Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ቁርጠኝነቱ…

0 285

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ቁርጠኝነቱ…

                                                      ይሁን ታፈረ

በአሁኑ ሰዓት ቀደም ባሉት ጊዜያት በጽንፈኝነት የተፈረጁ እንደ የሚዲያ አውታሮች ከውጭ ደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ጥረት እየተደረገ ነው። ይህ ሁኔታ በግሌ ነፃ መውጣታቸውን የሚያመላክት ነው። እርግጥ አሁን ባለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን ከአንድ ወገን ብቻ በሚንቆረቆር የመረጃ ፍሰት የሚረካ ህዝብ የለም። የሚፈጠሩ ሁነቶችን በሚዛናዊነት ማቅረብ ትክክለኛ እርምጃም ነው።

እንደ ኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክና ኢሳት የመሳሰሉ ሚዲያዎች አገራችን ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ መፈቀዱ በራሱ እውነተኛው የፖለቲካ ምህዳር መስፋት እየመጣ መሆኑን አመላካች ነው። እንዲሁም በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ “ኢህአዴግ ፖለቲካዊ ሥራውን መስራት አቅቶት በራሱ ስንፍና የወደቀ እንደሆነ፣ መከላከያ ሠራዊቱ ህዝብ ከመረጠው ፓርቲ ጋር መቀጠል የሚችል ሠራዊት መሆን አለበት” ሲሉ የተናገሩትም ሌላኛው የፖለቲካ  ምህዳሩ መስፋት ማሳያ ነው።

ሌላውን ትተን እነዚህ ሁለት ጉዳዩች ብቻ መንግሥት በፖለቲካው ምህዳር ውስጥ ማናቸውም ሃሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ እንዲሁም ሰራዊቱም በገለልተኛነት ተግባሩን እንዲወጣ ያለውን ቁርጠኝነት ናቸው። ታዲያ እነዚህን ሁለት ጉዳዩች በዚህ ፅሁፍ ላይ ትንሽ ሰፋ አድርጌ ለመመለከት እሞክራለሁ።

ሚዲያ አራተኛው የመንሥት አካል (The fourth Estate) ተደርጎ ይወሰዳል። ዛሬ በእኛ ሀገር ውስጥ የሚዲያ ተግባር ወሳኝ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለህዝብ በሚጠቅሙ ጉዳዩች ላይ በማተኮር ሃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል። የህዝቦችን ግጭት የማያባብስ፣ በምርመራ ጋዜጠኝነት (Investigative Journalism) አሰራር የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚችል መሆን ይኖርበታል።

የማስተማር፣ የማሳወቅና የማዝናናት ሚናን ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው ሚዲያ፤ የመልካም አስተዳደርን ምንነት ከማስተማር ባሻገር፣ በሀገራችን ውስጥ በጉዳዩ ዙሪያ የሚከሰቱ ችግሮችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ በማሳየትና ችግሮቹን በማረም ረገድ የሚኖረው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ሚዲያ አግባብ ባልሆነና ከራሱ ስነ ምግባር ባፈነገጠ መንገድ ጥቅም ላይ ከዋለ የሚያስከትለውን ችግር ያህል፤ በአግባቡና ስነ ምግባሮቹን ጠብቆ ከሰራ የሚያበረክተው ማህበራዊ ኃላፊነት ከፍተኛ ነው።

በተለይ የሚዲያ ሙያ እምብዛም ባልዳበረባቸው እንደ እኛ ባሉ ሀገራት ውስጥ ሚዲያ የህብረተሰቡን መሰረታዊ ፍላጎት ተመርኩዞ ሚዛናዊና ትክክለኛ ዘገባዎችን ከሰራና ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ህብረተሰቡና መንግስት ተገቢውን ውሳኔ እንዲወስዱ ማድረግ ከቻለ የሚጠበቅበትን ተግባር በበቂ ሁኔታ ሊወጣ ይችላል። በመሆኑም እንደ መልካም አስተዳደር ዓይነት ተግባሮችን የማስተማርና የማሳወቅ ብሎም ከህብረተሰቡ የሚነሱ ችግሮችን በመመርኮዝ በምርመራ ጋዜጠኝነት በማረጋገጥ ህዝባዊ ተግባሩን ይወጣል።

ሚዲያው በቅድሚያ በግርድፉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመንቀስ በፊት በጉዳዩ ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ እንዲያዝ ማስተማርና ማሳወቅ ይኖርበታል። ይህም በተለያዩ ወገኖች መካከል በጉዳዩ ዙሪያ ያለውን የተለያየ አስተሳሰብ በተቻለ መጠን ወደ አንድ ለማምጣትና አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ያግዛል።

ያም ሆኖ ግን የፖለቲካ ምህዳሩን መስፋት በመጠቀም ህዝቦችን ለማጋጨትና ማህበራዊ መስተጋብራቸውን ብሎም እሴቶቻቸውን ለመናድ ተግባር መዋል የለበትም። ከዚህ ይልቅ ተግባሩን ህዝቦችን በማቀራረብና በአንድነት ሀገራቸውን ለማልማት የሚያደርጉትን ጥረት ማገዝ ይኖርበታል። እነ ኦኤምኤንና ኢሳት እዚህ ሀገር ውስጥ ገብተውና ትክክለኛ መረጃ አግኝተው እንዲሰሩ መፈቀዱ ከፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ባሻገር፣ ተግባራቸውን አገርን ለመገንባት ሊጠቀሙበት ይገባል። እናም በውጭ የሚገኙ ሚዲያዎች አገር ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ መደረጉ የአገርንና የህዝበን ጥቅም ያማከለ በመሆኑ ተገቢነቱ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም።

የመከላከያ ሰራዊታችንም ተግባሩን በህገ መንግስቱ መሰረት በመከወን በህዝብ ብልጫ የፓርቲዎች መለወጥ ቢፈጠርም ተግባሩ አገርን ማዕከል አድርጎ እንዲሰራ ያስችለዋል። ይህም የፖለቲካ ምህዳሩ ይበልጥ እንዲሰፋና ሰራዊታችንም በፓርቲዎች መለዋወጥ እንዳይቀያየርና የኢትዮጵያና የህዝቦቿ ሰራዊት ብቻ እንዲሆን የሚያደርገው ነው።

የአንድ ሀገር መከላከያ ሠራዊት የሚቋቋመው ሀገሪቱን ሉዓላዊ አንድነት ከወራሪዎች ለመከላከል እንዲሁም የተቋቋመበትን ህገ-መንግስታዊ ስርዓት ከማንኛውም አደጋ ለመጠበቅ በመሆኑ ተግባሩን በዚህ ላይ እንዲከውን ያስችለዋል።

ሰራዊታችን ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን ከማንኛውም የውስጥና የውጭ ፀረ-ሰላም ኃይሎችና አሸባሪዎች የመከላከል ተልዕኮን ያነገበ ነው። በሀገሮች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በሠላማዊና በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ እገዛ ማድረግም የተልዕኮው አካል መሆኑ ይታወቃል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት እንደ አንድ ሀገር ሰራዊት በተሰጠው ተልዕኮ መሰረት የሚያከናውናቸው ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው፤ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሰላምና ለልማት መሆኑ ግንዘቤ ሊያዝ የሚገባ ይመስለኛል።

የህዝብና የአገር ጠባቂ የሆነ ሰራዊት ህገ -መንግስታዊ ሥርዓቱን ከማናቸውም የውስጥና የውጭ ፀረ ሰላም ኃይሎችና አሸባሪዎች እንዲከላከል የሚያደርገው ነው። በከፋ ኋላ ቀርነትና በድህነት አረንቋ ውስጥ ጠልቃ ለኖረችው ኢትዮጵያ ሰላምና ልማት የህልውናዋ ጉዳይ ነው። ይህን ህውናዋን ለማረጋገጥ ሰራዊቱ የአገርን ዳር ድንበር በማስከበር የተሰጠውን ተልዕኮ ይወጣል። ሰራዊቱ ራሱን በፕሮፌሽናሊዝም የማጠናከርና በአፍሪካ የምድርና አየር ኃይል ቀዳሚነቱን ይበልጥ የማስፋት እንዲሁም በባህር ኃይል በኩል እንደ አዲስ እመርታን ለማስመዝገብ መጣር አለበት።

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት እንደ ደነገገው ሰራዊታችን ተግባሩን ከማንኛውም ፖለቲካዊ ወገንተኝነት ነፃ በሆነ አኳያ ይከውናል። ይህም በፕሮፌሽናልነት ሙያውን እብዲያሳድግና ተግባሩን እንዲወጣ የሚያደርገው ነው። እንዲህ ዓይነት ሰራዊት የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲዎች መቀያየር በአገራችን ውስጥ ቢከሰት አብሮ እንዲቀጥል የሚያደርገው ነው። ዶክተር አብይ እንዳሉት ሰራዊቱ ህዝብ ከመረጠው ጋር አብሮ የሚሰራ (adaptable) ይሆናል ማለት ነው።  

ከላይ ከሚዲያ ነፃነት ጋር በተያያዘ በውጭ የሚገኙ ሚዲያዎች ወደ አገር ቤት ገብተው እንዲሰሩ መጋበዛቸው እንዲሁም መከላከያ ሰራዊታችን የትኛውም ዓይነት ፓርቲ በህዝብ ቢመረጥ በተግባሩ ላይ አተኩሮ አብሮ መስራት እንደሚኖርበት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ መገለፁ፤ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር መንግስት ምን ያህል ቁርጠኛ አቋም እንደያዘ የሚያመላክት ነው። ለዚህ ቁርጠኝነት ህዝቡና የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል።    

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy