Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተቀባይነቱ

0 383

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተቀባይነቱ

                                                        ታዬ ከበደ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሀገራችን ህዝቦች እንዲሁም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት እየጨመረ መጥቷል። በሀገር ውስጥ ከህዝቡ ጋር ባደረጓቸውውይይቶች ኢትየጵያዊ አንድነትንና ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር የቻሉ ናቸው።

በውጭ ሀገራት ያደረጓቸው ጉዞዎችም የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም ከማስከበር በተጨማሪ በእስር ቤት የሚገኙ ዜጎች እንደፈቱ ያደረጉ ናቸው። ይህም ፍቅርንና ይቅርታን የተመሰረተና የዜጎችን ኢትዮጵያዊ ክብር ያስጠበቀ ነው። በእነዚህ ጉዳዩች ሀገር ቤትና በውጭ ባለው ህዝብ ዘንድ አመኔታንና ከበሬታን ማግኘት ችለዋል።

በዲፕሎማሲው ረገድ በበሰለ ሁኔታ ለሀገራችን ያስገኙትን ስኬቶች እንዲሁም የግንቦት 20ን በዓል አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔኦ አገራቸው ዶክተር አብይ አህመድ ለሚመሩት  መንግሥት ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደምታደርግ መግለጻቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በልዕለ ሃያላን ሀገሮች ሳይቀር ምን ያህል ተቀባይነት እንዳላቸው የሚያሳይ ነው።።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ትልቅ የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት ባላቸው ቁርጠኝነት በቅርብ ዓመታት የተመዘገበውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማስቀጠል አሜሪካ ሙሉ ድጋፍ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኗ የልማት አጋሮቻችን ምን ያህል በእርሳቸው አመራር እምነት እንዳላቸው የሚያረጋግጥ ነው።

በተጨማሪ የቻይናና የሩሲያ መሪዎችም በተመሳሳይ በግንቦት 20 የድል በዓል ባስተላለፉት መልዕክት ከዶክተሩ ጋር አብረው ለመስራት መፈለጋቸው ለሌላኛው የእርሳቸው ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ማሳያ ይመስለኛል። እነዚህ ሃቆች ዶክተር አብይ ከአገራችን አልፎ በዓለም አቀፉ አገራት ያላቸውን ተቀባይነት የሚያሳዩ ናቸው። ይህ ተቀባይነት አገራችን በኢንቨስትመንት በኩል የምታደርገውን ጥረት በእጅጉ ሊያሳድገው የሚችል ነው።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መጥቷል። አገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን የተገነዘቡ በርካታ የውጭ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት የማሳየታቸው ምስጢርም ይኸው ይመስለኛል።

አገራችን በምትከተለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ትክክለኛ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ በግሉ ባለሃብት መሰራት የሚገባቸውና በመንግስት ሊከናወኑ የሚገቡ ተግባራት ተለይተው በመካሄዳቸው በሁለቱም በኩል ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው።

በአሁኑ ሰዓት የውጭ ባለሃብቶችን የሚሰማሩባቸውን ዘርፎች በመለየት አንፃራዊ በመሆነ መንገድ ለሀገሪቱ ዕድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ እየተደረገ ነው። የውጭ ባለሃብቶች በአገራችን መንግስት መሪ ተቀባይነት እስካመኑ ድረስ ወደ አገር ቤት መጥተው ኢንቨስት ያደርጋሉ። ይህም ለኢኮኖሞ ዕድገታችን ወሳኝ ሚና ሊጫወት እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት መርህ የሀገሪቱን ገፅታ ከመለወጡ ባሻገር፤ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ መድረኮችም ተሰሚነቷንና ተፅዕኖ ፈጣሪነቷን ከፍ እንዲል አድርጓል። የዶክተር አብይ በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ ተቀባይነት ማግኘት ይሁን ሁኔታ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግረው ነው።

አገራችን እያካሄደች ያለው ዲፕሎማሲ ስኬት አንዱ ማሳያ እየተመዘገበ ያለው ፈጣንና ተከታታይ የምጣኔ ሃብት ዕድገት ነው። ይህ ፈጣንና ተከታታይ ልማትን በመደገፍ ረገድ የምጣኔ ሃብት ዲፕሎማሲው ጉልህ ሚና በመጫወቱ በችግር ጊዜም ለውጥ አምጪነታችን ተረጋግጧል። በተለይ የፖለቲካው ሽግግር ብስለት በተሞላበት ሁኔታ መከናወኑ ከእኛ ጋር አብረው ለመስራት የሚፈልጉ አካላትን ቁጥር ከፍ አድርጎታል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ባካሄዱት ከፍተኛ ጥረት ሀገራችን በአለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ በቅታለች። በዚህም ከሰሃራ በታች ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት በአምስተኛ ደረጃ፣ የነዳጅ ምርት ከሌላቸው ሀገሮች ደግሞ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘችው ኢትዮጵያ፤ የበርካታ ኢንቬስተሮችን ቀልብ በመሳብ ላይ ትገኛለች። ይህ ሁኔታ ከመንግስት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ጋር ሲደመር ወደ ተሻላ ደረጃ የሚያደርሰን ነው።

ይህም ባለፉት ጊዜያት የሀገራችንን ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ተጠቅመው መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ላይ የሚገኙት የቻይና፣ የአሜሪካ፣ የሩሲያ፣ የቱርክ፣ የህንድ፣ የአውሮፓ፣ የአረብ ሀገሮች ትልልቅ ኩባንያዎችና ባለ ሃብቶች ይገኛሉ። ይህን መሰሉ ኢትዮጵያ የኢንቬስተሮች መዳረሻነታችን ከዶክተር አብይ ተቀባይነት ጋር አገራችንን ይበልጥ ሊያሳድጋት የሚችል ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ የአገራችን ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳርና ፖሊሲ አብዛኛዎች የዓለማችን ሀገራት ዓይናቸውን እንዲጥሉባት ያደረገ ነው። አዲሱ አመራር ይህም ሁኔታ ይበልጥ ለመለወጥ ይሰራል። ወደፊትም ባለው ተቀባይነት ባለ ሃብቶችን ይበልጥ በመሳብ ይህችን አገር ወደ ነበረው ክብሯ የሚመልሳት እንደሚሆን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

ለዚህም በአዲስ መልክ የተከፈተው የዲፕሎማሲ መስመር ጉልህ ሚና አለው። የዲፕሎማሲው ትስስር ገመድ የቀጣናውን ህዝቦች ጥቅም የማከለ ነው። የምስራቅ አፍሪካ ህዝቦች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ በባህል፣ በታሪክ፣ በአብሮ መኖር፣ በመዋለድና አንዱ የሌላኛውን ሀገር እንደ ሁለተኛ መኖሪያው በመቁጠር የቅርብ ግንኙነት የታጠረ ነው። በመሆኑም የቀጣናው ሀገራት ይህን ዘመናትን የተሻገረ የህዝቦች ጥብቅ ቁርኝት በዘመናዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ይበልጥ አጥብቀው ማሰር ይኖርባቸዋል። ለዚህ ደግሞ በየጊዜው እየተገናኙ የሚያደርጓቸውን ስምምነቶች ወደ ተግባር መለወጥ ይጠበቅባቸዋል።

እርግጥ ሀገራችን በራሷም ሆነ በአካባቢው ሀገራት የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ግጭቶችና ውዝግቦች በሰላማዊ ጥረት እንዲፈቱ ብቻ ሳይሆን፤ የሰላምና የትብብር አድማስ በዲፕሎማሲ ታጅቦ እንዲሰፋ ግንባር ቀደም ሚና መጫወት ይኖርባታል። ለዚህም ሀገራችን የምትከተለው የትብብርና የሰላም ዲፕሎማሲ መርሆዎች ያግዟታል።  

የአገራችን የልማት እመርታ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በዙሪያዋ ያሉት ጎረቤቶቿም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጠንካራ አካባቢያዊ ትብብርና የዲፕሎማሲ ቁርኝት እየፈጠረች ነው፤ በጠቅላይ ሚኒስትራችን አማካኝነት። ይህ የጋራ ተጠቃሚነት ቁርኝት ይበልጥ ይጎለብታል። በእርሳቸው የሚመራው መንግስት በሀገር ውስጥና በውጭ ያለውን ድጋፍ ይዞ የመሪነት ሚናችንን የሚያስጠብቅ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy