Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ምህዳሩ እንዲሰፋ…

0 226

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ምህዳሩ እንዲሰፋ…

ገናናው በቀለ

የኢፌዴሪ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በርካታ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት በተለያየ ምክንያት የአገር ቤቱ የፖለቲካ ሁኔታ አልመች ብሏቸው ከአገር የተሰደዱ ፖለቲከኞችና የሚዲያ ባለሙያዎች ወደ አገራቸው ተመልሰው ህገመንግስቱንና ህገመንግስታዊውን ስርዓት አክብረው መስራት የሚችሉበትን ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር አመቻችቷል።

አገር ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር በማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ ላይ መነጋገር እንዲችሉ ሁኔታዎችንም ፈጥሯል። በተለይም ከዚህ ቀደም ተዘግተው የነበሩ ወደ 246 የሚጠጉ ድረ ገፆችንና ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመክፈት በአዲስ ሁኔታ የተጀመረው ዴሞክራሲን የማጎልበት ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል። በመሆኑም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሚዲያዎች ይህን ምህዳር ሀገርን በሚጠቅም የሃላፊነት መንፈስ መገልገል ይኖርባቸዋል።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፖርቲዎች በአስተሳሰብ ደረጃ የዴሞክራሲን ምንነት በውል የሚረዱና በአገራችን የተፈጠረውን ሰላም ከግምት በማስገባት ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱ ልህ ድርሻ አላቸው። የአገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በአዲስ ሁኔታ እየሰፋ ነው። ተፎካካሪ ፖርቲዎች የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ ሂደቱ ስር እንዲሰድና የተፈለገውን ርቀት ያህል እንዲጓዝ ገንቢ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል።

ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ምህዳሩን ለማስፋት በሚደረግ ውይይት ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አክብረው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል። ህገ መንግስቱ ከሚፈቅደው ውጭ መንቀሳቀስ ተገቡ አይሆንም።

ለሰላማዊ ትግል ቁርጠኛ አቋም መያዝ ይገባል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሚመራው የኢፌዴሪ መንግስት ዴሞክራሲውን ለማስፋት በሙሉ አቅሙ መንቀሳቀሱን እስካሁን ድረስ ከወሰዳቸው ምህዳሩን የሚያሰፉ እርምጃዎች ለመገንዘብ አያዳግትም። ይህም እዚህ አገር ውስጥ ማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ ምልከታ ያለውና የአገሪቱን ህዝብ የሚወክል አካል እንደልቡ ሃሳቡን እንዲገልፅና እየሰፋ በመጣው ምህዳር ውስጥ እንአዲንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

ታዲያ ይህን ምቹ ሁኔታ በተገቢው መንገድ መጠቀም በእጅጉ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚያደርጓቸው እያንዳንዱ እንቅስቃሴዎች በአገራችን በአዲስ መንፈስ የተጀመረውን እጅግ ተስፋ ሰጪ የምህዳር መስፋት የሚያጎለብተው ስለሆነ ነው።

መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ እንዲጎለብትና እንዲሰፋ እያደረገ ያለው ጥረት  የኢትዮጵያ ህዝቦች የአገራቸው ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት መሆናቸውን ስለሚያምንና ሉዓላዊነታቸው የሚገለፀውም በህገ መንግስቱ መሰረት በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካኝነት እንደሆ ስለሚገነዘብ ነው።

በመሆኑም አገራችን ውስጥ ያሉ ሁሉም ዓይነት አስተሳሰቦች እየሰፋ ባለው ምህዳር ውስጥ እንዲንፀባረቁ ይፈልጋል። የሁሉም የአገራችን ህዝቦች ድምፅ እንዲሰማ ደግሞ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተገቢው ሁኔታ ተደራጅተው የሚወክሉትን ህዝብ ፍላጎት ማንጸባረቅ ይኖርባቸዋል።

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቡ እንዲያስተዳድሩት የሚፈልጋቸውን ይመርጣል እንጂ፣ እንዳለፉት ስርዓቶች የሚያስተዳድሩት ራሳቸውን መርጠው አሊያም በገዥ ፓርቲ ተመርጠው የሚሄዱበት አሰራር ዶሴው ተዘግቷል። ይህን የተዘጋ ዶሴ ዳግም እንዳይከፈት የፖለቲካ ፓርቲዎች ፅኑ አቋም ይዘው መስራት ይኖርባቸዋል።

ጊዜው የሰላም፣ የአንድነት፣ የፍቅርና የዴሞክራሲ ነው። የመጠላለፍና ለምን እንዲህ ዓይነት አመለካከት ኖረህ ተብሎ የሚፈረጅበትና እያሳደዱ የሚታሰርበት ዘመን ላይመለስ ተሰናበቷል። ይህም ምህዳን ሰፊና ምቹ እያደረገው ነው። ስለሆነም በአዲስ መንፈስ ህዝብን ለማገልገል የተሰለፉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይህን በመስፋት ላይ የሚገኝ ምህዳር ለህዝብ በሚጠቅም የኃላፊነት ስሜት መገልገል ይኖርባቸዋል።

አገራችን ውስጥ ልማትንም ይሁን ዴሞክራሲን ለማሳለጥ የሚከናወኑ ማናቸውም ሁነቶች ማንንም ለማስደሰት አሊያም ለማስከፋት ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝቦች የታገሉላቸውን መብቶች በፅኑ መሰረት ላይ ለማቆመ ታስቦ ነው። መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ በመስራት ላይ የሚገኘው አሁን ካለንበት ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የህዝቡን የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ለመመለስ ካለው ቁርጠኝነት በመነጨ ነው። ዶክተር አብይና መንግስታቸው የሚያከናውኗቸው ማናቸውም ጉዳዩች ለአገርና ለህዝብ ጠቀሜታ ሲባል ብቻ የሚደረጉ መሆናቸውን በመገንዘብ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለምህዳሩ መጎልበት የሚጠበቅባቸውን አገራዊ ድርሻ መወጣት ይኖርባቸዋል።

የሚዲያ ነፃነት የዴሞክራሲው መገለጫ ነው። የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ማሳያ ነው። ለዚህም ሲባል ከላይ እንደገለፅኩት ቀደም ሲል ተዘግተው የነበሩ ወደ 246 የሚጠጉ ድረ ገፆችና ማህበራዊ ሚዲያዎች እንዲከፈቱ ተደርገዋል።

ይህ የተደረገው በአገራችን ውስጥ እየተፈጠረ ያለውን የአስተሳሰብ ብዝሃነትን በማስተናገድ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ነው። መንግስት ማናቸውም ሚዲያዎች ሃሳባቸውን እንዲገልጹ ሲያደርግ፣ ሚዲያዎቹም ሃላፊነት በሚሰማውና ህዝብን በሚጠቅም ሁኔታ ተግባራቸውን ሊወጡ ይገባል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የሚዲያ ሙያ እምብዛም ባልዳበረባቸው እንደ እኛ ባሉ አገራት ውስጥ ሚዲያ የህብረተሰቡን መሰረታዊ ፍላጎት ተመርኩዞ ሚዛናዊና ትክክለኛ ዘገባዎችን ከሰራ የሚጠበቅበትን ተግባር በበቂ ሁኔታ ሊወጣ ይችላል። በተለይ በአሀኑ ወቅት አንገብጋቢ ችግር የሆኑትን እንደ መልካም አስተዳደር ዓይነት ተግባሮችን የማስተማርና የማሳወቅ ብሎም ከህብረተሰቡ የሚነሱ ችግሮችን በመመርኮዝ የህዝቡ ዓይንና ጆሮ ሆኖ መስራት ይኖርበታል።

ያም ሆኖ ሚዲያው ‘ከመጠምጠም መማር ይቅደም’ እንደሚባለው፣ በቅድሚያ በግርድፉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመንቀስ በፊት በጉዳዩ ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ እንዲያዝ ማስተማር ይኖርበታል። መልካም አስተዳደር የሂደት እንጂ የአንድ ጀምበር ስራ አለመሆኑን ማስተማር ይገባል። ይሁን እንጂ በተጨባጭ የሚታዩ ችግሮችን ከህዝቡ በመቀበል እንዲስተካከሉና የእርምት እርምጃም እንዲወሰድ ለመንግስት ማቅረብ አለበት።

አሁን በምንገኝበት ሁኔታ መንግስት በመልካም አስተዳደር ችግር ህዝቡን እያማረሩ በሚገኙና የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲባል ግጭትን የሚያራምዱ አካላትን በተጠና መረጃና ማስረጃ ላይ በመደገፍ እንዲጋለጡ ይፈልጋል። በመልካም አስተዳደር መጓደል ምክንያት የሚፈጠሩ የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነት ወንጀሎችን በሙያዊ አሰራሮች በታገዙ ተጨባጭ ማስረጃዎችና መረጃዎች ላይ ተመርኩዞ ክትትል እንዲደረግም ይሻል። እንዲሁም የሚዲያ ሙያ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ስኬታማነት የህዝብን ተሳትፎ የሚያጎለብት አጀንዳ በመንደፍ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት ይኖርበታል። ህዝብን ከህዝብ ከሚያጋጩና ለህብረተሰቡ ምንም ዓይነት ፋይዳ የሌላቸውን ዘገባዎች ማስተናገድ አይጠበቅበትም። ከዚህ ይልቅ የመንግስት አሰራር ግልፅነትንና ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ ሙስናንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማሳወቅ ከፍ ሲልም በማጋለጥ ሀገራዊ ሚናውን መወጣት ይኖርበታል። ይህም የሚዲያው ሃላፊነት እንዲጎለብት ያደርጋል።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy