Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተጠቃሚው ማነው?

0 303

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተጠቃሚው ማነው?

                                                    ደስታ ኃይሉ

መንግስት በቅርቡ በተለያዩ ወንጀሎች ተከሰው በቁጥጥር ስር የነበሩ እስረኞችን ፈትቷል። ይህ የሆነውም የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና የተሻለ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር መሆኑን አስታውቋል። ታዲያ እዚህ ላይ ‘የፖለቲካ ምህዳሩ በመስፋቱ ተጠቃሚው ማነው?’ የሚል ማንሳት ያስፈልጋል።

እርግጥ በፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ተጠቃሚዊቹ ህዝብና አገር ናቸው። ዴሞክራሲው ሲጎለብትና ማንኛውም ዓይነት ሃሳብ ያለው ዜጋ በምህዳሩ ውስጥ ሲንቀሳቀስ ተጠቃሚዎቹ ህዝብና አገር መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ሆኖም መንግስት ሁሉንም እስረኞች በጅምላ አልለቀቀም።

ለምሳሌ ያህል ከእስር የተለቀቁት ኢትዮጵያዊያን ውስጥ በ3ኛ ወገን ላይ ጉዳት ያላደረሱትን በመለየት ጭምር እየታየ የተከናወነ ነው። በሂደቱ በአስገድዶ መደፈር ወንጀል የተከሰሱ ግለሰቦች እንዲለቀቁ አልተደረገም። ይህ የመንግሥት ተግባር የህዝብ ወገናዊነቱን በተጨባጭ የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ ተጠቃሚዎቹ ህዝብና አገር መሆናቸውን የሚያሳይ ይመስለኛል።

በየትኛውም አገር ውስጥ መግባባትን መፍጠርና ዴሞክራሲን ማጎልበት ዋነኛ ተጠቃሚው ህዝብ ነው። ያለ አንዳች መረጃ በጥርጣሬ ብቻ ሰዎችን መያዝና ሰር የግለሰቦቹን ቤተሰቦች ከማንገላታት ውጭ ምንም ዓይነት ፋይዳ የለውም። ይህም የህግ የበላይነት እዚህ አገር ውስጥ በተገቢው ሁኔታ ተግባራዊ እንዳይሆን የሚያደርግ ክስተት ነው።

በአገራችን ውስጥ የዴሞክራሲ አሳታፊነት ይበልጥ መጎልበት ይኖርበታል። እዚህ አገር ውስጥ ተፎካካሪዎችን የሚደግፍ ህዝብ መኖሩ አይቀርም። የዚህ ህዝብ ድምፅም በተፎካካሪዎች አማካኝነት መሰማት አለበት።

መንግስትም በሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ድርድር አካሂዳለሁ ብሎ ወደ ተግባር ገብቷል። የምርጫ ህጉን ከማሻሻል ጀምሮ ሌሎች ማሻሻያዎችን በማከል የዴሞክራሲ ምህዳሩን ይበልጥ ለማስፋት እየሰራ ነው። አሁንም በአዲስ መልክ ድርድሩ ተጀምሯል። በውጭ የሚገኙ እንደ “ኦዴግ” ዓይነት ፓርቲዎችም ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ነው። ይህ የመንግስት ጥረትም ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ያም ሆኖ መንግስት ዴሞክራሲውን ለማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ለማድረግ የተያዘው ቁርጠኝነት በሚፈለገው ፍጥነት መጎልበት አለበት። ዴሞክራሲውን ለማስፋት በመንግስት በኩል የተያዘው ቁርጠኝነት ተጨባጭ መገለጫዎችን የሚያሳዩና የሀገራችን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ማሳያ ናቸው።

ህገ መንግስቱ ዜጎች በሰላማዊ መንገድ ማናቸውንም ተቃውሞዎች ማቅረብ እንደሚችሉ መብት ይሰጣል። ህገ መንግስቱ ለሰላማዊ ተቃውሞ መብት ይሰጣል ሲባል፤ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድ የሚደረጉ ማናቸውም ፍላጎቶች አይፈቀዱም ማለት ነው።

እናም ህገ መንግስቱ ለሰላማዊ ተቃውሞ መብት የሚሰጠውን ያህል ህግና ስርዓትን ለሚጥስ ማናቸውም ተግባር ምንም ዓይነት ዕውቅና የማይሰጥ ከመሆኑም በላይ፣ የህግ የበላይነትን መፃረር በመሆኑ በወንጀል ተጠያቂነት ያለበትም ነው።

እንደሚታወቀው በህግ ካለተደነገገ በስተቀር በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ የህግ የበላይነትን በመፃረር እንዳሻው ሊኖር አይችልም። የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ስርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም። በመሆኑም ማንኛውም ዜጋ የሚንቀሳቀሰው ህግ ባለበት ሀገር ውስጥ ነውና ህገ-ወጥ ተግባርን ከከወነ የህግ የበላይነት ተፈፃሚ እንደሚሆንበት ማወቁ ተገቢ ይመስለኛል።

እርግጥ የአገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ገና ለጋ በመሆኑ ምንም ዓይነት ተግዳሮቶች የሉበትም ለማለት ባይቻልም፤ ከዕድሜ አኳያ ስንመለከተው ግን አሁን ያለንበት ደረጃ የመራጩ ህዝብ አስተሳሰብ እያደገና የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳርም እየሰፋ መሆኑን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

ይህም በቀጣይነት የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታን ይበልጥ ለማጎልበት ከወዲሁ ተስፋ መኖሩን አመላካች ነው። እናም በተፎካካሪነት የተሰለፉ ወገኖች ይህን ዕውነታ ማወቅ ይኖርቸዋል።

በተፎካካሪነት የተሰለፉ ወገኖች ችግሮችን በጥላቻ መንፈስ ለመፍታት ከተሞከረ ሰላማዊነትን አያመላክትም። በመሆኑም ሰላማዊ ለመሆን የሁሉም ወገኖች መቻቻልና ለዴሞክራሲ መጎልበት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ይህን ለማድረግ መንግስት እየወሰዳቸው ያሉት እርምጃዎች ወሳኝ ናቸው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ያለፉት ስርዓቶች በሀገራችን ህዝቦች መካከል ፈጥረውት ያለፉት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች በቀላሉ የሚሽሩ አይደሉም። ፀረ ዴሞክራሲያዊ እሳቤዎችን በዴሞክራሲያዊነት ለመቀየርም አስተሳሰብንና ስለ ዴሞክራሲ ያለንን አመለካከት መለወጥ ይገባል። በህዝቦች ውስጥ ለዘመናት ሲፈጠሩ የነበሩትን የተዛቡ ግንኙነቶች በጥቂት ዓመታት ውስጥ መቀየርም አይቻልም።

እርግጥ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጊዜንና የአስተሳሰብ ልህቀትን ይጠይቃል። ይህ ሁኔታም ምናምባትም ችግሮችን በዴሞክራሲያዊ ማዕቀፍ ውስጥ ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን ሊያሰናክል ይችላል። እናም ዴሞክራሲው እንዲሰፋ እነዚህን ሁለት ተግዳሮቶች መፍታት ይገባል።

ይህን ዕውን ለማድረግም የህዝቡ ወኪሎች የሆኑት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይገባል። የህዝብ ወኪል የሆነ ፓርቲ ምንግዜም ማሰብ ያለበት ህዝቡን ነው። ሌላ ማንንም አይደለም። ህዝቡን ወክሎ ሲወያይም ዴሞክራሲው እንዲጎለብት የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ነው።

በአሁኑ ወቅት የአገራችንን ዴሞክራሲ ለማጐልበት የተለየ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። ከዚህ አኳያ አንዱ በገዥው ፓርቲና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል በሚደረግ ድርድር ወሳኝ ነው።

በተጨማሪም ሲቪክ ማህበራት በአገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። ከእነዚህ ውስጥ መንግስት ከሲቪክ ማህበራቱ ጋር ያካሄዳቸው ውይይቶች ተጠቃሽ ናቸው።

ሲቪክ ማህበራቱ ለአገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መጠናከር የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ እየተደረገ ነው። ይህም ማህበራቱ መንግስት በሞት ሽረትነት እውን እንዲሆን በማድረግ ላይ የሚገኘው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ፍሬ እንዲያፈራ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው።

በአጠቃላይ መንግስት የሀገሪቱን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በፅኑ መሰረት ላይ እንዲቆም ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው። ይህም የኢትዮጵያ መንግስት ዴሞክራሲን እውን ለማድረግ ሁሌም ዝግጁ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። በመገለጫውም የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እስረኞችን ፈትቷል። በዚህም በውስጥም ይሁን በውጭ ህዝባዊ ድጋፍ ተገኝቷል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy