Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“ንባብ ይገድላል፤ ትርጉም ያድናል

0 1,036

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“ንባብ ይገድላል፤ ትርጉም ያድናል”
እምአዕላፍ ህሩይ
ማህበረሰባችን የስነ-ቃል ሃብታም ነው። የተትረፈረፉ ስነ- ቃሎች ባለቤት ነው። በሀገሬ የሚገኝ ህዝብ በየቋንቋው የዳበረ የስነ- ቃል ክምችት አለው። በውስጡ አንድ ደርዝ ያለው ጉዳይ ሲነገር፣ የጉዳዩን ፍሬ ነገር አብጠርጥሮ ማጤን እንደሚገባ ሲያስገነዝብ፤ “ነገርን አዳምጦ፣ እህልን አላምጦ” ይላል፤ ማህበረሰቡ። እንዲህ ዓይነቱ ይትብሃል አንድን ጉዳይ ከተባለበት አግባብ አኳያ በጥልቀት መመልከት እንደሚገባ የሚያስረዳ ነው። በሌላ አገላለፅ፤ የአንድን ጉዳይ “እማሬያዊ” (ፊት ለፊት የሚታየውን) እና “ፍካሬያዊ” (ውስጠ-ምስጢሩን) መመልከት ተገቢ መሆኑን ያመላክታል።
አበው “ንባብ ይገድላል፤ ትርጉም ያድናል” የሚሉትም ለዚሁ ነው። ‘ምን ማለታቸው ነው?’ ብለን ብንጠይቅ፤ አንድ ጉዳይ በመንግስት አሊያም በማህበረሰቡ አካል ሲነገር፤ “ንባቡን አትመልከት” እያሉን ነው። ፊት ለፊት ያለውን ዝሩውን እውነታ ከመመልከት ይልቅ ወደ ውስጥ ጠለቅ ብለህ በመግባት ምስጢሩን እወቅ እያሉን ነው። እንዲሁም “የጉዳዩን ትርጉም ማየት ያድናል” ጭምር እያሉን ነው። ርግጥም አንድ ጉዳይ ሲነገር፤ የጉዳዩን ጥልቅ ትርጓሜ እንዲሁም የተባለበትን አግባብ በጥልቀት መረዳት ያስፈልጋል። ከላይ ብቻ ያለውን ነገር በመመለከት አንጠልጥሎ መሮጥ ለስህተት ይዳርጋል።
አንድ ትዝ የሚለኝ ታሪክ አለ። ነገሩ እንዲህ ነው።…በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የሀገራቸው መንግስት የሞት ህግን ከህጉ ውስጥ እንዲያወጣ አጥበቀው ይጠይቁ ነበር። በተለያዩ ቀናቶች “የሞት ህግ ሰብዓዊነትን የሚጋፋ ነው፤ ከህጋችን ውስጥ እንዲወጣልን እንጠይቃለን” የሚሉ መፈክሮችን እየያዙ ሰላማዊ ሰልፍም ያደርጉ ነበር።…
….ከሰልፉ በአንዱ ቀንም የሞት ህግን የሚቃወሙ በርካታ መፈክሮችን አንግበው አደባባይ ሲወጡ፤ አንድ ግለሰብ ከእነርሱ ጎን ለጎን ባለው አስፋልት ሲጓዝ ይመለከቱታል። ከቅዳጅ ካርቶንና ከጣውላ የተዘጋጀ መፈክር ይዞ ለብቻው እጁን እያወዛወዘ፣ መፈክር እያሰማ ሲሄድ ይመለከቱታል። ወዲያውኑም “እስቲ ተመልከቱት! ያ ሰው ምን የሚል መፈክር ነው የያዘው?” ይባባላሉ። የሰውየውን መፈክር ጠጋ ብለው አተኩረው ተመለከቱት። እንዲህም ይላል—“ሰዎች የህግን የበላይነት እንዲያከብሩ ሲባል የሞት ህግ ሊኖር ይገባል!”።…የሞት አለመኖርን የሚደግፈው ሰልፈኛው እጅግ በጣም ተቆጣ። መጋል አስፓልቱ ላይ ሁከት ተፈጠረ። “እንዴት ሀገራችን ውስጥ የሞት ህግ ይኑር ይላል?፤ ከእኛ ሃሳብስ እንደምን ይለያል?” በማለት ግለሰቡ የያዘውን መፈክር ቀዳድው ይጥሉታል። በዚህ አላበቁም። ሁሉም የመፈክሩን እንጨት በመያዝ ሰውዬውን እየተፈራረቁ እንደ እባብ አናት አናቱን ይቀጠቅጡት ያዙ።…ብቸኛው በሀገራቸው የሞት ህግን የሚደግፈው ሰውም ድብደባው በዝቶበት ራሱን ሰቶ እስከ መጨረሻው ያሸልባል። የዕለቱ ሰላማዊ ሰልፍም በዚሁ ይደመደማል።…
የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እነዚህ ሰዎች የሳቱት አንድ እውነት እንዳለ መገንዘቡ የሚቀር አይመስለኝም። ይኸውም ራሳቸው የሞት ህግ እንዳይኖር እየተከራከረሩና ለተግባራዊነቱም ሰላማዊ ሰልፍ ጭምር የወጡለት የ“ሞት ይቅር” ህግ ራሳቸው መሻራቸውን ነው። ይህም የሚከራከሩለትን ጉዳይ ከላይ…ከላይ ብቻ በመገንዘባቸው ወይም አበው እንደሚሉት “ንባቡን ብቻ በመመልከታቸው” ሰውን ያህል ነገር በሃሳብ ተለየን ብለው እንዲገድሉ አድርጓቸዋል— “ንባብ” ይገድላልና።
ሰዎቹ የመግደላቸውን “ትርጉም” ቢገነዘቡት ኖሮ፤ ራሳቸው የፈፀሙት “ሀገራችን ውስጥ ሊኖር አይገባውም” ያሉትን የሞት ቅጣት ተግባር ከመከወን ይድኑ ነበር። እናም የፈፀሙትን “ትርጉም” ባለመረዳታቸው ምስኪኑን ግለሰብ ከህይወት ወደ ሞት ምዕራፍ እንዲሸጋገር አድርገውታል። ለዚህም ነው—አበው “ንባብ ይገድላል፤ ትርጉም ያድናል” የሚሉት። እናም “ንባብ” እንዳይድገለን መጠንቀቅ አለብን። “ትርጉም” እንዲያድነንም የጉዳዩን ስረ- መሰረትና የምናደርገውንም እውነታ ጠንቅቀን ማወቅ ይኖርብናል።
ይህን ታሪክ ያስታወስኩት ያለ ምክንያት አይደለም— በቅርቡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከፓርላማ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ “ንባቡን” (የፊት ለፊት ገፅታውን) ብቻ በመመልከት አንዳንድ ወገኖች የተሳሳተ ግንዛቤ በመያዛቸው ነው። ይኸውም እነዚህ ወገኖች “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢህአዴግ አሸባሪ ነው ብለዋል” የሚል “ንባባዊ” ዕይታን በመያዛቸው ነው። በእውነቱ የእነዚህ ወገኖች ምልከታ ከተባለበት አውድ ውጭ ነው። እናም “ትርጉሙን” በሚገባ መገንዘብ ሊገነዘቡ ይገባል ባይ ነኝ።
የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፓርላማ ቀርበው ጥያቄዎች ሲቀርቡላቸው በቴሌቪዥን መስኮት ተከታትያለሁ። እያንዳንዱን ጥያቄዎች በተገቢውና በትክክለኛው መልኩ ምላሽ ሰጥተዋል። ከዚህ ፅሑፍ አኳያ ከፓርላማ አባላቱ የቀረበላቸው ጥያቄ፤ ‘በፀረ- ሽብር ህጉ ላይ የተቀመጠውን አሰራር በተላለፈ ሁኔታ ታራሚዎች ከእስር ተለቀዋል። ይህ ለምን ሆነ?’ የሚል ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም የሽብርተኝነትን አሰራር አንፃራዊነት አብራርተዋል። መከላከያው፣ ደህንነቱና ፖሊሱ በህገ መንግስቱ መሰረት ስለ መደራጀታቸውና አለመደራጀታቸው አጠይቀዋል። ዶክተር አብይ ኢህአዴግ ባለፉት ዓመታት “አሸባሪ ነበር” የሚል “እማሬያዊ” ነገር አልተናገሩም። ርግጥ ንግግሩን በፊት ለፊት ቁመናው የሚያይ ሰው፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢህአዴግ አሸባሪ ነው ብለዋል” ብሎ ሊያስብ ይችላል። ያ ህገ መንግስታዊ መብቱ ነው።
ዳሩ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ጉዳዩ ያሉበትን አውድ (context) መረዳት ያስፈልጋል። እርሳቸው ያሉት ነገር፤ በተለያዩ የመንግስት የኃላፊነት ደረጃዎች ውስጥ (ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ) ስህተት ተከናውኗል፤ ለዚህም መንግስት ኃላፊነቱን ወስዷል ነው። ጉዳዩን በተገቢው ሁኔታ ለማስረዳትም “ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጋችሁ ስትመርጡኝ እዚሁ ቆሜ በይፋ ይቅርታ ጠይቄያለሁ” ብለዋል።
ባለፉት ጊዜያት ለተፈጠረው መዛነፍ ወይም ስህተት መንግስት ኃላፊነቱን ከመውሰዱም በላይ፤ ኢህአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲ የበደለውን ህዝብ እንደሚክስ በይፋ መግለፁ ይታወሳል። ርግጥ ማንኛውም ከዛሬ ሶስት ወር በፊት በሀገሪቱ ታላላቅ ተቋማት (ማለትም በመከላከያው፣ በደህንነቱ፣ በፖሊሱ፣ በፍርድ ቤቶችና በማረሚያ ቤቶች…ወዘተ) የነበረውና ተቋሞቹን በህገ መንግስቱ መሰረት ከፖለቲካ ነፃ አድርጎ የማደራጀት ጉዳይ ጥያቄ የሚያጭር ነው።
ኢህአዴግ በተሃድሶው ወቅት ባሉት መንግስታዊ ተቋማት ውስጥ የተለያዩ ኢ-ህገ መንግስታዊ ተግባሮች ሲፈፀሙ እንደነበር አምኖ ህዝቡን ይቅርታ የመጠየቁ ተገቢነት አያጠያይቅም። የሰለጠነም ፖለቲካ የሚያደርገውም እንዲህ ነው። ርግጥ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉት ሰዎች ግለሰቦች ናቸው። ስህተት ሊፈፅሙ ይችላሉ። ይሁንና ስህተቱ መሰረታዊና ኢ ህገ መንግስታዊ እንዳይሆን ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህም ነው— ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ “ህገ መንግስት በህግ መሠረት የተያዘን ግለሰብ ግረፉ፣ ጨለማ ቤት አስቀምጡ ይላል እንዴ?” በማለት ፓርላማውን መልሰው ሲጠይቁ የተመለከትናቸው። አክለውም፤ “መግረፍ፣ ጨለማ ቤት ማስቀመጥ የእኛ የአሸባሪነት ተግባር ነው” በማለት በመንግስታቸው የተለያዩ መዋቅሮች ውስጥ ሲከናወን የነበረው ተግባር (በተለይም በታራሚዎች ላይ) ከህገ መንግስቱ አግባብ ውጭ መሆኑን አሰረግጠው አስረድተዋል።
ታዲያ ይህ ማለት “ንባቡን” ብቻ ወስዶ በምንም ዓይነት ሁኔታ “ኢህአዴግ አሸባሪ ነው” ብለዋል የሚያሰኝ አይደለም። ሊሆንም አይችልም። ዶክተር አብይ ያሉት ነገር፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት ኢህአዴግና ገዥው ፓርቲ ከህገ መንግስቱ አግባብ ውጭ የአሰራር ስህተት ሲፈፅሙ ነበር ብቻ ነው። አባባሉ “በንባብ” ካልሆነ በስተቀር፤ “በአሸባሪነት ስንንቀሳቀስ ነበር” የሚል ትርጓሜ ሊሰጠው አይችልም። ምክንያቱም ‘በህግ አግባብ የተያዘን ሰው፤ መግረፍ፣ ጨለማ ቤት ውስጥ ማስቀመጥ የእኛ የአሸባሪነት ተግባር ነው’ ማለት የተፈፀመውን ኢ ህገ መንግስታዊ ተግባር ለማሳየት እንጂ፤ ገዥው ፓርቲ በአሸባሪነት ሲሰራ ነበር ማለት ስላልሆነ ነው።
በእኔ እምነት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉት ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ባሉ ማረሚያ ቤቶች ስህተቶች መፈፀማቸውን ነው። ስህተቶቹን ለመጠቆም የፈለጉት፤ ጥያቄው ከታራሚዎች ጋር ተያይዞ የተነሳ ስለሆነም ነው። በዋነኛነት በታራሚዎች ላይ ሲፈፀም የነበረው ተግባር፤ በርካታዎችን የጎዳ፣ የአካልና የሞራል ውድቀት ብሎም የልብ ስብራት ያደረሰ ስለሆነም ነው። ይህን እውነታ ደግሞ ታራሚዎቹ ራሳቸው በሚዲያ ቀርበው ሲገልፁ አድምጠናል።
እናም ስህተትን በስህተት ማረም ስለማይቻል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አባባል የታራሚዎቹ ህገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ በይቅርታና በህግ መለቀቅ አስፈላጊ መሆኑንም ለማመላከት እንጂ፤ “ኢህአዴግ አሸባሪ ነው” ከሚል አኳያ መታየት ያለበት አይመስለኝም።
እንዲህ ዓይነት “ንባብ” የተባለውን ፍሬ ነገር በአግባቡ እንዳንረዳ የሚያደርገን ነው። ጉዳዩን በአውዱ ልክ ካልተረዳነው ደግሞ፤ እኛ ራሳችን ስህተትን በስህተት ወደ ማረም ውስጥ እንገባለን። በዚህ የተሳሳተ እርማት ውስጥም መልሰን እንሳሳታለን። ለነገሩ አሁን የምንገኝበት ወቅት፤ የይቅርታ፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የሰላም እንጂ “አገሌ እንዲህ ነው ወይም ነበር” እያልን ስህተትን በስህተት በማረም ወደ ኋላ የምንሸራተትበት አውድ አይደለም። ፍቅርን፣ ይቅርታንና አንድነትን የሚሰብኩትና የአንድ እጅ ጣቶችን እንኳን በማይሞሉ የወራት ዕድሜ ውስጥም ለውጥ በማምጣት አገራዊ መግባባትን በማስፈን ላይ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይና ድርጅታቸው፤ ትናንትን በትምህርትነት በመቀመርና የነበሩ መዛነፎችን በማቃናት ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ ሊመለሱ አይችሉም።
ርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት ድርጅትም ከቀጣናውና ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ሽብርተኝነትንና ታናሽ ወንድሙን ፅንፈኝነትን ለመዋጋት የተሰለፉ እንጂ፤ “አሸባሪነትን” የሚያነግሱ አይደለም። ያ ቢሆንማ የቀጣናው ሀገራት የመሪነት ብቃታቸውን አምነው አብረው ለመስራት ባልተሰለፉ ነበር።
እናም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የፓርላማ ንግግር “ድርጅቴ አሸባሪ ነው” የሚል አንድምታ ያለው አለመሆኑን የአባባሉን “ትርጉም” መረዳት ይገባል እላለሁ። ያሉትን በደንብ ማድመጥና ማገናዘብ “ንባብ” እንዳይደግለን፣ “ትርጉም”ም እንዲያድነን ያደርጋል። አሊያ ግን ሞትን እንደተቃወሙት ሰዎች፤ “በንባብ” ብቻ የምንቃወመውን “አሸባሪነት” ባልዋለበት ቦታ አውለነው ወደ ስህተት ሊመራን እንደሚችል ማወቅ ይኖርብናል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy