Artcles

በቀል ውድቀትን እንጂ …

By Admin

June 18, 2018

በቀል ውድቀትን እንጂ …

 

አባ መላኩ

 

በበቀል  አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ አይኖርም። ለየትኛውም አካል ቢሆን የበቀልና የእልህ መንገድ መዳረሻው እልቂትና  ወድቀት መሆኑን ከሌሎች ልንማር ይገባል። ዛሬ ላይ በአንዳንድ አካባቢዎች እየተመለከትናቸው ያለው አካሄድ ለአገራችንም ሆነ ለህዝባችን የሚበጅ አይደለም።  በቀል መለያየትን፣ በቀል እልቂትን፣ በቀል ውድቀትን እንጂ በቀል ስኬትን፣ በቀል አንድነትን፣ በቀል መደመርን አያመጣም። በቀል ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን የሞራልም ውድቀት ጭምር  ማሳያ ነው። አንዳንድ ተማርንና አክቲቪስት ነን ባዮች በየሚዲያው በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ የሚያደረጉት ሃላፊነት የጎደለው አካሄድ ቀውሶች እንዲበርዱ ከማድረግ ይልቅ ህዝቦች እርስ በርሳቸው  እንዲጠራጠሩና ወደ ግጭት እንዲያመሩ በማድረግ ላይ ናቸው።

 

በቀል ቁስልን አያደርቅም። አንዳንድ ወጣቶች በተለይ አክቲቪስት ነን ባዮች  በስሜት ነጉደው ትንሹንም ትልቁንም ነገር ከእነርሱ ብሄር፣ ሃይማኖትና የፖለቲካ  ቡድን ጋር በማገናኘት የተለያየ ትርጉም በመስጠት ላይ ናቸው።። እነዚህ ሃይሎች  የወጣቱን ጊዜያዊ ችግሮች መጠቀሚያ በማድረግ ወጣቱን ለመጠቀም በመሯሯጥ ላይ ናቸው። አገራችን  በነውጥና ሁከት ውስጥ የቆየች ከመሆኗ ባሻገር ባለፉት ጥቂት ወራት አረፍ ማለት መጀመሯ ነው። ይሁንና አንዳንድ ሃይሎች ይህን አንጻራዊ ሰላም  ለማናጋት በመሯሯጥ ላይ ናቸው። በመሆኑም በዚህ ወቅት ወጣቱ ረጋ ብሎ ማሰብ፤ ቆም ብሎ አካባቢን መቃኘት፤ አባቶች የሚሉትን ማድመጥ የሚበጅበት ወቅት ነው። በምንም መስፈርት  ችግር በችግር አይፈታም። ነውጥና ሁከት ለችግር ዘላቂ መፍትሄ ይዘው አይመጡም። በሁከትና ነውጥ የሚመጣ ለውጥም በተቃራኒው አቅጣጫ ይሆንና መዘዙ የከፋ እንደሚሆን ከሌሎች አገራት ተሞክሮ ልንማር ይገባል።  

አሁን ላይ  የምናስተውላቸው ነገሮች ከነችግሮቻቸውም ቢሆኑ አገራችን  በለውጥ ምህዋር ውስጥ መሆኗን የሚያሳይ ነው። ይህ መልካም ጅምር ቀጣይነት የሚኖረው  ሁላችንም በመደጋገፍ መስራት ስንችልና ባለን ላይ በመደመር ብቻ ነው። የአገራችን ህገመንግስት ከሰማይ በታች ማንም የፈለገውን ነገር መጠየቅ የሚያስችል መብት   አጎናጽፎናል። እንኳን የማንነት መብት ይከበርልኝ፣ እንኳን ልዩ ወረዳ ወይም ልዩ ዞን ወይም ክልል ልሁን ይቅርና መገንጠል እፈልጋለሁ የሚል አካል ካለ እንኳን ህጋዊ መስመሩን ተከትሎ  ጥያቄውን ማቅረብ የሚችልበት ሁኔታ ተመቻችቷል። ህብረተሰቡ ላቀረቧቸው ጥያቄዎች መንግስት ለሁሉም ተገቢውን ምላሽ እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል። የሚነሱ ጥያቄዎች በሙሉ ትክክል ናቸው ማለትም አይደለም። “ይሆናል”  ወይም “አይሆንም” በራሱ መልስ በመሆኑ መንግስትም ህዝብ ላነሳቸው ጥያቄዎች በወቅቱ ምላሽ መስጠት ይኖርበታል።

 

ህብረተሰቡ  ያለውን ጥያቄ  ለሚመለከተው አካል  ሰላማዊ በሆነ መንገድ   በማቅረብ መፍትሄ መሻት ይኖርበታል  እንጂ በሁከትና ነውጥ ለችግሮች መፍትሄ መፈለግ ለአገርና ህዝብ የሚበጅ አካሄድ  አይደለም። አሁን ላይ በአገራችን በመነጋገር ለችግሮች መፍትሄ ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ ተመቻችቷል። በመሆኑም ችግሮችን በሁከትና ብጥብጥ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በሰከነና በሰለጠነ መንገድ መፍትሄ መፈለግ  የመጀመሪያም የመጨረሻም አማራጭ ሊሆን ይገባል። አገራችን የጀመረችውን ዘርፈ በዙ ለውጥ ማስቀጠል የአገር ወዳድ ዜጋ ሁሉ ግዴታ መሆን መቻል ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ ግን ትላንት የወጣንበትን ሁከትና ነውጥ ተመልሰን የማንገባበት ምንም ምክንያት

 

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የተረጋጋ ፖለቲካና ፈጣንና  ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ከቻሉ ጥቂት አገራት መካከል በቀዳሚነት የምትጠቀስ አገር ናት።  ከዚህም ባሻገር አገራችን በአፍሪካ ጠንካራ የመከላከያ ሃይል ያላት አገር በመሆኗ ለቀንዱ አካባቢ ሰላም ለመረጋገጥ  ትልቁን ድርሻ በማበርከት ላይ ናች። የእኛ መጠንከር ወይም መድከም በአፍሪካ በተለይ በቀንዱ አካባቢ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ቀጥተኛ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው  የመጣንባቸው መንገዶች ያመላክታሉ። እኛ ወደ መናቆርና በቀል ፖለቲካ የምንጓዝ ከሆነ በዕርግጠኝነት ምስራቅ አፍሪካ ወደ ስርዓት አልበኝነት ማምራቱ አይቀርም። ለአገራችን ስኬቶች መሰረት የሆነው የፌዴራል  ስርዓታችን ነው። ይህ ስርዓት ውለው ላደሩ የአገራችን ችግሮች ዕልባት መስጠት ችሏል። ይህ ስርዓት ምንም ችግር የለበትም ባይባልም ከነእጥረቱም ቢሆን አገራችንን ወደተሻለ ደረጃ አሳድጓታል። ይሁንና አንዳንድ ሃይሎች ሆን ብለው ይህን የፌዴራል ስርዓት ወደ ሁከትና ስርዓት አልበኝነት ለማምራት የደባ ሴራቸውን በመተብተብ ላይ ናቸው።  

 

በአገሪቱ  የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን  ሁሉ የፌዴራል ሥርዓቱ እንከኖች አድርገው ለማቅረብና ይህ ስርዓት ለብጥብጥና ሁከት እንደዳረገን አድርገው ለማቅረብ  ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላሉ። ኢትዮጵያ በርካታ ልዩነቶች የሚንጸባረቅባት አገር ናት። አብሮ መኖር ያስቻለን ደግሞ ልዩነቶቻችንን ማስተናገድ የስቻለን  የፌዴራል ሥርዓታችን ነው። አንዳንዶች ደግሞ ለህዝብና አገር ተቆርቋሪ በመምሰል ትናንሽ ግጭቶችን በማጎን እከሌ የተባለው ብሄር ሊያጠቃህ ነው፤ ተነስ፣ ለወገኖችህ  ድረስላቸው ወዘተ በማለት በግጭቶች ላይ ቤንዚን ሲያርከፈክፉ ተመልክተናል፤ የሚሰጧቸውን መግለጫዎችም አድምጠናል። የሌለን ነገር እየፈጠሩ ወይም ትንንሽ ነገሮችን በማጎን  ህዝቦችን ለግጭት ማነሳሳት ይዋል ይደር እንጂ ከተጠያቂነት የሚያመልጡ አይሆኑም።

 

በአገራችን  ችግሮች አሉ። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርካታ ንጹሃን  ያለበደላቸው ጥቃት ደርሶባቸዋል። አሁንም አንዳንዶች ከዚሁ ጥቃተ አልዳኑም።  ይህ አሌ የማይባል ነው። ይሁንና ስህተትን በስህተት ለማረም መነሳት መፍትሄ ሳይሆን የበለጠ  ወደ አዘቅት የሚያመራ አካሄድ ነው። በአገራችን የተዘረጋውን ፌዴራላዊ ሥርዓት ህዝቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ  አንዳንዶች ዘንግተውት ሳይሆን ለፌዴራል ስርዓቱ ባላቸው በጥላቻ ላይ በመመስረት ብቻ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የፌዴራል ስርዓቱን  ሲያጣጥሉ ተመልክተናል። ይህን አይነት አካሄድ ደግሞ ለማንም የሚበጅ አይደለም። ግጭት የተፈጥሮ ሃብት እጥረት ባለባት ዓለማችን ውስጥ በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ሊከሰት የሚችል፣ ነገም ይሁን ከነገ ወዲያ ላለመከሰቱ አንዳችም ዋስትና የሌለው መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል።

 

የፌዴራል ሥርዓታችን  ዘላቂ ሠላም አስፍኖልናል፤  ልንለማ፣ ልናድግና ልንለወጥ እንደምንችል በተጨባጭ አሳይቶናል። የፌዴራል ስርዓት ዴሞክራሲን ይፈልጋል። የእኛ አገር ዴሞክራሲ ደግሞ ገና ታዳጊ ከመሆኑ አኳያ ህብረተሰቡም በአግባቡ መብቱን እየጠየቀ እንዲሁም ግዴታውንም  እየተዋጣ አይደለም። በአገር አቀፍ ደረጃም ዴሞክራሲያችንን ለማጎልበት የተቋቋሙት ተቋማትም የሚፈለገውን ያህል የተጠናከሩም አይደሉም። በመሆኑም የፌዴራል ስርዓታችንን መንከባከብ የመንግስት ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሰላም ወዳድ ዜጋ ግዴታ ሊሆን ይገባል።  እንደእኔ እንደኔ ኢትዮጵያ ከፌዴራል ሥርዓት ውጪ ማሰብ ራስን በራስ እንደማጥፋት የሚቆጠር ተግባር ይመስለኛል። ዛሬ ላይ ተመልሰን ሌላ የአስተዳደር ዘይቤ እንከተል ማለት በህብረተሰቡ ተቀባይነት ይኖረዋል ብዬ አላስብም። ምክንያቱም ከነእጥረቱም ቢሆን በዚህ የፌዴራል ስርዓት ያገኘውን ጥቅም  ህብረተሰቡ ያውቀዋል። በነውጥና ሁከት የሚመጣ ለውጥ መዳረሻው አይታወቅም። በቀል የሠላምን መንገድ እየዘጋ ነውጥና ሁከትን እያባባሰ ወደ ውድቀትና እልቂት ይመራል እንጂ መልካም ነገርን አያመጣም። ህብረተሰቡ እርስ በርሱ እንዲጋጭ ጥገኞች የሚያደርጉትን ስውር አካሄድ ሊነቃባቸው ይገባል ባይ ነኝ።