Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስኬቶቹና ችግሮቹ

0 305

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስኬቶቹና ችግሮቹ

                                                        ይሁን ታፈረ

በማንኛውም ተግባር ውስጥ ስኬትና ተግዳሮት የማይነጣጠሉ ጉዳዩች ናቸው። እነዚህ ሁነቶች በግለሰብ፣ በቡድን ወይም በአገር ክንዋኔዎች ውስጥ መንጸባረቃቸው አይቀርም። ከዚህ አኳያ ፌዴራላዊ ሥርዓታችን በርካታ ስኬቶች እንዳሉት ሁሉ፤ ተግዳሮቶችም መኖራቸው አይቀርም። ላለፉት ጊዜያት አገራችን ባለፈችባቸው መንገዶች ውጤታማ ተግባራት የመከናወናቸውን ያህል ተግዳሮቶች ቢኖሩም፤ ወደፊት ያሉት ጊዜያተ ግን የተስፋ ነጸብራቆቻቸን ናቸው።

በፌዴራላዊ ሥርዓታችን ውስጥ በአብዛኞቹ ጉዳዩች አገራዊ መግባባት የተፈጠረባቸው ቢሆኑም ቅሉ፤ በአንዳንዶቹ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አሁንም ያልጠሩ እይታዎች መኖራቸው ግልፅ ነው። እነዚህን ያልጠሩ ጉዳዩች አዲሱ አመራር ጠንክሮ በመስራት ላይ ስለሆነ ይበልጥ በማጥራት የአገራችንን ተስፋና መጻዒ ዕድል ብሩህ ያደርገዋል። ይህም አገራችን እድለኛ መሆኗን የሚያመላክት ነው።

የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ሕዝቦች ገና ከጅምሩ ይዘዋቸው የተነሱትን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ህልሞቻቸውን አውን እንዲያደርጉ አስችሏል። በእነዚህ ዓመታት ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት የስልጣን ክፍፍል የተደረገ ቢሆንም፤ ከአፈፃፀም አኳያ የሚታዩ ችግሮች አሁንም ድረስ አልተፈቱም።

ኢትዮጵያ የምትከተለው ሥርዓት ሰላምን እንጂ ግጭትን የሚያነግስ ባለመሆኑ ባለፉት ዓመታት የበርካታ ድሎች ባለቤት መሆን ችለናል። ኢትዮጵያ ላለፉት 27 ዓመታት በሠላም፣ በልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ከፍተኛ እመርታ ማስመዝገቧ አያከራክርም። ለዚህም የምትመራበት የፖለቲካ መስመር ትክክለኛ በመሆኑ ይመስለኛል።

በህገ መንግሥቱ ውስጥ የሰፈሩት ህገ መንግሥታዊ የዴሞክራሲና የልማት ድንጋጌዎች ጭምር እንደሆነም ይታመናል። በቅድሚያ ህገ መንግሥቱ በሰፊው የሕዝብ ተሳትፎ የተዘጋጀ ነው፤ በህገ መንግሥቱ ውስጥ የሰፈሩት ድንጋጌዎችም አገራዊ መግባባት እንዲመጣ ጉልህ ሚና ነበረው።  

በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሥር እየሰደደ እንዲሄድ ብሎም አገሪቱ ፈጣን ወደሆነ የልማት ጐዳና እንድትገባ ለዴሞክራሲና ልማት ድንጋጌዎች ተግባራዊነት ቁርጠኛ መንግሥት መኖር ውጤቱን አፋጥኖታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ለህዝብ ይፋ ሆኖ ወደ ተግባር የተገባበት ሁለተኛው የዕድገት ዕቅድ ዋናው ማጠንጠኛ ግብርና ልማታችንን ማዘመን፣ ኢንዱስትሪያላዜሽን፣ ትራንስፎርሜሽንንና የኤክስፖርት ልማትን ማረጋገጥ ነው፡፡ የሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በዋነኛነት አገራችን የመጀመሪያ ደረጃ መካከለኛ ገቢ ያላት ሀገር ዕውን የማድረግ ራዕይን መነሻ ያደረገ ነው፡፡

እርግጥ በመጀመሪያው የዕድገት ዕቅድ ወቅት የተረጋገጠው ዕድገት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በአገር ውስጥም ከአገር ውጭ ሰፊ ዕውቅና እና ተቀባይነት ያገኘ ነው፡፡ በመጀመሪያው ዕቅድ የተመዘገበው ፈጣን ዕድገት በሀገራችን ሕዝቦች ዘንድ ከፍተኛ መነሳሳት ከመፍጠር ባለፈ ምርትና መርታማነት እንዲያድጉ ያደረገ ነው፡፡ በዕድገቱም አርሶ አደሮች፣ የግሉ ዘርፍ እና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች በፍጥነት ማደግ እንደሚቻል አረጋግጠዋል፤ ለላቀ ዕድገት እንዲተጉም ከፍተኛ መነቃቃትን እየፈጠረም ነው፡፡  

በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጠንካራ የማስፈፀም አቅም ያላቸው መንግስታዊ መዋቅር የመፍጠር፣ ግልፅነትን የማስፈንና ሙስናን ከምንጩ የማድረቅ፣ የህዝብ ተሳትፎን የማረጋገጥ እና የባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮችን በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የማካተትና የመተግበር አቅጣጫዎች ተይዘው በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ የግልፅነትና የተጠያቂነት አሠራርን በማስፈን የኪራይ ሰብሳብሳቢነት አመለካከትና ተግባራትን ለመቀነስ በየደረጃው የሚደረጉ የሚደረጉ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ የህብረተሰብ ተሳትፎ የሚጠናከርበትና ከመንግስት ተቋማት ጋር ቋሚ ግንኙነት የሚፈጥርበት አሰራርም ተዘርግቷል፡፡

በተለይም የሀገራችን ህዳሴ እንቅፋት ይሆናል ተብሎ የሚታሰበውን ሙስናንና ኪራይ ሰብሳቢነትን አስተሳሰብና ድርጊት ከምንጩ ለማድረቅ ሲባል መንግስት የራሱን ከፍተኛ ባለስልጣናት ሳይቀር በህግ ፊት በማቅረብ ቁርጠኝነቱን አሳይቷል። በዚህም አስተማሪ በሆነ መንገድ ትምህርት ለመስጠት ተሞክሯል።

ምንም እንኳን የሙስና እና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር በአጭር ጊዜ በቁጥጥር ስር ሊውል የሚችል ባይሆንም፣ ድርጊቱን በሂደት የመቅረፍ ስራዎች ተከናውነዋል። ግና በቂ አይደሉም። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አዲሱ አመራር ሌብነትን የሚታገስበት ጫንቃ እንደሌለው ግልፅ አድርጓል።

ሙስና የማይታለፍ ቀይ መስመር ሆኑንም ግልጽ አድርጓል። ያም ሆኖ በሁለተኛው ልማት ዕቅድ ወቅት በዘርፉ ዙሪያ እየተከናወነ ያለው ተግባር በቀዳሚው የዕቅድ ዘመን የተካሄደውን ሁሉን አቀፍ ክንዋኔዎች የሚያጠናክርና አዳዲስ አሰራሮችን ተከትሎ እየተካሄደ ነው። አጋማሽ ግምገማው ላይም ደርሷል።

ባለፉት ዓመታት መልካም አስተዳዳርን ለማስፈን በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ህብረተሰቡን በተደራጀ መልኩ የማንቀሳቀስ ሥራዎች ተከናውነዋል። በተለይም በገጠሩ አካባቢ መልካም ውጤቶች ተገኝተዋል። እስሁን ድረስ የተከናወኑት ተግባራት ውጤታማ ቢሆኑም አሁንም ጠንካራ ስራ መከናወን ይኖርበታል። የልማት ዕቅዱ አፈፃፀም የታዩበት ጠንካራ ጎኖች ቢኖሩም፣ አሁንም ድረስ ችግሮች አሉ።

በከተሞች ውስጥ የበላይነት ያለው የኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካ ኢኮኖሚ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰቡ ዛሬም ስር የሰደደ መሆኑን ነው። እናም ልማታዊነትን ይበልጥ በማጐልበትና ሙስናን ከምንጩ ለማድረቅ ጥረት ማድረግ ይገባል። ይህን የዕቅዱን ትልም ዕውን ለማድረግ የፖለቲካ አመራሩና የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኛው ከህዝቡ ጋር በተደራጀ መንገድ በመቀናጀት መስራት ይገባቸዋል።

ለዚህ ደግሞ ‘ይህ ስራ የእገሌ ነው’ ሳይባል ሁሉም የበኩሉን ገንቢ ሚና ሊጫወት ይገባል። እርግጥ ሀገራችን አረጋግጠዋለሁ ብላ ለተነሳችው የህዳሴ ጉዞ ትልልቆቹ አደጋዎች ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት በመሆናቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ላሰመሩት ቀይ መስመር ሁሉም መረባረብ ይኖርበታል።

ማንኛውም የመንግስት ተቋም በአሰራሩና በአደረጃጀቱ የመሰረታዊ የአፈፃፀም ለውጥን ባልተሸራረፈ መልኩ በመከተልና የአገልግሎት አሰጣጡም ተገልጋዮችን የሚያረካ፣ ቀልጣፋና ተልዕኮውን በተሟላ ውጤታማነት መፈጸም እንዲችል አስፈላጊው ክትትልም ሆነ ድጋፍ ይደረጋል።

ዶክተር አብይ ማንኛውም የመንግስት ተቋም ከህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ጋር ውል ተፈራርሞ ስራውን እንደሚፈፅምና በየሶስት ወሩ እንደሚገመገም ያስቀመጡት አቅጣጫ ይህን የሚያመላክት ነው። ይህም በመንግስት ተቋም ውስጥ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን አስተማማኝ በሆነ መንገድ ለመፈፀም የሚያስችል ነው።

እኔ እንደምረዳው በዚህ የመንግስት ቁርጠኛ አሰራር በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ማጠናቀቂያ የህዝብ እርካታና አመኔታ ደረጃ አሁን ካለበት 60 በመቶ ወደ 85 በመቶ ለማድረስ የተያዘውን ግብ የሚያሳካ ይሆናል። እናም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን ቀይ መስመር ሁሉም ዜጋ ተረድቶ ሊደግፋቸው ይገባል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy