Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

 ትብብርና ጉርብትናን  የሚያጠናክር ግንኙነት

0 486

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 ትብብርና ጉርብትናን  የሚያጠናክር ግንኙነት

 

ስሜነህ

 

ግብፅና ኢትዮጵያ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት አላቸው፤ ከሰማኒያ በመቶ በላይ ከኢትዮጵያ የሚፈልቀው ጥቁር አባይ፣ ከነጭ አባይ ጋር ተጨምሮ፣ ለግብፃውያን የህልውናቸው መሰረት ነው፡፡ የጥንትም ይሁን ዘመናዊ የግብፅ መሪዎች፤ ይህንን የግብፃውያን የህልውና መሰረት መጠቀምና ማስቀጠል የሚፈልጉት በኢትዮጵያውያን ኋላ ቀርነት፣ ደካማነትና ኪሳራ ላይ ብቻ ሆኖ መዝለቁ፣ የሁለቱን ሃገሮች ግንኙነት እስከ ዛሬ አሉታዊ አድርጎታል፡፡ ይህ በዲፕሎማሲ ቋንቋ፣ በተሸናፊነት መንፈስ፣ በኢትዮጵያ መሪዎችና ፖለቲከኞች የሚሸፋፈን ቢሆንም፣ በኢትዮጵያውያን ዜጎች ልቦና ሁሉ እንደ ሰማዩ ፀሃይና ጨረቃ፣ በግልፅ ለዘመናት ለተያዘ ቅሬታና የቁጭት ስሜት ምክንያት ነው፡፡

 

የሁለቱ ሃገሮች አጀንዳ ዛሬ ለሃይል ምንጭ ብቻ ነው ተብሎ እየተገነባ ካለው፣ ከህዳሴው ግድብ የውሃ አሞላልና ከውሃ ክፍፍል በላይ፣ በወቅቱ የውሃ ሃብቱን የመጠቀም፣ በተለይ በኢትዮጵያ በተፈጥሮ ላይ ያለው ጥገኝነት በወቅቱ የቀነሰ ህዝብና ኢኮኖሚ ዕውን የማድረግ፣ ተፈጥሮን የመጠበቅና ግብፃውያን መሪዎች በኢትዮጵያውያን ስሜት ላይ የፈጠሩትን ቁስል የሚያሽር ግንኙነት፣ እውነተኛ ትብብርና ዕርቅ መሆን ይኖርባቸው ነበር፡፡ በሁለቱም ሃገሮች መሪዎች እየተደረጉ ያሉ ድርድሮች፣ ውይይቶችና ስምምነቶች የጋራ ሆነው፣ በዚህ መሰረት ላይ ካልተፈፀሙ፣ ለሁለቱም ህዝቦች ችግርን የሚያራዝሙ፣ ከላይ የተጠቀሰውን የኢትዮጵያውያን ስሜት የሚያስቀጥሉ ብቻ ይሆናሉ፡፡

 

ይህ አይነቱ አማራጭ አሁን በአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ በኩል ከመቋጫው የደረሰ መስሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ከግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር በነበራቸው ውይይት፣ ኢትዮጵያ ግብፅን የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት ሲገልጹ  “ለግብፅ ሕዝብ መናገር የምፈልገው እኛ ኢትዮጵያውያን ወንድምነትና ጉርብትና የምናውቅ፣ ደግሞም እግዚአብሔርን የምንፈራ ስለሆንን ወንድም ሕዝብ የሆነውን የግብፅ ሕዝብ በፍፁም የመጉዳት ሐሳብም ፍላጎትም የሌለን መሆኑን ነው፡፡ የዓባይን ወንዝ መጠቀም እንደምንችልና እንደሚገባን ብናምንም፣ ዓባይን በመጠቀም ኢትዮጵያን ስናለማ ግብፃውያንን በፍፁም እንደማንጎዳ፣ በዚህ የግብፅ ሕዝብ በመንግሥቴና በሕዝቤ ሙሉ እምነት እንዲኖረው እፈልጋለሁ፤” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዓባይ ለሁለቱም ሕዝቦች የተሰጠ በረከት ስለሆነ ኢትዮጵያ የድርሻዋን ተጠቅማ ለግብፅ የሚገባትን ብቻም ሳይሆን፣ ወደፊት እየጨመረ የሚሄድ የውኃ ፍሰት ልታገኝ ስለምትችልበት ሁኔታም በንግግራቸው ጠቅሰዋል፡፡

