Artcles

አቅም ይፈጥራል፣ ስጋትም ይቀንሳል፤

By Admin

June 05, 2018

አቅም ይፈጥራል፣ ስጋትም ይቀንሳል፤

አባ መላኩ

ሰሞኑን የቀድሞው የኦነግ መስራችና መሪ የነበሩት አሁን ደግሞ የኦዴግ መሪ በሰላማዊ መንገድ ትግሉን ለማካሄድ ወደ አገር ቤት ተመልሰዋል። በቀጣይም ሌሎች ይህን መንገድ እንደሚከተሉ በዕርግጠኝነት መናገር ይቻላል። በዚህ ሂደት በርካታ ኢትዮጵያዊያን  በመንግስት ውሳኔ ተደስተናል፤ ሌሎችም ሃይሎች የኦዴግን መንገድ እንድትመርጡ ተመኝተናል። ጽንፈኛ አሸባሪ ስንላቸው የነበሩ ሃይሎች ወደ ሰላማዊ ትግሉ መመለሳቸው ለአገራችን ተጨማሪ አቅም ከመፍጠሩም ባሻገር ስጋትንም ይቀንሰዋል።

የግንቦት ሰባቱ  መሪ የነበሩትና ሰሞኑን ከእስር  የተፈቱት አቶ አንዳርጋቸው እንዳሉት “ትግላችን የነበረው እንደዶ/ር አብይ አይነት አመራር ወደ ሃላፊነት እንዲመጣ ነበር ይህን በተግባር አይተናል” ብለዋል። ይህ የሚነግረን ነገር ቢኖር በቀጣይ የትጥቅ ትግል ማድረግ አያስፈልግም ማለት ነው።  አዎ ዛሬ አገራችን ፍጽም ተቀይራለች። በፖለቲካ ጉዳይ ፓርቲዎች ሃሳባቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማራመድ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ በአገራችን ተፈጥሯል። ዛሬ ላይ አንተ ግንቦት ሰባት፣ አንተ ደግሞ ኦነግ፣ አንተኛው ኦብነግ ወዘተ የሚል አተያይ እንዳይኖር አዲሱ አመራሮች ሁኔታዎችን  ቀይረውታል። እነዚህ ሃይሎች ወደ ሰላማዊ ትግሉ መመለሳቸው ለህዳሴው ግድብ ስራችን ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ ለውጭ ሃይሎች ተጋላጭነት ስጋትን የሚቀንስ ሆኖ አገኝቼዋለሁ።

የህዳሴው ግድብን  በተመለከተ ቀድሞ ላይ ስጋት ይፈጥርብን የነበረው አንዱ  ጉዳይ የውጭ ሃይሎች በተለይ ኤርትራና ግብጽ የእኛኑ ሃይሎች(በፖለቲካ አኩራፊዎችን)  በመጠቀም በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ በመግባት አገራችንን ይጎዷታል የሚል ስጋት በበርካታ ኢትዮጵያዊያን  ዘንድ ነበረ። ይህን የምንክደው ነገር አይደለም። ይሁንና የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ምህዳር ዛሬ ላይ ፍጹም መቀየር በመቻሉ ሁኔታዎች ወደ መልካምነት በመቀየር  ላይ ናቸው። እድሜ ለጠቅላይ ሚንስትር ለክቡር ዶ/ር አብይ አገራችንን ወደ አንድነት በመሰባሰብ አኩራፊዎችን በሙሉ ወደ አገራቸው እንዲመጡና ሰላማዊ ትግሉን እንዲቀላቀሉ ሁኔታዎችን አመቻችተዋል።  በዚህም ጥሪ መሰረት ቀድሞ ጽንፈኛ ብለን የለየናቸው አካሎች ሳይቀሩ ልዩነቶቻቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማራመድ ወደአገር ቤት በመግባት ላይ ናቸው። ይህ የሚያመላክተን የአገራችን የፖለቲካ ምህዳር  መቀየር በመጀመሩ፤ እንዲሁም ዛሬ ላይ በግብጽ ወይም በኤርትራ በኩል ወደ አራት ኪሎ ለመምጣት የሚፈልግ አካል አለመኖሩን ነው። ይህን ላስገኙት ሃይሎች ምስጋና ይግባቸው ባይ ነኝ።

የአራት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር (ይህ ዋጋ  ምንአልባት አሁን ላይ ይጨምራል ብዬ አምናለሁ) ወጪን የሚጠይቅ ፕሮጀክት በራስ አቅም  ለመገንባት መንግስት ሲነሳ ህብረተሰቡን ተማምኖ እንጂ በራሴ አቅም እወጣዋለሁ ብሎ አይደለም፤ በዕርግጥም  የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ ኢትዮጵያዊያኖች ከመንግስት ጎን መቆም በመቻላቸው ይህ ግድብ ዛሬ ላይ ወደ 66 በመቶ  አካባቢ ደርሷል። አንድ ታዳጊ አገር በራሷ የውስጥ አቅም ብቻ እንዲህ ያለ ባለ ብዙ ቢሊዮን ዶላር ወጪን የሚጠይቅ ፕሮጀክት እውን ማድረጓ የፕሮጀክቱን ህዝባዊ ድጋፍ የሚያሳይ ነገር ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ  የምታራምደው አቋም ወጥነት ያለውና ሁሉንም የተፋሰሱን አገራት ጥቅም የሚያስጠብቅ አቋም ነው። “ፍትሃዊ  የሃብት ተጠቃሚነት” የሚል መርህን ነው።  አንዳንዶች ይህን ግድብ ለማሳነስ ሲሉ እንደኢትዮጵያ ያለ ደሃ አገር ይህን አይነት ትልቅ ፕሮጀክት የመገንባት አቅም  ስለማየኖራት ጥራቱ ላይ ችግር ይገጥመዋል ይሉ እንደነበር እናስታውሳለን። ይሁንና ኢትዮጵያ ከአራት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ የምትገነባው የህዳሴ ግድብ ዓለም ዓቀፍ ደንብና ስታንዳርዱን የተከተለ እንደሆነና፣ ታዋቂና ልምድ ባለው   የጣሊያኑ ሳሊኒ ኩባንያ እንዲከናውን አድርጋለች። ኢትዮጵያ ይህን ያደረገችው የግድቡን ደረጃ ከፍ እንዲልና ሌሎች አገሮች በግድቡ አመኔታ እንዲያተርፉ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን፤ አገሪቱ ይህን ያህል እጅግ ከፍተኛ በሆነ ወጪ በማድረግ የገነባችው ግዙፍ ፕሮጀክት አስተማማኝ  ደህንነትና ዋስትና እንዲኖረው ለመድረግ ጭምር ነው።

እስካሁን  የነበሩት ኢትዮጵያ  መንግስታት በአገር ውስጥ  ችግር ይኖርባቸው እንደሆን እንጂ  ለጎረቤት አገራት ከዚያም አልፎ ለአፍሪካ አገራት ጥቅም ሲሰሩ ኖረዋል። ለአፍሪካ ነጻነት ትግል እስከ አፍሪካ አንድነት ምስረታ እንዲሁም ለአፍሪካ ሰላም መከበር  ኢትዮጵያዊያኖች ከፍተኛ መሰዋዕትነት ከፍለናል፤ በመክፈልም ላይ ነን። አሁን ላይ ኢትዮጵያ የአካባቢውን ሰላም ዘላቂነት ለማረጋገጥ አገሮች በዘላቂ ልማት እንዲተሳሰሩ በመስራት ላይ ነች።  ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብም አንዱ የአካባቢው አገራትን በልማት የማስተሳሰር አንዱ ፕሮጀክት ነው። አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብም ኢትዮጵያ ለቀጠናው  አገራት ያበረከተችው ስጦታ አድርገው ይገልጹታል። ምክንያቱም ይህ ግድብ ከኢትዮጵያ ባሻገር ለታችኞቹ የተፋሰስ አገራት የሚበጅ ሆኖ ሳለ የግድቡ ወጪ ግን ሙሉ በሙሉ የሚሸፈነው በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት መሆኑ  ነው።

 

ኢትዮጵያ ደሃ ትሁን እንጂ  ጠንካራና ተባባሪ ህዝብ ያላት አገር ናት። ለዚህ ጥሩ ማሳያው ደግሞ  ይህን ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚጠይቅ ፕሮጀክት በራስ ወጪ መሸፈን መቻሏ ነው።  አሜሪካን የምታክል አገር የሆቨር ግድብን ስትገነባ ወጪው የተሸፈነው በብድር እንደሆነ  መረጃዎች ያመላክታሉ። ይህ ፕሮጀክት ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገር ኢትዮጵያዊያኖችን በአንድ ጥላ ስር  ማሰባሰብ ችሏል። ታላቁ የህዳሴ ግድብ “የይቻላል” መንፈስን በኢትዮጵያዊያን ዘንድ እንዲፈጠር፣ አገራዊ መግባባት እንዲጎለብትና የአገራዊ የገጽታችን እንዲሻሻል ያደረገ  ታላቅ ፕሮጀክት ነው። በዚህ ፕሮጀክት ላይ ከአዋቂ እስከ ህጻን፣ ከምሁር እስከ አልተማረው፣ ከሃይማኖት መሪው እስከ ምዕመኑ፣ አገር ቤት ከሚኖረው እስከ ዳያስፖራ ወዘተ አሻራውን በዚህ ፕሮጀክት ላይ ያላሳረፈ አገር ወዳድ ዜጋ የለም። ዛሬ በአገራችን በርካታ ስራዎች እይተከናወኑ ቢሆንም እንደህዳሴው ግድብ የህብረተሰቡን  ቀልብ የገዛ ፕሮጀክት የለም።

 

በተደጋጋሚ ሲገለጽ እንደነበረው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ከኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫነት በዘለለ ለመስኖ የሚያገለግል ፕሮጀክት አይደለም። በዚህ ፕሮጀክት ሳቢያ የአባይ ውሃ  ሊቀንስ አይችልም። ምክንያቱም ይህ ፕሮጀክት በሚካሄድበት የኢትዮጵያ አካባቢ ለመስኖ የሚውል መሬት እዚህ ግባ አለመሆኑን ግብጻዊያኖች ጠንቅቀው ያውቁታል። አባይ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊያገለግል የሚችለው ለሃይል ማመንጫነት እንጂ   ለመስኖ የሚውልበት ሁኔታ እጅግም ነው። ይህ በመሆኑም በውሃው ላይ የሚፈጥረው ጫና የለም። ኢትዮጵያ ከዓለም አገራት ዝቅተኛ የሚባል የሃይል አቅርቦት ያላት አገር ናት።

አንድ መቶ ሚሊዮን ህዝብ ያላት አገራችን አሁን ላይ  4,315 ሜ.ዋ. ያለዘለለ የሃይል አቅርቦት እንዲሁም ኢትዮጵያን የሚያክል የቆዳ ስፋት ያላት አገር  15,872 ኪ.ሜ. የሃይል ማስተላለፊያ መስመር ብቻ ነው ያላት፡፡ ይህ አሃዝ የሚነግረን የዜጎች የነፍስ ወከፍ የኤሌክትሪክ ድርሻ  በዓለም ዓቀፍ መስፈርት መሰረት እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን ነው። ይህን ለማሻሻል መንግስት በርካታ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ የገኛል። የባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል    GTP2 አፈጻጸምን በተመለከተ ሰሞኑን ግምገማ በመካሄድ ላይ ነው። በግምገማው ላይ እንደተገለጸው ኃይል ማመንጫ ግንባታዎችን በተመለከተ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አሁን ላይ  65 ነጥብ ስምንት ደርሷል። የGTP2 አፈጻጸም የተፈለገውን ያህል እንዳልሆነ መካድ አይቻልም። ይሁንና አገራችን ይህን ማሳካት የቻለችው በከፍተኛ ቀውስና ድርቅ ውስጥ ሆና እንደሆነ ለተገነዘበው ውጤቱ ደካማ ነው ማለት አይቻልም። በቀሪዎቹ ሁለት ዓመታት ለማካካስ  ሁላችንም ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ዛሬ ላይ ሁኔታዎች በመቀየር ላይ ናቸው ቀድሞ ጽንፈኛና አሸባሪ ብለን የለየናቸው ሃይሎች ወደ ሰላማዊ ትግሉ መመለስ መጀመራቸው ለአገራችን ተጨማሪ አቅም ከመፍጠሩም ባሻገር ስጋትንም ይቀንሳል። እነዚህ ሃይሎችም ከመንግስትና ህዝብ ጋር በመተባበር  አገራችን ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ የምታደርገውን ጥረት መደገፍ ይኖርባቸዋል።