አሳዛኙ ክስተት—ለምን?
ይሁን ታፈረ
በቅርቡ በህገ ወጥ መንገድ በየመን የባህር ጠረፍ በጀልባ ሲጓዙ የነበሩ የ46 ወገኖቻችን በአሳዛኝ ሁኔታ ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸው ልብ ሰባሪ ክስተት ሆኖ አልፏል። ዜጎቻችን እስከ 86 ሺህ ብር እየከፈሉ በህገ ወጥ ስደት ለከፋ አደጋ እየተዳረጉ ናቸው። ያሳዝናል። ያስቆጫልም።
የኢፌዴሪ መንግስትም በኢትዮጵያውያኑ ላይ በደረሰው ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘንም ገልጿል። መንግስት ወደ ስፍራው ሰዎችን በማሰማራት፣ በአካባቢው የሚገኙ ኤምባሲዎችን በማንቀሳቀስ እንዲሁም የመንና አዲስ አበባ የሚገኘው የዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት ጋር በመሆን አደጋውን በቅርበት ሲከታተል መቀየቱ ህዝባዊነቱን የሚያሳይ ነው።
መንግስታችን ባደረገው ክትትል 100 ያህል ኢትዮጵያውያንን የጫነች ጀልባ ከሶማሊያ ቦሳሶ ወደብ ተነስታ ስትጓዝ ካደረች በኋላ፤ ግንቦት 29 ቀን 2010 ዓ.ም የመን የባህር ጠረፍ ላይ ስትደርስ በደረሳባት አደጋ 46 ያህል ኢትዮጵያውያን በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወታቸውን አጥተዋል። እንዲሁም 15 ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም።
ቀሪዎቹ ከአደጋው የተረፉ 39 ኢትዮጵያውያን በአከባቢው የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት ጋር በመተባበር የመን ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ የህክምና ድጋፍ እንዲስጣቸው ተደርጓል።
ታዲያ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልን ስር ነቀል በሆነ መልኩ ለመቅረፍና የድርጊቱን ተዋንያን ለፍርድ ለማቅረብ በመንግስት በኩል በጥናት ላይ የተደገፈ ስራ ለማከናወን አስፈላጊው ሁሉ በመደረግ ላይ ነው። ይህም ከምንግዜውም በላይ በአሁኑ ወቅት መንግስት ለህዝቡ በማሰብ ችግሩን ለመቅረፍ ያለውን ፍላጎት የሚያሳይ ነው።
እንደሚታወቀው ሁሉ በአሁኑ ሰዓት መንግስት በውጪ አገራት በስደትና በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ባሉበት አገር ከመደገፍ ባሻገር እንዲፈቱና ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እያደረጋቸው ያለው ተግባሮች እጅግ የሚያስደስቱ ህዝቡም በኢትዮጵያዊነቱ ኩራት እንዲሰማው ያደረጉ ናቸው። ይህ ሁኔታ ባለበት በዚህ ወቅት አደጋው መድረሱ ህጋዊ ያልሆነ ሰዎች ዝውውር እንቅስቃሴው ምን ያህል ውስብስብና በዜጎች ደህንነት ላይ የተጋረጠ መሆኑን ለመገንዘብ ሚከብድ አይደለም።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው መንግስት ችግሮችን ለመቅረፍና ሀገሪቱ የሁሉም የለውጥ መሰረት እንድትሆን ያለመታከት እየሰራ ነው። ዘላቂ ውጤቶችን ማግኘት እንደሚቻል በትንሽ ጊዜያት ውስጥ እየታየ ነው። ይሁንና ዜጎች ችግሮች ሁሉ በአንድ ጀምበር የሚፈቱ አለመሆናቸውን መገንዘብ አለባቸው።
ምንም እንኳን ችግሩን በመንግስት በጎ ፍላጎት ብቻ መፍታት የማይቻል ባይሆንም፤ በኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራው ብሄራዊ ኮሚቴም ይሁን በየክልሉ የተዋቀሩ አደረጃጀቶች እንቅስቃሴያቸው አጥጋበ ባለመሆኑ ሊጠናከር ይገባል። ምክንያቱም በዜጎቻንን ላይ በቅርቡ የደረሰው አሳዛኝ ክስተት አሁንም ችግሩን ለመቅረፍ መንግስትና ህዝብ ተቀናጅተው በተጠናከረ ሁኔታ መስራት እንደሚኖርባቸው የሚያመላክት በመሆኑ ነው።
ህገ ወጥ ስደት እንዲህ ዓይነቱን እጅግ የሰውን ልጅ እንደ ዕቃ እስከመሸጥና ህይወትን እስከማጣት ድረስ የሚያደርስ ተግባር ነው። ዛሬ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት ህገ መንግስታዊ እውቅና እና ጥበቃ ያለው ነው። ማንኛውም ዜጋ በፈለገው ጊዜና ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራትና ሃብት የማፍራት የማይገሰስ ህገ መንግስታዊ መብት አለው። ይህን ማንም ሊቀለብሰው አይችልም።
ይህን ህገ መንግስታዊ መብት በአግባቡና ህጋዊ በሆነ ሁኔታ መጠቀም ይገባል። አንድ ዜጋ ባሻው ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ስላለው ብቻ ራሱን እስከ ህይወት መጥፋት ለሚደርስ አደጋ ቤተሰቡን ደግሞ ለችግርና ለስጋት አጋልጦ ህገ ወጥ መንገድን መጠቀም የለበትም።
የኢፌዴሪ መንግስት ይህን የዜጎችን እንግልትና ችግር በመመልከት ዜጎች ለስራ ወደ ውጭ ሲጓዙ ከሞት፣ ከእንግልትና ከስቃይ ይላቀቁ ዘንድ ህጋዊ የአሰራር ማዕቀፍን በአዋጅ መልክ አበጅቷል። እንዲያውም ያሉበት አገር ድረስ እየሄደ ጋሻና መከታ መሆኑን አሳይቷል።
መንግስት ባዘጋጀው በዚህ አዋጅ ተመርቶ በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ የስራ ስምሪት ማድረግ ራስን ከአደጋ ቤተሰብን ደግሞ ከሃሳብና ከሰቀቀን የሚታደግ ይሆናል። ይህን አዋጅ ተጠቅሞ በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ መጓዝ የህገ ወጥ ደላላዎችን መንገድ ይዘጋል። በጥቅሉ ህጋዊነትን ተቀብሎ በህግ አግባብ ማንኛውንም ነገር ማከናወን ራስን ከህልፈተ ህይወትና ከውርደት በመጠበቅ የአገርን ክብርም የሚያስጠብቅ ነው።
ያም ሆኖ አሁንም መንግስት በጥናት ላይ የተመሰረተ ተግባርን በማከናወን የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት ብርቱ ጥረት ማድረግ አለበት። እርግጥ ለህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መፍትሔው በመንግስት ተግባሮች ላይ ብቻ የተጣለ አይደለም። ህዝቡም በችግሩ ላይ መምከር ይኖርበታል።
እርግጥም ከህዝቡ የተሰወረ ነገር የለም። ህዝቡ በየአካባቢው የህገ ወጥ ዝውውሩ አቀናባሪና ስደተኞችን ወደ ሞት የሚገፉ አካላት እነማን እንደሆኑ በሚገባ ያውቃል። አሁን ደግሞ በባዕድ ሀገር ውስጥ ህገ ወጥ ስደቶኞችን እንደ ዕቃ መሸጥ ተጀምሯል።
ሰዎችን ወደ ህገ ወጥ መንገድ መግፋት የሚጀምረው እዚሁ አገር ቤት ውስጥ ነው። የአካባቢ ደላሎች በመገኙባቸው ቦታዎች የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨትና በሌሎች ዘዴዎች ለህገ ወጥ ስደር አመቺ ሁኔታ የመፍጠር እንዲሁም ተጋላጭ ግለሰቦችን የመለየት ስራን ከሌሎች ጋር በመሆን ያከናውናሉ።
እነዚህ ህገ ወጦች ህዝቡ ‘እገሌ እና እገሌ’ በማለት ለይቶ ያውቃቸዋል። እናም የኢፌዴሪ መንግስት በጥናት ላይ ተመስርቶ ችግሩን ለመቅረፍ ለያዘው አቋም ህዝቡ በሁሉም መስኮች አስተማማኝ ግብዓት ስለሚሆን የዜግነት ድርኛውን መወጣት ይኖርበታል።
በህገ ወጦች አማካኝነት አንድ ግለሰብ ምን ያህል ገንዘብ ሊያወጣ እንደሚችል ግልፅ ነው። አሁን ባለው መረጃ አንድ ሰው 86 ሺህ ብር ያህል ገንዘብ ይከፍላል። ይህን ገንዘብ ይዞና መንግስት ካመቻቸው አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት በመበደር ህይወትን መለወጥ ይቻላል። በሰው አገር ከንቱ ሆኖ መሞትንም ያስቀራል።
ምናልባት የገንዘቡ ምንጭ ቤተሰብ ወይም ሃብትና ንብረት በመሸጥ የተገኘ ሊሆን ይችላል። ከገንዘብም ይሁን ከህይወትም ሳይኮን ህልምን በአጭሩ የሚቀጭ መንገድ ነው። ታዲያ ችሩን ለመቅረፍ መንግስት በሚያደርገው ጥረት ህዝቡ ሁነኛ የመረጃ ምንጭ በመሆን መስራት ይኖርበታል።