Artcles

ምህረተ መንግስት ለምሉዕ አንድነት

By Admin

June 11, 2018

ምህረተ መንግስት ለምሉዕ አንድነት

ኢብሳ ነመራ

በኢትዮጵያ በወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው ጥፋተኛ ተብለው የተፈረደባቸውን ታራሚዎች ወይም ፍርደኞች በይቅርታ መልቀቅ የተለመደ ነው። ይቅርታ አድራጊው መንግስት ነው። በመንግስት የሚሰጠው ይቅርታ ህገመንግስታዊ መሰረት አለው። ይቅርታ የሚሰጥበትን ስርአት የሚደነግግ የይቅርታ ህግ ወይም አዋጅም አለ።  በዚህ መሰረት የፌደራልና የክልል መንግስታት የተለያዩ ሁነቶችን መነሻ በማደረግ በዓመት ሁለት ሶስት ያህል ጊዜ በተለያዩ ወንጀሎች ለተፈረደባቸው ግለሰቦች ይቅርታ ያደርጋሉ። ከፖለቲካ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በተፈጸሙ ወንጀሎች የጥፋተኝነት ብይን ተላልፎባቸው ቅጣት የተወሰነባቸው ግለሰቦችም ይቅርታ ሲደረግላቸው ቆይቷል። ምርጫ 97ን ተከትሎ በተፈጸመው ሁከት በወንጀል ተከሰው የተፈረደባቸው የቅንጅት አመራሮችና አባላት እንዲሁም ሌሎች ግለሰቦች በይቅርታ መለቀቃቸው ይታወሳል። በቅርቡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ፍርደኞች በተመሳሳይ ሁኔታ በይቅርታ ተለቀዋል።

ከይቅርታ በተጨማሪ ከሳሽ አቃቤ ህግ በማንኛውም የክስ ሂደት ደረጃ ላይ ፍርድ ከመተላለፉ በፊት ክስ አቋርጦ ተጠርጣሪዎችን ሊያሰናብት የሚችልበት የህግ አግባብ አለ። የክሱ ጉዳይ ሃገራዊ ይዘት ሲኖረው አቃቤ ህግ ክስ ለማቋረጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያነጋግራል። በቅርቡ ከፖለቲካና ከሙስና ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው ተጠርጣሪዎች ክሳቸው ተቋርጦ የተሰናበቱት በዚህ መሰረት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የኢፌዴሪ መንግስት በተለያዩ ጊዜዎች ህገወጥ የሃይል እንቅስቃሴ ሲያካሂዱ ለነበሩ ቡድኖች በከፊልና በሙሉ ምህረት ሲሰጥ የቆየበት ሁኔታ መኖሩም ይታወቃል። ምህረትም ህገመንግስታዊ መሰረት አለው። ከዚህ ቀደም ለኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) በከፊል፣ ከሁለት ዓመት በፊት ደግሞ በኤርትራ ሲንቀሳቀስ ለነበረው የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ምህረት መሰጠቱ ይታወሳል። በሃገሪቱ ከዚህ ቀደም ምህረት ሲሰጥ የቆየ ቢሆንም፣ የምህረት አሰጣጥ ስነስርአት አዋጅ ወይም ደንብ ግን አልነበረም። ይህን የሚመለከት ድንጋጌ በሃገሪቱ የወንጀል ህግ ላይ የሰፈረ ነው። እርግጥ በቅርቡ  የምህረት አሰጣጥ ስነስርአት ህግ ወይም ደንብ ረቂቅ ተዘጋጅቶ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወያይቶበት ለዝርዝር እይታ ለህግ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል።

በሃገራችን በተለይ መገናኛ ብዙሃን ይቅርታና ምህረትን እንደ ተመሳሳይ እሳቤ በመውሰድ እያለዋወጡ ሲጠቀሙባቸው ይስተዋላል። በመሆኑም ህዝቡ ውስጥ በይቅርታና ምህረት እሳቤዎች መሃከል ያለው ልዩነት ላይ የጠራ ግንዛቤ የለም። በመሰረቱ ይቅርታና ምህረት የተለያዩ እሳቤዎች ናቸው። ይቅርታ በተፈጸመ ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ ለተፈረደበት ግለሰብ፣ በግለሰብ ደረጃ የሚሰጥ ከቅጣት ነጻ የማደረግ ውሳኔ ነው። ይቅርታ በፍርድ ቤት የተወሰነ ቅጣትን ያስቀራል እንጂ ይቅርታ የተደረገለትን ሰው ወንጀለኝነት አይቀይርም። የግለሰቡ የወንጀል ሪከርድ ይቀጥላል። ይቅርታ የሚሰጠው በፌደራል መንግስት ደረጃ በይቅርታ ቦርድ አቅራቢነት በፕሬዝዳንቱ ነው። በክልል ደረጃ ደግሞ በክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ነው።

በሌላ በኩል ምህረት በወንጀል ለተፈረደበት ግለሰብ የሚሰጥ አይደለም። ምህረት በወንጀልነት የሚታሰብ ድርጊት ውስጥ ለተሳተፉ ግለሰቦች፣ እከሌ ከእከሌ በሚል ሳይለይ በቡድን የሚሰጥ ነው። ምህረት ክስ ከመመስረቱ አስቀድሞ፣ ወይም ጉዳዩ በክስ ሂደት ላይ ሳለ የቅጣት ፍርድ ከመተላለፉ አስቀድሞ የሚሰጥ ነው። ምህረት ወንጀሉ ፈጽሞ እንዳልተፈጸመ እንዲታሰብ የማድረግ አቅም አለው። ምህረት በአብዛኛው የሚሰጠው ከፖለቲካ ጋር ለተያያዙ የወንጀል ድርጊት ፈጻሚ ቡድኖች ነው። መንግስትን በሃይል ለማስወገድ የሃይል ተግባር ውስጥ ለተሳተፉ፣ ጦርነት በመቀሰቀስ የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት ለሆኑና መሰል ወንጀሎች ውስጥ  ለተሳተፉ ቡድኖች የሚሰጥ ነው። ምህረት እንዲሰጥ ምህረት ተቀባዮቹ ወደሰላማዊ ህይወት ለመመለስ ፍቃደኞች መሆን ይኖርባቸዋል። ምህረት እንደ ይቅርታ በፕሬዝዳንት/በርዕሰ ብሄር ውሳኔ የሚሰጥ አይደለም። ምህረት በአዋጅ ነው የሚሰጠው።

አሁን በውይይት ሂደት ላይ ያለው የኢትዮጵያ የምህረት አሰጣጥ ስነስርአት ረቂቅ ደንብ ከተለያዩ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት የተወጣጡ የስራ ሃላፊዎችን የያዘ የምህረት ቦርድ እንደሚቋቋም ይገልጻል። በረቂቅ ደንቡ መሰረት ይህ ቦርድ የምህረት ጥያቄዎችን ይቀበላል፣ ይመረምራል፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የምህረት የውሳኔ ሀሳብ ያቀርባል፣ የውሳኔ ሃሳቡን በአብላጫ ድምጽ ያጸድቃል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምህረት የውሳኔ ሃሳቡ አዋጅ ሆኖ እንዲወጣ ወደየህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይመሩታል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማንኛውም ህግ የሚጸድቅበትን ሂደት ተከትሎ የምህረት የውሳኔ ሃሳቡን አዋጅ አድርጎ ያጸድቃል። ምህረት የሚሰጠው በዚህ አዋጅ መሰረት ነው።

የይቅርታና የምህረት አሰጣጥ ገደብ አለው። ይህ ገደብ በህገመንግስት ተደንግጓል። የኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀጽ 28 በስብዕና ላይ ስለሚፈጸሙ ወንጀሎች በሚል ርዕስ ስር፣ በአንቀጽ 1፤

ኢትዮጵያ ባጸደቀቻቻው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና በሌሎች የኢትዮጵያ ህጎች በሰው ልጅ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው የተወሰኑትን ወንጀሎች፤ የሰው ዘር የማጥፋት፣ ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ የመውሰድ፣ በአስገዳጅ ሰውን የመሰወር፣ ወይም ኢሰብአዊ የድብደባ ድርጊቶችን በፈጸሙ ሰዎች ላይ ክስ ማቀረብ በይርጋ አይታገድም። በህግ አውጭው ክፍልም ሆነ በማንኛውም የመንግስት አካል ውሳኔዎች በምህረት ወይም በይቅርታ አይታለፍም።

ይላል።

እንግዲህ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሃገራዊ አንድነት መላላትና በህገመንግስት የተረጋገጠውን የአመለካካትና አመለካካትን የማራመድ ፖለቲካዊ ነጻነት መሸራረፍ ምክንያት የሆኑ ችግሮች መኖራቸው ይታወቃል። ከዚህ በተጨማሪ የፍትህ አሰጣጥ ስርአቱ ችግር አለበት። ይህ ሁኔታ ባለፉ ዓመታት በመላ ሃገሪቱ ለሰላም መደፍረስና አለመረጋጋት ምክንያት ሆኗል። የሰላም መደፍረሱና አለመረጋጋቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ አስከትሏል። ይህን መነሻ በማደረግ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ዜጎች ነጻ እንዲለቀቁ  ፖለቲካዊ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል። የኢፌዴሪ መንግስትና ክልላዊ መንግስታት በዚህ ፖለቲካዊ ወሳኔ መሰረት በሺህ ለሚቆጠሩ ፍርደኛ እስረኞች ይቅርታ አድርገዋል። ሌሎች በሺህ የሚቀጠሩም ክሳቸው ተቋርጦ ተሰናብተዋል። ከዚህ በተጨማሪ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው ግለሰቦችም ክሳቸው ተቋርጦ እንዲሰናበቱ ተደረጓል።

በወንጀለኝነት የተፈረደባቸው ፖለቲከኞች የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙት ሆን ብለውም ይሁን ከቁጥጥራቸው ውጭ በሆነ ፖለቲካዊ ነባራዊ ሁኔታ ገፊነት፣ ደጋፊዎች አላቸው፤ እንደሁኔታው በመቶ ሺህ፣ በሚሊየን የሚቆጠሩ ደጋፊዎችና ተከታዮች። የፖለቲከኞቹ መታሰርና መከሰስ ደጋፊዎቻቸውን አሳዝኗል፤ አስቀይሟል፤ አስቆጥቷልም። ይህ ሁኔታ ህዝቡን በመከፋፈል ለሃገራዊ አንድነት መላላት ምክንያት ሆኗል።

ከዚህ በተጨማሪ የሃገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ሁሉንም አመለካካት ማስተናገድ የሚችል አይደለም። በተለይ በክልሎችም ሆነ በፌደራል መንግስት ደረጃ ስልጣን በአንድ ፓርቲ ስር መውደቁ፣ ሌሎች አመለካከቶች የሚሰሙበትን መድረክ አሳጥቷል። ከዚህ ባሻገር የሃገሪቱ የዴሞክራሲ ባህል ባለመጎልበቱና የመልካም አስተዳደር ችግር በመኖሩ የተለያዩ አመለካከቶች በህገመንግስት የተረጋገጣለቸውን መብቶች የሚጠቀሙበት እድል ተገደቧል። ከፖለቲካ ጉዳይ ውጭ ባሉ ለምሳሌ ሙስናን በመሰሉ ወንጀሎች የተጠረጠሩ ተከሳሾች ጉዳይም ቢሆን፣ የፍትህ ስርአቱ ባለው ችግር ምክንያት የፍርድ ሂደቱ አልፎ አልፎ ተጠርጣሪዎቹ በእስር ሊቀጡ ከሚችሉበት ጎዜ በላይ የሚጓተትበት ሁኔታ አለ። ይህ የፍርድ ሂደት መጓተት ፍትህን ከመከለከል ያልተለየ ወጤት አስከትሏል።

የኢፌዴሪ መንግስት  ለታራሚዎች ይቅርታ ሲያደርግ፣ የተጠርጣሪዎችን ክስ ሲያነሳ ከላይ የተገለጹትን የሃገሪቱን ነባራዊ ፖለቲካዊና የፍትህ አሰጣጥ ስርአት ሁኔታዎች ከግምት አስገብቷል። የይቅርታና ክስ የማቋረጡ ዓላማ የላላውን ሃገራዊ አንድነት ማጠናከር፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋትና  በፍትህ ስርአቱ ችግር ምክንያት ያጋጠመውን የፍትህ መስተጓጎል ማስተካከል ነው።

የሃገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት፣ ሃገራዊ አንድነት የመፍጠርና አንድነቱን ጠንካራ መሰረት ላይ የማኖር፣ የፖለቲካ ምህዳሩን በሚገባው ልክ የማስፋት ጉዳይ ፍርደኞችን ከመፍታትና የተጠርጣሪዎችን ክስ ከማቋረጥ በላይ እርምጃዎችን የሚፈልግ ይመስላል። ባለፉ አርባ ዓመታት በተለያየ ዓላማና መነሻ ምክንያት ከትጥቅ ትግል ጀምሮ አመቺ ሆነው ባገኟቸው በማናቸውም መንገዶች በትግል ላይ የቆዩ ቡድኖች መኖራቸው ይታወቃል። በሃገሪቱ በህገመንግስት በተረጋገጠው ፖለቲካዊ ነጻነት መሰረት፣ ከነችግሩም ቢሆን ህጋዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በማደረግ ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸው ሳይዘነጋ፣ በህግ ያልተፈቀደ ትግል ውስጥ ያሉት ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም። እነዚህ በህገወጥ የትግል እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ቡድኖች አነሰም በዛ ደራጊዎች አላቸው። የተወሰኑቱ የተከተሉት የትግል ስልት ተገቢ እንዳልሆነና እንደማያዘልቅ የተገነዘቡ መሆናቸውንም የሚጠቁሙ እውነታዎች አሉ። የሁን እንጂ በወንጀል ድርጊት ውስጥ ስለተሳተፉ ወደሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የመመለስ ነገር ቀላል አልሆነላቸውም።

እነዚህ ደጋፊዎች ያሏቸውና ወደሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መመለስ ያልቻሉ ቡድኖች ለሃገራዊ አንድነት መላላት ወይም ለህዝብ መከፋፈል ምክንያት ሆነዋል። በህገወጥ እንቅስቀሴ ውስጥ ቆይተው ወደሰላማዊ ትግል መመለስ የሚፈልጉት፣ በህገወጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ሳሉ በግልና በቡድን ለፈጸሟቸው ጥፋቶች በህግ ተጠያቂነት እንዳለባቸው ስለሚያውቁ ከደጋፊያቸው ርቀው በውጭ ሃገራት ለመኖር የተገደዱበት ሁኔታ አለ። በዚህ ሁኔታ የተፈጠረውን የሃገራዊ አንድነት መላላት ለማስተካከልና በሃገሪቱ አስተማማኝ ዘላቂ ሰላም ለማሰፈን ከይቅርታ በተጨማሪ ህግ በሚፈቅደው መሰረት ለአንዳንድ ቡድኖች ምህረት የሚደረግበት አግባብ ሊኖር ይገባል።

እንግዲህ፤ ሃገራዊ አንድነትን ለማጠናከር፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት፣ የፍትህ መጓደልን ለማስቀረት ይቅርታ ሲደረግ ቆይቷል። በቀጣይ ደግሞ ሃገራዊ አንድነት የመፍጠሩ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋትና የሃገሪቱን ዘላቂ ሰላምና ልማት የማረጋገጥ እርምጃዎች ውጤቶች ምሉዕ እንዲሆኑ ምህረት የሚደረግላቸው ቡድኖችም ሊኖሩ ይገባል። በሂደት ላይ ያለው የምህረት አሰጣጥ ስነስርአት ደንብ ይህን የማድረግ ዓላማ አለው ብለን እንገምታለን። ምህረተ መንግስት ለምሉዕ አንድነት፣ ሰላምና ልማት።