Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እነሆ አስረጅዎቹ…

0 303

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እነሆ አስረጅዎቹ…

                                                      ቶሎሳ ኡርጌሳ

ግንቦት 20ን የድል በምታከብርበት ወቅት የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያስተላለፏቸውን ‘የእንኳን አደረሳችሁ’ መልዕክቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩና መንግስታቸው በዓለም አቀፍና በአካባቢው ሀገራት ያላቸውን ተቀባይነት ምን ያህል እየጎላ መምጣቱን ማሳያ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ለአብነት ያህል፤ የዓለም ልዕለ ኃያሏ ሀገር አሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ በፊት በአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ዘንድ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ለመጀመሪያ ጊዜ የግንቦት 20 ድል በዓልን ምክንያት በማድረግ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው አማካኝነት ያስተላለፉትንና በበርካታ መገናኛ ብዙሃን የተሰራጨው መልዕክት በይዘቱ በለውጥ ላይ አተኩሮ እየሰራ ላለው የኢፌዴሪ መንግስት ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደሚሰጡ መናገራቸውን መግለፅ ይቻላል።

በተጨማሪም የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀገራቸው ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ቃል መግባታቸውን እንዲሁም ጂኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጥ አኳያ በአትዮጵያ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ማሳረፍ ከሚችሉ ሀገራት መካከል የኩዌቱ ንጉስ፣ የግብፁ ፕሬዝዳንት፣ የሳዑዲ ዓረቢያው ንጉስ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬት ሱልጣን የላኳቸው መልዕክቶች ተጠቃሽ ናቸው። እንዲሁም የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር “ኢትየጵያ የምትረዳን የጎረቤት ሀገር ብቻ ሳትሆን ሀገራችንም ናት” ሲሉ መናገራቸው፤ ‘ካለ ኢትዮጵያ ሰላምና ዕድገት አይሆንልንም’ ማለታቸው እንደሆነ ስንገነዘብ የሀገራችን ፖለቲካዊ አመኔታ እስከየት ድረስ እንደዘለቀ ለማወቅ አስቸጋሪ አይደለም።

ታዲያ የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት፤ ሀገራችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከውጭ ሀገራት ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየተጠናከረ ለመምጣቱ አስረጅ ነው ማለት ይቻላል። ከላይ የጠቀስኳቸው እውነታዎች የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬት እየተጠናከረ ለመሆኑ ማሳያ ብቻ ሳይሆኑ፣ በዚያው ልክም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና መንግስታቸው በዓለም አቀፉም ይሁን በጎረቤት ሀገሮች ዘንድ ያላቸውን  ተቀባይነትንና አመኔታን በግልፅ የሚያሳዩ ናቸው።

ርግጥ ይህ ተቀባይነት ዝም ብሎ የተገኘ አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩና መንግስታቸው ከሁለት ወራት በማይዘልቅ ዕድሜ ውስጥ በሀገር ቤት ባከናወኗቸው ተግባሮች በዜጎች ውስጥ እየተፈጠረ ያለው የአንድነት ስሜት ነው። የሀገር ውስጥ የቤት ስራዎቻችንን በአንድነትና በኢትዮጵያዊነት ስሜት ማከናወን ከተቻለ፣ የውጭ ግንኙነታችን በዚያው መጠን የሚያድግና ተቀባይነታችንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ እንደሚሄድ ከላይ በማሳያነት ያቀረብኳቸው አብሮ የመስራትና የተቀባይነት ሁኔታችን እንደሚጨምር ማረጋገጫዎች ናቸው።

ዛሬ የምዕራቡን ዓለም ቀልብ በመግዛት የዓለም ሃያላን ሀገራት በሮቻችንን እያንኳኩ ነው። የሚያንኳኩት በር፣ የሰላምና የእርቅ እንዲሁም የተስፋ ማዕድ ያለበት መሆኑን በሚገባ ይገነዘባሉ። ከሁለት ወራት በፊት በተለያዩ ምክንያቶች ሀገራችንን ለመመልከት ፍላጎት ያልነበራቸው አሊያም ‘የኢትዮጵያ ጉዳይ ያሳስበናል’ በማለት ሃሳባቸውን የሚገልፁ ልዕለ-ሃያላን ሀገራት፤ ዛሬ ‘ለኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት ድጋፍ እናደርጋለን፤ በቅርበት አብረንም እንሰራለን’ በማለት እየገለፁ ነው።

ይህ ማንነታቸው በአዲስ መልክ የተገነባው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በሁለት ወራት ውስጥ በሀገር ቤት ከህዝብ ጋር ፊት ለፊት በመገናኘት ያደረጉት ውይይት የፈጠረው ሀገራዊ ድባብ፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ያደረጓቸው ስምምነቶችና በቀጣናውና በአፍሪካ ጉዳዩች ዙሪያ ያላቸው የጋራ ተጠቃሚነት መርህ መሆኑን በርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በአዲስ መልክ የተቀየደው የሰላም አውድና ህዝቡም በዶክተር አብይ ላይ ያሳደረው ከፍተኛ አመኔታ የለውጡ ሂደት እምብርት ተደርጎ የሚቆጠር ነው። ህዝብ እምነት የጣለበት ማንኛውም መሪ ለውጥ ያመጣል። ዶክተር አብይ ህዝብ እዚህ ሀገር ውስጥ ለውጥ ያመጣሉ ብሎ አመኔታ የጣለባቸው መሪ ናቸው።

ታዲያ ይህን አመኔታና ተቀባይነት የተመለከቱት ሃያላን ሀገራት ‘አብረን እንስራ’ ማለታቸው የሚገርም አይደለም። ምክንያቱም ህዝብን በአግባቡ አሳምኖና አደራጅቶ በአንድ መንፈስ ለልማት የማንቀሳቀስ ብቃት ያለው መሪ ምን ያህል ሀገርን የመለወጥ አቅም ሊኖረው እንደሚችል ስለሚገነዘቡ ነው። ዴሞክራሲው በአዲስ መልክ ምህዳሩ እየሰፋና ማናቸውም ዓይነት ሃሳቦች እንዲንሸራሹ እንዲሁም ቀደም ባሉት ጊዜያት በአሸባሪነት የተፈረጁና በውጭ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ወደ ሀገር ቤት ገብተው ሃሳባቸውን እንዲያንሸራሽሩ መፈቀዱ የምህዳሩ ልኬታ እስከየት ድረስ ሊዘልቅ እንደሚችል ማሳያ ነው። ዘመኑ አንድ ዓይነት መረጃ እንደ ወራጅ ውሃ የሚፈስበት ሳይሆን፣ የተለያዩ የመረጃ ዘውጎች የሚሰሙበት በመሆኑ ይህን እውነታ መንግስት ከግምት ውስጥ አስገብቶ ሚዲያዎቹ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጋቸው ዴሞክራሲውን ለማስፋት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያመላክት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ እዚህ ሀገር ውስጥ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከበር መንግስት ተጨባጭ ማስረጃ ያልተገኘባቸውን ወገኖች ከእስር እንዲፈቱ ማድረጉ ብሔራዊ መግባባትን ከመፍጠር ባሻገር፣ የዜጎችን እንግልትንም የታደገ ነው። እነዚህ ሁሉ ሀገራዊ ለውጦች በልዕለ ሃያላኑ ሀገራት ተፈላጊ እንድንሆን ያደረጉን ከመሆናቸውም በላይ፣ እኛ ኢትዮጵያዊያን ከሁከትና ከብጥብጥ ወጥተን ወደ ተጀመረው ልማት በሙሉ ልብ መግባት የምንችል ህዝቦች መሆናችንን የሚያመላክቱ ናቸው።

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማርዲያት ሀገራችን ውስጥ በነበራቸው የጉብኝት ቆይታ “ኢትየጵያ የምትረዳን የጎረቤት ሀገር ብቻ ሳትሆን ሀገራችንም ናት” በማለት መናገራቸው፣ አዲሲ ሀገር ደቡብ ሱዳን ልማቷና ሰላሟ ያለ ኢትዮጵያ እንደማይሆንላት መግለፃቸው ይመስለኛል። ርግጥ ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳንን ሁኔታ ከኢጋድ ጋር በመሆን በቅርበት እየተከታተለች ነው።

ወንድም የሆነው የደቡብ ሱዳን ህዝብ ከስደትና ከእንግልት ተላቅቆ ወደ ሰላም መንገድ እንዲመለስ ኢትዮጵያና ኢጋድ በከፍተኛ ሁኔታ እየሰሩ ነው። በደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና በምክትላቸው ዶክተር ሪክ ማቻር ሳቢያ እያሰለሱ የሚከሰቱት ግጭቶች በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈት የዳረጉና በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ደግሞ የስደት ሰለባ ያደረጉ መሆናቸው ይታወቃል። ይህ ደግሞ ሀገራችንን ጨምሮ ሰላም ወዳድ ኃይሎችን በአያሌው ማሳሰቡ አልቀረም። ሀገራችንም እስካሁን ድረስ እያካሄደች የነበረውን ብርቱ ጥረት ከኢጋድ ጋር ሆና በተጠናከረ ሁኔታ እንድታካሂድ ግድ ብሏታል።

ምንም እንኳን የኢፌዴሪ መንግስት ከመነሻው ጀምሮ ለደቡብ ሱዳን ሰላም መስፈን እስከ ዛሬ ድረስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ቢሆንም፤ በዶክተር አብይ የስልጣን ዘመን ሁለት ወራት ውስጥ ይህን ጥረቱን አጠናክሮ ቀጥሎ ሁለቱን ተቀናቃኞች (ማለትም ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርንና ዶክተር ሪክ ማቻርን) ፊት ለፊት ለማገናኘት የውሳኔ ሃሳብ በኢጋድ በኩል እንዲተላለፍ አድርጓል። የውሳኔ ሃሳቡ የሁለቱም ተቀናቃኝ ወገኖች ይሁንታ ያለበት በመሆኑ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል ተደርጎ መወሰድ የሚችል ነው።

ምን ይህ ብቻ። ቀደም ባሉት ጊዜያት ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን የሰላም አስከባሪ ሃይል አዋጥታቸል። ይህ ሃይል በደቡብ ሱዳን ውስጥ የተሻለ ሰላምን ለመፍጠር እየሰራ ነው። እስላሁን ድረስም በዚያች ሀገር በመፈፀም ላይ የሚገኘውን የህዝቦች ሰቆቃ በማስቆም ረገድ ጉልህ ሚና እያበረከተ ነው። እናም ከእነዚህ ጥቅል እውነታዎች በመነሳት ፕሬዚዳንት ኪር ዐያለ ኢትዮጵያ አይሆንልንም’ ማለታቸው ትክክል ይመስለኛል።

በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በሃያላኑም ይሁን በጎረቤት ሀገሮች ያላት ተቀባይነት እየጨመረ መምጣቱ ሀገራችን የምትገኝበትን የሰላም አውድ እንዲሁም አንድ ስንሆን ተስፋ ኖረን ከእኛ ባለፈ ሌሎችንም ልንጠቅም እንደሚችል የሚያሳይ ነው። እናም ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገኘው የተቀባይነትና የአመኔታ አውድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዜጎች ሰላማቸውን በመጠበቅ ውስጣዊ አንድነታቸውን ይበልጥ ማጠናከር ይኖርባቸዋል። የተፈላጊነታችን ምስጢሩ በሀገር ውስጥ የምናከናውናቸው ሁለንተናዊ ለውጦች ናቸውና።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy