Artcles

ስምምነቱና ተደማሪው ሰላም

By Admin

June 22, 2018

ስምምነቱና ተደማሪው ሰላም

                                                       እምእላፍ ህሩይ

ብዙውን ጊዜ ‘የሰላም ዋጋው ስንት ነው?’ የሚል ጥያቄ ሲነሳ አደምጣለሁ። አንድ ሰው በማንኛውም ክዋኔው ላይ ‘ስንት ነው?’ የሚል ጥያቄ ካነሳ፤ ‘ይህን ያህል ነው’ የሚል ምላሽ በቁጥር ይነገረዋል። ሆኖም ቁጥር ከሰላም ኑባሬያዊ እውነታ ጋር አይገናኝም። ሰላም በቁጥር ተተምኖ ሺህ፣ ሚሊዮን ወይም ትሪሊዮን…ወዘተ ተብሎ ሊገለፅ የሚችል አይመስለኝም። የትመናው ልኬት፤ ዳርቻ አልባ አሊያም ፈረንጆች እንደሚሉት “Infinity” ይመስለኛል። በእኔ እምነት የሰላም እሴት መለኪያ፤ በህዝቡ ሁለንተናዊ የህይወት መስተጋብር ውስጥ የሚፈጥረው ወሰን የለሽ ልማት ወይም አይለኬ ጥፋት ነው።  

ርግጥም የሰላምን እሴት በቁጥር ለማስላት መሞከር ዋጋውን ማሳነስ ነው። የሰላም መኖር፤ ሰዎች በምድር ላይ የተገኙበትን ግብ አሳክተው እስኪያሸልቡ ድረስ ያለ አንዳች ኮሽታ በሐሴት፣ በፍስሐና በደስታ እንዲኖሩ ያደርጋል። በአንፃሩም የሰላም እጦት፤ ሰዎች እንኳንስ ህይወታቸውን በደስታ ሊኖሩ ቀርቶ፤ ማቅ መስለውና ማቅ ለብሰው በስቃይና በእሪታ እንዲኖሩና እንዲያልፉ የሚያደርጋቸው ነው። ይህም የሰላም ዋጋ ከህይወት ወደ ሞት የመሸጋገር ያህል ልዩነት ያለው እጅግ ውድና በቁጥር ተገማች እንዳይሆን ያደርገዋል። በመሆኑም ለሰላም ሲባል በመደመር ይህን የማይገመት ቁጥር ይበልጥ ተገማች እንዳይሆን ማድረግ ያስፈልጋል።

እናም በእያንዳንዱ የሰው ልጅ መስተጋብር ውስጥ ስለ ሰላም የሚደረጉ ማናቸውም ግንኙነቶች፣ የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይቶችና ውሳኔዎች ከመጀመሪያው ረድፍ የመጀመሪያ ሆነው የሚታዩና ከፍተኛ ግምትም የሚሰጣቸው ናቸው። ይህን ጥቅል እሳቤ ወደ ሀገራችን ስንመልሰው፤ በኢትዮ-ኤርትራ መካከል ያለው ድንበር የአልጀርሱ ስምምነት በወለደው የድንበር ኮሚሽነ ውሳኔ መሰረት የዛሬ 16 ዓመት ባለመካለሉ ሳቢያ በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው ‘ሞት አልባ ጦርነት’ የሀገራቱን ሰላም አውኳል። የሰላም አለመኖርም የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች በአያሌው ጎድቷል።

ታዲያ ይህን ሁኔታ ለመቀየር፤ በአዲስ የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ የምትገኘው ሀገራችን በፍቅር፣ በሰላምና በአብሮነት ፈር ቀዳጁ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አማካኝነት የሰላም ዘንባባ ዝንጣፊን ለኤርትራ አቅርባለች— ‘የአልጀርሱን የሰላም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ እቀበላለሁ፤ የኤርትራ መንግስትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስድ እጠይቃለሁ’ በማለት። ከሳምንታት በኋላም የኤርትራ መንግስት የኢትዮጵያ መንግስት ላቀረበው የሰላም ጥሪ ምላሽ ሰጥቷል—ሀገሪቱ በየዓመቱ በምታከብረው የሰማዕታት መታሰቢያ ዕለት ላይ። በዕለቱ የኤርትራው ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው የለውጥ ሂደት ተገቢ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በመጠቆም፣ የድንበር ጉዳዩንና በሁለቱ ሀገራት ቀጣይ ሰላም ዙሪያ የሚመክር የልዑካን ቡድን ወደ አዲስ አበባ እንደሚልኩ አስታውቀዋል።

በእውነቱ ይህ የኤርትራ መንግስት ሰላምን የሚደምር ውሳኔ እጅግ አስደሳች ነው። ለሁለቱ ሀገራትም ይሁን ለቀጣናው ሰላም መደመር ሁነኛ መንገድም ነው። የመደመሩ ውጤትም፤ ቀደም ሲል የነበረውን የድንበር አካባቢ ዜጎችን ህይወትን ወደ ሞት አፋፍ ከሚያደርስ ስጋትና ሰቆቃ የሚያስቀር፣ የሀገራቱን ህዝቦችም ከሰላም ወደሚገኝ የላቀ ተጠቃሚነት የሚያሸጋግር እንደሚሆን በርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል። ምክንያቱም ከሰላም ትርፍ እንጂ ኪሳራ ስለማይገኝ ነው። የሰላምና የይቅርታ መሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም የኤርትራ መንግስት ላሳለፈው ውሳኔ ምስጋና አቅርበዋል። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የሚልኩትን ልዑክ እንደ ኤርትራዊ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያ በመመልከት እንደሚያስተናገዱም አስታውቀዋል።   

ይህን ሁኔታ ተከትሎም በጉዳዩ ዙሪያ አንዳንድ ወገኖች ጥያቄዎችን ሲያነሱ ይደመጣል። ጥያቄዎቹ የግንዛቤ እጥረት የፈጠራቸው ብዥታዎች ይመስሉኛል። እናም ከዚህ ከዚህ ፅሑፍ አኳያ ሁለት ብዥታዎችን ገለጥለጥ አድርጎ መመልከት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። አንደኛው፤ የአልጀርሱ ስምምነት የነበረ እንጂ አዲስ አለመሆኑን የተመለከተ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ፤ በሁለቱ ሀገራት የድንበር አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች በስጋት ቆፈን ውስጥ ሆነው ላለፉት 18 ዓመታት ተጠቃሚ አለመሆናቸውን የሚያስረዳ ነው።

የአልጀርሱ የሰላም ስምምነት የተደረገው ዛሬ አይደለም። ኢትዮጵያ በ1993 ዓ.ም ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ አስገዳጅና ተፈፃሚ እንዲሆን በፊርማዋ አረጋግጣለች፤ በአልጄሪያ ርዕሰ ከተማ አልጀርስ ላይ። ይህን የሰላም ስምምነትም የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ባካሄደው ስብሰባ በቃለ ጉባኤ ከማፅደቁም በላይ፤ በነጋሪት ጋዜጣ በቁጥር 225/1993 ህዳር 29 ቀን 1993 ዓ.ም ታትሞ አዋጅ ሆኖ እንዲወጣ አድርጓል። የኢፌዴሪ መንግስትም በወቅቱ ስምምነቱን መቀበሉን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ለአፍሪካ ህብረትና ለሌሎች ሶስተኛ ወገን አደራዳሪዎች አሳውቋል። ባለ ስድስት አንቀፁ የአልጀርስ ስምምነት፤ “የመጨረሻና አስገዳጅ” (Final and Binding) እንዲሆን ብሎም የድንበር አካላይ ኮሚሽን እንዲቋቋም የሚያዝ ነው።

በዚህም መሰረት የድንበር አካላዩ ኮሚሽን በሁለቱ ሀገራት ስምምነት ተቋቁሞ የአየር ላይ ካርታ እንዲያነሳ ተደረገ። ኮሚሽኑም እ.ኤ.አ ኤፕሪል 13 ቀን 2002 ዓ.ም የሁለቱን ሀገራት ድንበር አካሎ ውሳኔውን አሳወቀ።…እንግዲህ ከዚህ ሁሉ ሂደት በኋላ ነው—ሀገራችን ‘የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ቤተሰቦችን ይበታትናል’ በሚል ባለ አምስት ነጥብ የሰላም ሃሳብን ያመጣችው።

ታዲያ እዚህ ላይ የሰላም ሃሳቡ ጉዳይ የተነሳው ሀገራችን የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ እቀበላለሁ ብላ ፈርማ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ከሰማች በኋላ እንጂ፣ ከአልጀርሱ ስምምነት ጋር በሰነድነት ተካትቶ አለመሆኑን ግንዛቤ መያዝ ይገባል። ይህም አስገዳጁ ጉዳይ የአልጀርሱ ስምምነት እንጂ፣ ስምምነቱ የወለደው የድንበር ማካለል ጉዳይ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ በ1993 ዓ.ም የተፈረመው የሰላም ስምምነትን መቀበል የኢትዮጵያ ግዴታ እንደነበር ሊዘነጋ አይገባም—ስምምነቱ “የመጨረሻና አስገዳጅ” ስለሆነ።

እናም አዲሱ የዶክተር አብይ መንግስት ከዚህ በፊት የተፈረመውንና ፓርላማው ሳይቀር በአዋጅ ያፀደቀውን የአልጀርስ ስምምነት አሁን ካለው ሁኔታ አንፃር መዝኖ የነበረውን ለማሰፈፀም ከመፈለጉ ውጭ አዲስ የተፈራረመው ስምምነት አለመኖሩን መገንዘብ ያሻል። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ዶክተር አብይና መንግስታቸው ያደረጉት፤ ስምምነቱ ውስጥ የተካተቱን በርካታ ጉዳዩች በማዕቀፍ ወይም “በፓኬጅ” ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ነው። በሰላም ወዳዱ አዲሱ አመራር የተደረገው ነገር፤ ለህዝቦች የሚበጀውን ሰላም ተደማሪ አድርጎ ለላቀ ተጠቃሚነት መስራት ነው—የነበረውን በማስፈፀም።

እንግዲህ ከላይ ያነሳኋቸው ሃቆች አንዳንድ ወገኖች ‘የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ መንግስት ባለ አምስት ነጥብ የሰላም ሃሳቡን ትቶ ለምን ስምምነቱን ሙሉ ለሙሉ ተቀበለ?’ በማለት የሚያነሱት ጥያቄ የተሳሳተ መሆኑን ያስረዱልኛል ብዬ አስባለሁ። በዚህ ዙሪያ የሚነሱ ብዥታዎችን እንደሚያጠሩ መሆናቸውም እንዲሁ። ምክንያቱም መንግስት በአሁኑ ወቅት የወሰደው አቋም ከ18 ዓመታት በፊት ሀገራችን “የመጨረሻና አስገዳጅ ይሁን” ብላ ከፈረመችው የአልጀርስ ስምምነት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለው በመሆኑ ነው። እናም ለህዝቦች ዘላቂ ሰላምና ጥቅም ሲባል ስምምነቱን በተፈረመው መሰረት መቀበል፤ አሁን ባገኘነው ላይ ሌላ ሰላም መደመር ብቻ ነው—የሆነው ይኸው ነውና።  

የሰላም ስምምነቱ የህዝቦችን ጥቅም የማያረጋግጥ እንደሆነ በአንዳንድ ወገኖች የሚነሳው ሃሳብም የተሳሳተ ነው በዬ አምናለሁ። የስምምነቱ ገቢራዊ መሆን በስጋት ቆፈን ተቆፍድደው የዕለት ህይወታቸውን በመምራት ላይ ለሚገኙት የድንበር አካባቢ ዜጎች እፎይታን የሚያጎናፅፍ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሀመድ ከህዝቡ ጋር ፊት ለፊት ለመወያየት ወደ ትግራይ ባቀኑበተ ወቅት ከእነዚህ ዜጎች የቀረበው ጥያቄ ‘እነዴት ያለ አንዳች ጥቅም ለ16 ዓመታት ሚሊሻ ሆነን እንቆያለን?፣ መንግስት መላ ይበለን’ የሚል ነበር። ይህ ሁኔታ የሚያሳየው ነገር ቢኖር የድንበር አካባቢ ዜጎች የልማት ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ነው።

ርግጥ የጦርነት ስጋት ጥላ በሚያጠላበት አካባቢ ውስጥ ልማትና ኢንቨስትመንት ሊስፋፉ አይችሉም። ኢንቨስትመንት ባልተስፋፋበት ቦታ ደግሞ የስራ ዕድልን ማሰብ አይቻልም። የስራ ዕድል የሌለው ዜጋ ራሱንና ቤተሰቡን ሊለውጥ አይችልም። ለሀገሩ ዕድገትም አስተዋፅኦ አያደርግም። ይህ ሁኔታም በድንበር አካባቢ የሚገኙ ዜጎቻችን ከሌላው አካባቢ ህዝቦች በከፋ ድህነት ውስጥ እንዲዘፈቁ አድርጓቸዋል።

ሰላምን በመደመር የላቀ የህዝብ ተጠቃሚነት በተጨባጭ በህዝቡ ዘንድ እንዲኖር አዲስ መንገድ ቀይሶ የተነሳው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መንግስት፤ ይህ ህዝብ አሁን በሚገኝበት የተራቆተ ድህነት ቁመናን ይዞ እንዲቀጥል አለመፍቀዱ ትክከል ነው። ለህዝብ ከሚያስብ መሪና ከሚመራው መንግስት የሚጠበቅ ተግባርም ነው። በእኔ እምነት ሌላው የህብረተሰብ ክፍልም ይህን ህዝብ ማሰብ አለበት። ነገሩ “በሰው ምንትስ እንጨት ስደድበት” እንዲሉት ዓይነት መሆን የለበትም። የሰላምን ዋጋ አይተመኔነት በዚያ ድንበር አካባቢ ያሉትን ዜጎች ሄዶ በመመልከት ማረጋገጥ ይቻላል።

ታዲያ እንደ ዶክተር አብይ ያለ ከሰላም በሚገኝ ልማት የህዝቡን ህይወት በሚታይና በሚቆጠር ሁኔታ ለመቀየር የሚያልም መሪ፤ ያለውን የሰው ሃብት በአግባቡ መጠቀም ይኖርበታል። እጥረቱ የሆነውን ገንዝብን በመቆጠብ ለልማት ብቻ ማዋልም አለበት። ከዚህ አኳያ፤ በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር አካባቢ ያለው ውጥረት እጅግ ያየለ ነው። ይህም በአንድ በኩል፤ መከላከያ ሰራዊታችንም ‘መቼ ይሆን ጦርነት የሚከፈተው?’ በሚል የስነ ልቦና ጫና ውስጥ እንዲገኝ ያደረገው ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ፤ መንግስት በርካታ ሰራዊትን በአካባቢው በማስፈር የወታደራዊ ወጭያችን እንዲንር ምክንያት ሆኗል።

እናም በእኔ እምነት ሁለቱንም ችግሮች ለማስወገድ መንቀሳቀስ ለህዝብ ከሚጨነቅ መሪና ህዝባዊ ከሆነ መንግስት የሚጠበቅ ተግባር ነው። በድንበር አካባቢ በተፈጠረ ውጥረት ምክንያት፤ በአንድ እጁ ለልማት የሚሆን አካፋ የያዘው፣ በሌላኛው ደግሞ ህገ መንግስታዊ ተልዕኮውን የሚወጣበት ጠብ-መንጃ የያዘው ጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን ሌት ተቀን የስነ ልቦና ችግር ተጠቂ መሆን የለበትም። ይህ ችግር አንድ ቦታ መቆም አለበት። ስምምነቱ ይህን የሚያደርግ ነው።

ከዚህ ጎን ለጎንም እንደ እኛ ለማደግ የሚታትር ሀገር፤ ድንበሩ አካባቢ ከሚያስፈልገው በላይ በርካታ ሰራዊት አስፍሮ የሎጀስቲክስና የሌሎች ወጭዎቹን ማናር የለበትም። ምንም እንኳን የሰራዊት ተልዕኮ በገንዘብ የሚተመን ባይሆንም፤ ያለንን አነስተኛ ገንዘብ በመቆጠብ ለልማት ማዋል ይገባናል። ሰራዊቱም ከሀገሪቱ ልማታዊ ዕድገት ተጠቃሚ መሆን ይኖርበታል። ይህን ለመከወን ደግሞ፤ በድንበር አካባቢ ሰላም መስፈን አለበት። የስምምነቱ አስፈላጊነትም ተደማሪ ሰላምን በመፈጠር የህዝቡን የላቀ ተጠቃሚነት በሚታይና በሚዳሰስ መንገድ ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት አካል መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል። ሰላም ለሁለቱ ሀገራት! ሰላም ለቀጣናው! ሰላም ለአፍሪካ!