Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እድል ሰጪ ድሎች

0 265

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እድል ሰጪ ድሎች

                                                       ታዬ ከበደ

በቅርቡ ግብጽ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ባካሄዱት የሶስትዮሽ ስብሰባ የግድቡን ግንባታ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መቀበላቸውን አሳውቀዋል። አገራቱ በግድቡ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ ራሱን የቻለ ሳይንሳዊ ጥናት ለማካሄድ ከሶስቱ ሃገራት የተውጣጣና ከእያንዳንዳቸው አምስት አባላት ያሉት ቡድን ለሟቋቋም ተስማምተዋል። እ

ንዲሁም በአማካሪው የቀረበው የጥናት ማስጀመሪያ ሪፖርት ላይ አገራቱ ያላቸውን የማብራሪያ፣ ጥያቄና አስተያየት፥ በሶስትዮሽ ብሄራዊ የቴክኒክ ኮሚቴው ተደራጅተው ለአማካሪው በማቅረብ አማካሪው በሚሰጠው መልስ ላይ በቀጣይ ውይይት ለማድረግ ሰምምነት ላይ ደርሰዋል።

መንግሥትም ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ በእንጥልጥል ላይ በነበሩ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ መደረሱን ገልጿል። ስምምነቱ የሶስቱን አገራት የህዝብ ለህዝብ ትስስር የሚያጠናክር ነው። ይህም በአገራቱ መካከል ችግሮችን በጋራ የመፍታት ባህል እንዲጎለብት የሚያደርግ ነው ማለት ይቻላል። የአገራችንን ጥቅም የሚያስቀድመው ዲፕሎማሲያችን ፍሬ እያፈራ መሆኑንም የሚያመላክት ነው።

እርግጥ ከውስጥ ወደ ውጭ የሚዘልቀው ጥንካሬያችን ለዲፕሎማሲያዊ ውጤታችን መሳካት አስተዋጽኦ ያበረክታል። የዲፕሎማሲ ስኬቶቻችን የህዳሴው ግድብ ግንባታ በተያዘለት ዕቅድ መሠረት እንዲከናወን እድል የሰጡን ድሎች ናቸው።

ሶስቱ አገራት አሁን ለደረሱበት አቋም ሀገራችን ያካሄደችው በድል የታጀበ የዲፕሎማሲ ጥረት ነው። ምንም እንኳን ይህ የስምምነት ምዕራፍ በመካሄድ ላይ ባለው የግድቡ ግንባታ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ባይኖርም፤ ስምምነቱ ግን የዚሁ የዲፕሎማሲ ድል ውጤት ነው።

እርግጥ ሀገራችን ከህዳሴው ግድብ አኳያ እያከናወነችው ያለችው ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ ዛሬ ላይ የታችኛዎቹን የተፋሰስ ሀገራት በተለይም ግብፅንና ሱዳንን በጊዜ ሂደት አሁን ለያዙት አቋም አብቅቷቸዋል። በእኔ እምነት ይህ የዲፕሎማሲ ጥረት የትናንት ገፅታችንን ከመቀየር ጋር ተያይዞ የመጣ ነው። ምክንያቱም ባለፉት ስርዓቶች ሀገሪቱን ጨምድዶ ይዞ የነበረው የከፋ ድህነትና እነዚያ መንግስታት የነበራቸው የአስተሳሰብ ውስንነት ዛሬ ላይ እየተሰበሩ መምጣታቸው ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢፌዴሪ መንግስት በህዝብ ተሳትፎና በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት፣ ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ያላት ኢትዮጵያ እውን የማድረግ ራዕይን ሰንቆ ተጉዟል።

በሂደቱም የህዝቡን ልማታዊ ተጠቃሚነት በየደረጃው የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ቀርፆ ለውጤት መብቃት ችሏል። በዚህም ህዝቡን ከጫፍ እሰከ ጨጠጫፍ በማንቀሳቀስ ሀገራችን የያዘቻቸውን ፕሮጀክቶች በራሳችን አቅም መገንባት የምንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።

በዚህም የዘመናት ቁጭታችን የሆነውን በተፈጥራዊው የውኃ ሀብታችን የመጠቀም መብታችንን በበቂ ዲፕሎማሲያዊ ክህሎት ታጅቦ በማረጋገጥ ላይ ይገኛል። ይህም ሀገራችን ትናንት የነበራትን የአቅም ውስንነት የቀረፈና የተለየ የአስተሳሰብ ዘውግ በመፍጠርም የታችኛውን የተፋሰስ ሀገራት በአመዛኙ ወደ እኛ እሳቤ ማቅረብ የቻለ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይመስለኝም።

እርግጥም ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት እያስመዘገበች በመሆኑ፤ በተፈጥሯዊ የውሃ ሀብቷ በመጠቀም መብቷ በማትደራደርበት ደረጃ ላይ ትገኛለች። በአሁኑ ወቅት እየተጠናከረ የመጣው የህዝቧ የልማት ቁርጠኝነት እንዲሁም መንግስት የሚያከናውናቸው ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ዘላቂና ከባቢያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ መሆን ችለዋል።

ይህ ተግባሯም ከጋራ ተጠቃሚነት መርህ ውጭ አሮጌና ዘመን ያለፈባቸው አስተሳሰቦች ዋጋ ቢስ እንዲሆኑ ያደረገና ግብፆች አሁን ለደረሱበት የአቋም ለውጥ መሰረት የጣለ ነው ማለት ይቻላል። የአገራችን ፍትሐዊ አስተሳሰብ አንዱን ለመጉዳትና ሌላውን ለመጥቀም ከማሰብ የመነጨ አይደለም።

 

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የህልውና ጉዳይነቱ የዜጎችንና የሀገራችንን ዕድገት በማፋጠን ብቻ የተወሰነ አይደለም—የጎረቤቶቻችንን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ጭምር መሆኑ በሀገራችን በተደጋጋሚ ተገልጿል።

እናም ግድቡ ከከፍተኛ የኤሌትሪክ ሃይል እጥረት ላለባቸው እንደ ኬንያ፣ ጅቡቲና ሱዳን ለመሳሰሉ ጎረቤቶቻችን ለችግራቸው ምላሽ የሚሰጥ፣ ኢኮኖሚያዊ ትስስሩተን የሚያሳድግ፣ ግንኙነታችንንም የማጠናከር ሚናው በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ይህ ደግሞ የግድቡ ግንባታ ለቀጣናዊ ኢኮኖሚያዊ ትስስር የሚያበረክተው ድርሻ ከፍተኛ ይሆናል።

አገራችን ከምትከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አኳያ ሌሎችን የመጉዳት አስተሳሰብን ትናንትም፣ ዛሬም ሆነ ነገ አታራምድም። ይልቁንም በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የምታምንና ይህንንም በተግባር እያረጋገጠች የምትገኝ መሆኗን በተለያዩ መድረኮች ማስመስከር ችላለች።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገንባት ላይ የሚገኘው በህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ላይ ተመስርቶ ነው። በዚህም ሳቢያ ግድቡ ቀደምት የተመፅዋችነት አስተሳሰብን የቀረፈ፣ ለፀረ- ድህነት ትግሉ ስኬት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው፣ የማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ስሜት የኮረኮረ ነው።

ምንም እንኳን ትናንት ሐብትን በጋራና በፍትሐዊ ሁኔታ የመጠቀም መርህን ተከትላ የህዳሴውን ግድብ በመገንባት ላይ የምትገኘው አገራችን፤ ዛሬም ከዚህ መርህዋ ዝንፍ የምትል አይሆንም። ግድቡም ወንድም የሆነውን የግብፅ ህዝብ እንደማይጎዳ፣ ይልቁንም ከግድቡ ግንባታ ተጠቃሚ እንደሚሆን በፅናት ታምናለች።

ኢትዮጵያ እምነቷንና የትኛውንም ወገን ያለመጉዳት መርህዋን በተለያዩ ወቅቶች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት መንግስታትና ህዝቦች አስረድታለች። በሰፊ የዲፕሎማሲ ጥረቷም ግንዛቤም ማስያዝ ችላለች። አሁን በሶስቱ አገራት የተደረሰው ስምምነት የዚህ ውጤት ነው።

እናም የኢፌዴሪ መንግስት ይህን የዲፕሎማሲ ጥረት አጠናክሮ በመቀጠሉ ሶስቱም አገራት እውነታውን እየተረዱ መምጣት ችለዋል። ሶስቱ አገራት አሁን የያዙትን አቋም መፍጠር የተቻለውም ለዚሁ ይመስለኛል። ድል አምጪ የዲፕሎማሲ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy