Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከግራ ኪስ ወደ ቀኝ

0 332

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከግራ ኪስ ወደ ቀኝ

                                                          ይሁን ታፈረ

ባለፉት ዓመታት ከግብር ትመና እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዩች ጋር በተያያዘ በተከሰቱ የተለያዩ ችግሮች ሳቢያ መንግስት ተገቢውን ግብርና ገቢ መሰብሰብ አልቻለም ነበር። ታዲያ ችግሩ እንዳለፉት ዓመታት እንዳይሆን ዜጎች ከወዲሁ ግብር ለመክፈል በመዘጋጀት የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።

ግብር መክፈል የዜጎች ግዴታ፣ ኩራትና ክብር ነው። የሚሰበሰበው ግብር መንግስት ወደየትም የሚወስደው አይደለም። መልሶ ለህዝቡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍላጎቶች የሚያውለው ነው። ይህም ግብር ማለት ከግራ ኪስ ወደ ቀኝ የማዛወር ያህል ወይም ከህዝብ ተወስዶ ለህዝብ የሚሰጥ መሆኑን መገንዘብ ይገባል።

እርግጥ ያለ ግብር መንግስታዊ አገልግሎቶችንና መሰረተ ልማቶችን ለህዝቡ ማሟላት አይቻልም። መንገድ የሚሰራው፣ ጤና ጣቢያና ሌሎች በህዝቡ የሚፈለጉ መሰረታዊ ልማቶችን ማከናወን አይቻልም። ስለሆነም ህብረተሰቡ ከወዲሁ የሚጠበቅነትን ግብር ለመክፈል ከወዲሁ መዘጋጀት አለበት።

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመገንባት አቅዳለች። አገራችን በምታራምደው የፊሲካል ፖሊሲ መሰረት በ2012 ዓ.ም ፍፃሜውን የሚያገኘው የሁለተኛው የዕድገት እቅድ የወጪ በጀትን በሂደት በዋናነት በሀገር ውስጥ ገቢ በመሸፈንና የበጀት ጉድለት ዝቅተኛ እንዲሆን በማድረግ ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ምቹ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ ለማስፈን ያለመ ነው።

በመሆኑም ባለፉት ዓመታት የታክስ ፖሊሲዎቹን በተሻለ ሁኔታ በማስተዳደር የመንግስት ገቢ ከፍተኛ ዕድገት እንዲያሳይ ተደርጓል። ሆኖም የታክስ ገቢው እያደገ ከመጣው የመንግስት የወጪ ፍላጎት አንፃር ብዙ የሚቀረው ሆኖ ተገኝቷል። እንዲሁም የታክስ ገቢው ዕድገት እየሳየ ቢመጣም፣ ምጣኔ ሃብቱ ሊያመነጭ ከሚችለው ጋር ሲነፃፃር የሚጠበቀውን ያህል መሻሻል አሳይቷል ተብሎ የሚገመት አይደለም።

ስለሆነም ባለፉት ዓመታት የታክስ ገቢው ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ብዙም ለውጥ ማሳየት አልቻለም። እናም በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የታክስ ገቢው ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ወደ 17 በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል። በተለይም ቀደም ባሉት ዓመታት ውስጥ በምንም ዓይነት የተክስ ስሌት ውስጥ ያልነበሩ ነጋዴዎችን ወደ ታክስ ስርዓቱ ማስገባት ይገባል።

የታክስ አስተዳደር መረጃ ሥርዓቱን ይበልጥ ማጠናከርና አሟጦ ጥቅም ላይ ማዋል፣ የታክስ ከፋዮችና የህብረተሰቡ በአጠቃላይ የታክስ ትምህርትና ግንኙነትን ማሳደግ፣ የታክስ ህግን ማስከበር እና የታክስና ገቢዎች መዋቅር ተቋማዊ አቅም ማሳደግ አሁንም ተገቢ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ ነው።

በያዝነው የዕቅድ ዘመን የታክስ ስርዓቱን በጥብቅ ዲስፕሊን ተፈፃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው። በተጨማሪም የመንግስት ፋይናንስ አጠቃቀሙ ውጤታማነትን ለማሳደግ፣ የተሟላ ግልፅነትና ተጠያቂነት ለማስፈን፣ ብክነትን ለማስወገድና በጀቱን በቁጠባ ለመጠቀም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ስራው እየተከናወነ ነው። ይህም ከህዝቡ በታክስ መልክ የሚሰበሰበው ግብር እንዳይባክንና ለታሰበለት ዓላማ እንዲውል በጥብቅ የሚሰራበት ይሆናል።

እርግጥ የህዝቡ ግብር በጥሩ ሁኔታ ለታለመለት ግብ ከዋለ የመንግሥት ጠቅላላ ገቢ በ2007 ዓ.ም ከነበረበት 199 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በሁለተኛ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመጨረሻ ዓመት (ማለትም በ2012 ዓ.ም) ወደ 627 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ከፍ ይላል።

ታዲያ እዚህ ላይ በ2012 ከሚጠበቀው ገቢ ውስጥ 605 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር የሀገር ውስጥ ገቢ (ታክስና ታክስ ያልሆኑ) የሚሰበሰብ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ይህም አገራችን በዕቅድ ዘመኑ አሳካዋለሁ ብላ ላቀደቻቸው የልማት ስራዎች የሚውል ይሆናል።

ከዚህ ውስጥ መንግስት ዕድገትን በማፋጠን ድህነትን ለማስወገድ የሚረዱ የድህነት ተኮር ዘርፎች አወጣዋለሁ ብሎ በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ ላይ ለያዛቸው የልማት ፕሮጀክቶች 469 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር እንዲደርስ ያደርገዋል። ይህም ከጠቅላላ የመንግስት ወጪ 64 ነጥብ 7 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ እቅዱ ያመላክታል። እንግዲህ እነዚህ እውነታዎች የሚያሳዩን ነገር ቢኖር በመንግስት የሚከናወኑት ማናቸውም ስራዎች በዋነኛነት ህዝቡ በሚከፍለው ግብር ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን ነው።

እርግጥ ዜጎች ግብር ካልከፈሉ ምንም ዓይነት የልማት ስራዎችን ማከናወን አይቻልም። ከላይ እንደጠቀስኩት ግብር ካልተከፈለ መንግስት በእርዳታና ብድር ብቻ ለመኖር ይገደዳል።

ይህ ደግሞ መላው ስራው ብድርና እርዳታ ለሰጡት አካላት አስፈፃሚ እንዲሆን ያደርገዋል። ዜጎችም በአገራቸው መጠቀም አይችሉም። እናም ግብር መክፈል መልሶ ራስን መጥቀም መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

የመንግስት አገልግሎቶችን በጥራት ለማግኘትም ግብር ወሳኝ ሚና አለው። መንግስት ከዜጎቹ ተገቢውን ግብር ካገኘ ለህዝቡ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች በዚያው ልክ ጥራታቸው፣ ፍትሐዊነታቸው፣ ዴሞክራሲያዊነታቸውና ሁሉን አቀፍነታቸው ይደረጃል።

ቀደም ሲል እንዳልኩት ግብር መክፈል አገራዊ ኩራትና የውዴታ ግዴታ ነው። ግብር መክፈል ጠንካራ አገርን መፍጠር እንዲሁም ግብርን መክፈል አገራዊ ኩራት መሆኑን አውቆ የእነዚህን ሃይሎች ተግባር ሊያመክነው ይገባል።  

ለራሱ የልማት ክንዋኔዎች ዓመታዊ ግብሩን የሚከፍለው የህብረተሰብ ክፍል ግብሩ የውዴታ ግዴታ መሆኑን ማወቅ ይኖርበታል። ግብር ሳይከፍል የሚኖር ህዝብ የትም አገር የለም። ግብር መክፈል አገርን ለማጠንከርና የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ከዳር ለማድረስ ያግዛል።

በእቅድ የተወጠኑና ስራቸው የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማስከናወን ከዜጎቿ ግብር መሰብሰብ አለባት። ይህ ካልሆነ ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ እውን ማድረግ አይቻልም። ፈጣንና ተከታታይ ዕድገትን ማምጣትም አይታሰብኝ። መንግስት በሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች ተጠቃሚዎቹ ዜጎች ናቸው።

የኢንቨስትመንት ለመከወን የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን ከፍተኛ ነው። አንዱና ዋነኛው ፈታኝ ጉዳይ ለኢንቨስትመንቱ መሸፈኛ የሚያስፈልገው የአገር ውስጥ ፋይናንስ ግኝት መሀኑ ግልፅ ነው። ለዚህም ግብርን መሰብሰብ የግድ ይላል።

አገራችን ያሰበችውን መዋቅራዊ ለውጥ ማከናወን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው የኤክስፖርት ሚናው ሁነኛ ማሳያ ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ አሁን ካለው ሁኔታ አኳያ ሲታይ ከጠቅላላው የኤክስፖርት ገቢ ከአስር በመቶ አይበልጥም። ይህን አሃዝ ከፍ ለማድረግ ገንዘብ ያስፈልጋል።

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዕድገት ሊረጋገጥ የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ እንጂ ለብቻው ተፈፃሚ እንዲሆን ብቻ አይደለም። የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ኢንቨስትመንትን ዕውን ከማድረግ አኳያ መቆራኘት ይኖርበታል።

እየተከናወኑ ያሉትም ይሁኑ በቀጣይ ወደ ስራ የሚገቡት ኢንዱስትሪዎች፤ የቴክኖሎጂ አቅማቸውን፣ ምርታማነታቸውን፣ የጥራት አመራር አቅማቸውን ብሎም ተወዳዳሪነታቸውን በቀጣይነት መገንባት ይችሉ ዘንድ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረግላቸዋል። እነዚህን ድጋፎች ለማድረግ አሁንም ገንዘብ በበቂ ሁኔታ መገኘት አለበት።

ታዲያ ይህ ገንዘብ የሚገኘው ከግብር ከፋዩ መሆኑ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል። ስለሆነም ግብር ከህዝቡ ወስዶ መልሶ ለህዝቡ መስጠት ወይም በሌላ አገላለፅ ከግራ ኪስ ወስዶ ወደ ቀኝ ኪስ የማስተላለፍ ያህል በመሆኑ፣ ከቀጣዩ ወር ጀምሮ ለሚሰበሰበው ግብር ከፋዩች ከወዲሁ ራሳቸውን ማዘጋጀት ይኖርበታል። ግብርን በወቅቱ በመክፈል የአገራችንን ልማት እናፋጥን!

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy