Artcles

አጋርነቱ

By Admin

June 30, 2018

አጋርነቱ

                                                  ታዬ ከበደ

በቅርቡ በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ማይክ ሬነር ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ እየወሰዷቸው ባሉ አዎንታዊ እርምጃዎች በእጅጉ ተበረታትተናል ብለዋል። አምባሳደሩ ኢትዮጵያ አሳሳቢ ለሆኑ ጉዳዮች ምላሽ ለመስጠት እያደረገች ያለችውን ጥረት ለመደገፍ አገራቸው የምትችለውን ሁሉ እንደምታደርግም አስታውቀዋል።

እንዲሁም አገራቸው እስካሁን ድረስ ከኢትዮጵያ ጋር በቀጠለው አጋርነት እንዲሁም በይበልጥ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም ሲባል አገሪቱ ጠንካራ፣ የተረጋጋችና የበለፀገች ብሎም ስኬታማ እንድትሆን መሆኑን ገልጸዋል። ይህ የአምባሳደሩ ገለጻ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውንና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ጠንካራ ግንኙነትን የሚያሳይ ነው። በተለይም የአገራቱን ጠንካራ የዲፕሎማሲ ትስስር የሚያመላክት ነው ማለት ይቻላል።

እርግጥ ኢትዮጵያና አሜሪካ ከ115 ዓመታት በላይ የዘለቀ ወዳጅነት ያላቸው አገራት ናቸው። ወዳጅነታቸው በሁሉም መስኮች ነው። በተለይም አገራችን በምስራቅ አፍሪካ ሽብርተኝነትን ለማክሰም በሚደረገው ትግል የአሜሪካ ዋነኛ አጋር ናት። ለበርካታ ጊዜያት ከአሜሪካ ጋር በቁርኝት ስትሰራ ቆይታለች።

ይህ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ነው። ለዚህ ጠንካራ ግንኙነት መፈጠር አገራችን በተለይም በዶክተር አብይ አህመድ አጭር የስልጣን ዘመን የተገኙት ለውጦችና ሁሉን አቀፍ የዲፕሎማሲ ትብብሮች ይመስሉኛል።

አሜሪካኖች የረጅም ጊዜ ወዳጆቻችን በመሆናቸው የአገራችን ህዝቦች ባለፉት ስርዓቶች ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ባይተዋር እንደነበሩ ያውቃሉ። ያኔ ሰብዓዊ መብቶች በአገራችን ይከበር የነበረው ለገዥዎች እንጂ ለህዝቡ አይደለም።

ህዝቡ በገዛ ሀገሩ ሰብዓዊ መብቶቹ ተጥሶበት፣ ሰው መሆኑም ሳታወቅ እጅግ ዘግናኝ ሁኔታዎችን እንዳሳለፈም ያውቃሉ። ይህ ሁኔታም ህዝቦች አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲጓዘ ያስችላቸው ዘንድ ለትግል ያነሳሳቸው ጉዳይ እንደነበር ይገነዘባሉ። አሁን ያለውንም ለውጥ ያውቃሉ።

በተለይ ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን በመጡበት አጭር ጊዜ ውስጥ ህዝቦች ራሳቸው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን መጎናፀፍ እንደቻሉም ይረዳሉ። የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር አለመኖር በመሆኑና ይህ የአገራችን ህዝቦች የዘመናት ጥያቄ በአሁኑ ወቅት በቂ ምላሽ እያገኘ ነው። እነዚህ መብቶች የራሳቸው ተግዳሮቶች ቢኖሩባቸውም፣ ችግሮች በሂደት የተፈቱ ሰብዓዊ መብቶች በተሻለ ሁኔታ እንዲተገበሩ የለውጡ ሂደት ፈር ቀዳጅ መሆኑንም ይገነዘባሉ።

በጥቂት ወራቶች ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄዱት ሰላማዊ ሰልፎች በአገራችን ውስጥ የሚታየው ተደራጅቶ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን የሚያመላክትና ለፖለቲካ ሂደቱ አዲስ መንገድ በሂደት እየታየ መሆኑን ስለሚገነዘቡ ከወዳጅነታቸውና ከአጋርነታቸው አኳያ ለውጡን ለመደገፍ አሜሪካ ቁርጠኛ መሆኗ ተገቢ ይመስለኛል።

አገራችን ውስጥ ዛሬም ሊፈቱ ተግዳሮቶች ቢኖም የዜጎችን ሁለንተናዊ መብት ማክበርና ማስከበር ትልቅ እመርታ ተገኝቷል። እርግጥ ዛሬ እዚህ ሀገር ውስጥ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እየተከበረና የፖለቲካ ምህዳሩም ሁሉንም በሚያሳትፍ መልኩ እየተቃኘ መሆኑ ይታወቃል። ይህን ተጨባጭ እውነታ መደገፍ ከአንድ አጋርና ተባብሮ ከሚሰራ ወዳጅ አገር የሚጠበቅ ተግባር ነው።

አሜሪካኖች የሁለትዮሽ ግንኙነቱን የፈጠሩት ኢትዮጵያን በሚገባ ስለሚያውቋት ሀገራችን በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደትና በልማት ላይ ማተኮርዋን ስለሚገነዘቡ፣ በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን ጂኦ- ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ስለሚያውቁ፣ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እየተጫወተች ያላችውን የላቀ ሚና ስለሚረዱ እንዲሁም በዓለም አቀፍና በአህጉር ደረጃ ያላትን ተቀባይነት ስለሚያጤኑ ነው።

እነዚህ የመንግስታችንና የህዝባችን የማንነት መገለጫዎችና ቁልፍ ተግባራት የአሜሪካ መንግስትም ፍላጎቶች በመሆናቸው፤ የሁለትዮሽ የጋራ ተጠቃሚነት ግንኙነቱ የማዕዘን ድንጋይ ሆነው አብረው በመስራት ላይ ናቸው።

እነዚህ የግንኙነት መሰረቶች በእኩልነት ላይ በተመረኮዘ ሚዛናዊ ተጠቃሚነት ላይ የሚያተኩቱ ናቸው። የአሜሪካ መንግስት ዶክተር አብይ የያዙትን የለውጥ መንገድ በመደገፍ ሁሉንም የሚያሳትፍ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሀገራችን ውስጥ እንዲገነባ ድጋፍ እያደረገ ነው።

እርግጥ አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ አጋር አገራት በአገራችን ውስጥ ዴሞክራሰ እንዲሰፋ ይደግፋሉ። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ መንግስትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ዴሞክራሲውን ለማስፋት በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል።

በተለይም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከሚወክሉት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በአገር ውስጥ ውይይት እያደረገ ነው። በውጭ ነፍጥ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችም ወደ አገር ቤት ገብተው በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ እየተሰራ ነው።

ሚዲያዎችም ያለ ገደብ የህዝቡ ዓይንና ጆሮ ሆነው እንዲሰሩ ተፈቅዷል። ቀደም ሲል ታገደው የነበሩ እጅግ በርካታ ድረ ገፆችና ጣቢያዎች ተከፍተዋል። ወደ አገር ቤት እንዲገቡም ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥሮላቸዋል።

ምንም እንኳን የዴሞክራሲ ግንባታ በአንድ ጀምበር የሚከናወን ባይሆንም፤ የኢፌዴሪ መንግስት በአጭር ጊዜ ውስጥ ያከናወናቸው የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት ስራ ስር እንዲሰድ እያደረገ ነው። ይህም እዚህ ሀገር ውስጥ ዴሞክራሲንና ልማትን የሚያፋጥን እርምጃ ነው።

የአሜሪካ መንግስት በአገራችን የኢንቨስትመንት ስራ ውስጥ ለመሳተፍ ፍላጎቱን በቅርቡ ገልጿል። ይህም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ባስገኙት አንፃራዊ ሰላም እምነት ስላደረበት መሆኑ ግልጽ ነው።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካና በአፍሪካ ያለት ተጽዕኖ ፈጣሪነትና የመሪነት ሚናን አሜሪካ ስለምትገነዘብ ግንኙነቱ በአሁኑ ሰዓት የበልጥ ጠንካራ እንዲሆን አድርጎታል። በመሆኑም በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ስለ ሁለቱ አገራት የጋራ ትስስርንና አጋርነትን አስመልክተው የተናገሩት እውነታ ከላይ የጠቀስኳቸውን ጉዳዩች በመመርኮዝ ይመስለኛል።