Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በአዲስ መንፈስ…

0 355

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአዲስ መንፈስ…

                                                         ይሁን ታፈረ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሰየሙ ወዲህ፣ የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉ የመጀመሪያው መሪ ሆነዋል። ፕሬዚዳንት ካጋሜ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል። ወደም ባሉት ጊዜያት ሁለቱ አገራት የነበራቸው ግንኙነት ጠንካራ ነበር። ኢትዮጵያ ሩዋንዳ ዛሬ ለምትገኝበት ደረጃ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጋለች።

እንደሚታወቀው ሁሉ ታሪክን የኋሊት ስንቃኘው የመጀመሪያው የሆነው የሩዋንዳ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ህገ-መንግስቱ ከመጽደቁ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ በሠራዊታችን ተከናውኗል፡፡ ይህ ግዳጅ፤ ህገ-መንግስቱ እየተረቀቀ በነበረበት ዓመት ውስጥም በመሆኑ የሠራዊቱን የነበረ ህዝባዊ ባህሪ የሚያመላክት ነው ማለት ይቻላል፡፡

ወቅቱ በሩዋንዳ ውስጥ  በሁቱና ቱትሲ መካከል በተነሳው የጎሳ ግጭት የዘር ማጥፋት  ተግባር የተቀጣጠለበት ነበር፡፡ ይህን የዘር ማጥፋት ወንጀል  ለማስቆም የሚችል ኃይል አልነበረም፡፡ እናም የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት  በጉዳዩ ላይ መክሮ በ“UNAMIR” (የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተልዕኮ በሩዋንዳ) ጥላ ስር  ተሰማርቶ ተልዕኮውን ሊወጣ የሚችለው የኢትዮጵያ ሠራዊት እንደሆነ በማመን ጥያቄውን ለኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት አቀረበ፡፡

መንግስትም ሠላም ወዳድ በመሆኑና  በሠራዊቱም ህዝባዊ አመለካከት ላይ ከፍተኛ እምነት ስለነበረው፤አስቸጋሪውን ተልዕኮ ለመወጣት ቃል ገባ፡፡ “ጉና ሻለቃ” የተሰኘው  የሠራዊታችን አካል ተዘጋጀች፡፡

አንዳንድ ተንታኞች “ሠላም ማስከበር  በማይቻልበት ሁኔታ የመንግስታቱን ሠራዊት ለሰላም ጥበቃ መላክ መሰረታዊ ስህተት ነው” ወደተባለባት ሩዋንዳ ዘመቶ በአምባገነኑ የደርግ ሥርዓት ወቅት ተቋርጦ የቆየውን የሀገራችንን የሠላም ማስከበር ተሳትፎ በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፈተው፡፡

በመሆኑም ሠራዊታችን በሩዋንዳው የሠላም ማስከበር ተልዕኮው ድንቅ ያሰኘውንና ለማንም ያልወገነ ግዳጅን በተሰማራበት ቀጣና ፈጽሟል፡፡ ቦታዋ “ቻንጉጉ” ትባላለች፡፡ አስቸጋሪና ሽብር ፈጣሪዎች የተከማቹባት ናት ተብላም ትፈራ ነበር፡፡

ይሁንና የመከላከያ ሠራዊታችን ለየትኛውም ጎሳ ሳይወግን ገለልተኛ እንቅስቃሴ በማድረጉ፤ በዚያች ስፍራ ከሁለቱም ተቀናቃኝ ጎሳዎች (ሁቱና ቱትሲ) እኩል ፍቅርን ማትረፍ ችሏል፡፡ በዚህም ሠላምን በኃይል ሳይሆን በህዝባዊ ፍቅር በእጁ በማስገባቱ፤ የመንግስታቱን ድርጅት  ጨምሮ በርካታ ሠላም ወዳድ ኃይሎችን አስደንቋል፡፡

ሠራዊታችን ለሁሉም ሩዋንዳዊያን ፍቅርን ሰጥቶ ፍቅርን በመቀበሉ፤ ለስኬታማነቱ ቁልፍ ምስጢር ነበር፡፡ ከመሰረቱ ጀምሮ በባህሪው የህዝብ አጋር በመሆኑ፣ ህዝብ ውስጥ ዘልቆ በመግባት የዘር ማጥፋቱ ወንጀል እንዲቀጥል ፍላጎት ያላቸው ፀረ ሠላም ኃይሎችን አፍራሽ ወሬ እርቃኑን እንዲቀር አድርጓል፡፡ በዚህ ዓይነት መልኩ ከህዝብ ጋር የተዋሃደው “የጉና ሻለቃ”፤ተልዕኮውን “ለውጋገን ሻለቃ” ሲያስረክብ ሁሉም ሩዋንዳውያን በለቅሶ ነበረ የሸኙት፡፡

“ውጋገን” ሻለቃም ልክ እንደ “ጉና” ሻለቃ፤ በግዳጆቹ በሙሉ የሁሉም ወገኖች ታማኝ ሆኖ በማገልገል ታላቅ  አክብሮትን አትርፎ ተልዕኮውን ፈጽሟል፡፡ በዚህም በዓለም የሠላም ማስከበር ታሪክ ውስጥ “ለብጥብጥና ሁከት መፍትሄው የመሣሪያ ጋጋታ ሳይሆን ህዝባዊ አመለካከትን ይዞ ህዝቡን በቅንነት ማገልገል ነው” መሆኑን ሠራዊታችን ታላቅ ትምህርት ለመስጠት ችሏል፡፡

በአጠቃላይ በሩዋንዳው ተልዕኮ በሁለቱም ዙሮችየሠራዊታችን አባላት ግዳጃቸውን በብቃት በመወጣታቸው  ተመድም ለፈፀሙት ክቡር ተግባር በወረታው ሜዳሊያ ሸልሟቸዋል፡፡ “ለህዝብ የወገነ ሠራዊት ለድል ይበቃል” ይሏል እንዲህ ይመስለኛል፡፡

ታዲያ ሩዋንዳ ከተረጋጋች በኋላም 15ኛው የድል በዓሏን ስታከብር ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ መንግስታቸውና ሰራዊታቸው ለሩዋንዳ ሠላም ባሳዩት ቁርጠኝነት የአገሪቱን ታላቅ የኒሻን ሽልማት ሰጥታለች፡፡

በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያ የሩዋንዳ የቅርብ ወዳጅ መሆን ችላለች። በመግቢያዬ ላይ ዛሬ ለሩዋንዳ የዛሬ ገፅታ ኢትዮጵያ ጉልህ አስተዋፅኦ አድርጋለች ያልኩትም ለዚሁ ነው። በዚህ ታሪካዊ ግንኙነት የተቆራኙት ሁለቱ አገራት እስከ ዛሬ ድረስ በበርካታ ጉዳዩች አብረው ሲሰሩ መጥተዋል። ዶክተር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሰየሙ በኋላ የመጀመሪያው ጎብኚ የሆኑት ፕሬዚዳንት ካጋሜ፤  በታላቁ ቤተ መንግሥት ይፋዊ አቀባበል ሥነ ሥርዓት ተደርጎላቸዋል። የሁለቱ አገራት መሪዎች በተለያዩ የሁለትዮሽ፣ እንዲሁም ባለ ብዙ ፈርጅ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ላይ ተወያይተዋል። ከዚህ ቀደም የደረሷቸውን ስምምነቶች ተግባራዊ ለማድረግ በሚቻልበት ሁኔታም ላይ ከስምምነት ደርሰዋል።

በዚህ መሠረትም ሁለቱ አገሮች ከዚህ ቀደም የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ከማጠናከር አኳያ የተፈራረሟቸውን 20 የሚሆኑ ስምምነቶች ተግባራዊ ለማድረግ ተስማምተዋል። እንዲሁም የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ለማጠናከር፣ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት፣ በአህጉሪቱ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይ በተቀናጀ መንገድ ለመሥራት፣ የአፍሪካ ህብረት የተሃድሶ አጀንዳዎችን ማስፈጸምና የፓን አፍሪካ እሴቶችን በአህጉሪቱ ለማስፋፋትና ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በመምከር ስምምነት ላይ መድረሳቸው ታውቋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል በተከሰተበት ወቅት፤ ኢትዮጵያ ከላከቻቸው የሰላም አስከባሪ ወታደሮች መካከል አንዱ የነበሩ ሲሆን ከላይ የገለጽኳቸውን የሰራዊቱን ተግባራት በመወጣት ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።

አሁን ደግሞ ከዓመታት በኋላ ከሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ጋር በተለየ ደረጃ መገናኘታቸው የነበራቸውን የአጋርነት መንፈስ በአዲስ መንገድ የሚያጠናክረው ነው። የትላንቱን በማስታወስ የሁለቱን አገራት ጠንካራ ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግሩት እሙን ነው።

ምንም እንኳን ሩዋንዳ ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ የከተፈችው በ1970 ዓ.ም እንዲሁም ኢትዮጵያም ኤምባሲዋን በኪጋሊ የከፈተችው አምና ቢሆንም በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ጥብቅና ታሪካዊ ነው። ሁለቱ መሪዎች ባደረጓቸው ንግግሮች ይህን ታሪካዊና ስር የሰደደ ግነኙነት በአዲስ መንፈስ እንደሚያስቀጥሉት ተናግረዋል። በአጠቃላይ በአገራቱ መካከል ያለው ሁለንተናዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት በምሳሌነት የሚታይ እንዲሁም ከአዲሱ የአገራችን አመራር ጋር ሩዋንዳ የሚኖራት የወደፊት ግንኙነት በአዲስ መንፈስ፣ አዲስ ጎዳናን ይዞ ለተሻለ የዲፕሎማሲ ድል የሚያበቃን መሆኑን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy