Image processed by CodeCarvings Piczard ### FREE Community Edition ### on 2018-06-10 00:34:17Z | http://piczard.com | http://codecarvings.com

Artcles

‘…ውሃ አይጠማውም!’

By Admin

June 25, 2018

‘…ውሃ አይጠማውም!’

                                                             ይሁን ታፈረ

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጎረቤት አገራት በተለይም በሱዳን፣ በኬንያ፣ በዩጋንዳና በግብፅ ያካሄዱት ጉብኝት በአገራቱ መካከል መግባባትንና ትብብርን እያጠናከረ መጥቷል። ይሀም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አመቺ ሁኔታን ፈጥሯል።

በዓባይ ውሃ ፍትሃዊ አጠቃቀም ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በካይሮ ካደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ የግብፅን ህዝብ የመጉዳት ምንም ዓይነት ፍላጎት እንደሌላት ለአገሪቱ ህዝቦች አረጋግጠዋል። አገራችን የዓባይ ውሃ ወደ ግብፅ እንዲሄድ ብቻ ሳይሆን በትክክል መድረሱንም እንደምታረጋገጥ አስታውቀዋል። እርግጥ በጋራ ተጠቃሚነት እሰከሰራን ድረስ የትኛውም የዓባይ ለጅ ውሃ ሊጠማው አይገባም።

ኢትዮጵያ ዓባይን በመጠቀም ራሷን ስታለማ ግብፃውያንን በፍፁም እንደማትጎዳ፣ በዚህ ጉሳይ ላይ የግብፅ ህዝብ በመንግስታቸውንና በህዝባቸው ሙሉ እምነት ሊኖረው እንደሚገባም አስረድተዋል። ዓባይ ለሁለቱም ህዝቦች የተሰጠ በረከት ነው።

ኢትዮጵያ የድርሻዋን ተጠቅማ ለግብፅ የሚገባትን ብቻም ሳይሆን፣ ወደፊት እየጨመረ የሚሄድ የውኃ ፍሰት ልታገኝ ስለምትችልበት ሁኔታም ታስብበታለች ማለታቸው አገራችን ‘የዓባይ ልጅ ውሃ አይጠማም’ የማለት አንድምታ ያለው ነው።

ዓባይ በአግባቡ ከተጠቀምንበት ለተፋሰሰሱ አገራት ይበቃል። የሁለቱ አገሮች  ግንኙነት ዓባይ ብቻ ባለመሆኑም ከዓባይ ባሻገር በሌሎችም መስኮች ላይ አብሮ ለመሥራት የሚያስችላቸውን መግባባት ሊፈጥሩ ይገባል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በግብፅ ቆይታቸው፤ በኢንዱስትሪ፣ በመንገድ፣ በባቡር ትስስርና በሌሎችም መስኮች የሁለቱን አገራት ህዝቦች ለማስተባበር ስምምነት ላይ የደረሱትም ለዚሁ ነው። ታዲያ አሁንም ቢሆን አገራችን በዓባይ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ የትኛውንም የተፋሰሱን አገር የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት ጠንካራ መተማመን መፍጠር ያስፈልጋል።

በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ባለችበት ደረጃ አገሪቱን የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ብርቱ ጥረት እየተደረገ ነው። ይህን የዕድገት ፍላጎት በአግባቡ ለማስኬድ የኤሌክትሪክ ሃይልን ከከባቢ ብክለት በነፃ መንገድ መጠቀም ያስፈልጋል።

ለዚህም ታዳሽ የተፈጥሮ ሃይላችንን መጠቀም ይኖርብናል። ይህን ካላደረግን አሁንም ከነበርንበት የከፍታ ቦታ ተንሸራትተን የኋሊት በድህነት አረንቋ ውስጥ ልንዘፈቅ እንችላለን። ይህን ደግሞ የሚፈቅድ ትውልድ ዛሬ ላይ የለም። እናም የህዳሴውን ግድብ መገንባት የግድ ነው።

እርግጥ እኛ ስናድግ የታችኛው የተፋሰሱ አገራትም ይሁኑ ሌሎች የቀጠናው አገራት ተጠቃሚ ይሆናሉ። እኛ ከምስራቅ አፍሪካም ይሁን ከግብፅ ተነጥለን ልንለማ አንችልም። የእኛ እድገት የቀጠናው ሀገራትና የግብጽም ጭምር ነው። የግድቡ ግንባታ የምስራቅ አፍሪካ አገራት የኤሌክትሪክ ሃይል ችግርን የሚቀርፍ ነው። ለግብፅም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ህዝቦች እነዚህን እውነታዎች በሚገባ ይገነዘባሉ። ምንም ዓይነት ብዥታ የለባቸውም። ለግድቡ ግንባታ የቦንድ ግዥ እንዲሁም ዋንጫው በየክልሉ ሲዞር ከተጠበቀው በላይ ገንዘብ በማውጣት ቦንድ የሚገዙትም ለዚሁ ነው።

ይህ የህዝቦች አንድነት የራስን የተፈጥሮ ሃብት በራስ አቅም የማልማትና በእርሱም ራስንና ከባቢውን የመጥቀም ተምሳሌት በመሆኑ ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው። ይህን የማስተባበር ስራ የሚያከናውኑት አካላትም ስራቸውን ሳያቆራርጡና ያዝ ለቀቅ ሳያደርጉ በቋሚነት እያከናወኑ ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ እንጂ ሌሎች አገራትን የሚጎዳ ፕሮጀክት የመገንባት ፍላጎት የለውም። ሌሎችን የመጉዳት ታሪክም የለውም። የሚከተለው ሁሉንም ተጠቃሚና አሸናፊ የሚያደርግ ፖሊሲም ይህን እንዲያደርግ አይፈቅድለትም።

ይልቁንም መንግስት እየሰራ ያለው ግድቡ አገራችን ኤሌክትሪክ በመሸጥ የምስራቅ አፍሪካን አገራት በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር የምታደርገው ጥረት አንዱ ማሳያ እንዲሆን ነው የሚፈልገው። ከግድቡ ኬንያ፣ ጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያና ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ተጠቃሚ ይሆናሉ። ግብፅን ጨምሮ ሌሎች የተፋሰሱ አገራትም መጠቀማቸው አይቀርም።

ኢትዮጵያ የራሷን ፕሮጀክት በራሷ አቅም በመገንባት ላይ ያለች እንዲሁም ከድህነት ለመውጣት ስትል የምትገነባቸውን ማናቸውንም የልማት ግድቦችን ስትገነባ የሌሎችን ተጠቃሚነትና መብት በማክበር እንጂ በመጉዳት አይደለም።

የኢትዮጵያ ህዝቦች በአሁኑ ሰዓት የራሳቸውና የቀጠናው አገራት ድህነት፣ ኋላቀርነት፣ ረሃብና ጦርነት ማብቃት አለበት ብለው በአዲስ የለውጥ መንፈስ ተነስተዋል። በድህነት ላይ ለመዝመት ከሌሎች የምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር አብረው እየሰሩ ነው። በተለይ በዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው አዲሱ አመራር ይህን ጥረት እያፋጠነው ነው።

ይህን በማሰብም የተፋሰሱን አገራት ተጠቃሚ ለማድረግ በእኩልና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ የግንኙነት ፖሊሲን በመከተል ሁሉም ወገን አሸናፊ የሚሆንበትን መንገድ እየተከተለ ነው።

መንግስት ከህዝቦች ጋር መክሮ በሁሉም መስክ ፈጣን ልማትን ሊያመጡላቸው የሚችሉ አቅጣጫዎችን በመከተል በትግበራ ሂደቶች ላይ የጋራ መግባባትን ከህብረተሰቡ ጋር እየፈጠረ ነው።

የመንግስትና የህዝብ የጋራ መግባባት የሌላውን አገር ህዝብ ባለመጉዳት ላይ የተመሰረተ ነው። የግድቡ ስራ የሚከናወነው የሌሎችን ህዝቦች ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ያማከለ መርህን ተከትሎ እንጂ መጎዳዳትን በማሰብ አይደለም። ምክንያቱም የአገራችን መንግስት ህዝባዊ ከመሆኑና የሚከተለውም መርህ በፍትሐዊና በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ የሚያጠነጥን ስለሚያጠነጥ ነው። በመሆኑም ግብጻዊያን ወንድሞቻችን አገራችን በግድቡ ምክንያት እንደማትጎዳቸው ሊተማመኑባት ይገባል።

ኢትዮጵያ በእኩልነትና በፍትሃዊነት የምታምን አገር ናት። የምታካሂዳቸውን ማናቸውንም ፕሮጀክቶች ከዚህ አኳያ የተቃኙ ናቸው። ስለሆነም በዓባይ ወንዝ ላይ በመገንባት ላይ የሚገኘው ታላቁ የህዳሴ ግድብም ይህን ዕውነታ ተመርኩዞ የሚከናወን ነው። ይህ የአገራችን ተቀባይነት ያለው አቋም የሚቀየር አይደለም።  

አገራችን በህዳሴው ግድብ ላይ የምትከተለው አቋም የማንንም ጥቅም የማይነካ ፍትሃዊ ብቻ አይደለም። እንዲያውም ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ቀጠናውንና ግብጻውያን ወንድሞቻችንን የሚጠቅም ነው። ስለሆነም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በጉብኝታቸው ወቅት እንዳረጋገጡት የአገራችን ህዝቦች ወንድሞቿ የሆኑትን ግብጻዊያን እንደማትጎዳ መገንዘብ ያስፈልጋል። ያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት በግብጻዊያን ወንድሞቻችን በኩል የተፈጠረው ስሜት መተማመንን የፈጠረ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።