ቢታረም ይበጃል!
ዳዊት ምትኩ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ የኦሮሞ አክቲቪስቶች ዶክተር አብይን አስመልክቶ እያራመዱት ያለው የተሳሳተ ትክከል ባለመሆኑ ሊታረም የሚገባ ይመስለኛል። በተለይ በቅርቡ ከእስር ተፈትተው በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱና በውጭ የሚገኙ አክቲቪስቶች ‘እኛ በሞትነው፣ እኛ በተጎዳነው የተጠቀመው ሌላ ነው’ በሚል የሚያራምዱ አስተሳሰብ የተሳሳተ ተገቢ አይመስለኝም። ከእስር የተፈቱት አቶ በቀለ ገርባም ይሁኑ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ አሊያም ሌሎች ታሳሪዎች የተለቀቁት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥረት ነው ጥረት መሆኑ ግልፅ ነው።
ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኦሮሞ ብሔር አብራክ የተገኙ ቢሆንም፤ የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች መሪ መሆናቸው ሊዘነጋ አይገባም። ከአንድ ብሔር የተገኘ አመራር የሚሰራው ለኦሮሞም ለሌላውም የአገሪቱ ህዝቦች ነው። ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚመለከተው በእኩል ዓይን ነው። ሊያበላልጥ አይችልም። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የታገሉት ለሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች እኩልነት ለማምጣት እንጂ ለአንድ ብሔር ባለመሆኑ ይመስለኛል። በመሆኑም በአንዳንድ አክቲቪስቶች እየተላለፈ ያለው የተሳሳተ መልዕክት ትክክል ባለመሆኑ ሊታረም የሚገባው ነው።
እንደሚታወቀው ሁሉ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ኢትጵያዊ በህግ ካልተደነገገ በስተቀር በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮች እኩል መብት እንዲኖራቸው ተደርጓል። ምስጋና ለአዲሱ አመራር ይሁንና የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሰላም እየተረጋገጠ ነው። ዜጎች በህግ ፊት እኩል ሆነዋል። የሚከተሉት የኃይማኖትና እምነትም በእኩልነትን የሚታዩበት ህገ መንግስታዊ ስርዓት ተረጋግጧል። ፍትሕን እንዲቋደሱና በፍትሕ ስርዓቱ ውስጥ ሁነኛ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል። በዚህ አዲስ የእኩልነት ግንኙነትም ሁሉም በየደረጃው ተጠቃሚ እንዲሆን ተደርጓል። እናም ለአንዱ ብሔር ተሰጥቶ ለሌላው የሚነፈድ የፍትህ ስርዓት የለም።
የሕብረ ብሄራዊ ፌዴራል ሥርዓቱ አንዱ መሠረታዊ እምነት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል በመሆኑ ይህ እንዲረጋገጥና ህገ መንግስታዊ ዋስትና እንዲያገኝ ተደርጓል። ባለፉት መንግሥታት በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የኖረውን የተዛባ ግንኙነት በመፋቅ አዲስ ኢትዮጵያዊ ማንነት ለመገንባት የሚያስችሉ የማንነቶች እኩልነት ማረጋገጥ፣ ሁሉም ዜጎች ኢትዮጵያን በመገንባት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ፣ በአካባቢ ጉዳዮቻቸው ላይ ወሳኝ የሚሆኑበትን የራስ አስተዳደር ማረጋገጥ በአጠቃላይ ከአገሪቱ ልማት ተመጣጣኝ ጥቅም እንዲያገኙ እየተደረገ ነው።
የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማንነቶች አዲስ የእኩልነት መንገስ መክፈቱንነና እንደ ማረጋገጫ መሣሪያ ስለተወሰደም በዚህ አወቃቀር አዲስ የእኩልነት ግንኙነትና የጋር ህልውና እንዲመሠረት ተደርጓል።
በፌዴራል ስርዓቱ አመሰራረት ወቅትም እነዚህን የተራራቁ ፍላጎቶች የነበሯቸው የፖለቲካ ኃይሎች ተቀራርበውና ተሰባስበው በህብረቱ እንዲቀጥሉ በመስማማታቸው፤ ለቁርሾ የሚያበቃ ነገር እንዳይኖር ላመድረግ ተሞክሯል። ይሀን ሁኔታ ይበልጥ በማጠናከር ሁሉም ህዝቦች በእኩልነት የሚንቀሳቀሱባትን አገር ለመፍጠር ዶክተር አብይና መንግስታቸው እየሰሩ ነው።
እርሳቸው አንዱን ኢትዮጵያዊ ከሌላው ሊያበላልጡ አይችሉም። የመላው ኢትዮጵያዊ መሪ ናቸው። የሁሉም ህዝቦች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ያለ አንዳች አድልኦ እንዳይፈፀም እየሰሩ ነው። ከአንድ ህዝባዊ መሪ የሚጠበቀውም ይህ ነው። እናም “አኛ በሞትነው…” የሚለው የአንዳንድ አክቲቪስቶች አባባል ሊታረም ይገባል።
እንደሚታወቀው ሁሉ ህገ መንግሥቱ ፀድቆ በአገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት እውን ከሆነ ወዲህ የሠላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ምላሽ እያገኙ መጥተዋል። ግን አጥጋቢ አይደሉም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህን ጉዳዩች በበለጠ ሁኔታ ምላሽ እንዲያገኙ ጥረት እያደረጉ ነው። ይህ ጥረታቸው የሚሰምረው ሁሉንም ህዝብ በማካተት ነው። ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ የሚፈልጉትን ኃይማኖት የመከተል፣ በቋንቋቸው የመናገር እና የመጻፍ፣ ባህላቸውን እና እሴቶቻቸውን በነጻነት የመግለፅ መብቶቻቸው ለሁም ኢትዮጵያዊ የተሰጡ ናቸው። የአገራችን ህዝቦችም የታገሉት ምክንያትም እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ነው። አንዱ ብሔር አግኝቶ ሌላው እንዲያጣ አይደለም። በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየሄዱበት ቦታ ሁሉ ኢትዮጵያዊያንን ከእስር ሲያስፈቱ በመጀመሪያ የሚመለከቱት ኢትዮጵያዊነትን ነው። እናም አክቲቪስቶቹ የሚያራምዱት የተሳሳተ አስተሳሰብ ሊታረም ይገባዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በበዓለ ሲመታቸው ላይ ፓርላማ ውስጥ “እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለስራም ሆነ ለትምህርት በሄደበት ሁሉ ኢትዮጵያን ተሸክሟት ይዞራል። ኢትዮጵያዊውን ከኢትዮጵያ ታወጡት እንደሆነ ነው እንጂ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያዊው ልብ ውስጥ አታወጧትም የሚባለውም ለዚህ ነው። ሁላችሁም በታታሪነታችሁ፣ በልቀታችሁ እና የትም በሚከተላችሁ የሀገራችሁ የጨዋነት ባህሪ የኢትዮጵያና የእሴቶቿ እንደራሴዎች ናችሁ።…” በማለት የገለፁት ስለ ኢትዮጵያዊያን ያላቸውን ትክክለኛ ምልከታ የሚያሳይ ነው።
በእርሳቸው አስተሳሰብ ውስጥ ‘ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ይኑር’ ብሎ የተነሳው የሶስት ዓመት ትግል መልሶ የተነሳበትን ዓላማ ሊፃረር አይችልም። በመሆኑም ሁሉም የአገራችን ብሔር በእኩልነት የሚጠቀምበትን መንገድ እየቀየሱና ኢትዮጵያዊ ክብር ከፍ እንዲል ማድረጋቸው ዶክተር አብይን የሚያስመሰግናቸው ተግባር ነው።
እንደ እኛ ያለና ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መርስቶ አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብን ለመገንት በሕገ መንግስቱ ላይ ሳይቀር ያሰፈረ ህዝብ ማሰብ ያለበት ስለ አንድነት ነው። እገሌ ተጠቀመ እገሌ ደግሞ አልተጠቀመም የሚል አስተሳሰብ ተገቢ አይደለም። እዚህ ያለው እዚያ ሄዶ ካልሰራ፣ እዚያ ያለው እዚህ መጥቶ መስራት ካልቻለ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሊያመጡት ያሰቡት አንድ የጋራ ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ መገንባት አይቻልም። ልዩነት ተፈጥሮአዊ ቢሆንም አንድነት ደግሞ እንደ አገር ኢትዮጵያዊ ስሜትን ለመፍጠርና አገር ለመገንባት ወሳኝ ነው። ዶክተር አብይ እያደረጉት ያለው ይህንን አኩሪ ተግባር ነው።
እናም አንድ በምጣኔ ሃብት የዳበረ ማህበረሰብ ለመገንባት በኢትዮጵያ ሶማሌ ውስጥ ያለው ዜጋ ኦሮሚያ ክልል ሄዶ፣ በኦሮሚያ ክልል ያለውም የኢትዮጵያ ሶማሌ አሊያም አማራ ክልል ሄዶ መስራት ይኖርበታል። ማንኛውም ዜጋ በየሄደበት በየትኛውም ክልል ተዘዋውሮ ሃብት ማፍራት ይኖርበታል። ምክንያቱም ዜጎች የመንቀሳቀስና በየትኛውም ክልል ሄዶ ሃብት የማፍራት ህገ መንግስታዊ መብት ያላቸው በመሆኑ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩና መንግስታቸው ይህን የአንድነት አስኳል ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ባሉበት በአሁኑ ወቅት አንዳንድ አክቲቪስቶች “እኛና እነርሱ” በማለት የሚያራምዱት የተሳሳተ ሃሳብ ቢታረም ለአገር የሚበጅ መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል።