Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስንዋደድ ያምርብናል

0 464

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስንዋደድ ያምርብናል

ለሚ ዋቄ

ባለፈው አርብ  1439ኛውን የኢድ አል ፈጥር በአል አክበረናል። ከአንድ ወር የሮመዳን ጾም በኋላ የሚከበረው የኢድ አል ፈጥር በአል በእስልምና ሃይኖት ተከታዮች ዘንድ ልዩ ስፍራ አለው። የሮመዳን ጾምና የኢድ አል ፈጥር በአል እንኳን ለሙስሊም ኢትዮጵያውያን ለክርስቲያን ኢትዮጵያውያንም ልዩ ስፍራ አላቸው። በርካታ ክርስቲያን ኢትዮጵያን ከሙስሊም ጓድኞቻቸው ጋር ሮመዳንን ይጾማሉ። የሮመዳን ጾም ሲገባ ክፉውንና ደጉን ከሚጋሯቸው ሙስሊም ጓደኞቻቸው ተለይቶ መብላትና መጠጣት የማይሆንላቸው ብዙዎች ናቸው። እናም ሮመዳንን አበረው ይጾማሉ፣ ምሽት ላይ አብረው ይጾማሉ፣ ሌሊት ዱኣ ይቀመጣሉ፣ ኢድ አል ፈጥርን አብረው ያከበራሉ። ይህ ለዘመናት የዘለቀ የክርስቲያንና  የሙስሊም ኢትዮጵያውያን አብሮነት መገለጫ ነው።

በቀደሙት ስርአቶች በተለይ በዘውዳዊው ስርአት ለእስልምና ሃይማኖት የህግ እውቅና ነፍገው እንደነበረ ይታወቃል። በዚያ ስርአት መንግስታዊ ሃይማኖት ነበር። ከዚህ መንግስታዊ ሃይማኖት ውጭ የሆኑ ሃይማኖቶች በሙሉ እውቅና ተነፍገው ነበር። የሙስሊሞች ሃይማኖታዊ በአላት ይፋዊ (official) አልነበሩም። በሙስሊም በአላት እለት የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶችም መደበኛ ሰራቸው አይቋረጥም። ሙስሊም የሆኑ ሰራተኞችና ተማሪዎች ግን በዚህ እለት ከአለቆቻቸውና መምህራኖቻቸው የእረፍት ፍቃድ ይጠይቃሉ። ፍቃድ ሊያገኙም፣ ላያገኙም ይችላሉ። አለየው ፍቃድ የመስጠት የሞራል እንጂ የህግ ግዴታ የለበትም። ይህ ሁኔታ የእስልምና ሃይማኖት በህግ አጥቶት የነበረውን እውቅና ያሳያል። የእውቅና መነፈጉ በዚህ የሚያበቃ አልነበረም። ብዙ ያስከተላቸው የመብት ገደቦች ነበሩ። ዝርዝሩ ውስጥ መግባት ያረፈ ሴጣን ቀስቃሽ እንዳያስብለኝ እንደተከደነ እተወዋለሁ።

የሚያስገርመው ግን ዘውዳዊው መንግስት ለሙስሊሞች የህግ እውቅና ነፍጎ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከማለት ይልቅ ባእዳን ይመስል በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሙስሊሞች በሚልበት ዘመን፣ በሙስሊምና ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን መሃከል ግን ጥብቅ ወዳጅነትና መከባበር ነበር። በኢትዮጵያ፣ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች በተለያየ መንደር አይደለም የሚኖሩት። ተቀላቀለው ነው። የተያያዙ ሁለት ደጃፍ ቤቶች አንዱ የክርስቲያን ሌላው የሙስሊም መኖሪያ የሚሆኑበት ሁኔታ የተለመደ ነው። ክርስቲያንና ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በጋራ እድር የተሰኘውን የማህበራዊ መደጋገፍና ትብብር ተቋም ይመሰርታሉ። ሃዘንና ደስታ ይጋራሉ። ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን በሙስሊም ጾም ወቅት ሰርግ አይደግሱም። ሙስሊም ኢትዮጵያውያንም በክርስቲያን ጾም ወቅት ሰርግ አይደግሱም። የማህበረሰብ መሰረት የሆነው ቤተሰብ የሚመሰረተበትን ታላቅ ሁነት ተነጣጠለው ማሳለፍ አይፈልጉም። ተነጣጥለው መበላትም አይመቻቸውም። ቢላ ቢለዩም በአንድ ድግስ ይታደማሉ።

በኢትዮጵያ ውስጥ የእስልምናና ክርስትና እምነት ተከታዮች በጉርብትና እንደሚኖሩት ሁሉ፣ የአምልኮ ስርአት የሚፈጽሙባቸውን መስጊድና ቤተክርስቲያም ጎን ለጎን፤ ፊት ለፊት ይገነባሉ። የሃገሪቱ ርእሰ መዲና አዲስ አበባ መርካቶ ያለውን የአንዋር መስጊድና የራጉኤል ቤተክርስቲያን ለዚህ ማሳያነት መጥቀስ ይቻላል። ራጉኤል ቤተክርስቲያንና አንዋር መስጊድ አጥር የሚጋሩ ጎረቤታሞች ናቸው። ቤተክርስቲያን መገንባት የክርስቲያኖች ጉዳይ ብቻ አይደለም። መስጊድ መገንባትም እንዲሁ የሙስሊሞች ጉዳይ ብቻ አይደለም። የጋራ ጉዳያቸው ነው። ክርስቲያኖች በአጥቢያቸው ሙስሊሞች መካነ መቃብር ማጣታቸው ያሳስባቸዋል። ሙስሊሞችም እንዲሁ ክርስቲያኖች በአጥቢያቸው መካነ መቃብር ማጣታቸውን እንደራሳቸው ችግር ነው የሚመለከቱት። እናም ተባብረው መስጊድና ቤተክርሰቲያን ያንጻሉ።

ሙስሊምና ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን አበረው ይህችን ሃገር ገንብተዋል። በአንድ ግንባር ጎን ለጎን ተሰልፈው የሃገሪቱን ወራሪ ጠላት ተዋገተው መስዋዕት ሆነዋል። በጦር ሜዳ በአንድ ጉርጓድ ተቀብረው የኢትዮጵያ አፈር ሆነዋል። ለእኩልነትና ለነጻነት፤ ለዴሞክራሲ በተካሄዱ እልህ አስጨራሽ የትጥቅ ትግሎች ውስጥ በአንድ ተደራጅተው በአንድ ግንባር ተሰልፈው ተዋግተዋል። አብረው ሞተዋል፣ በአንድ እስር ቤት ታጉረው ስቃይን ተጋርተዋል። አንዱ ሌላውን አጽናንቷል፤ አበረታቷል።

አሁን የሃይማኖት እኩልነት በህገመንግስት በተረጋገጠበት ዘመንም ይህ ድንቅ የአብሮነት እሴት ቀጥሏል። ሙስሊምና ክርስቲያን ኢትዮጵያን አሁን ይህችን ሃገር ያለምንም ልዩነት፣ ልዩነት የሚባለውን ነገር ፈጽሞ ሊያስቡ በማይችሉበት ሁኔታ በጋራ ነው የሚመሩት። ሙስሊሞች የሚያነሱት የሃይማኖታዊ መብት ጥያቄዎች ክርስቲያኖችንም ያይመለከታቸዋል። የመብት ጥያቄ ሲያነሱ አንዱ ላይ የሚደርስ ጫና  ሌላውን ይቆረቁረዋል።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህን ዘመናትን የተሻገረ የሙስሊምና ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን የመከባበርና የህብረት እሴት በማያውቁ በአመዛኙ በባእዳን አነሳሽነት ብቅ ብቅ ያሉ የአክራሪነት ዝንባሌዎች አብሮነቱን ለማፋለስ የሞከሩበት ሁኔታ አጋጥሟል። ይህ በሁለቱ ሃይማኖቶች የዘመናት የአብሮነት ታሪካችን ላይ እንዳረፈ ጥቁር ነቁጥ ይቆጠራል። በጥቂት አካባቢዎች በሃይማኖት ሰበብ ግጭት እንዲነሳና በሁለቱም ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ጉዳት እንዲደርስ የተደረገበት ሁኔታ አለ። ነባሩ የአብሮነት እሴት መጠበቅ አለበት ያሉ የሃይማኖት አባቶች በራሳቸው ሃይማኖት ተከታይ አክራሪዎች የጥቃት ሰለባ የሆኑበትንም ሁኔታ ታዝበናል። ይሁን እንጂ እነዚህን ችግሮች በህግ ሳይሆን በነባር የአብሮነትና ችግሮችን ተማክሮ የመፍታት ባህል ራሳቸው አክመው የዘለቁበት ሁኔታ ይታያል። ከዓመታት በፊት በሁለቱ ሃይማኖቶች መሃከል ግጭት ተቀስቅሶ በነበረባቸው አካባቢዎች አሁን ያለውን ሁኔታ መመልከት ለዚህ በቂ አስረጂ ነው።

ይህን ነባር የኢትዮጵያ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች የአብሮነትና የመከባበር እሴት የማያውቅ ኢትዮጵያዊ አለ የሚል ግምት ስላለኝ አይደለም ያነሳሁት። ሁሉም ኢትዮጵያዊ የኖረበትና አሁንም የሚኖርበት መሆኑን እገነዘባለሁ። ማንሳት ያፈለኩት በሮመዳን የጾም ወር ውስጥ በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚስተዋለውን የሞራል ልቀት፤ መተሳሰብ፣ መከባበር፣ መረዳዳት፣ ከክፉ ሃሳብና ድርጊት መታቀብ ወዘተ በክርስትናና እስልምና ሃይማኖቶች ተከታዮች መሃከል ለዘለቀው አብሮነት፣ መሰረት መሆኑ ጎልቶ ታይቶኝ ስላሳሳኝ አንድ ነገር ሳልል ላለማለፍ ያህል ነው። በሮመዳን የጾም ወር የሚታዩት የሞራል እሴቶች በዚህ የጾም ወር ጎልተው ይታዩ እንጂ የዘውትር የኑሮ ዘይቤ ውስጥም ይገለጻሉ። እናም እነዚህን እሴቶች ጠብቆ ለተተኪ ትውልድ ማወረስና የሁሉም ኢትዮጵያውያየን የዘውትር የኖሮ ዘይቤ እንዲሆኑ ማድረግ መቻል እጅግ እድለኝነት ሆኖ ይታየኛል።

በአጠቃላይ፣ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች እንዲሁም የሌሎች ሃይማኖቶች ተከታዮች ለዘመናት የኑሮ ዘይቤያቸው የሆነውን ከሃይማኖት ልዩነት በላይ የሆነ ዝምድና በመጣበት አኳኋን እንዲዘልቅ ማደረግ ይኖርባቸዋል። ይህ ከሃይማኖታዊ ልዩነት በላይ ያለ አንድነት እንደሃገር እዚህ ያደረሰን መሆኑን አዲሱ ትውልድ ሊገነዘብ ይገባል። ሊጠብቀውም ይገባል። ለማንኛውም ለኢትዮጵያውያን ሙስሊም ወገኖቼ ሁሉ ኢድ ሙባረክ አያልኩ ከልዩነታችን በላይ ያለውን ኢትዮጵያዊ ዝምድናችንን ይዘን እንድንዘልቅ እመኛለሁ። ስንወደድና ስንከባበር ያምርብናልና።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy