Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

…ማን ሊቆም ይቻለዋል?

0 438

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

…ማን ሊቆም ይቻለዋል?

                                                          ታዬ ከበደ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በአዲስ አበባ በተካሄደው የድጋፍና የምስጋና የመደመር ቀን ባደረጉት ንግግር፤ ዕለቱ የህዝቦችን አንድነት የሚያጠናክር፣ መቻቻልና አብሮነት የሚያጎለብት፣ ይቅር ባይነትን የሚያሰፍን መሆኑን ገልፀዋል። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በአገራችን እየተካሄደ ያለው ለውጥ የህዝቡን እሴቶች በማጎልበት ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ጥላ ስር እንዲሰባሰቡ የሚያደርግ ነው።

መደመር ኢትዮጵያዊያን ተባብረው ችግሮቻቸውን ለመፍታትና በተጀመረው የለውጥ ጎዳና ያለ አንዳች ችግር እንዲጓዙ የሚያደርግ ነው። ይህ በአገራችን እየተካሄደ ያለው ለውጥ፤ ጥቅማቸው ከተነካባቸው ጥቂት ‘እኔ ብቻ ልብላ’ ባዮች ውጭ በአብዛኛው ህዝብ የተደገፈ በመሆኑ በህዝባዊው የለውጥ ማዕበል ፊት ማንም ደፍሮ ሊቆም አይችልም።  

ሰሞኑን በጅግጅጋ፣ በጎንደር፣ በደብረ ማርቆስ፣ በደሴ፣ በኮምቦልቻ የነበረው የድጋፍና የምስጋና ሰልፎች የለውጡ ባለቤት ሀዝቡ መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው። በየአካባቢው በተካሄዱ የመደመር ቀን ሰልፎች ለድጋፍና ለምስጋና የወጣው ህዝብ ብዛት እንዲሁም በራሱ ተነሳሽነት ካናቴራ ገዝቶ፣ በእግሩ ከርቀት ተጉዞ በሰልፎቹ ላይ ለመታደም በነቂስ የወጣው ህዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ የማይታወቅ ነው።

የህዝቡ የባለቤትነት ስሜት እጅግ የሚያስደምም ነው። ይህ ህዝባዊ ስሜት ‘እውን ከለውጡ ፊት ማን ሊቆም ይቻለዋል?’ የሚያስብል ነው። እርግጥም የህዝብ ጽኑ ፍላጎት በሆነው ለውጥ ፊት ማንም ችሎ የመቆም አቅም አይኖረውም፤ የህዝብ ሃይል እንደ ማዕበል ጠራርጎ የሚወስድ ነውና።

እርግጥ ህዝብ የለውጡ ባለቤት ሆኖ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላከናወኑት አገራዊ ተግባር ድጋፍ ለመስጠትና እውቅና ለመቸር የወጣው ያለ ምክንያት አይደለም። በዚህች አጭር ጊዜ ውስጥ በአገራችን በርካታ የህግ ታራሚዎች በይቅርታ ከእስር መለቀቃቸውን፣ በአገር ውስጥ ከሚገኙ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር መልካም ግንኙነትን መፈጠሩን፣ በትጥቅ ትግል ላይ የተሰማሩ ሃይሎችም ሰላማዊ የትግል መስመርን መቀላቀላቸው ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት መንግስት እየተጫወተ ያለውን ሚና ስለሚገነዘብ ነው።  

በተጨማሪም ህዝቡ በውጭ አገር የነበሩ ሚዲያዎች በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ወደ አገር ቤት መጀመራቸውን፣ የዳያስፖራውም የፖለቲካ አተያይ አየተቀየረ መሆኑን፣ ከኤርትራ ጋር የነበረው ሞት አልባ ጦርነትም መቋጫ እያገኘ እንደሆነ ተገንዝቧል። ይህ ሰላም ወዳድና ለውጥ ፈላጊ ህዝብ እነዚህን እውነታዎች በመረዳቱ ለውጡ የራሱ እንደሆነ በማመን ለመደመር ቀኑ በየአካባቢው በነቂስ ወጥቶ የድጋፍና የምስጋና ሰልፍን አካሂዷል።

ሆኖም እየተካሄደ ያለው አገራዊ ለውጥ ቀደም ሲል ለፈጸሙት በደልና ጥፋት ተጠያቂነትን ያስከትልብናል ወይም ቀጣይ ህገ ወጥ የሆነውን የጥቅም ማጋበሻ መንገድ ይዘጋብናል የሚል ስጋት የፈጠረባቸው ቡድኖች ይህን ህዝባዊ የለውጥ ማዕበል ሊጋፉት ሲሞክረየ እየተስተዋለ ነው።

ቡድኖቹ ህዝባዊውን የለውጥ መንፈስ ለማደናቀፍ እስከ ታችኛው እርከን በዘረጓቸው የጥፋት መረቦቻቸው አማካኝነት በረቀቀና ውስብስብ በሆነ መንገድ የለውጥ ሂደቱን አቅጣጫ ለማስቀየር ጥረት እያደረጉ ነው። ለምሳሌም መንግስት እስካሁን ላካሄዳቸው ለውጦች ምስጋና ለማቅረብና በቀጣይም ድጋፉን ለማረጋገጥ ህብረተሰቡ በመስቀል አደባባይ ባካሄደው የድጋፍ ሰልፍ በህዝብ ላይ ቦምብ ወርውረዋል። በዚህም ንፁሃንን ገድለዋል፤ የአካል ጉዳትም አድርሰዋል። ይህ ፈፅሞ መወገዝ ያለበት የህዝብን ፍላጎት የመግታት አጉል ድፍረት ነው። የሴረኝነት ተግባርም ነው።

ሴራቸው በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የህዝብን ትክክለኛ ጥያቄዎች ከለላ በማድረግ አብረው ለዘመናት የኖሩ ህዝቦችን እርስ በርሳቸው እንዲጋጩ ለማድረግ የሚጥሩት እነዚህ የለውጥ እንቅፋቶች፤ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በፈጠሩት ነውጥ ህይወት እንዲጠፋ፣ አካል እንዲጎድልና ንብረት እንዲወድም ምክንያት ሆነዋል።

ተግባራቸው እጅግ መሰሪ በመሆኑም በህዝቡ ውስጥ ባደራጇቸው የጥቅም ተጋሪዎቻችው አማካኝነት ህብረተሰቡ በመንግስት ላይ ቅሬታ እንዲያነሳና የለውጥ ሂደቱን አቅጣጫ ለማስቀየር በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ጉዳት እንዲደርስና የሃይል አቅርቦት እንዲቋረጥ አድርገዋል። እንዲሁም የስልክ ኔትዎርክ እንዲጠፋ፣ መሰረታዊ የሸቀጦች አቅርቦት ላይ ጫና በመፍጠር የዋጋ ንረት እንዲከሰት እንዲሁም የተለያዩ ህዝባዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ስራዎች እንዲደናቀፉ እያደረጉ ነው።

ይህ እኩይ ምግባራቸውም ህዝቡ በመንግስት ላይ እንዲማረርና የተጀመረው የለውጥ ፍላጎት አቅጣጫውን ስቶ ወዳልተፈለገ መንገድ እንዲጓዝ በመወራጨት ላይ ይገኛሉ። ህዝቡ እነዚህ አካላት እየፈጠሩ ያሉት ተግባር ለውጡን ለመቀልበስና ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያመራ ለማድረግ መሆኑን ተገንዝቦ የተለመደውን ጥንቃቄ በማድረግ ለለውጡ ቀጣይነት ሊታገል ይገባል።

የህዝቡን የለውጥ ስሜት በማደናቀፍ ተጠቃሚ ለመሆን የሚሹ እነዚህ ሃይሎች ሌላው ቀርቶ ልክ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እንዳደረጉት ዓይነት ችግርን በመፍጠር የህዝቡን የለውጥ ስሜት ሊቀለብሱት ይፈልጋሉ። ሆኖም ግን ከቶም የሚሳካላቸው አይሆንም።

በቅርቡ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የተካሄደውን የለውጥ ድጋፍና ምስጋና የመደመር ቀን ለማጠልሸትም ሞክረዋል። እነዚህ ለውጡን የማይፈልጉ አንዳንድ አካላት በአሉባልታ ‘የኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ተመረጠላችሁ’ በማለት ጭምር ህዝቡን በማስፈራራት የክልሉ ህዝብ የለውጡ አካል እንዳይሆን ለማድረግ ሲሞክሩ ተስተውሏል። ሆኖም ይህን የተሳሳተ አካሄድ ለውጥ ፈላጊው የጅግጅጋ ህዝብ ሰባብሮ በመውጣት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ጎን መቆሙንና የለውጡ አካል መሆኑን በሰልፉ ላይ በነቂስ በመገኘት አስመስክሯል። እንዲያውም የጅግጅጋ ህዝብ በአዲስ አበባ የመደመር ቀን ለምስጋናና ለድጋፍ ሰልፍ በወጡ ንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ድርጊት ህዝቡ አውግዟል።  

ይህ ሁኔታም ለውጡን ለማደናቀፍ አሰፍስፈው ለነበሩ አካላት ውርደት ብቻ ሳይሆን ለውጡን መንካት ህዝቡን መንካት እንደሆነ ያስተማራቸው ይመስለኛል። ከሁሉም በላይ በህዝባዊ ለውጡ ፊት ማንም ደፍሮ ሊቆም እንደማይችል ያረጋገጠ ክስተት ሆኗል ማለት ይቻላል።

የለውጡ ባለቤትነት ስሜት በሁሉም የአገራችን ክፍሎች በግልፅ የታየ በመሆኑ የህዝቡን ፍላጎት ለማደናቀፍ የተሰለፉ አካላት ከመፍጨርጨር ውጭ የሚያመጡት አንዳችም ችግር ሊኖር አይችልም። ምክንያቱም ህዝብን እየገደሉ፣ እያቆሰሉና እያሸበሩ መቀጠል ጊዜው ያለፈበት አስተሳሰብና ድርጊት ስለሆነ ነው።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy