጋራ ለመከላከል አገራቱ እንደሚሰሩ ማስታወቃቸው አይዘነጋም።

እርግጥ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ ኢኮኖሚ እየገነባችና በየዓመቱም የገቢና ወጪ ምርቷ በፍጥነት በማደግ ላይ በመሆኑ ተጨማሪ የባህር በር ያስፈልጋታል። ለዚህ ደግሞ ሶማሊያ ሰፊ የባሀር በር ያላት አገር ስለሆነች የሁለቱ አገራት ተቀራርበው መስራት አለባቸው። በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሶማሊያን በጎበኙበት ወቅት፤ ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጋር ባደረጉት ውይይት፤ ኢትዮጵያና ሶማሊያ አራት ወደቦችን በጋራ ለማልማት ከስምምነት መድረሳቸው ትብብሩ ለጋራ ተጠቃሚነት የሚያስገኘውን ፋይዳ በመገንዘብ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም ሁለቱ መሪዎች የደረሱባቸው ስምምነቶች፤ አገራቱን በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር የህዝቦችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያለመ ነው። እንዲሁም የአካባቢውን ዘላቂ ሰላም ለማስቀጠል የደረሱበት ስምምነት አገራችን ለሶማሊያ አንድነትና ዘላቂ ሰላም መስፈን እስካሁን እያደረገች ያለውን ጥረት የሚያጠናክር ነው። እ

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ ሶማሊያ አሁን ለምትገኝበት ሰላም የህይወትና የንብረት መስዋዕትነት ከፍላለች። እየከፈለችም ነው። በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ  ትልቁን ድርሻ በመውሰድ እየተወጣችም ነው። ይህም አገራችን ለቀጠናው ሰላም ያላትን ቁርጠኛ አቋም የሚያረጋግጥ ነው።

ኢትዮጵያ በሶማሊያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ በሶማሊያ (አሚሶም) ጥላ ስር በርካታ የሰላም አስከባሪ ሰራዊት አዋጥታለች። በዚህም የሶማሊያ የሰላም ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ መሻሻል እንዲያሳይና ዛሬ የአገሪቱ ህዝብ የመረጠው መንግስት መቋቋም እንዲችል አድርጓል።

ከላይ እንደጠቀስኩት የሶማሊያና የኢትዮጵያ ህዝቦች ትስስር ዛሬ የተጀመረ አይደለም። እጅግ በርካታ ዘመናትን ያስቆጠተ ነው። ይሁንና ሶማሊያ መንግስት አልባ በነበረችበት ወቅት የቀጠናው አገራት ስጋት የሆነ ፅንፈኞችና የሽብር ሃይሎች መሸሸጊያና ስጋት ነበረች። ዛሬም ድረስ ራሱን በአል ቃዒዳ ክንፍነት አደራጅቶ ቀጠናውን በማወክ ላይ የሚገኘው አልሸባብም የተሰኘው ቡድን በዚህች አገር መሽጎ የጽንፈኝነትና የሽብርተኝነት ተግባርን እያካሄደ ነው። ኢትዮጵያም በአሚሶም ውስጥ ሆና ይህን የሽብር ቡድን ከቀጠናው ለማጥፋት ጥረት በማድረግ ላይ አድርጋለች።  

እርግጥ አገራችን በሶማሊያ የመሸጉ አልሸባብን የመሳሰሉ አሸባሪዎችን በቁርጠኝነት የምትታገልበት ምክንያቶች ሁለት ናቸው። አንደኛው መንግስት የሚከተለው ሰላምንና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ፖሊሲ ነው። ሁለተኛው ደግሞ፤ ወንድም ከሆነው ከሶማሊያ ህዝብ ጋር ያለን በደም የተሳሰረ የማይሻር ግንኙነት ነው።

ኢትዮጵያ ሶማሊያን አስመልክቶ የምትከተለው ፖሊሲ፤ ከሶማሊያ ጋር ያለን ጉርብትና ለልማታችን የተሻለ አስተዋፅኦ ሊያደርግ የሚችለው በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ከማድረግ አንፃር ነው። ጽንፈኝነትን፣ ሽብርተኝነትንና አክራሪነትን በመዋጋት በአካባቢያችን ሰላም ሊኖር የሚችለው በዚሁ መስክ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር በአጋርነት የሚሰለፍ መንግስት በሶማሊያ ሲቋቋም መሆኑን አገራችን ታምናለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሞቃዲሾ ያቀኑት ከዚህ ጠንካራ ትስስርና የጋራ ተጠቃሚነት በመነሳት ነው።

ሶማሊያ ውስጥ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር ከተቻለ የሀገራችን ውሰጥ የተጀመሩት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ጉዳዩች ሳይስተጓጎሉ በሚፈለገው ፍጥነት ሊተገበሩ ይችላሉ። ይህ ማለት የሶማሊያ ሰላም መሆን አገራችን የጀመረችው የህዳሴ ጉዞ ግለቱን ጠብቆ እንዲሄድና በስተመጨረሻም እውን እንዲሆን ያደርጋል። የጎረቤቶቻችን ሰላም መሆን ለእኛ ሁለንተናዊ ዕድገት ፋይዳው ከፍተኛ ነውና።

የኢትዮጵያና የሶማሊያ ህዝቦች የረጅም ጊዜ ታሪካዊና ባህላዊ ግንኙነት ያላቸው ናቸው። በደም፣ በታሪክ፣ በባህል፣ በቋንቋና በሃይማኖትም ተሳስረዋል። አንዱ ህዝብ በሌላኛው ውስጥ የህይወት ቁርኝትን የፈጠረ ነው። ስር የሰደደው ይህ የህዝቦች ግንኙነት በቀላሉ ሊበጠስ የሚችል አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ አገራቱ ያላቸው የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና የሚጋሩት በሺህዎች ኪሎ ሜትሮች የሚቆጠር የጋራ ድንበር ለንግድ ግንኙነታቸው አመቺ ሁኔታን የሚፈጥር ነው።

እነዚህ ሁኔታዎች አገራችን መቼም ቢሆን ወንድም ከሆነው የሶማሊያ ህዝብ ጎን እንድትቆም ያደርጋታል። የሶማሊያ ህዝብ በአሸባሪዎችና በጽንፈኞች እንግልት ሲደርስበት የሚመጣው ወደ ኢትዮጵያ ነው። ዛሬም ቢሆን ፅንፈኞች በተቆጣጣሯቸው ቦታዎች ውስጥ የሚገኙ የዚያች ሀገር ህዝቦች አገራችንን እንደ ሁለተኛ አገራቸው በመቁጠር በስደተኝነት እየተጠለሉባት ይገኛሉ። ይህም በሀለቱ አገራት ህዝቦች መካከል ያለውን የቅርብ ግንኙነት የሚያረጋግጥ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሶማሊያ ቆይታቸው እንደተመለሱ በሰጡት መግለጫ፤ ሁለቱ አገራት የትናንቱን ታሪክ ከማውሳት ይልቅ ያላቸውን የተፈጥሮ ፀጋ በጋራ ማልማትና ማደግ ይገባቸዋል ያሉት የህዝቦችን ጠንካራ ቁርኝት በመገንዘብ ነው።  

በመሆኑም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት በአዲስ ምዕራፍ፣ በአዲስ ግንኙነትና ራዕይ እንዲሁም በአገራቱ መካከል መቀራረብንና መተባበርን ለመፍጠር የሚያስችል ነው። ሶማሊያም እንደ አገር አሁን ካለችበት ችግር በመላቀቅ የተሻለችና የበለፀገች እንደምትሆን ያደርጋታል። አገራቱ ካላቸው ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ኢኮኖሚያዊ ውህደት ያስፈልጋቸዋል። በተለይ በባቡር፣ በሃይል አቅርቦት፣ በመንገድና በኢንቨስትመንት አገራቱን ለማስተሳሰር የተደረሰው ስምምነት የህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት ከፍታ የሚጨምር ነው።