Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እናስታውስ…!

0 559

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እናስታውስ…!

ገናናው በቀለ

የኢትዮጵያ መንግስት ከዜጎች የሚሰበስበውን ግብር መልሶ ለህዝብ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎት የሚያውል ነው። መንገዶች፣ የጤና ኬላዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች…ወዘተ በየጊዜው የሚሰሩት ከየትም በመጣ ገንዘብ አይደለም፤ ከህዝቡ በሚሰበሰብ ግብር እንጂ።

ከግብር አከፋፈል ጋር ተያይዞ ባለፉት ዓመታት በተከሰቱ ልዩ ልዩ ችግሮች ሳቢያ መንግስት ተገቢውን ግብርና ገቢ ሊሰበስብ አልቻለም። ይህም ሊሰሩ በታሰቡ የልማት ዕቅዶች ላይ የበኩሉን አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፏል። ታዲያ ዘንድሮም ይህ ችግር ሊደገም አይገባም።

ዜጎች ግብር በመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል። ግብር መክፈል የአገርን ኢኮኖሚ የሚያሳድግና የዜጎችን ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው። ግብር ከፋይ መሆን ማንኛውንም የመንግስት አገልግሎቶችን በመብትነት መጠየቅ ያስችላል።  

ከዚህ በተጨማሪ ግብር መንግስት ለህዝቡ የሚጠቅሙ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባትና ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑ ሁኔታዎችን በመፍጠር የስራ ዕድልን የሚያስፋፋ ነው። ግብርን መክፈል እነዚህን አገራዊና ዜጋዊ መብቶችን የሚያጎናጽፍ ነው።

ስለሆነም በአሁኑ ሰዓት የግብር መክፈያ ወቅት በመድረሱ ዜጎች ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው። ግብር መክፈል ራስን መጥቀም መሆኑን በማስታወስ ልንዘጋጅ ይገባል። ምክንያቱ የአገራችን ኢኮኖሚ የሚገነባውና የሚያድገው ዜጎች በምንከፍለው ግብር ስለሆነ ነው።

መንግስት በአሁኑ ሰዓት የታክስ ስርዓቱን በማዘመን ግብርን በወቅቱ ለመሰብሰብ ተዘጋጅቷል። ህዝቡም የሚጠበቅበትን አገራዊ መብትና ግዴታ ለመፈፀም መዘጋጀት ይኖርበታል። እንደሚታወቀው ሁሉ መንግስት የታክስ ስርዓቱን በማሻሻል ከታክስ የሚሰበሰበው ገቢ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የማድረግ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። የታክስ ስርዓቱን የማሻሻል ስራ በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ በማድረግ የግብር ከፋዩ ገቢና ንብረት በትክክል የሚታወቅበት፣ ህጋዊ ዕውቅናና ጥበቃ የሚያገኝበት ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት ተዘርግቷል።

ይህም የጉምሩክ ስርዓቱ ልማታዊ ባለሃብቱን ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግ የታለመ ነው። በዚህ መሰረትም የሽያጭ ማሽኖችን መጠቀምና ግብይት የማካሄድ ስራ በሁሉም የንግድ ማህበረሰብ አካላት ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፤ ውጤት እየተገኘበት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የተጀመረው የከተማ መሬትና በመሬቱ ላይ ያለውን ንብረት በዘመናዊ መረጃ ሥርዓት የመመዝገብና የማወቅ፣ በመሬቱ ላይ ማን ምን መብት እንዳለው የተሟላና ወቅታዊ መረጃ የመያዝ፣ ህጋዊ ዕውቅናና ጥበቃ እንዲያገኙ የማድረጉን ስራ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል። ከዚህ መረጃ በመነሳትም መሬት ይበልጥ ልማታዊ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውልና በዕቅድ የሚመራ የመሬት አቅርቦት ስርዓት እንዲኖር ርብርብ እየተደረገ በመደረግ ላይ ይገኛል።

መሬትን ጨምሮ የንብረት መረጃና የንግድ እንቅስቃሴ መረጃ ስርዓት መፍጠር በኢኮኖሚና በፖለቲካው መስክ ግልፅነትንና ተጠያቂነትን በማስፈን ረገድ የሚጫወተውን ሚና ከግምት ውስጥ በማስገባት ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተከናውነዋል። ባለፉት ዓመታት እነዚህ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ነበሩ።

እርግጥ እነዚህ በመጠኑ ለመጠቃቀስ የሞከርኳቸው መንግስታዊ ስራዎች ያለ ገንዘብ የሚከናወኑ አይደሉም። የአገር እቅድ ስለሆኑ ብቻ በራሳቸው ተፈፃሚ አይሆኑም። ተግባሮቹን ተፈፃሚ ለማድረግ ዜጎች ግብር መክፈል ይኖርባቸዋል።

የግብር አሰባሰብ ዓላማው እነዚህን ማሳያ ጉዳዩችና ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀከቶችን በማሳካት ህዝቡን መጥቀም የሚችል ጠንካራ መንግስት እንዲሁም አገር እንዲኖረን ለማድረግ የታሰበ ነው።

ግብርን በወቅቱ  አለመክፈል መልሶ የሚጎዳው እኛን ነው። መንግስት በህዝብ ይሁንታ ህዝቡን ለማገልገል የተመረጠ እንደመሆኑ መጠን፤ ግብር ካላገኘ ለዜጎቹ የተለያዩ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች የሚሰጠው ምላሽ ሊኖር አይችልም። ግብር መክፈል መልሶ መብትን ለመጠየቅ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ፤ ልማታዊው መንግስትም አገራችን እንድታድግ ዋነኛው መሰረቱ ህዝባችን ነው በማለት ለላቀ የልማት ክንዋኔ እንዲነሳሳ ያደርገዋል።

ግብር ከፋይ ዜጋ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመረጠውን መንግስት አገልግሎት አሰጣጡን በተገቢው መንገድ ሊጠይቅ ይችላል። “እኔ እኮ ግብር ከፋይ ነኝ” ብሎ ማናቸውንም ግልጋሎት የማግኘት መብቱንም ይጎናፀፋል።

ሆኖም እንደ እኛ ባለ አገር ውስጥ ግብር መክፈል የአገርን ኢኮኖሚ ለማረጋጋት፣ ኢኮኖሚው ጠንካራ እንዲሆንና ለህዝብ የሚሰራ መንግስት እንዲኖር ያደርጋል። እናም ኢትዮጵያ ውስጥ ግብር መክፈል የዜግነት ክብር ማረጋገጫ እንጂ ግዴታ ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለዜጎቿ ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠርና የተጋረጠባትን የድህነት ፈተና ለመሻገር ብርቱ ጥረት እያደረገች ትገኛለች። ይህምን ጥረቷን እውን ለማድረግም በቂ በጀት ያስፈልጋታል። ይህ በጀት ደግሞ ከየትም የሚመጣ አይደለም። ህዝቡ ለመንግስት ከሚከፍለው ግብር መሆኑ ይታወቃል።

አገራችን ውስጥ ያለው መንግስት ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ እንደመሆኑ መጠን፤ የግሉ ባለሃብት በቂ ሁኔታ ሊፈፅማቸው የማይችላቸውን ጉዳዩች መንግስት በተመረ አኳኋን ጣልቃ ገብቶ ይፈፅማል። ታዲያ ይህን ተግባር ለመከወን መንግስት ገንዘብ ያስፈልገዋል። የግሉ ባለሃብት በማይሰማራባቸው፣ ነገር ግን አብዛኛውን ህዝብ ተጠቃሚ ሊያደርጉ በሚችሉ የገጠር ልማቶችን ለመተግበር መንግስት በጀት ሊኖረው ይገባል።

ለአገርና ለወገን የሚያስብ ህዝብ ግብር መክፈልን እንደ እዳ ሳይሆን እንደ መብት ይቆጥራል። በመሆኑም ስለ ግብር መክፈል ሲወሳ እነዚህ ጉዳዩች ሁሉ ከግምት ውስጥ ገብተው ከህዝብ ተጠቃሚነት አኳያ መመዘን ይኖርባቸዋል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ በፈጣን እድገት ውስጥ ናት። መሰረተ ልማቶች፣ ማህበራዊ አገልግሎቶችና ሌሎች የመንግስትና የህዝብ ወጪዎች የሚሸፈኑት በግብር ነው። መንግስት መልሶ ለህዝቡ ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚያውላቸው እንጂ የትም የሚሄድ አይደለም። ከዚህ ቀደም በተለያዩ እክሎች ሳቢያ ተገቢውን ግብር መሰብሰብ ባይቻልም፣ ዛሬ ትናንት ባለመሆኑ ግብርን መሰብሰብና ለህዝቡ ጠቀሜታ መልሶ ማዋል ያስፈልጋል። ግብር ከፋይ ዜጎች ኢኮኖሚው የሚመነጨው ራሳችን በምንከፍለው ግብር መሆኑን መረዳት ይኖርብናል። የስራ ዕድል የሚፈጠረውም ኢንቨስትመንት ተንቀሳቅሶ ውጤታማ ሲሆን ነው። በመሆኑም ግብር የሚከፈልበትን ቀን በመረዳት ከወዲሁ ልንዘጋጅ ይገባል። እናም እናስታውስ…!፤ ግብር መከፈል ራስን በተደላደለ የኢኮኖሚ መሰረት ላይ ማቆም መሆኑን።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy