Artcles

ስምምነቱ ምንድነው?

By Admin

June 18, 2018

ስምምነቱ ምንድነው?

                                                          ሶሪ ገመዳ

ኢትዮጵያና ኤርትራ ከ1990 ዓ.ም እስከ 1992 ዓ.ም ድረስ ደም አፋሳሽ ጦርነት አካሂደዋል። ጦርነቱ በሁለቱም አገራት መካከል የዜጎችን ህይወት ከመቅጠፍ ባሻገር ለመፈናቀልም ምክንያት ሆኗል። ጦርነቱ እየተስፋፋ ሲመጣ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ሕዝብን ለመፈናቀል ዳርጓል። በሁለቱም አገራት ያሉ ቤተሰቦችንም ያፈረሰ ነው።

የሁለቱ አገራት ህዝቦች ድንበር ተሻግረው በጋብቻ የተሳሰሩ ናቸው። ሆኖም አንዳቸው ለአንዳቸው ሰርግም ሆነ ቀብር ላይ ሊገናኙ አልቻሉም። ሰቆቃው ብዙ ነው። የጦርነቱ ተፅዕኖ በቤተሰብ ግንኙነት ላይ ብቻ አይደለም። በድንበር አቅራቢያ በንግድ የሚተዳደሩ ሰዎች ላይም ጭምር እንጂ።

ይህም የሁለቱን ህዝቦች ተጠቃሚነት በእጅጉ የጎዳው ነው። ከጦርነቱ በፊት ሞቅ ብሎ የነበረው የንግድ እንቅስቃሴ አሁን ባለመኖሩ ከጋራ ንግድ ይገኝ የነበረው የጋራ ጠጠቃሚነት የለም። እነዚህ እውነታዎች ከማህበራዊና ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት አኳያ ሲሆኑ ከስነልቦናዊ ጫናም በኩል ህዝቦቹ ጦርነት መቼ ይነሳ ይሆን በማለት በስጋት ውስጥ ወድቀዋል። እነዚህ ተፅዕኖዎች ከባድ ናቸው።

ያም ሆኖ አገራችን ጦርነቱን ለማስቆም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ በወቅቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲሁም በሌሎች ሶስተኛ ወገን አደራዳሪዎች የሰላም ስምምነት ቀርቦ አገራችን በ1993 ዓ.ም የአልጀርስ ስምምነትን ፈርማለች።

እርግጥ በአገራቱ መካከል የዛሬ 20 ዓመት የተካሄደው ጦርነት በኢትዮጵያውያን በኩል ፍትሃዊ ጦርነት ነበር። አገራችንም በጦርነቱ ሉዓላዊነቷን ማስከበር ችላለች። ሉዓላዊነታችንን ለማስከበር መስዋዕትነት ለከፈሉ ወገኖቻችን ታላቅ ክብርም አላት። ይህ ስምምነት የመጨረሻና ገዥ ነው። ሰነዱን የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በወቅቱ ተቀብሎ በማፅደቅ አዋጅ ሆኖ እንዲወጣ አድርጓል። ዛሬ የተፈጸመ ምንም አዲስ ነገር የለም።

ታህሳስ 3 ቀን 1993 በቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና የኤርትራው ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተፈረመው ባለ 6 አንቀጽ ሰነድ አራት መሰረታዊ ግቦች ያሉት ነው። እነርሱም በሁለቱ ሀገራት መካካል ያለውን የባላንጣነት መንፈስ ማቆም፣ ሀገራቱ ከዛቻ እና የሃይል እርምጃ እንዲቆጠቡ ማድረግ፣ ቀደም ብሎ ማለትም በሰኔ አንድ ቀን 1992 ዓ.ም የተደረሰውን በባለንጣነት ያለመተያየት ስምምነት እንዲከበር እና እንዲፈጸም ዋስትና መስጠት፣ በእስር ያሉ የጦር ምርኮኞች እና ግለሰቦች ተለቀው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማስቻል እንዲሁም ሁለቱ አገራት በግዛቶቻቸው ውስጥ ላሉ የሌላኛው ወገን ዜጎች ሰብአዊ እንክብካቤ እንዲያደርጉ ድልድልይ ሆነው እንዲያገለግሉ ማስቻል ናቸው።

ከላይ የተጠቀሱት ግቦች በየተራ ይሳኩ ዘንድ፣ ሰነዱ ነጻ የድንበር እና የካሳ ኮሚሽኖች እንዲቋቋሙ መሰረት እንደሚሆን ያትታል። በተጨማሪም አምስት አባላት ያሉት የኢትዮ- ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን የራሱን ምርመራ አድርጎ፣ አለመግባባት የፈጠሩ የድንበር ቦታዎች ለየትኛው አገር እንደሚገቡ ለመወሰን እንዲችል የተስማሙበት ሰነድ ነው።

በሰነዱ አንቀፅ አንቀጽ 2 (2) ላይ እንደተገለፀው ቀደም ብለው የተገቡ የቅኝ ግዛት ህጎችን እና ዓለም አቀፍ ህግን ተመስርቶ ኮሚሽኑ ውሳኔውን እንዲያስተላልፍ የሚያደርግ ነው። እንዲሁም በአንቀጽ 2 (15) ላይ ኮሚሽኑ የሚሰጠው የወሰን እና ማካለል ውሳኔ የመጨረሻ እና ገዢ እንደሚሆን ተዘርዝሮም ተቀምጧል።

ከዚህ በኋላም በአልጀርሱ ስምምነት ሰነድ መሰረት ሁለቱን አገራት ህዝቦችን ድንበር የሚያካልለው የድንበር ኮሚሽኑ በአየር ላይ ካርታ በማንሳት አካልሏል። የቅኝ ግዛት ውሎችና ሌሎች ዓለም አቀፍ የህግ ማዕቀፎች ለኮሚሽኑ የድንበር ማካለል ስራ ውለዋል።

ሆኖም የኢትዮጵያ መንግስት የማካለል ስራው አንድን ቤተሰብ ሳይቀር ለሁለት ይከፍላል በሚል ጉዳዩ በመነጋገር እንዲፈታ ባለ አምስት ነጥብ የሰላም ጥሪ አቀረበ። ሆኖም የኤርትራ መንግስት የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ መተግበር አለበት በእምቢታ ጸና። ይሀ ሁኔታም ላለፉት 18 ዓመታት ሰላም የሌለበት ሁኔታን ፈጠረ።

ታዲያ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በቅርቡ ይህ ሁኔታ እንዲለወጥና የሁለቱም አገራት ህዝቦች ጥቅም እንዲጠበቅ በእንጥልጥል የነበረውን የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንደሚቀበል አስታውቋል። ይህም ቀደም ሲል የነበረውን የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤትን ውሳኔ እንዲፀና ያደረገ ነው። አዲስ ክስተት አይደለም።

ውሳኔው ላለፉት 18 ዓመታት በሁለቱም አገራት ህዝቦች ላይ መጠነ ሰፊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ የፈጠረውን ሁኔታ የሚቀይር ነው። ይህም የሁለቱ ሀገራት የወደፊት ግንኙነት ምን ሊሆን ይችላል? የሚለው ጥያቄ ሊመልስ የሚችል ነው።

ከጦርነቱ በኋላ በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በተባበሩት መንግስታት አደራዳሪነት የአልጀርሱ ስምምነት ቢደረግም፤ ላለፉት 20 ዓመታት በሁለቱ ወንድማማች ሀገሮች መካከል ጦርነትም ሆነ ሰላም የሌለበት ሁኔታ ከመፍጠር ውጭ የተገኘ ለውጥ እንደሌለ ይታወቃል።

ስለሆነም የሁለቱን አገራት ወዳጅነት ወደነበረበት መመለስ ያስፈልጋል። ላለፉት 20 ዓመታት የተደረጉ ሙከራዎች በሙሉ ውጤት ስላላመጡ አዲስ መንገድ መከተል ተገቢ ነው። ሰላምን ለማፈሰን አዲስና ሁለቱንም አገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ መንገድ መከተል ተገቢ ነው።

በአገራቱ መካከል የሚያስፈልገው ፉክክር ሳይሆን ስምምነት ነው። ይህም ለአፍሪካ ቀንድ ሀገሮችና አካባቢ የፖለቲካ ቀውስ መብረድና መረጋጋት ዘላቂው መፍትሄ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጤናማ ግንኙነት ስለሆነ ለቀጠናው የሚኖረውም ፋይዳ ከፍተኛ ነው። እስካሁን ድረስ ሁለቱ አገራትም የሁኑ ቀጠናው ከመልካም ጉርብትና እና ትብብር መጠቀም ያለባቸውን ነገሮች አላገኙም። ይህ ሁኔታ አንድ ቦታ ላይ መቆም አለበት።

ውሳኔው ቀድሞም ቢሆን በአንድ አገር ይተዳደሩ የነበሩት የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ለጋራ ጥቅማቸው ሲሉ አዲስ የሰላም መንገድ መከተል ያስፈልጋል። እናም የኢትዮጵያ መንግስት የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰነውና ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት የሚሰራ የገለፀው ከላይ የጠቀስኳቸውን የጦርነት አስከፊ ሁኔታዎችን ለመቀየር በማለም ነው።

አዲስ የሰላም፣ የእርቅና የፍቅር መንገድን የሚከተሉት አዲሱ የለውጥ አመራር ዶክተር አብይና መንግስታቸው ይህን የአብሮነት መንገድ ሲፈጥር፣ የኤርትራ መንግስትም ሁለቱ አገራት በነበረው የማይጠቅም ሁኔታ እንዳይቀጥሉ ኃላፊነት የተሞላበት ተመሳሳይ ውሳኔ ማሳለፍ ይጠበቅበታል።