Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ቀጣናዊው ሚና

0 540

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ቀጣናዊው ሚና

                                 ገናናው በቀለ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ በኡጋንዳና በግብፅ ያደረጓቸው ጉብኝቶች የዲፕሎማሲያችንን ድሎች ከፍታ የጨመሩ ናቸው። ኡጋንዳ ሀገራችን በደቡብ ሱዳን ሰላም ጉዳይ የመሪነት ሚና ከመጫወት አኳያ ከኢትዮጵያ ጋር ለተወሰነ ጊዜ ፉክክር ውስጥ ገብታ እንደነበር ቢታወስም፣ በአሁኑ ወቅት አገራችን ከዑጋንዳ ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ትብብር እንድትፈጥር ያደረገ ጉብኝት ነው።

ኢትዮጵያና ኡጋንዳ በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ባደረጉት ውይይት፤ የሁለቱን አገራት የንግድና ፖለቲካ ግንኙነት ለማጠናከር ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ መጠን ማሳደግ እንደሚገባም ተወስኗል። አገራቱ ቅድሚያ በሚሰጣቸው እንደ ንግድ፣ ሃይል፣ ግብርና፣ ትራንስፖርት፣ ቱሪዝምና የባህል ዘርፎች በትብብር መስራት እንደሚኖርባቸውም ተወስቷል።

ከዚህ በተጨማሪ በሰሜን ኬንያ በኩል የሚያልፍና ሁለቱን ሃገራት የሚያስተሳስር የመንገድ ፕሮጀክት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል። የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮችን በተመለከተም የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል፤ዶክተር አብይና ሙሴቬኒ። በኢጋድ መሪነት የሚካሄደውን የደቡብ ሱዳን የሰላም ማሳለጫ ፎረምን በማጠናከር በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል።

እንዲሁም በደቡብ ሱዳን ላይ የሚመክር የኢጋድ አስቸኳይ ጉባኤ እንዲካሄድም ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ይህም የግንኙነቱን ከፍታ የሚያሳይ ነው። በጉብኝቱ ወቅት ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ለአፍሪካና ለኡጋንዳ መልካም ስራ ለሰሩ ሰዎች አገራቸው የምታበረክተውን ሜዳሊያ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሰጥተዋል። ይህም ዲፕሎማሲውን ምን ያህል ከፍ እንዳደረገው የሚያሳይ ይመስለኛል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት በኡጋንዳ ውስጥ ለረጅም ዓመታት የኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ወደ አገራቸው ተመልሰው በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲያለሙ የሚችሉበትን ሁኔታ ያመቻቸ ነው። በኡጋንዳ የሚገኙት የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላትም በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ተስፋ የሰጣቸውና ይህም ወደ አገራቸው ተመልሰው በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሳተፍ ፍላጎት እንደፈጠረባቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነግረዋቸዋል።

በአገሪቷ ውስጥ ባለ ሃብቱን የማያሰሩ ህጎች መቀየርና ውስብስብ ቢሮክራሲያዊ አሰራሮች መፈታት እንደሚኖርባቸው የገለጹት ኢትዮጵያዊያኑ፣ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች እንዳያጋጥሟቸው ከወዲሁ መሰራት አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል። ይህ የኢትዮጵያኑ አስተያየት ተገቢ ሲሆን አሁን እየተከናነ ባለው የለውጥ ሂደት ችግሮች መፈታታቸው ስለማይቀር ወደ አገራቸው ገብተው ቢሰሩ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።

ይህም መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው ገብተው ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት የሚያጠናክር ነው። በመሆኑም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኡጋንዳ ጉብኝት ከአገሪቱ ጋር ብቻ ሳይሆን በዚያች አገር ከሚገኙና ለአገራቸው ዕድገት አስተዋጽኦ ማድረግ ለሚችሉ ኢትዮጵያዊያንም የተመቻቸ ሁኔታ እንዲፈጠር ያደረገ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በግብፅ ያደረጉት ጉብኝትም በኢትዮጵያ ላይ ዘመናትን የተሸጋገረ ጥርጣሬ ካላት ካይሮ ጋር መተማመንና የአገራችንን ጥቅም ያስከበረ ትብብርን መፍጠር ችሏል። በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ዘንድ ከፍተኛ ተሰሚነት ካላት እንዲሁም አረባዊና አፍሪካዊ ቅርፅ ካለት ግብፅ ጋር መልካም ጉርብትናን እና ትብብርን የሚያጠናክር ግንኙነት በመፍጠር ላይ ያለመው የዶክተር አብይ ጉብኝት፤ ለአገራችን ብሎም ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላምና ልማት ወሳኝ ሚና የሚጫወት ነው።

በጉብኝቱም ሁለቱ አገራቱ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሁለቱን አገራት የመልማት ፍላጎት ባከበረ መልኩ በአዲስ መንፈስ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል። አገራቱ በተለያዩ መስኮች በተለይም በፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ያላቸውን ትብብር ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል። ኢትዮጵያና ግብፅ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በማጠናከር በጋራ መስራት የሚኖርባቸው ሲሆን በወንድማማችነት መንፈስ በሃይል ዘርፍ መሰረተ ልማቶችን በጋራ ለማልማት እንደሚሰሩም ገልፀዋል።

ጉብኝቱ ከዚህ በፊት የነበረውን የጥርጣሬ መንፈስ ያስወገደና በትብብር መንፈስ በተቃኘ ስትራቴጂክ አጋርነት ለመስራት ያስቻ ነው። አገራቱ በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ባደረጉት ውይይት በደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት በትብብር ለመስራት ተስማምተቃል። ይህም ኢትዮጵያ በቀጠናው ላይ ያላትን የመሪነት ሚና በግልፅ የሚያመላክት ነው።

ኢትዮጵያና ግብፅ ቀደም ባሉት ጊዜያት አንዱ ሌላውን ባለማመን ላይ የተመሰረተው ግንኙነታቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ዘመን መቀየሩን የግብፅ ሚዲያዎች ሳይቀሩ ዶክተር አብይን በማድነቅ ዘግበዋል። ይህ ሁኔታ ዶክተር አብይ ከፕሬዚዳንት አል ሲሲ ጋር ያደረጉት ውይይት የአገሪቱን ሚዲያና ህዝብ አመለካከት የቀየረ መሆኑን የሚያስረዳ ነው።

የዶክተር አብይ የግብፅ ጉብኝት ዲፕሎማሲን ብቻ ሳይሆን የዜግነት ክብራችንንም ከፍ ያደረገ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ጋር ተነጋግረው በደረሱት ስምምነት መሰረት በተያዩ ምክንያቶች ታስረው የነበሩት 32 እስረኞች እንዲለቀቁ አድርገዋል።

እነዚህ ኢትዮጵያንም ከእርሳቸው ጋር በአንድ አውሮፕላን ወደ አገር ቤት እንዲገቡ አድርገዋል። የፖለቲካው ምህዳር በመስፋቱ ምክንያት የቀድሞው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አባል የሆኑት አቶ ዮናታን ዲቢሳና የመከላከያ ሰራዊት አባል የነበሩት ኮለኔል አበበ ገረሱ በሰላማዊ ትግል ለመታገል አብረዋቸው ወደ አገራቸው መጥተዋል።

እንዲሁም ቀደም ሲል ራሱን አይኤስ (IS) እያለ በሚጠራው የሽብር ቡድን በሊቢያ የባህር ዳርቻ የተገደሉ ኢትዮጵያውያን አስከሬንን ለማግኘት በሚደረገው ጥረት ግብፅ እገዛ እንደምታደግር ፕሬዚዳንት አል ሲሲ ቃል መግባታቸው ዶክተር አብይ በቁም ለሚገኙ ዜጋቸው ቀርቶ ለሞቱትም ምን ያህል እንደሚቆረቆሩ የሚያሳይ ይመስለኛል።

በጥቅሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኡጋንዳና በግብፅ ያደረጓቸው ጉብኝቶች አገራዊ ጥቅምን ያስጠበቁና መተማመንን የፈጠሩ ከመሆናቸውም በላይ፤ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ያላትን የመሪነት ቦታም ያሳዩ እንዲሁም ያላትን ሚናም ያጎሉ ናቸው። ዲፕሎማሲው ከፍታውን እንዲጨምርና በቀጠና ውስጥ ተሰሚነታችን እንዲያድግ ያደረጉም ናቸው።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy