Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መልዕክቶቹ

0 275

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መልዕክቶቹ

                                                            ሶሪ ገመዳ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ግንቦት 20ን የድል በዓለ አስመልክተው ያስተላለፏቸው ባለ ስድስት ነጥብ መልዕክቶችን ትናንትን ያጣቀሱ፣ ዛሬን ያማከሉና ነገን ያመላከቱ ነበሩ። በፖለቲካዊ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በህዝቦች የመጡትን ለውጦችና እነዚህን ለውጦች በምን መንገድ ማስቀጠል እንዳለበትም የሚያስረዱ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግንቦት 20 የድል በዓል ስናከብር ራሳችንን ከውስጣችንም ሆነ ከውጭያችን በመታረቅ ለራሳችንም ሆነ ለሌላው አዎንታዊ እይታን በሚያስታጥቁን መልካም ተግባራት መታጀብ እንዳለብን አሳስበዋል። እንዲሁም ከዚህ በፊት ከነበረው በተጨማሪ የሚከተሉትን ስድስት ጉዳዮችን እንደሚያስፈልግ ገልፀው ነበር። እነዚህን ስድስት ነጥቦች ለአንባቢያን ማስረዳት ይገባል። እኔም በገባኝ መጠን ጉዳዩቹን ለመቃኘት እሞክራለሁ። የዚህ ፅሑፍ ዓላማም ይኸው ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በፊት በድሉ የተገኙትን ውጤቶች እንደተጠበቁ ሆነው፤ ተደማሪ ያደረጓቸው ስድስት ነጥቦች ውስጥ፣ አንደኛው ሁሉም ሰው ከራሱ ጋር ተፈላልጎ ለመገናኘት ግንቦት 20 የጥሞና ጊዜ እንዲሆን ወደራስ ተሰዶ ከራስ ጋር መገናኘትም ሆነ ዓለምን አነፍንፎ አጽናፋዊ መስተጋብር በመፍጠር ዛሬን በውል እንድንኖርም ሆነ ነጋችንን እንድናሳምር የሚያደርግ መሆኑን የሚገልፅ ነው።

ይህም የሰው ልጅ ራሱን ወደ ውስጥ በመመልከት ዕለቱ የጥሞና ጊዜ እንዲሆን የሚመኝ ነው። ከባቢን ለማወቅ ራሰን ወደ ውስጥ መመልከት እንደሚያስፈልግም ያስረዳል። ከባቢን ለመረዳትም ሆነ ለመግራት ወደ ውስጣችን በመመልከት ከራስ ጋር በሚደረግ እርቅ እና የጥሞና ሰዓት ነፍሳችንን በአዎንታዊ ሃይል የሚሞላ ነው። ይህም ወሳኝ ልምምድ በመሆን ራስንና ከባቢን ለመግራት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል።

ራሳችንንና አካባቢያችንን መቃኘት ስንጀምር፤ የአርበኝነት፣ የድል፣ የትግልና የአይበገሬነታችን ተምሳሌት የሆኑ ብሔራዊ በዓሎቻችን በምናከብርበት ወቅት ከክበረ በአልነት ባሻገር የአሸናፊነት ስነ ልቦና እንድንላበስ የሚያደርጉን ናቸው። ይህም በእኔ እምነት በዓሎቻችንን ስናስብ ሁሌም ኢትዮጵያዊ የአሸናፊነትንና የይቻላል መንፈስን በመሰነቅ መሆን እንዳለበት የሚያስተምር አባባል ነው።

ማንም ሰው ለራሱ የጥሞና ጊዜ ሰጥቶ ራሱንና አካባቢውን በውል ለመረዳት እና ከራስ ጋር እርቅ ለማድረግ ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር የሚያትተው የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት፤ የሰው ልጅ ከሁሉም ነገር በቅድሚያ ከራሱ ጋር በመታረቅ እንደሚገባው ይገልጻል። ለዚህም በምክንያትነት ከራሱ ጋር የታረቀ ዜጋ ከሌላው ሃሳብም ይሁን ግለሰብ ጋር ለመታረቅ በፍጹም ሊቸገር አይችልም። ይህ የእርቅ ሃሳብ በፖለቲካውም ይሁን በግለሰባዊ መስመር ይቅር ባይነት መስፋት እንዳለበትና ዕለቱን ስናስብ ሁሉንም ይቅር ለማለት ውስጣዊና ከባቢያዊ ተነሳሽነት ሊኖር እንደሚገባ የሚያስረዳ ነው።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት በሁለተኛነት የተቀመጠው፤ የግንቦት 20ን በዓል ዜጎች ሲያከብሩ ከጎረቤቶቻቸውና ከቅርብ ወይም ሩቅ ወዳጆቻቸው ጋም ያሉ ክፍተቶችን በእርቅና በይቅርታ የማከም የጋራ ባህል እንዲኖራቸው መመኘት ነው። እርሳቸው እንዳሉት የእርቅና የይቅርታ ከባቢ ሰላምን ለዚህች አገር የሚያመጣ ነው። እርቅና ይቅታ ያለበት መንደር፣ ከባቢና አገር ብሎም አፅናፍ የሰላም አየር የሚነፍስበት አውድ መሆኑ አይቀርም። እነዚህን በጽናት የሚለማመድ ዜጋ፣ ማህበረሰብና አህጉር ብሎም ዓለም ሰላምን በማረጋገጥ በየደረጃው ሁከትንና ብጠብጥን ሊቀንስ ብሎም ሊያስወግድ ይችላል።  

ለዚህም ይመስለኛል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ “ይህች የምንሳሳላትና የምንወዳት አገራችን ሰላም የምትሆነው፣ ጋራ ሸንተረሯ የሞት ሲላ የሚዞርበት ሳይሆን የሰላም ምሳሌዎቹ እርግቦች በጣፋጭ ዜማቸው ዙሪያ ገባውን የሚደምቁት፤ ከራሳችን ጋር ስንታረቅ ከወዳጅ ዘመድ ጋር ይቅር ስንባባል ብቻ ነው” በማለት የድል በዓሉ የይቅርታና የሰላም በመሆን መከበር እንዳለበት ያስገነዘቡት። ዕለቱ በተለያዩ ምክንያቶች የተኳረፉ ወዳጆች፣ ጎረቤታሞች፣ የትዳር አጋሮች…ወዘተ. ይቅር የሚባባሉበትና ሰላም የሚያወርዱበት መሆን እንደሚገባው ለማስገንዘብ የፈለጉትኝ ለዚሁ ነው።

ዶክተር አብይ አህመድ በግንቦት 20 የድል በዓል በሶስተኛ ደረጃ ውስጣዊ እርጋታና ጽናታችን ያልተሸራረፈ ውጫዊ አረዳድና ተግባቦታችንም ያልተዛነፈ ሆኖ ከራስ እስከ ሀገር የሚዘልቅ ፍቅር እና ሰላም እንዲኖረን የሚመኝ ነው። በዚህም በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ድጋፋችንን ከሚሹ ወገኖች ጎን መቆምና የታመሙ ሰዎችንም መጠየቅ፣ የታረዙትን የማልበስና ደካሞችን በማገዝ ግንቦት 20ን ማክበር እንደሚገባ አሳስበውናል። በእኔ እምነት ይህ አባባላቸው ከእኛ እርዳታ ለሚሹ ወገኖች ድጋፍ ማድረግን፣ ያለንን ተካፍለን በመብላት የህሊና ሰላም የሚያጎናፅፈን መሆኑን የሚያስረዳ ነው።

ሰዎች የሚፈፅሟቸው መልካም ተግባሮች ሰላምን የሚያመጡና በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች አስተሳሰብ ውጤት ናቸው። ለዚህም ነው “እኛ ያለነው በእኛና በሌሎች አእምሮ ውስጥ በመሆኑ ከሁላችንም አእምሮ የሚፈልቁ መልካም ነገሮች ሁለንተናችንን መልካም ያደርጋሉ” በማለት በዓሉን ሰላምን ሊያጎናጽፉን በሚችሉ መልካምነት ማክበር እንደሚገባን ያሳሰቡት።

መልካምነት ማንንም አይጎዳም። እንዲያውም ውስጣዊና ውጫዊ ሰላምን ሊያጎናጽፍ የሚችል እሴት ነው። ከመልካምነት ራሰንና ሌላውንም ማክበርና ማስደሰት ይቻላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም የታመሙትን ስንጠይቅ፣ ደጋፊ ያጡ አዛውንቶችን ስናበላ/ስናጠጣ እንዲሁም ስንደግፍ ለራሳችን ያለን ክብር አድጎና ሌሎችም ለኛ ያላቸው ፍቅር ተመንድጎ ሰላማችንን እንደሚያበዛው የገለፁትም ለዚሁ ነው። ይህም በተራው ሀገር ቀያችንን፤ ውስጥና ውጪያችንን ሰላም በማድረግ የህሊና እፎይታን የሚሰጥ ነው። እናም ዜጎች በዓሉን ሲያከብሩ፤ በሰላም መታገያ ውስጥ መልካምነትን፣ ፍቅርንና አብሮነትን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። እነዚህ ጉዳዩች በሀገራችን ውስጥ እየተሸራረፉ የጠፉትን እሴቶቻችንን መልሰው የሚያስገኙልን በመሆናቸው ዕለቱን ስናከብር ብንጠቀምባቸው ሁለንተናዊ ሰላማችንን ልንጎናፀፍባቸው የምንችልባቸው ይመስለኛል።

ዶክተር አብይ አህመድ የአገራችን ህዝብ የማንበብ፣ የመመርመር እና ከሚታየው ሁነት ጀርባ የሚኖረውን እውነት የማጥናት የዘመናት ልምምድ ያለው ህዝብ መሆኑን በገለፁበት አራተኛው መልዕክታቸው፤ አሁን…አሁን የሚታዩት እና ማህበረሰባችን ውስጥ የሚስተዋሉት አዝማሚያዎች ከትላንት ታሪካችንና ከአያት- ቅድመ አያቶቻችን የአንባቢ- ጠያቂነት አሻራችን ጋር የሚሰምር ባለመሆኑ አንባቢ ትውልድን ለመፍጠር ሁሉም ዜጋ እንደየ ዝንባሌው የማንበብን ክቡር ተግባር የህይወቱ አካል አድርጎ ሊይዝ እንደሚገባ አሳስበዋል።

እርግጥ ይህ ለሀገራችን ህዝቦች እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ማንበብ በግለሰብ ደረጃ ሙሉ ሰው የሚያደርገውን ያህል አካባቢንና ህብተረሰብንም የመለወጥ አቅም አለው። የማያነብ ሰው ከስማ በለው በስተቀር የትናንትን በጥሞና አይመለከትም፤ ዛሬንም አያውቅም። ነገም ‘እንዲህ ሊሆን ይችላል’ ብሎ ግንዛቤ ሊይዝ አይችልም።

ስለሆነም ለራም ይሁን ለሀገር በማንበብ መመራመርና ለአገር ፋይዳ ያላቸውን ጉዳዩች መፍጠር የዜግነት ግዴታ ይመስለኛል። ይህም ጠያቂና ተመራማሪ ትውልድን በመፍጠር ጉልህ ሚና ይጫወታል። እናም የአበውንና እመውን የተመራማሪነት ታሪክ በመሰነቅ አንባቢ ዜጋን መፍጠር የእውቀት ድባብ እንዲኖረን ማድረግ ያስፈልጋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓሉን ስናከብር     በማንበብ እውቀትን በውስጣችን ለማሰባሰብ በመወሰን ቢሆን እጅጉን እንደምናተርፍ የገለጹት ለዚሁ ይመስለኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአምስተኛ ደረጃ የጠቀሱት መልዕክት የማወቅ መሰልጠን- የማደግ መዘመን ልካችን የሚታወቀው ወይም የሚገለጠው ለአካባቢያችን በምንሰጠው ትኩረት- እንክብካቤ እና ንጽህና ልክ መሆኑን ነው። ቤታችን ምን ቢያምርና ቢጸዳ አካባቢያችን እስካልጸዳ ድረስ የቤት ጊቢያችን ውበትና ጽዳት የሚሰጠን ዋጋ የዜሮ ብዜት እንደሆነም ገልጸዋል። ትክክል ነው ንፅህና የዘመናዊነት ምሳሌ ነው። የሰለጠነ ህብረተሰብ ቤቱን ብቻ ሳይሆን አካባቢውንም ይቃኛል። ለዕይታ የሚያስቸግሩ አካባቢያዊ ህጸጾችን በጋራ በመሆን ይነቅሳል። ይህም ዕዱና አረንጓዴ በመሆን የሚገለጽ ነው። ቤቱን ብቻ አፅድቶ አካባቢውን ችላ የሚል ማህበረሰብ የጋራ የሆነ እንደ ወረርሽኝ ዓይነት በሽታ ሰለባ መሆኑ አይቀርም። ዶክተር አብይ “የበዓል አከባበራችን አንዱ መልክ ከአካባቢ ጽዳት ጋር ቢሰናሰል ጠቀሜታው ብዙ ነው” ያሉት ለዚሁ ነው። እናም አካባቢን ማጽዳት ራስንና ጎረቤትን ብሎም አገርን ማዘመን መሆኑ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል።  

“የዘመናዊነታችንና የስልጣኔያችን ዓይነተኛ ማሳያ ሊሆን የሚችለው ሀገራዊ እሴት ለሴቶች የምንሰጠው ክብር ነው” የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ስድስተኛው መልዕክት፤ ሴቶች በማህበረሱ ውስጥ ያላቸውን ሚና በትክክል ያስቀመጠ ነው። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንደ ግለሰብም ይሁን እንደ ማህበረሰብ ነገን የተሻለ ለማድረግ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴ ውስጥ ለሴት እህቶቻችን የሚሰጠውን ክብር ሊያሳድግ ግድ ይለዋል። ምክንያቱም ሴት እህቶቻችን የማህበረሰቡ ግማሽ አካል መሆናቸው ብቻ ሳይሆን እነርሰሱን ማክበር የስልጣኔና የዘመናዊነታችን መገለጫ ጭምር ስለሆነ ነው። እናም ሁሌም ክብር ለእናቶቻችን፣ ለእህቶቻችንና ለሚስቶቻችን እንዲሁም ለሴት ልጆቻችን በመስጠት በግለሰብም የሀን በማህበረሰብ ደረጃ ከፍ ወዳለ የግበረ ገብነት ደረጃ መሻገር እንችላለን።

በአጠቃላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የግንቦት 20 መልዕክቶች ከራስ እስከ አገር ድረስ ውስጣዊ ጥንካሬ የሚሰጡን፣ ፍቅርን፣ ሰላምን፣ አብሮነትንና ተካፍሎ መብላትን እንዲሁም የጋራ እንጂ የግል ጽዳት ብቻ የዘመናወነት መገለጫ እንዳልሆነ እንዲሁም ሴቶችን ማክበር አስፈላጊና ተገቢ መሆኑን የሚገልጹ ናቸው። ባለፉት ጊዜያት በሂደት እየተሸረሸሩ ያጣናቸውን እሴቶች ዳግም እንድንጎናጸፋቸው እንዲሁም ያሉብንን ግለሰባዊና ማህበራዊ ክፍተቶች በመድፈን ነገአችን የተሻለና ብሩህ እንዲሆን የሚያግዙን ናቸው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy