Artcles

በሁሉም የሚወደድ…

By Admin

June 30, 2018

በሁሉም የሚወደድ…

                                                    ሶሪ ገመዳ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብይ አህመድ የሚያከናውኑት ማናቸውም ተግባር ድርጅታቸው በተሃድሶው ወቅት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በመከናወን ላይ የሚገኝ ነው። ዶክተር አብይ እያከናወኑ ያሉት የራሳቸውን ፍላጎት ሳይሆን የድርጅታቸው ኢህአዴግን አሰራር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ ህዝብ አብራክ የተገኙ ኢህአዴግ ያፈራቸው የድርጅቱ ውጤት ናቸው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የእስከ ዛሬ ክንዋኔዎች፣ ኢህአዴግ ለእውነተኛ ለውጥ መሰለፉን እንዲሁም ይህን አቋሙን በሊቀመንበሩ በኩል በተግባር አያሳየ እንደሆነ የሚያረጋግጥ ነው። ህዝቡም ከዶ/ር አብይና ከድርጅታቸው ጎን የቆመው በአጭር ጊዜ ውስጥ እውነተኛና ተጨባጭ ለውጦችን ማምጣት ስለቻሉ ነው።   

እርሳቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ጨምሮ በሁሉም የህብረተሰቡ ክፍል የተወደዱና የተመሰገኑ ለመሆን ያበቃቸው ለለውጥ ያላቸው ጠንካራ ፍላጎትና በተጨባጭ ያመጧቸው በገሃድ ስለሚታዩ ነው። ዛሬ ዶክተር አብይን የማያመሰግን ተቃዋሚ፣ ቀድሞ ጽንፈኛ ተብለው የተሰየመ የዳያስፖራ አባል እንዲሁም ሚዲያ የለም። የትክክለኛ ተግባር ምላሹ ውዴታና ምስጋና በመሆኑ ዶክተር አብይ ዛሬ በሁሉም የሚወደዱ አድርጓቸዋል። እነዲያውም እነዚህ አካላት ራሳቸው የለውጡ አካል በመሆን ከጎናቸው ሊሰለፉ ችለዋል።

ቀደም ሲል በትጥቅ ትግል ላይ የተሰማሩ አካላት ሳይቀሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ አክብረው ወደ አገር ቤት መመለሳቸው ዶክተር አብይ እያካሄዱት ያለው ለውጥ የእውነትና በተጨባጭ የሚታይ መሆናቸውን ስላመኑ ነው። ይህም ዶክተር አብይ በድርጅታቸውም ይሁን በተፎካካሪዎች ሳይቀር ክብርና ውዴታን እንዲያገኙ አድርጓቸዋል።

እርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ተፈጥሮ ባደላቸው ብሩህ አዕምሮ በጥቂት ጊዜ ውስጥ በአገራቸው ያመጡትን ለውጥ፤ በቀጣናው ብሎም በአፍሪካ ሊከውኑት እንደሚችሉ ሁሉም ተገንዝቦታል። አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ የአፍሪካን ችግር ለመቅረፍ ወሳኙ ጉዳይ፤ መፍትሔውን በማመንጨት ህዝቡን ወደ አንድነት በማምጣት ለለውጥ በቁርጠኝነት ሰርቶ የሚያሰራ መሪን ማግኘት መሆኑን ሁሉም የአገራችን ህዝብ ይገነዘባል።

ዶክተር አብይ ህዝባቸውንና ሀገራቸውን እንደሚወዱ በተግባር ያረጋገጡ መሪ በመሆናቸው ደጋፊም ይሁን ተፎካካሪ እንዲወደዱ አድርጓቸዋል። በሀገር ውስጥ ህዝባቸው ከነበረበት የቀውስ አዙሪት ውስጥ እንዲወጣ፤ የፍቅር፣ የእርቅና የሰላም እንዲሁም የመደመር ተግባሮችን በመፈፀም አንፃራዊ ሰላምን ማምጣት የቻሉ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትራችን በጥቂት ወራቶች ውስጥ ብቻ ለህዝብ ያላቸውን ፍቅር ተግባር ማሳየት ችለዋል። ሌላው ቀርቶ የለውጡ ደንቃራዎች ጧት መስቀል አደባባይ ቦንብ አፈንድተው በህዝቡ ላይ ጉዳት ሲያደርሱ እርሳቸው ወዲያውኑ ከሰዓት ሆስፒታል ተገኝተው ተጎጂዎችን አበረታትተዋል።

በሀገር ውስጥ የህዝቡን ጥያቄዎች ሊመልሱ የሚችሉ ጉዳዩችን አንስተው ከህብረተሰቡ ጋር ፊት ለፊት በመወያየት ለውጥን ሊያመጡ የሚችሉ ምላሾችን ሰጥተዋል። ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ፤ የታመመን በመጠየቅና በማበረታታት ተግባራቸው ምን ያህል ለህዝብ አሳቢ መሆናቸውን በተግባር አስመስክረዋል። በመሆኑም እንዲህ ዓይነት መሪ በሁሉም እኩል ቢወደድ ምንም ዓይነት ግርምታን አይፈጥርም። ምክንያቱም ለህዝብ የቆመ መሪ ወሮታውን የሚያገኘው ከማንም ሳይሆን ከህዝብ ስለሆነ ነው።  

ጠቅላይ ሚኒስትራችን ለጉብኝት በሄዱባቸው ሀገራት ሁሉ የዜጎችን ጉዳይ ቅድሚያ በመስጠት ከእስርና ከእንግልት የታደጉ ህዝብ አፍቃሪ መሪነታቸውን አስመስክረዋል። በጂቡቲ፣ በሱዳን፣ በኬንያ፣ በሳዑዲ አረቢያ፣ በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች፣ በኡጋንዳና በግብፅ ባካሄዷቸው ጉብኝቶች የዜጎቻችንን ክብር አስመልሰዋል።

ዶክተር አብይ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሰላም እንዲጠበቅ ከጎረቤቶቻቸው ጋር በሰላም ውስጥ በእኩል ተጠቃሚነት ተሳስሮ ለማደግ ሰፋፊ ስምምነቶችን የተፈራረሙ ናቸው። ለሰላም ካላቸው ልባዊ ቁርጠኝነት ተነስተውም ላለፉት 16 ዓመታት በኢትዮ ኤርትራ መካከል የነበረው የውጥረት ሁኔታ እንዲያበቃ ረጅም ርቀት ተጉዘው የሰላም እጃቸውን ዘርግተዋል። ውጤት ማምጣትም ችለዋል።

ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ሁሉ የከወኑትና የሚከውኑት ለህዝባቸውና ለሀገራቸው ካላቸው ፍቅር በመነጨ ነው። ህዝብን ያለ አንዳች አድልኦ የሚያፈቅር መሪ በሁሉም ዘንድ ተወዳጅና ተመስጋኝ መሆኑ የሚቀር አይደለም።     

ዶክተር አብይ የመፍተሔ ሰው ናቸው። አገራችን በሁከት በምትታመስበት ወቅት እርሳቸው መፍትሔውን ለማምጣት ምን ማድረግ እንደሚገባ ‘ከኦቦ ለማ ቲም’ ጋር ሲመክሩ ነበር። ምክክራቸውም አገራችን በአሁኑ ወቅት ያገኘችውን ምቹ አጋጣሚ በለውጥ ሂደት ውስጥ በማስገባት አንዣቦብን የነበረውን የስጋት ደመና መግፈፍ ችለዋል። እንዲህ ዓይነት መሪ በወዳጅም ይሁን በጠላት የሚወደድና የሚወደስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሔ በማበጀት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አንፃራዊ ሰላምና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንድንሻገር አድርገዋል። የእርሳቸው ብስለትና የመፍትሔ አባትነት ወደፊትም ለአህጉሪቱ መስራት የሚያስችላቸው እምቅ አቅም ባለቤት እንደሆኑ የሚያረጋግጥ ይመስለኛል። እንዲህ ዓይነት መሪ አገር ስታፈራ የማይወድና የማይደሰት ይኖራል ብዬ አላስብም።

ዶክተር አብይ በአገራችን አንፃራዊ ሰላምን የማምጣት፣ የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት እንዲሀም ህዝቡ ሙሉ በሙሉ ወደ ልማት በማተኮር ዕድገቱን እንዲያሳልጥ የማድረግ መንገዶችን በይቅርታ፣ በምህረትና በፍቅር እያሳዩን ነው። በውጭ አገር ነፍጥ አንግበው ሰነቀሳቀሱ የነበሩ ሃይሎች ሳይቀሩ ዶክተር አብይን በአንድ ቃል ያመሰግኗቸዋል።

ይህ የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያካሄዱ ባሉት ለውጥ እውነተኛነትና ትክክለኛነት ሃይሎቹ ስለሚያምኑ ነው። የዚህ ማረጋገጫ ደግሞ ባለፉት ጊዜያት በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩት ኦነግ፣ ግንቦት ሰባትና ኦብነግ ከሽርብ መዘገብ እንዲፋቁ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰሞኑን መወሰኑ ይመስለኛል።

ዶክተር አብይንና ድርጅታቸውን ለይቶ መመልከት አይቻልም። የእርሳቸው ተግባር የድርጅታቸው ፍላጎት ነውና። ጠቅላይ ሚኒስትሩና ድርጅታቸው ህዝቡ በተሻለ ህይወት ውስጥ እንዲያልፍና በአገራችን እየተከናወነ ያለው የልማት ስራ ወደ ታች ወርዶ ህዝቡን ምን ያክል ጠቅሟል? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ፣ በቅድሚያ እንቅፋቶችን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ ከድርጅታቸው ጋር መምከራቸው የዚህ ሃቅ አስረጅ ነው። በተጨማሪም የአገራችንን ዕድገት ከፍታ ለመጨመር ከፊት ለፊት የተደቀነውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትሩና ድርጅታቸው በመንግስት እጅ የነበሩት የልማት ድርጅቶች በከፊልና ሙሉ ለሙሉ ወደ ግል ይዞታ እንዲዞሩ መወሰናቸው እውነታውን የሚያሳይ ነው። እንዲህ ያለ በሁሉም ወዳጅም ይሁን ተፎካካሪ ወገን የሚወደድ መሪ ማግኘታችን ትንሳኤያችን ቅርብ መሆኑን የሚያረጋግጥ ይመስለኛል።