 

“ዓባይ ለሁለቱም ሕዝቦች የተሰጠ በረከት ስለሆነ የእኛ ሥራ የእኛን ድርሻ መጠቀምና የእናንተን ድርሻ በተገቢው መንገድ ወደ እናንተ መላክ ብቻ ሳይሆን፣ መድረሱንም ማረጋገጥ ጭምር እንደሆነ አውቃችሁ በእኛ በኩል ሥጋት እንዳይገባችሁ፡፡ ዓባይን እንጠብቃለን፡፡ የእናንተን ድርሻ ሁሌም እንጠበቃለን፡፡ ድርሻችሁ እንዲያድግም ከወንድሜ ጋር በመሆን እንሠራለን፤” በማለት የሁለቱ አገሮች ሚዲያዎች የሚያስተጋቡትን የጥላቻና የቅሬታ ስሜት እንዲያስወግዱ አሳስበዋል፡፡ ከአልሲሲ ጋር ከዓባይ ባሻገር በሌሎችም መስኮች ላይ አብሮ ለመሥራት የሚያስችላቸውን መግባባት እንደፈጠሩ ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በኢንዱስትሪ፣ በመንገድ፣ በባቡር ትስስርና በሌሎችም መስኮች የሁለቱን ሕዝቦች ለማስተባበር እንሠራለን ብለዋል፡፡ ስለሆነም እስከሁን የግብፅና የኢትዮጵያ ግንኙነትና ድርድር የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ከተጀመረ ጀምሮ ባለመግባባት የታጀበ አዙሪት ውስጥ ሲንሸራሸር የቆየበትን ዘይቤ ምን ያህል ሊቀይረው እንደሚችልና ሁለቱን አገሮች ምን ያህል ሊያስማማ እንደሚችል  መገመት አይከብድም። በሌሎች ሃገራትም የነበረው የጠቅላዩ ጉብኝት በተመሳሳይ ስኬት የታጀበ ነው።

 

ከህዝቡ ጋር እየተገናኙ ተስፋ ሰጪ ንግግር አድርገዋል፡፡ ህዝቡም ንግግራቸውን ወድዶ ተስፋ አድርጓል፡፡ሃገሪቱ ከጎረቤቶቿ ጋር በጎ የሆነ ግንኙነት ያስፈልጋታል፡፡ በጣም ውስብስብ ችግር ያለበት አካባቢ ነው፡፡ ከዚያ አንፃር ብዙ ጠንካራ ስራ ሊሰራበት የሚገባ ቀጠና ነው። ስለሆነም በሱዳን የሁለት ቀናት ጉብኝት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ኢትዮጵያ በሱዳን ወደብ ባለድርሻ እንድትሆን ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት፣ ከፕሬዚዳንት አልበሽር ጋር በጋራ የመስራት ስምምነት ተፈራርመዋል። በሌላ በኩል በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እስረኞች እንዲፈቱ የጠየቁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ አፋጣኝ አዎንታዊ መልስ አግኝተዋል፡፡  ዶ/ር አብይ ለጅቡቲ ያቀረቡትን የወደብ ድርሻ ጥያቄ፣ ለሱዳንም ያቀረቡ ሲሆን የሱዳን መንግስትም ጥያቄውን ተቀብሎ፣ ኢትዮጵያ በሱዳን ወደብ ድርሻ እንዲኖራት መስማማቱ ይታወሳል፡፡ በተለይ ሱዳን እና ኢትዮጵያ የተፈራረሙት የወደብ ድርሻ ስምምነት፤ ከዚህ ቀደም የነበረው የገዥና ሻጭ አይነት ሳይሆን በጋራ አልምቶ፣ በጋራ የማስተዳደር እድልን የሚፈጥር መሆኑ ደግሞ የስኬቱን ደረጃ ያሳያል፡፡ የመጀመርያ የውጭ አገር ጉብኝታቸውን በጅቡቲ ያደረጉት ዶ/ር አብይ አህመድ፤ ኢትዮጵያ በጅቡቲ ወደብ ላይ የባለቤትነት ድርሻ እንዲኖራትና ወደቡን በጋራ ለመጠቀም ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ጅቡቲም በቴሌኮም መስክ በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንድታደርግ ጋብዘዋል፡፡ይህ ደግሞ መልካም ጉርብትናን እና ትብብርን የሚያጠናክር ግንኙነት ነው።

 

በኒሻን የታጀበው የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን የዑጋንዳ ጉብኝት በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ላይ የመሪነት ሚና ከመጫወት አንጻር ከኢትዮጵያ ጋር ለተወሰነ ጊዜ ፉክክር ውስጥ ገብታ ከነበረችው ዑጋንዳ ጋር ትብብርን ያጠናከረ መሆኑንም ተመልክተናል።  የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ለአገራችን ብሎም በአጠቃላይ ለምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ልማት ወሳኝ ሚና የሚጫወት መሆኑን የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጠበብቶችም እየመሰከሩ ነው።

 

በጥቅሉ ጠቅላይ ሚንስትሩ በስራ ቆይታቸው በተለያዩ የክልል ከተሞች በመንቀሳቀስ በህዝቡ ውስጥ ያሉ ቅሬታዎችን አዳምጠዋል፣ የመፍትሄ አቅጫዎችን አመልክተዋል። ያሉብንን ችግሮች በመቅረፍ በአንድነት ወደፊት ለመጓዝ በኢሕአዴግ፣ በመንግስትና በህዝቡ መፈፀም ስላለባቸው የቅድሚያ ተግባሮች አብራርተዋል። በአዲስ አበባ ከተማ ሰፋፊ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከወከሉ ተሳታፊዎች ጋር ተወያይተዋል፤ በሀገር ግንባታ፣ በብሄራዊ መግባባትና የእቅር ጉዳዮች ላይ መክረዋል። ለሀገራዊ መግባባት፣ ለይቅርታና እርቅ ሲባል በርካታ ተጠርጣሪዎች ክሳቸው እንዲቋረጥና የፍርድ ሂደታቸውን በመፈፀም ላይ የነበሩ ታራሚዎች እንዲፈቱ አድርገዋል።

በሀገር ውስጥ በተካሄዱ አለም አቀፍ መድረኮች በመገኘትና የውጭ ልዑካን ቡድኖችን ተቀብለው በማነጋገር ሀገራችን በአለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተሰሚነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አድርገዋል። ከላይ በተመለከተው መልኩ ሀገራችን ከጎረቤቶቿ በተለይም ከሱዳን፣ ከኬንያና ጅቡቲ ጋር ያሏት የቆዩ ግንኙነቶች በጠንካራ መሰረት፣ በአዳዲስ የግንኙነት መንገዶችና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ተመስርተው እንዲጠናከሩ ማድረግ ያስቻሉ የስራ ጉብኝቶችን አድርገዋል።

 

ወደ ሳውዲ አረቢያ በመጓዝ የዜጎቻችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሚከበሩበት፣ የሀገራችን ብሔራዊ ጥቅምና የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት ቀጣይነት በሚረጋገጥበት ሁኔታ ላይ መክረዋል። የስራ ጉብኝት ባደረጉባቸው ሀገሮች በማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ከእስር እንዲፈቱና የተወሰኑትም ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ አድርገዋል። በሀገራችን ሰላም ላይ አጥልቶ የነበረውን አደጋ በመቅረፍ ከህዝብ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እንዲሁም መደበኛ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታዎችን ለማከናወን የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል።ይህንን ጠብቆ ማቆየትና  ማስቀጠል የመላው ህዝብ ሃላፊነት ይሆናል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy