ሰላሙ እንዲጎመራ
ገናናው በቀለ
በአገራችን በተፈጠው አንፃራዊ ሰላም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት እንዲነሳ ተደርጓል። ለአዋጁ መነሳት ምክንያት ህዝቡ የሰላሙ ባለቤት ስለሆነ ነው። ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ሕብረተሰቡ የየአካባቢውን ሰላም በባለቤትነት ተረክቦ በመስራቱ አዋጁ ሊነሳ ችሏል።
የአገሪቱ ሰላም በቀጣይም አስተማማኝ ሊሆን የሚችለው ሕዝብና መንግሥት በጋራ ተቀናጅተው ሲሰሩ መሆኑ ግልፅ ነው። በመሆኑም ህዝቡ ለሰላሙ ዘብ መቆሙን ተግባር አጠናክሮ በመቀጠል ሰላሙ ይበልጥ እንዲጎመራ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል።
እንደሚታወቀው ሁሉ የየትኛውም አገር ህዝብ ሁሌም ከማናቸውም ተግባር በፊት ግራና ቀኝ የሚያይ፣ ህጋዊ አካሄዶችን የሚያጤን እንዲሁም የአካሄዶቹን አሉታዊና አዎንታዊ ጎን በመገንዘብ ሚዛናዊ ውሳኔ የሚሰጥ ነው።
የአገራችንም ህዝብ የወደፊት ዕጣ ፈንታው የሚወሰነው ሀገራችን በምትከተለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሆኑን ስለሚያውቅ፤ ሁሌም ሰላም ወዳድ ኃይሎች ጋር የሚቆም ነው።
የሰላምን ጠቀሜታ ስለሚገነዘብም ከምንግዜውም በላይ በየአካባቢው ለሰላሙ ዘብ እንደቆመ ነው። ባለፉት ሁለት ወራቶች ከኮማንድ ፖስቱና ከፀጥታ ሃይሎች ጋር ተቀናጅቶ ያከናወናቸው ሰላምን የማረጋገጥ ተግባሮች የዚህ እውነታ አረጋጋጭ ናቸው።
በእነዚያ ወራቶች ህዝቡ የየቀየውን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ በመጠበቅ ዋነኛ መሰረት ሆኗል። የቀየው ለሚከሰት ማናቸው የፀረ ሰላም ሃይሎች ድርጊት መልሶ የሚጎዳው እርሱን መሆኑን ስለሚያውቅ ለሰላሙ ተግቶ ሰርቷል። ዛሬም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲነሳ ይህ የህዝቡ ሰላም ወዳድነት ስለሚታወቅ እርሱን በመተማመን ነው።
የአገራችን ህዝብ ሰላሙ የልማቱ፣ ሰላሙ ዕድገቱ፣ ሰላሙ የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደቱ ሀገር በቀል በሆነ መንገድ ስር እንዲሰድ መሰረት መሆኑን በሚገባ ያውቃል። ይህ ህዝብ የሀገራችንን መለወጥ የማይሹ አንዳንድ ወገኖች አማካኝነት የተከሰተውን ሁከት ለመቋቋም በባለቤትነት ስሜት የከፈለው መስዕዋትነት ከፍተኛ ነው።
ባለፉት ጊዜያት ወጣቶችን ከጥፋታቸው የመመለስ፣ የተሃድሶ ትምህርት ከወሰዱም በኋላ ወደየቀያቸው ሲመለሱ ምክርና ተግሳፅ በመስጠት እንዲሁም ወጣቶቹ የየአካባቢያቸውን ሰላም በኃላፊነት ስሜት እንዲጠብቁ አድርጓል። ታዲያ ይህ የህዝቡ ስሜት መነሻው ከምንም የተነሳ ሳይሆን፣ የሰላምን ጥቅም በሚገባ ስለሚያውቀው ነው።
እርግጥ ህዝቡ ላለፉት ሁለት ወራቶች የሰላሙ ዘብ ሆኖ መቆሙ ትክክልም ተገቢም ነው። ሁከቱን ለመቀልበስ በሀገራችን የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል ሲባል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአስፈጻሚው አካል ታውጆ ተግባራዊ በሆነበት በእነዚያ ወራቶች የህዝቡ ሚና ወደር አልነበረውም።
ህዝቡ ላለፉት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጊዜያቶች የተራመዳቸው ተስፋ ሰጪ መንገዶች እንዲሁም የታለፈባቸው ውጣ ውረዶች በአሁኑ ወቅት የሚቀራቸው ለውጦች ቢኖሩም፤ ከትናንቱ ዛሬ በተሻለ ቁመና እንደሚገኙ ያውቃል።
በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከህዝቡ ጋር ባካሄዷቸውና በሚያካሂዷቸው ኮንፈረንሶች በመግባባት ላይ በመድረሱ ሰላሙን በራሱ ለመጠበቅ ወስኗል። ለለውጥ የተነሳ መሪ ባለ ተስፋና ውጤት ሊያመጣ የሚችል መሆኑን ያውቃል።
የአገራችን ህዝብ በመንግስት ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመራ በተከናወኑት ልማት ተግባራት ራሱ በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ ነው። አገሩም በልማቱ መስክ የአፍሪካ ተምሳሌት ሆናለች።
የቀጣናውን አገራት በልማት ለማስተሳሰር በምታደርገው ጥረት ተጠቃሽ መሆኗንም ያውቃል። በአረንጓዴ የልማት ፖሊሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመሪነት ሚናዋን እየተጫወተችም እንደሆነ ይገነዘባል። እናም ይህን ሁለንተናዊ ለውጡን በአዲስ አስተሳሰብ ለማራመድ ሰላም ወሳኝ መሆኑን የሚገነዘብ ፍትሐዊ ህዝብ ነው።
ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ የቀጣናውን ሀገራት ሰላም እያስከበረችና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደማጭነት እንዳላትም ይረዳል። ይህ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ቁመናችን እንዳይሸራረፍም ሰላምን በፅኑ እንደሚሻ እሙን ነው። ባለፉት ሁለት ወራቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን ገቢራዊ ለማድረግ ያሳየው ቁርጠኝነት የዚህ እውነታ ማሳያ ይመስለኛል።
አዲሱ አመራር በጥቂት ጊዜያት ውስጥ አንፃራዊ ሰላም እንዳስገኘ የሚያውቀው ይህ ህዝብ፤ አዋጁ የተነሳው እርሱ ላይ እምነት ተጥሎ በመሆኑ ወደፊት ከሰላም ለሚያገኘው ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ሲል ሰላሙን በየመነገዱ እንደሚያጎመራው ግልፅ ነው።
እርግጥ ባለፉት ሁለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወራቶች የአገራችን ሰላም በመደበኛው ህግ ሊፈቱ ከሚችሉ ጥቃቅን ጉዳዩች ውጪ በአብዛኛው ወደ ነበረበት የተመለሰው ህዝቡ ለሰላም ካለው የማይናወጥ ፍላጎት ሳቢያ ነው።
ሰላምን በፅኑ የሚሸው የአገራችን ህዝብ ደሙን ዋጅቶና አጥንቱን ከስክሶ ያመጣው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መንገድ እንዳይደናቀፍ እንዲሁም የኋሊት እንዳይቀለበስ አይሻም።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ስለ አዋጁ መነሳት አስመልክተው በሰጡት መግለጫ አዋጁ የተነሳው መላው የአገራችንን ህዝብ በማመን መሆኑን አስረድተዋል። ይህም ህዝብን ከማክበርና ያለ እርሱ ምንም ዓይነት ለውጥ ሊመጣ እንደማይችል ከሚገነዘብ በሳል መሪ የተሰጠ አመኔታ ነው።
በመሆኑም ህዝቡ ዛሬ አገራችን ውስጥ የተገኘው አንፃራዊ ሰላም የተገኘውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጥ ከግምት ውስጥ በማስገባት የሰላም አደራውን ተቀብሎ ወደ ስራ ገብቷል። በዚህም ውጤት እንደሚመጣና ሰላማችንን አስተማማኝ ሆኖ እንደሚቀጥል እርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚቻል ይመስለኛል።
በአጠቃላይ የአዋጁ መነሳት የህዝቡን ተፈጥሮአዊ የሰላም ፈላጊነት ስሜት ከግምት ውስጥ በማስገባትና ህዝቡ ሰላም እንዲመጣ ያለውን ፅኑ ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ህዝብ የሚፈፅማቸው ማናቸውም ተግባሮች በለውጥ ፈላጊነት መንገድ ከተያዙ ውጤታማ ይሆናሉ። እናም በህዝቡ የነቃ ተሳትፎ ሰላማችን መጎምራቱ አይቀርም።